በነሲቡ ስብሐት
አገራችን አሁንም ለክብሯና ለነፃነቷ የሚሰውላትን እየፈለገች ነው። ልጆቿ ነንና የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ ዘንድ ትጣራለች። ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ ታሪክ ተረካቢውና አገር ተረካቢውን ትውልድና ወጣቱን ትውልድ ታያለች። የነገው ሰው ናችሁና አትጡኝ ትላለች።
ዛሬ ወጣቶች ተሰባስበውና ተደራጅተው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው አይታዩም። በየግል የሚወሰደውን እንቅስቃሴ እስከ መስዋዕትነት መክፈል እያሳዩን ነው። ግና የተጠናከረና የተባበረ ቤት የላቸውም። ለምን?
ለብዙ ዓመታት ለአገርና ሕዝብ ነፃነት የተጋደሉና እየታገሉ ላሉ ለጥንካሬያቸው ምሥጋና ይግባቸውና ተዋግተዋል፣ ታግለዋል። ግና ለድል ለመብቃት አይደለም፣ ለመብቃት የሚያስችላቸውን ኃይል መገንባት አልቻሉም። የትግሉን ዋልታና ምሰሶ ረስተውታልና ዘንግተውታል።
ትግሉ የነፃነት ነው። ለዚህ የነፃነት ትግል ሊታቀፍ የሚገባው መታቀፍ ይኖርበታል። የትግሉ ሞተር ቁልፍ ተዘንግቶ ተራራው ቁልቁለት አይሆንም። ለዚህም ነው የሚያንሸራትተው። ተራራውን ለመውጣት ምርኩዙ ወጣቶች ናቸውና።
ውድ ወገኖቼ አገራችን ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ምኞታችን ነው። ይህን ዛሬ አላየነውም። ዛሬ አገራችን ተደፍራለች፣ ክብሯን አጥታለች። ነገ በማን ዘመን ነው? በየትኛው ትውልድ ነው? አገርና ትውልድ ይጠይቁናል።
አገራችንና ሕዝባችን አንድ ቀን የነፃነት አየር ይተነፍሳሉ። ድል ይቀዳጃሉ። ግና ኢትዮጵያችን ለሁሉም ዕፎይ ብላ የልጆቿ የምትሆንበትን መሠረት ጥለናል ወይ? አስበንበታል ወይ? ወደድንም ጠላን ይህች አገር የሚረከባት አዲስ ትውልድ ነው። ያረጀው ይሄዳል፣ አዲስ ይመጣልና። ምን እያስተማርናቸው ነው? ወጣቶች ልጆቻችንን አገራቸውን እንዲያውቁ፣ ራሳቸውን እንዲያዩ ምክራችን ምንድነው? ‹‹እኔ የገባሁበት ፖለቲካ ይበቃል፣ አርፈህ ኑሮህን ኑር፣ ትምህርትህን ተማር፤›› ይኼንን ነው ልናወርስ የተዘጋጀነው። ምን ነገርናቸውና፣ ምን አስተማርናቸውና ይከተሉን። መባላትን፣ አለመስማማትን፣ ለአገር ሳይሆን ለግል ማሰብን፣ ስለሕዝብ የበላይነት ተረስቶ የድርጅት ቀደምትነትን፣ ስለሰፊዋ አገር ሳይሆን ስለጠባቧ።
ታሪክን ዘወር ብለን ለመቃኘት ፍላጐቱ ካለን የዛሬ አባወራዎች የወጣትነት ዕድሜያችሁን ስታሠሉ ያንን ጀግንነት ከየት አመጣችሁት? ለአገር መስዋዕትን፣ ለወገን እኔ ልቅደምን፣ እኔ ልሙትን በተግባር ያስረገጠ ትውልድ ብቅ ብሎ ድርግም ያለበት ዘመን እንዴት ተፈጠረ? ከምን መጣ? የፖለቲካ ድርጅት የፈጠረው ተዓምር እንዳይመስላችሁ። በተግባር የታየው ጀግንነት ግን አባቶቻችንና እናቶቻችን ያወረሱት ነው፡፡ ያስተማሩት አገር መጠበቅን፣ ለአገር መስዋዕት መሆንን፣ ለቆሙለት ዓላማ በፅናት መቆምን ተርከዋልና፣ በተግባር አሳይተዋልና።
እነሱ ያወረሱት ጀግንነት ነው የተገበረው። የእነሱን ኑዛዜ ነው ተግባራዊ የተደረገው። ቃል ኪዳናቸው ነው የተፈጸመው። በአገር ጉዳይ ላይ የፀና አቋም እንዲኖር ቅድሚያው አገርን ማፍቀር ነው። ይህ የአገር ማፍቀር ስሜት የሚፈጠረው ደግሞ ከትውልድ ትውልድ በተወረሰ ታሪክ፣ ወግና ባህል ውስጥ በማለፍ ነው። ቤተሰባዊ አስተዳደጋችን፣ ሃይማኖት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የኪነ ጥበብ ዘርፎች፣ ባህላችን የእነኚህ ውጤት ሁሉ በአገር ፍቅር ስሜት ተኮትኩተን እንድናድግ ያደርገናል። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ታሪክ፣ ወግና ባህል ለወጣቶች ያወርሱታል። ለአገር መሞትና ለአገር ቤዛ መሆንን የሞራል መሠረት ይጥሉለታል።
- በላይ ዘለቀ ተሰቅሎ ‹‹እንቢኝ ለአገሬን›› አስተምሮናል።
- አፄ ቴዎድሮስ በሽጉጣቸው ለጠላት እጅ አለመስጠትን፣ አለመንበርከክን የጀግና ሞት ሞተው አስተምረውናል።
- አፄ ዮሐንስ ለአገራችን ሉዓላዊነትና ለግዛታችን አንድነት አንገታቸውን በመቀላት ተምረን እንድናስተምር ዓሳይተውናል። አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጠላትን ድል ማድረግን አስተምረውና፣ አውርሰውናል።
ይህንን ውርስ ነው ያ ትውልድ፣ ያ ወጣት የመሰከረው። ዛሬ በዚያ ዘመን እየተባለ የዕድሜ ማሥሊያ ብቻ እንዲሆን መተው የለበትም። የዚያ ትውልድ ታሪክ በተለይ ደግሞ የአገር ወዳዱ ወጣት ታሪክ ደብዝዞ እንዲጠፋ፣ ጠቁሮና ከፍቶ እንዲጠላ፣ ረክሶ እንዲናቅ የሚደረገው ጥረት ሊያሳስብ ይገባል። ታሪክ በአግባቡ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ጊዜውን መጠቀም ግድ ይላል። ጊዜ በበረረ ቁጥር ሞትን ድል እንደማያደርግ ልንገነዘብ ይገባል። ተሸክመን የምንጓዘውን መዘንጋት የለባችሁም። እሱ እኮ ነግሮ አይመጣም። ልወስድህ ነውና ተዘጋጅ አይለንም። ዛሬ በትግሉ አውድማ ያሉቱ አብዛኛው ከጋሼ ወደ አባባ፣ ከእትዬ ወደ እማማ የዕድገት ደረጃ ላይ ናቸው። በመሆኑም አገር የማዳን ጉዞው፣ የነገዋ ኢትዮጵያ የዜጎቿ ትሆን ዘንድ ተተኪ፣ ተረካቢ ግድ ይላል። ወደ ማይቀረው የዘለዓለም ቤት ደጃፍ ተደርሷል።
አገራችን ግን ሁሌም ትኖራለች። እናሳ? እናማ አገር እንድትኖር፣ የነገ ሕይወቷን የምትመኙ ከሆነ ንብረታችሁን አውርሱ። ወጣቶችን እናስተምር። ወጣቶችን እንንከባከባቸው፣ እንያቸው፣ እናናግራቸው፣ እናዳምጣቸው። የማይገፋውን ዳገት የሚገፉት እነሱ ናቸውና። አዎ! ለራስ ሥልጣን አስፈላጊ አይደሉም። አዎ! ለግል ሥልጣን፣ ለግል ክብር ሚናቸው ውሱን ነው። ለአገርና ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ከሆነ ግን የትግሉ ሜዳ ላይ ወጣቶች ማጀብ ሳይሆን መታጀብ ይገባቸዋል።
በዘመነ ደርግ የሰባትና አሥር ዓመት ሕፃናት አስከሬን እያዩ ነው ያደጉት። በወንድምና በእህታቸው ላይ ‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋም›› እያሉ ነው ያደጉት። በጨቅላ አዕምሯቸው በየጊዜው ስለግድያ ሲዘመርላቸው ነው ያደጉት። ዛሬ እነዚህ ወጣቶች በ40 ዕድሜ ክልል የሚገኙት በፍርኃት ተገንነት ጨለማ ይዟቸዋል። በወያኔ የሰባትና የአሥር ዓመት ሕፃናት ዛሬ በ30ኛው ዕድሜ ክልል ይገኛሉ፡፡ ለ27 ዓመታት ስለዘረኝነት፣ ስለጎሳ ፖለቲካ፣ ስለጠባብነት እየተሰበኩ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን እየዘነጉ፣ እየረሱ እንዲያድጉ ነው የተደረጉት። እናም ፍርኃትና ዘረኝነት ተባብረው ልጆቻችንን ይዘዋቸዋል። እኛም ደግሞ ማራቁን ከመረጥን፣ ማስተማሩን ከነፈግናቸው፣ አናስጠጋ ካልናቸው፣ እየደነገጡ፣ ግራ እየገባቸው፣ የሚያዩት አልታይ እያላቸው፣ የሚያዳምጡት አልሰማ እያላቸው፣ የሚጻፈው አልነበብ እያላቸው ነው የሚጓዙት። ይህ ደግሞ ከተስፋ መቁረጥ ጋር መጤ ባህሎችን ቢያፈቅሩ፣ አገራቸውን ከመምሰል ይልቅ ሌላውን ቢመስሉ፣ በባህላቸው ቢያፍሩ፣ በቋንቋቸው ባይግባቡ ልንፈርድባቸው አግባብ አይደለም።
እንዴት ደርሰን እናድናቸው? ተብትቦ ከያዛቸው መርዝ እንዴት እንፈውሳቸው? የበሽታው መድኃኒቱ የቱ ነው? ይኼንን መመለስ ስንችልና ስንደርስላቸው ያን ጊዜ አገር ዳነች። ያን ጊዜ አገር ተኪ ዜጋ አገኘች። ያን ጊዜ አገር ሉዓላዊነቷና አንድነቷ ተጠብቆ እንደሚኖር እናስረግጣለን። ተስፋችንም ልምላሜ ያገኛል።
የነገው ሰው የዛፉ ቅርንጫፍ ይበዛል። ይህ ካልሆነ ለደካማ ጐናቸው ተባባሪ ከሆንን፣ እያየን እንዳላየን ካለፍነው፣ ነገ ለሚከሰተው ውጤት የእኛም እጅ እንዳለበት መዘንጋት አይኖርብንም። ልጄ ሆይ! ብለን ድምፅ ማሰማቱ ተስኖናል። አሁንም እኛን እንዲያዳምጥ እንፈልጋለን። አሁንም እኛን እንዲያይ እንፈልጋለን። መንገዱ ይህ አይደለም። እስቲ አዳምጧቸው፣ እስቲ አበረታቷቸው፣ እስቲ ተረከቡን በሏቸው፣ እስቲ መካሪ ሁኗቸው። የነገ አገር ተረካቢ ናቸውና። የነገዋ ኢትዮጵያ የእነሱ ናትና።
አሁን ያለውን ሁኔታ ጥለንላቸው ከሄድን ግን ብዙ ጥፋት ይኖራል። ራሳችንን መርምረን አንድነትን ልናስተምራቸው ይገባል። ራሳችንን ጠይቀን ኢትዮጵያዊነትን ልንተርክላቸው ግድ ይለናል። በኩራትና በክብር ዓርማችንን ልንሰጣቸው ይገባል። ውስጣችንን አነጋግረን ያለንን ሀብትና ንብረት የትግል ተመክሮ ሚስጥረ ተዓምር አይደለምና ሳንቆጥብ፣ ሳንሰስትና ሳናዛንፍ ልናስረክባቸው ይገባናል። አንፍራቸው ወጣቶች ናቸውና። አናርቃቸው እያዩን ነውና። አንሽሻቸው እየተከተሉን ነውና። ወጣቶች ወደኛ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው። ነገ የእነሱ ናትና። የልጅ ነገር አንበላቸው የልጅ አዋቂዎች ናቸውና። የእኛው ጣጣ ነው በጨለማ ያሰራቸው፣ በእነሱ አንፍረድ።
ዛሬ አገራችንና ሕዝባችን ከባድ ፈተና ከፊታቸው ተደቅኗል። ዛሬ የለውጥ ሐዋርያ ሆነው አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ዓብይ አህመድ ብቅ ቢሉም፣ አገዛዙ ላይ ወያኔ/ሕወሓትና አንዳንድ የዘር ድርጅቶች አሁንም ሚናቸው አልከሰመምና ኢትዮጵያን ሊበታትኗት የዕቅዳቸው የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል። የወያኔ/ሕወሓት የመጨረሻ ደረጃ ኢትዮጵያን መበታተን ነውና። ሕወሓት/ወያኔ በ27 ዓመታት አገዛዙ በዝርፊያው እጅግ ጠግቧል። በግድያው፣ በአፈናው አራራውን ተወጥቷል። በዘረኛ ጅራፉ ሁሉንም ገርፏል። በሁሉም አቅጣጫ የአገራችን ህልውና አጠያያቂ ደረጃ ላይ ነው። በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ በየቀኑ የሚሰማው ዜና ማኅበራዊ ገጾችን አጣቦ ይገኛል። ወያኔ በቁማችን ለባዕዳንና ለተወሰኑ ቱጃሮች እንደሸጠን ሁሉ ዛሬ አገር የሕዝብ ሳትሆን የወያኔና የተወሰኑ ቱጃሮች፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያን አንድነት በማይፈልጉ ባዕዳንና ዘረኞች ተባባሪነት ልትበጣጠስ ነው። የመበታተን ቦምቡ ተጠምዷል። ልናከስመው ግድ ይለናል። ይህን የምንተገብረው ትኩሱን ኃይል አነሳስተን ነው። አገሩን ይወዳልና። ለአገሩ መስዋዕትነት ይከፍላልና። በተቀናጀ መንገድ ይሆን ዘንድ ወጣቱ ትውልድ የሚያስተባብረው ነው ያጣው። ትብብርነቱን፣ መሰባሰቡን፣ መደራጀቱንና ማስተማሩን ዛሬ ካደረግነው ለነገ የአገራችን ራዕይ የተዘጋጀ ኃይል አለና ዕፎይ ብትሉ አይፈረድባችሁም፡፡ ተክታችኋልና፣ አምርታችኋልና። ዛሬ የተተከለው ችግኝ ነገ ያፈራልና።
ዛሬ ወጣቱን የአገር ውኃ ማጠጣት ይጠበቅባችኋል። መኮትኮት ያስፈልገናል። ለእኛ ሳይሆን ለአገሩ እንዲያስብ መምከር ይጠበቅባችኋል። ቅድሚያችን አገር ናትና። ጥረቱ አገር በድል አድራጊነት እንድትወጣ፣ ሁሉም ለአገርና ለሕዝብ ተሟጋች ዘብ፣ ቋሚ፣ ጠበቃ፣ ኃይል እንዳይሳሳ፣ ጠንክሮ እንዲገኝ፣ ታሪክ እንዳይበረዝ፣ እንዳይበላሽ፣ ያልነበረው እንደነበረ እንዳይተረክ፣ ውሸት ሀቅን እንዳያሸንፍ፣ ወደ ልጆቻችን እንጓዝ። ይህን ስታደርጉ ኃላፊነታችሁን ተወጥታችኋል። አደራ አስረክባችኋል። የታሪክ ዕዳችሁን ከፍላችኋል። ይዘነው ከተቀበርን፣ እጅና እግራችንን አጣጥፈን ከተቀመጥን፣ ማየቱ ካቃተን፣ መናገሩና ማድመጡ ከተሳነን ነገ ትውልድና ታሪክ ቢወቅሱን ልንቀበል ግድ ይለናል።
ዛሬ በፖለቲካው መድረክ ያሉ ተቃዋሚ/ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነታቸውን እያቻቻሉ የጋራ መድረክ ለመፍጠር ብዙ ጥረዋል። ግና ተሳክቶለት የወጣ የለም። ዛሬም የኅብረት ትግል በጥያቄ ላይ ነውና። ዛሬም የጋራ መድረክ በጥያቄ ላይ ነውና። ለምንድነው የምንመሠርተው የጋራ መድረክ ውጤት ሊያስመዘግብ ያልቻለው? ምክንያቱ ምንድነው? መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይ አንጋፋዎቹ በርግጥ በጥንት ዘመን በነበረባቸው ልዩነት አሁን በጋራ መድረኩን ሲጋሩ መተማመንን ፈጥረዋል? ወይስ በጥርጣሬ እየተጓዙ ነው? ድርጅቶች ምን እያደረጉ ነው? እየተንቀሳቀሱ ነው? ዕውን ስብስቡ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ነው? ይህን ስናይ ቅራኔን ያላዘለ፣ ቂምን ያልቋጠረ አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አገር ተረካቢ ኃይል እንኳ ለማፍራት ከተጣረ አንደኛውን የታሪክ አደራ ተወጥታችኋል። መፈራራት፣ አለመተማመንና ጥርጣሬ አጅበውት የሚጓዝ የጋራ መድረክ ቢመሠረትም ነገ ዳግም መጮኹ አይቀርም። የኅብረት ያለህ እየተባለ። መሠረቱ የተገነባው በወጣቱና በኅብረተሰቡ አይደለምና። እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት የአገራችንን ታሪክና የፖለቲካ ሒደት ሀቁን ሊያስጨብጡ፣ ሊሰነዝሩ ካልቻሉ ከተለያየ አቅጣጫ የተለያየ ታሪክና ትረካ እየሰማ ያለው ትውልድ ላይ ግራ መጋባትንና መዘበራረቅን ነው ተቀበል የሚባለው። ይህ ደግሞ ውሉን ያጣ መነሻና መድረሻውን ያላወቀ የጩኸት ፖለቲካ ውስጥ ይዘፍቃል።
ለመሠረታዊና ለዘላቂ ጉዳዮች፣ ለአገርና ለወገን ጥቅም ቅድሚያና ትኩረት ተሰጥቶ ድል ለመጎናፀፍ መንገዱ ክፍት ነው። የሁላችንም ዕውቀትና ተመክሮ መሠረት አድርገን መክረን ዘክረን የምናወጣው የትግል መርሐ ግብር፣ የምንቀይሰው ሥልት፣ እንዲሁም የሁላችንም ኃይል ጥረት አስተባብረን የምናጠነክረው የጋራ መድረክ ለድል እንደሚያበቃን አያጠያይቅም። ዕድሜ፣ ፆታ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ ድርጅት ሳይለይ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የምትበጀዋን ኢትዮጵያን ከመመሥረትና ከመገንባት የሚያግደን ኃይል ከቶ አይኖርም። የአገራችንና የወገናችን ችግር ለመፍታት እነሆ እኛም የትውልድ ግዴታችንን ለመወጣት፣ ራሳችንን እንድናዘጋጅና የነገውን ሰው ትኩረት እንድንሰጠው ጊዜው ግድ ይላል። ለውጥ አምጪ ወጣቶች ከዕምቅ ኃይላቸው ጋር ተደብቀዋል። ከአዲስ ፈጠራቸው ጋር ተሸፍነዋል። ጥሩ ነገራቸውን ይዘው ብቅ እንዲሉ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል። ሕዝብን ለማነሳሳት ተደማጮች ናቸው። ከሕዝብ ጋር ያላቸው ትስስር የጠነከረ ነውና እንዲጠቀሙበት፣ እንዲያወጡት አቅጣጫ መስጠት ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስፈላጊነቱን ማመን ያስፈልጋል። መቀበል። ዛሬ ወጣቶቻችን አገርን እንዲዘነጉ ተደርገዋል። በትምህርት ተቋማት፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ ትውልድ አገሩን እንዲረሳና በቀጣይነት የግል ፍላጐቱ ላይ እንዲያተኩር፣ የአገሩ ራዕይ እንዲጠፋው ስኬታማ ባይሆንም ተቀጥቅጧል፣ ተሰብኳል። ለዚህ ደግሞ ባዕዳን ኃይሎች በከፍተኛ እየገፉበት ነው።
በአገራችን ላላቸው ጥቅም፣ በኢሕአዴግ አገዛዝ ለመሠረቱት የተለያዩ ተቋም ቀጣይነትን ይፈልጋሉ። መንግሥት ቢቀያየርም ፍላጎታቸው፣ ጥቅማቸው ዝንፍ እንዳይል ይፈልጋሉ። ስለዓባይ መብታችንን ይገድባሉ። ተፈጥሮ ሀብታችን ካልገቡበት፣ በእነሱ በጎ ፈቃድና መሪነት ካልሆነ፣ ለእነሱ በሚያመቻቸው ዕይታ ካልሆነ በመብታችን፣ በዕልውናችን የሚያደርጉትን መፈታተን ነገም ከነገ ወዲያም በተወሳሰበ መንገድ ሊቀጥሉ ይፈልጋሉ።
ብሔራዊ ስሜታችንንና አንድነታችን ከተጠናከረ አሁንም ኢትዮጵያን አውራ ልናደርጋት እንደምንችል፣ ብቃቱ እንዳለን ቀድመውን ተረድተዋልና ያሰናክሉናል። ለዚህ ሁሉ ዕቅዳቸው የዘመቱት ታዳጊው ወጣት ላይ ነው። ስለነገ ዘረፋቸው የዛሬውን ትውልድ ማሰናከል ትልማቸው ነውና። ዘምተውበታል። በሃይማኖት፣ በዕርዳታ፣ በተለያዩ መንግሥታዊ በሆኑና ባልሆኑ ተቋማት በልማት ስም አዕምሮውን፣ አስተሳሰቡን እየሰለቡት ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ እንዳትታየውና በአገሩ እንዲያማርር እያደረጉት በምትኩ ባዕድ አፍቃሪ፣ ስደት ናፋቂ እንዲሆን እየተጫወቱበት እናያለን።
ይህ ሁሉ ዘመቻ በዚህ አረመኔ አገዛዝ ያገኙትን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ወደፊትም እንዳሻቸው እንዲያዙን፣ እንዲገዙን፣ መመርያ እንዲሰጡን ይፈልጋሉና ትውልዳችን ላይ ሲዘምቱ እያየን አለመንቀሳቀስ ከተጠያቂነት አልፎ አሳፋሪ ነው። የመከላከል ብቃቱን በአግባቡ አልተወጣነውምና። የፖለቲካው ሰው፣ ምሁሩ፣ አገር ወዳዱ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሁላችንም የዕድሜ ባለፀጋዮች ስለነገዋ ኢትዮጵያ ካሰብን ስለነገው ሰው እናስብ።
‹‹ይኖር ይሆን ወይ ባንዲራ፣ ሰውን የመሰለ አሻራ›› እንዳለው ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ወፎቹ እንዲዘምሩ፣ አራዊት እንዲቦርቁ፣ ወንዞች እንዲፈሱ፣ ዕፀዋት እንዲያብቡ ከተፈለገ የነገው ሰው ላይ እናተኩር።
ጋሼ/እትዬ ወገኖቼ ‹‹. . . እኔስ አዘንኩ ለዚህ አምባ፣ እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን ለሚፎክት ለሚያቃስት፣ በመፃጉዕ ደረመን ለሚሰቃይ ለሚታመም፣ በአዕላፍ ደዌ – ሰቀቀን፡፡
እኔስ አዘንኩ ለዚህ አምባ፣ እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን
ሕፃናት መንቆር፣ ማጉርጥ ባወጡበት
አጥንት በተገተጉበት
በድን – በላ በሆኑበት፣ እርመ – በላ በተባሉበት፣
እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን
እናቶች ሰብዕናቸውን በጠረጠሩበት
እንደ ትኋን እንደ ቅማል ዕጭ በፈለፈሉበት
የእንግዴ ልጅ እንደ ሕፃን በታቀፉበት
የራሔልን ዕንባ በዋጡበት
እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን።
አባቶች በነጭ ፀጉራቸው ባፈሩበት
አድባራቸውን በረገሙበት
ህልማቸውን በተሳቀቁበት
የሐበሻ ማቅ – ቱቢት በተፈተለበት
ነጭ ማተብ በተገመደበት
እኔስ አዘንኩ ለዚህ አምባ፣ እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን
የታሪክ ደረባ ሲከፈት፣ ሲከፈት የታሪክ መዝገብ ብራና
መቼም ሳያኖረው አይቀርና፣ ሳይከትበው አይዘነጋውና
ምንድን ብሎ ይጥራው፣ ይህን ዘመነ መንሱት
ይህን ዘመነ – ፈተና?
ይበቅል ይሆን ከዚህ ጠፍ ላይ፣ ከዚህ መና ከዚህ ወና
ተስፋ ማድረግን እሚያውቅ ህልው፣ ሳቅን እሚያቅ ስብዕና
የሰላም ሪቅ የጤና፣ የፍቅር አንድነት ጋዘና . . .
ይበቅል ይሆን?
በትንሣዔ እንድናምን፣ ያሸት ይሆን አዝመራው?
ያፈሩ ይሆን ተክሎቹ? ያብቡ ይሆን ዕፀዋቱ?
ይተሙ ይሆን ንቦቹ? ይዘምሩ ይሆን ወፎቹ?…
በትንሳዔ እንድናምን፣
ይደራ ይሆን ኮከበ ጽባህ፣ የእንቁጣጣሽ ችቦ
በእምነት በአለኝታ ጉንጉን ተውቦ፣ በቀስተ ደመና ተከቦ
ተሞሽሮ በፀደይ ወርቀ ዘቦ፣ . . .
ይደራ ይሆን?
ይኖር ይሆን ወይ ዓርማ፣ ይኖር ይሆን ወይ ባንዲራ
ሰውን የመሰለ ቀለም ያለው፣ ሰውን የመሰለ አሻራ
እማይወድቅ፣ እማይታጠፍ ሰንደቅ፣ እማይከስም፣
እማይዳፈን ደመራ?
ይኖር ይሆን? . . .
እንዲኖር የነገውን ሰው – ወጣቱን እንመልከት
ግጥሙ ነፍሱን ይማርና ከደራሲ፣ ገጣሚ፣ የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪውና ሃያሲ ደበበ ሰይፉ የግጥም መድበል የብርሃን ፍቅር ቁጥር 1 ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› ከሚለው የምዕተ ዓመቱ ብርቅዬ ግጥም የተቀነጨበ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡