Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ለብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ለብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን

ቀን:

በሰሎሞን ዳኞ

የዶ/ር ዓብይ መንግሥት አልተቻለም! እንደ ራስ ዳሸን ተራራ የተቆለሉትን የአገራችንን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡ የሰማነውን አጣጥመን ሳንጨርስ ሌላ አዳዲስ የምሥራቾችን በላይ በላዩ ያሰማናል፡፡ የተነገሩን ነገሮች ሁሉ ወደ ተግባር እንደሚለወጡም አንጠራጠርም፡፡ አንዳንድ ውጤቶችንም እየተመለከትን ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም የሚባል ኮሚሽን ስለመመሥረቱ የምሥራች ተበሰረልን፡፡ ዶ/ር ዓብይንና መንግሥታቸውን ምስር ብሉ ብለናል! ከሰላም በላይ ምን አለና! የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ የኮሚሽኑ አባሎችን ስብጥር ስመለከት አገራችን ለዚህ ጊዜ መድረስዋ በራሱ ተዓምር ነው አልኩኝ፡፡ ለዚህ ለተቀደሰ ተግባር አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከኮሚሽኑ ጎን እንደሚቆሙ አምናለሁ፡፡

ኮሚሽኑ የተቋቋመው ዕርቀ ሰላም በማውረድ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ቢሆንም፣ በዝርዝር ምን ሊሠራ እንዳሰበና ከየት ጀምሮ የት እንደሚጨርስ አላውቅም፡፡ ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለበትና በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቁት ግልጽ ነው፡፡ ለመሆኑ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጉዳይስ ይነሳ ይሆን? ስል ራሴን ጠይቅሁ (ከዚህ በኋላ እንዳስፈላገነቱ ጃንሆይ እያልኩ እጠራቸዋለሁ)፡፡ በእኔ እምነት አገራችን አሁን ለገጠማት ቀውስ ሁሉ መነሻው ጃንሆይና መንግሥታቸው በኃይል መወገዳቸውና በእነሱ እግር የተተኩት መሪዎች ሲያራምዱት የቆዩት የተሳሳተ ርዕዮተ ዓለምና ፖለቲካ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች በመሆኑ አብዛኛው ሰው ጃንሆይን አያውቃቸውም፡፡ ነፃ ሚዲያ ባልነበረበት አገር ውስጥ ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ስለእሳቸውም ሆነ ስለመንግሥታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመንግሥት ዜና ማሠራጫዎች ሲነገረን የኖረው መጥፎ መጥፎው እየተመረጠ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም የንጉሡ ስምና ታሪክ ሆን ተብሎ እንዲደበዝዝ ተደርጓል፡፡ አሁን የተፈጠረውን ምቹ የታሪክ አጋጣሚ በመጠቀም ይህ ጉዳይ ሊስተካከል የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አበው ‹‹ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ›› እንዲሉ መጠነኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ አንዳንድ ነጥቦችን ከሥር ጀምሬ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ ጽሑፉ ለንባብ እንዲመች በንዑሳን ርዕሶች ከፋፍየዋለሁ፡፡

ጃንሆይ ወደ መሪነት ሲመጡ ኢትዮጵያ ምን ትመስል ነበር?

ጃንሆይ የአገር መሪነቱን ሥልጣን ሲረከቡ አገራችን ከዘመናዊ ሥልጣኔ እጅግ ርቃ ጨለማ ውስጥ ነበረች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸው የማይካድ ቢሆንም፣ ከነበረው ፍላጎት አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ የአገሪቱ ዋና መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር በደሳሳ ጎጆ ቤቶች የተሞላች የገጠር ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡ ከኢትዮ ጂቡቲ ባቡር በቀር ዘመናዊ መጓጓዣ ስላልነበረ ከአንዱ የአገሪቱ ክፍል ወደ ሌላው ለመጓዝ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር፡፡ የባቡሩንም ሥራ ቢሆን ምኒልክ ቢጀምሩትም ግንባታው የተጠናቀቀውና ለአገልግሎት የበቃው ጃንሆይ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡

የነበረውን ችግር በምሳሌ ላስረዳ፡፡ መቀመጫውን ዳንግላ (ጎጃም) ላይ በማድረግ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ቆንስል የነበረው አርኢ ቺስማን (RE Cheesman)፣ በ1923 ዓ.ም. በተከናወነው የጃንሆይ የንግሥ በዓል ላይ አዲስ አበባ እንዲገኝ ተጋብዞ ነበር፡፡ ከዳንግላ አዲስ አበባ ያለው ርቀት ከ500 ኪሎ ሜትር የማይበልጥና በመኪና ከአንድ ቀን በላይ የማይወስድ ቢሆንም፣ በወቅቱ መንገድ ስላልነበረና ዓባይም ድልድይ ስላልተሠራለት ጉዞውን በሱዳን በኩል ለማድረግ ተገዷል፡፡ ከብዙ አጃቢና ጓዝ ጋር በበቅሎ ከዳንግላ ተነስቶ ጋላባት (መተማ አጠገብ የምትገኝ የሱዳን የጠረፍ ከተማ) ለመድረስ ስድስት ቀናት ፈጀበት፡፡ ሱዳን በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስለነበረች ከእኛ ይልቅ የተሻለ መሠረተ ልማት ነበራትና ከጋላባት እስከ ካርቱም፣ ከዚያም እስከ ፖርት ሱዳን ድረስ በመኪናና በባቡር እያቆራረጠ ተጓዘ፡፡ ከፖርት ሱዳን በመርከብ ተሳፍሮ ጂቡቲ ገባ፡፡ ከጂቡቲ በምኒልክ ባቡር አዲስ አበባ ገባ፡፡ በግምት ከ3,000 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን አድካሚ መንገድ ከሁለት ሳምንታት በላይ ተጉዞ በዓሉ ላይ ሊገኝ ችሏል፡፡

በዚያው ዘመን አካባቢ የሆነ ሌላም ተመሳሳይ ምሳሌ ልጨምር፡፡ በቅርቡ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ሲናገሩ እንደሰማኋቸው፣ በልጅነታቸው ከእናታቸው ጋር በእግር ከአዲስ አበባ ተነስተው በወሎ በኩል አድርገው ትግራይ ለመድረስ አንድ ወር ፈጅቶባቸዋል፡፡ ልዑሉ ጨምረው እንደተናገሩትም በአንድ ወቅት አባታቸው ከአዲስ አበባ ትግራይ ለመሄድ አስበው በወሎ በኩል ያለው የእግር ጉዞ አድካሚነቱን ስለተረዱ እስከ ጂቡቲ በባቡር ሄደው፣ ቀይ ባህርን በመርከብ አቋርጠው፣ ከዚያም በኤርትራ ዞረው ከብዙ እንግልት በኋላ ካሰቡበት ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች በቅድመ ጃንሆይ አገራችን የነበረችበትን የኋላቀርነት ደረጃ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ አንድ አገር እንደ መንገድ ያሉ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ከሌሏት ስለሌላ ሥልጣኔና ልማት ማሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ በዚያ ዘመን አገራችን በትምህርት፣ በጤናና በመሳሰሉት ዘርፎች የነበሩባትን ችግሮች ሁሉ ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል መተው ይሻላል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከኋላቀርነትና ከድንቁርና የማላቀቁ ሥራ የጃንሆይ ትልቅ የቤት ሥራ እንደነበርና ትግሉ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ጃንሆይ ምን አበረከቱ?

ጃንሆይ አገሪቱ በዕድገት ጎዳና ወደፊት እንድትራመድ የዘመኑ ነባራዊ ሁኔታና አቅም በፈቀደው መጠን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ አሁን ከምናያቸው ከኮምፒዩተርና ከሞባይል ስልክ በቀር ያላደረጉት ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህች ጽሑፍ ሁሉንም ለመዘርዘር አስቸጋሪ ቢሆንም ጥቂቶችን በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት ያደረጉትን ጥረት ብንመለከት ዜሮ ከሚባል ሁኔታ ተነስተው ዩኒቨርሲቲ እስከ መክፈት ደርሰዋል፡፡ ከእኛም አልፈው የበርካታ አፍሪካ አገሮች ተማሪዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) እንዲማሩ ማድረግ ችለዋል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በየጠቅላይ ግዛቱ (ክፍለ ሀገሩ) ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡ ዝነኞቹ እነ ተፈሪ መኮንን፣ ጄኔራል ዊንጌት፣ ተግባረ ዕድ፣ እቴጌ መነን፣ ልዑል በዕደ ማርያምና የመሳሰሉት ትምህርት ቤቶች የጃንሆይ የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡ በወቅቱ ሲሰጥ የነበረው ትምህርት እጅግ ጥራቱን የጠበቀ ስለነበረ አንዳንድ የድሮ ሰዎች ‹‹ትምህርት በጃንሆይ ጊዜ ቀረ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለትምህርት ወደ ምዕራባውያን አገሮች ይላኩ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር የትምህርት ቤትን ግንባታ አሀዱ ብለው የጀመሩበትንና የበርካታ ምሁራን መፍለቂያ የነበረውን ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ያሠሩት፣ አገራቸው በልፅጋ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ ገና አልጋ ወራሽ እያሉ በራሳቸው የግል ገንዘብ ነበር፡፡ በስድስት ኪሎ ይገኝ የነበረውንና ገነተ ልዑል በመባል ይጠራ የነበረውን ቤተ መንግሥታቸውን ‹‹ልጆቼ ይማሩበት›› ብለው ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ማበርከታቸውም ለትምህርት የነበራቸውን ቅናት ይመሰክራል፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም ሆነ የስድስት ኪሎውን ቦታ ከአባታቸው የወረሱት መሬት ነው ይባላል፡፡ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪም ማይምነትን ከአገራችን ለማጥፋት የፊደል ሠራዊት የሚባል ፕሮግራም ዘርግተው ነበር፡፡ በእሳቸው መልካም ፈቃድ በርካታ የሚሲዮን ትምህርት ቤቶችም በየቦታው ለመከፈት በቅተዋል፡፡

በመጓጓዣ በኩልም ከፍተኛ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የአገሪቱ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ጋር በመኪና መንገድ ከመገናኘቷም በላይ፣ ብዙዎቹ የአገሪቱ አውራጃዎችና ወረዳዎች የመንገድ ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከጠጠር አልፎ አሰፋልት መንገዶችም ለመሥራት ተሞክሯል፡፡ በዘመናዊ ድልድይ ዕጦት ምክንያት ለዘመናት ሕዝቡን ሲያንገላቱት የኖሩት እንደ ዓባይ ያሉት ትልልቅ ወንዞቻችንም እጃቸውን እንዲሰጡ የተገደዱት በጃንሆይ ጊዜ ነው፡፡ በደጀንና በጎሐ ጽዮን መካከል ዓባይ ላይ የተገነባው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ፣ በ1942 ዓ.ም. በራሳቸው በጃንሆይ ሲመረቅ የቀረበው ግጥም ይህን የሚመሰክር ነው፡፡

ሐዘንተኛ ሆኖ ዓባይ ካፋፍ በታች

ያስተዛዝኑታል አዞና ጉማሮች

ለምን አያልቅሱ አያዝኑ ባንድነት

ከእንግዲህ አይገኝ ሰውን ዘርፎ መብላት

የግዮን ኃይልና የብዙ ወስላታ

በኃይለ ሥላሴ ዛሬ ድል ተመታ፡፡

ዛሬ የምንፈላሰስበትና የምንኮራበት ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድም በእሳቸው አርቆ አሳቢነት የተመሠረተ ነው፡፡

ጃንሆይ ‹‹አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው›› በሚለው አቋማቸው የዜጎችን ሁሉ እምነት ሲያከብሩ የነበሩ ቢሆንም፣ በተለይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትውልድ ሁሉ ሊዘክረው የሚገባው ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለ1,600 ዓመታት ያህል በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ስትተዳደር ስለነበር ኢትዮጵያውያን ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስና ፓትርያርክ እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ እነዚህ ሹመቶች ለግብፃውያን ብቻ የተጠበቁ ነበሩ፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ እጅ መንሻ እያለች ብዙ ወርቅና የተለያዩ ገጸ በረከቶችን ለግብፅ ስትሰጥ ኖራለች፡፡ ከቋንቋ ችግር ጀምሮ የተለያዩ ጋሬጣዎች ስለነበሩ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሴ ልጆች ልመራ ይገባኛል በማለት ከግብፅ ጋር ለዘመናት ክርክር ስታደርግ ብትቆይም ሊሳካ አልቻለም ነበር፡፡ በዚህ ሲቆጩ የነበሩት ጃንሆይ አልጋ ወራሽ ከሆኑ ጀምሮ ለጉዳዩ ዕልባት ለመስጠት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ጥረታቸውም ተሳክቶ የኢትዮጵያ የዘመናት ጥያቄ መልስ አገኘ፡፡ በ1921 ዓ.ም. አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያውያን የጵጵስና ማዕረግ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሉ፡፡ በ1942 ዓ.ም. ደግሞ የሊቀ ጵጵስና ሥልጣን ለኢትዮጵያ ተፈቀደላት፡፡ በመጨረሻ በ1951 ዓ.ም. የፓትርያርክነትን ሹመት አገኘት፡፡ ኢትዮጵያዊው አቡነ ባስልዮስም በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታ በታሪክ የመጀመርያው ፓትርያርክ ለመሆን በቁ፡፡ ከ1951 ዓ.ም. ጀምሮም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ተላቃ ራሷን በራሷ ማስተዳደር ጀመረች፡፡ እውነት ለመናገር ድሮ የነበረው ሁኔታ ከአገር ደኅንነት አንፃርም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በጣሊያን  ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ሸሽተው አገራቸው ሲገቡ፣ ኢትዮጵያውያኑ አቡነ ጴጥሮስ (የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ) እና አቡነ ሚካኤል (የጎሬ ጳጳስ) ለአገራቸው መስዋዕት መሆናቸው ለዚህ ምስክር ነው፡፡

ከላይ እንዳልኩት ሁሉንም ሥራዎች መዘርዘር ይከብዳል፡፡ አገራችንን ከውጭው ዓለም ጋር ማስተዋወቅ ቢባል፣ ዘመናዊ ሕክምና ማስፋፋትና በርካታ ሆስፒታሎችን መክፈት ቢባል፣ የንግድ፣ የሆቴልና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ቢባል፣ ውትድርናንና የፖሊስ ሥራን ዘመናዊ ማድረግ ቢባል፣ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይል፣ ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ማተሚያ ቤት፣ ፖስታ ቤት፣ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ወዘተ የጃንሆይ የሥራ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አልፈው በታሪካችን የመጀመርያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት ያፀደቁ ናቸው፡፡ አገራችንንም የሁለት ወደቦች ባለቤት አደርገዋት ነበር፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለውጤት ሳይበቃ ቢቀርም በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራትና የአርበኞችን ሞራል በማነሳሳት የፋሺስት ጣሊያን  ጦር ድል እንዲመታ ማድረጋቸውም የሚካድ አይደለም፡፡ አገራችንን የሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ማድረግ ችለዋል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን ማድረጋቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በውጭው ዓለም ‹‹አቢሲንያ›› በመባል ትጠራ የነበረችውን አገራችንን ‹‹ኢትዮጵያ›› በሚለው ስም በሰፊው እንድትታወቅ ያደረጉትም እሳቸው ናቸው፡፡

ከአገራችን አልፈውም ለአፍሪካ አኅጉር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አደርገዋል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) እንዲመሠረት ግንባር ቀደም ሚና ከመጫወት አልፈው ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሲማቀቁ የነበሩት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ረድተዋል፡፡ የተጣሉ አገሮችን በመሸምገልም ይታወቃሉ፡፡ በኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅትም የሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ዕውቁ የደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ አገራችን መጥቶ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና እንዲያገኝ ከመርዳት አልፈው፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዲሰጠው በማድረግ ለትግሉ የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክም ከፍተኛ ተሰሚነትና አክብሮት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. 1936 በዝነኛው ታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብለው ለመመረጥ በቅተዋል፡፡ ለኮሪያ ጦርነት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመላክ አመርቂ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ምንም እንኳን በጥቁር አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) አሸናፊነት ቢጠናቀቅም፣ እ.ኤ.አ. በ1964 ለኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት ቀርበው እስከ መጨረሻው ዙር ማጣሪያ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡

ጃንሆይ ከላይ የተዘረዘሩትን ሲሠሩ ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም፡፡ በተለይ የፋሺስት ጣሊያን ጦርነት በአገሪቱ ላይ አሳድሮት የነበረው ከፍተኛ ጫናና ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ምንጊዜም የሚረሳ አይደለም፡፡ በአምስቱ ዘመን ወቅት የተሻለ ዕውቀትና ልምድ የነበራቸው ብዙ ሰዎቻችን ተገድለዋል፡፡ ሰላማዊ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ አገሪቱ ፈራርሳ ስለነበረ እንደገና መገንባቱ እልህ አስጨራሽ ነበር፡፡ ለጣሊያን መሸነፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገችው እንግሊዝም እየዋለች እያደረች፣ በጃንሆይ መንግሥት ላይ ትፈጥረው የነበረው ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የጎረቤታችን ሶማሊያ ትንኮሳም የሚናቅ አልነበረም፡፡

በጃንሆይ ላይ የተሠራው ግፍ

የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት የሆኑት የጃንሆይ ፍፃሜ ግን እጅግ የሚያሳዝንና ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ ‹‹ክረምት ያወጣን ቤት በበጋ ያቃጥሉታል›› የሚባለው ተረት በእሳቸው ላይ ደረሰ፡፡ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሰለባ ሆኑ፡፡ ያለ በቂ ማስረጃ የወሎን ሕዝብ ሆን ብለው አስርበዋል ተብለው ተብጠለጠሉ፡፡ በርካታ ገንዘብ ሰርቀው በውጭ ባንክ ደብቀዋል ተብለው ብዙ እንግልት ደረሰባቸው፡፡ ይህን ስለማድረጋቸው ተጨባጭ መረጃ ግን የለም፡፡ ‹‹ሌባ! ሌባ!›› ተብለው በአደባባይ ተዋረዱ፡፡ በመጨረሻም የለውጡ ደጋፊ የነበሩትንና እጃቸውን በሰላም የሰጡትን ጃንሆይንና ባለሥልጣኖቻቸውን በቅናት ሲቃጠሉና በበታችነት ስሜት ሲሰቃዩ የነበሩት ደርጎች ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ያለ ፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ ገደሏቸው፡፡ አስከሬናቸውም እንደ ሰባራ ገል የትም ተወረወረ፡፡ ሕዝቡም በነገሩ የተስማማ እስኪመስል ድረስ ፀጥ አለ፡፡ ግድያውን አልተቃወመም፡፡ ውሎ አድሮ ግን የደርግ ሰይፍ ወደ ሕዝቡ ደግሞ የሚዞርበት ጊዜ መጣ፡፡ ሞት የእያንዳንዱን ሰው በር ያንኳኳ ጀመር፡፡ ‹‹በመንግሥቱ ሬሳ ጎትቱ›› ተብሎም ተተረተ፡፡ ደርግ ያደረገውን አረመኔአዊ ድርጊት ሳስታውስ በአንድ ወቅት አንድ ሰባኪ፣ ‹‹ሰው ሰይጣን ነው፣ ሰይጣንም ሰው ነው›› ሲሉ የተናገሩት ትዝ ይለኛል፡፡

ደርግ ጃንሆይን ከገደለ በኋላም የልቡ አልደረሰም፡፡ ያለ ፍርድ ቤተሰቦቻቸውን ሕፃናት ሳይቀሩ እስር ቤት ወርውሮ አሰቃያቸው፡፡ እሳቸውንም ጥላሸት ከመቀባትና ፕሮፓጋንዳውን ከመንዛት ቦዝኖላቸው አያውቅም፡፡ አሻራቸውን ከምድረ ገጽ ማጥፋቱን ተያያዘው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሮችና ሳንቲሞች ላይ ምስላቸውን አስወገደ፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸውን አፈራረሰ፣ ንብረታቸውንም ወረሰ፡፡ በእሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ሲጠሩ የነበሩት ድርጅቶችና ተቋማትም ደርጉ በመረጣቸው አዳዲስ ስሞች ተተኩ፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል የነበረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን እንጦጦ ትምህርት ቤት፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል ይባል የነበረውን የካቲት 12 ሆስፒታል፣ እቴጌ መነን ትምህርት ቤትን የካቲት 12 ትምህርት ቤት፣ ልዕልት ዘነበ ወርቅ ሆስፒታልን አለርት ሆስፒታል፣ ልዑል መኮንን ሆስፒታል ይባል የነበረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታልን ጦር ኃይሎች ሆስፒታል፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ይባል የነበረውን ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት፣ ወዘተ በማለት ተሰየሙ፡፡ ከደርግ ያመለጠ ቢኖር ቤተ መንግሥቱ አጥር ላይ በልዩ ጥበብ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› ተብለው የተቀረፁት ፊደሎች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አጥሩን ሙሉ በሙሉ ካላፈረሰው እንደማይጠፉ ስለተረዳ ነው መሰለኝ እነሱን ትቷቸዋል፡፡

ኢሕአዴግም ቢሆን ንጉሡን ከማጥላላትና ከማንቋሸሽ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ የኢሕአዴግ መሪዎች እነሱን ሞት የማይነካቸውና ሥልጣናቸውም ዘለዓለማዊ ይመስል፣ ለንጉሡ ቀብር ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲለመኑ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ መንግሥታዊ ቀብር ሥርዓት እንዲደረግ መፍቀድ ይቅርና ቀብራቸው ላይም አልተገኙም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት መድረክ ላይም በኅብረቱ ግቢ ሐውልት ይቆምላቸው ዘንድ አልተከራከሩላቸውም፡፡ እንዲያውም ተቃውመዋል ይባላል፡፡ የዘመኑ የዘር ፖለቲካ ለእሳቸውም የተረፈ ይመስላል፡፡ ለሀቅ የሚቆሙ አይጠፉምና በመጨረሻ እግዚአብሔር የጋናውን መሪ አስነሳ፡፡  

ኢትዮጵያ ከጃንሆይ በኋላ ምን ትመስላለች?

ደርግና ጥራዝ ነጠቅ ኮሙዩኒስት ተማሪዎች ጃንሆይ ሲወገዱ የአገሪቱ ችግር አብሮ ይወገዳል ብለው አስበው ነበር፡፡ እሳቸው ከጠፉ ይኼው 50 ዓመታት ሊሞላ ነው፡፡ ረሃቡና ድህነቱ ግን ከወሎም አልፎ የመላ አገሪቱ ልዩ መታወቂያ ከሆኑ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር የትየለሌ ደርሷል፡፡ የአገሪቱ ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡ የውጭ ዕዳ ሰማይ ጥግ ደርሷል፡፡ በጃንሆይ ዘመን የማይታወቀው የጎሰኝነትና የጎጠኝነት ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ አገሪቱን መስቀለኛ መንገድ ላይ ጥሏታል፡፡ የሃይማኖት ግጭቶች አድማሳቸውን እያሰፉ ነው፡፡ በስማ በለው በጃንሆይ ላይ ሲፈርድ የነበረው ትውልድም እንኳን ጥሬ ብር አግኝቶ፣ አውሮፕላንና መርከብ ሳይቀር ከእነ ነፍሱ የሚውጥ ሆኗል፡፡

ከጃንሆይ መወገድ በኋላ በአገራችን የሆነውን ነገር ሳስብ አንዳንድ ባለፀጋ ወላጆች ሲሞቱ፣ የነበራቸውን ሀብት ከማስተዳደርና ከመከፋፈል ጋር በተያያዘ በልጆቻቸው መካከል የሚነሳውን አለመግባባትና ጠብ ያስታውሰኛል፡፡ የቤቱ ምሰሶ የነበሩት ወላጆች በሥርዓት ሲመሩት የነበረው ቤትና ንብረት በአንዴ ዶግ አመድ ይሆናል፡፡ ልጆች እርስ በርሳቸው እስከ መገዳደል የሚደርሱበት ሁኔታም አለ፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አለመደማመጥ፣ አለማወቅ፣ አርቆ አለማየት፣ እኔነት፣ ስግብግብነት፣ አቅምን አለማወቅ፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአገራችን የሆነውም እንዲሁ ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት ባካበቱት ዕውቀትና ልምድ አገሪቱን በሥርዓት ሲመሯት የነበሩት ጃንሆይና ሚንስትሮቻቸው ድንገት ከተጨፈጨፉ ጀምሮ ኢትዮጵያ ጥላዋ ተገፈፈ፡፡ መደማመጥና መከባበር ጠፋ፡፡ ሁሉ ነፃ አውጪ ነኝ ባይ ሆነ፡፡ አገሪቱ ተዋረደች፡፡ መሳቂያና መሳለቂያ ሆነች፡፡ ለማኝ ሆነች፡፡ ልጆቿ ለስደትና ለባርነት ተዳረጉ፡፡ የቀን ጅቦች እንደ እንጉዳይ የፈሉባት አገር ሆነች፡፡

ከ40 ዓመት በኋላ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ስለጃንሆይ ምን አሉ?

 • ‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሞታቸውንም አላምንም እንደ ጃማይካዎች፡፡ … በእውነት ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ አንዳንዴም ጃማይካዎች የሚሉት እውነታቸውን ነው፡፡ ቅዱስነትም ይኖራቸዋል፤›› ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፡፡
 • ‹‹ኢትዮጵያ እንደሚጠበቅባት የአፍሪካ ዓይን ትሆን ዘንድ ለስሟና ለምድሪቱ ነውር የሆነባትን የንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጉዳይ በግድ ማስተካከል ይኖርባታል፤››፣ ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና፡፡
 • ‹‹የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ቢቀጥል ኖሮ እስካሁን አገራችን ሌላ ትሆን ነበር፣ ትበለፅግ ነበር፤›› ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፡፡
 • ‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ ጉቦ አይበሉ! ከሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት የተራቀቁ ናቸው፡፡ በጣም በጣም ይተው ነው የሚያርጉት ሁሉን ነገር፡፡ ደግሞም ፍርድ ያስተካክላሉ፡፡ እኔ ኦሮሞ ነኝ እንደምታወቀው፡፡ እሳቸው በዚህ ጉዳይ ምንም ስሜት የላቸውም፡፡ ምንም፡፡ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የእሳቸው ጥፋት ምንም አይታየኝም በእውነቱ፤›› ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፡፡
 • ‹‹አሁን ሳስበው . . . የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የተሻለ ነው፣ ቀጥለው ከመጡት፡፡ ቀጥለው የመጡት እኮ የውሪ አገዛዝ ነው፤›› ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፡፡
 • ‹‹እኛ ትምህርት ቤት ስንማር ጃንሆይ እንደ ንጉሥ ሆነው ሳይሆን እንደ አባታችን ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ አባባ ጃንሆይ ነበር የምንላቸው፡፡ ምቾቱ ከፍተኛ ነው፡፡ በቀን ውስጥ አምስት ጊዜ ነው ምግቡ የሚበላው፡፡ ራት በምንበላበት ሰዓት በሳምንት ሦስት አራት ቀን ጃንሆይ ይገኙ ነበር በገበታ ላይ፡፡ የምንበላውን ምግብ እንጀራውንም ሆነ ዳቦውን እየቆረሱ እንደዚህ ነው የሚበላው? እንደዚህ ነው የምታጠቅሱት ወጡን? እያሉ እሳቸው እየበሉ እየጎረሱ እኛንም እያጎረሱ ነው የተማርነው፤›› አቶ ግርማ ቸሩ፡፡
 • በዘፈኖቹ ጃንሆይን ከማወደስ ተቆጥቦ የማያውቀው ዝነኛው አቀንቃኝ ቴዲ አፍሮ ‹‹የአፍሪካ አባት›› ይላቸዋል፡፡

ምን መደረግ አለበት?

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ጃንሆይ ለአገራችን ያበረከቷቸውን ነገሮች ስንመለከት የሚያኮሩ እንጂ የሚያሳፍሩ መሪ አልነበሩም፡፡ እዚህ ላይ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ንጉሡ እንከን የሌለባቸውና ፍፁም ሰው ነበሩ እያልኩ አለመሆኑን ነው፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ኃጢያት የማይሠራ ሰው ተገኝቶ አይታወቅም፡፡ ወደፊትም አይገኝም፡፡ እያልኩ ያለሁት አጥፍተዋል ከሚባለው ይልቅ የሠሩት መልካም ሥራ እጅግ ይበልጣል ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹ነብይ በአገሩ አይከበርም›› እንደሚባለው ንቀን የጣልናቸውን ጃንሆይን ልናከብራቸውና ተገቢውን ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል እላለሁ፡፡

የጃንሆይ ጉዳይ እንደ ዋዛ ተዳፍኖ ስለመቅረቱ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ስጫወት በአሁኑ ጊዜ አገራችን በርካታ አንገብጋቢ ችግሮች እያሉባት ስላለፈና ስለሞተ ነገር መጨነቅ አያስፈልግም፣ ደግሞም ደርግ ለሠራው ጥፋት እኛን አይመለከትንም ይሉኛል፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁላችንም በደለኛ ነን እላቸዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ሁሉ ነገር ለምን ልዩ እንደሚሆን አይገባኝም እንጂ፣ ከተለያዩ አገሮች ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ፡፡ በመጀመርያ ሩሲያን ላንሳ፡፡ ሩሲያ የሶሻሊዝምና የኮሙዩኒዝም ሥርዓት ፈጣሪና አቀንቃኝ የነበረች አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1917 በሩሲያ የፈነዳውን አብዮት ተከትሎ የመጨረሻው የአገሪቱ ንጉሥ (ዛር) የነበሩት ዳግማዊ ኒኮላስ ከባለቤታቸው፣ ከአምስት ልጆቻቸው፣ ከግል ሐኪማቸውና ከቤት ሠራተኞቻቸው ጋር በአብዮተኞች በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡ አስከሬናቸውም የትም ተጣለ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የተለያዩ መሪዎች ወደ ሥልጣን ቢመጡም፣ በንጉሡና በቤተሰቦቻው ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ በይፋ ያወገዘና የኮነነ ሳይገኝ 80 ዓመታት አለፉ፡፡ የቀብር ሥርዓትም አልተደረገላቸውም፡፡

እ.ኤ.አ. በ1998 ግን ፕሬዘዳንት ቦሪስ የልሲን ይህን ጉዳይ ዕልባት ሊሰጡት ተነሱ፡፡ የንጉሡን በግፍ መገደል በዝምታ ማለፍና አለመቃወም በድርጊቱ እንደመተባበር ይቆጠራል አሉ፡፡ ይህን አሳፋሪና ጥቁር ታካችንን መዝጋት አለብን አሉ፡፡ አፅሞቹ ከተጣሉበት ተቆፍረው እንዲወጡ አዘዙ፡፡ የሐዘን ቀን አወጁ፡፡ ባንዲራዎች ዝቅ ብለው ተውለበለቡ፡፡ መንግሥታቸውንና ሕዝባቸውን በመወከል ስለተፈጸመው ግፍ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ፡፡ ከተለያዩ አገሮች የመጡ በርካታ ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት በመንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓትም እንዲቀበሩ አደረጉ፡፡ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ድርጊቱን በይፋ አውግዛ ለሟቾቹ የቅዱስነት ማዕረግ አጎናፀፈቻቸው፡፡ ዛሬ ንጉሡ ‹‹ቅዱስ ኒኮላስ›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ደስ አይልም?

ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት ከአገረ እንግሊዝ የሰማነው ዜናም ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ ከ530 ዓመታት በፊት በጦርነት ተገድሎ የነበረውን ንጉሥ ሪቻርድ ሦስተኛ (Richard III) በችኮላ ስለተቀበረ የሚገባው ክብር አልተደረገለትም ተብሎ በከፍተኛ ድካምና ወጪ አፅሙ ተፈልጎ እንዲገኝ ከተደረገ በኋላ ንጉሣውያን ቤተሰቦችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በመንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በተዘጋጀለት ቦታ በክብር እንዲያርፍ ሆኗል፡፡ ንጉሡ የነገሠው ለሁለት ዓመታት ብቻ ሲሆን፣ የሞተውም በ32 ዓመቱ ነው፡፡ እጁ በደም የተጨማለቀና ክፉ ሰው ነበር ይባላል፡፡ በዚያን ዘመን እንግሊዝ እንደ ዛሬው ሰፊና ገናና አገር አልነበረችም፡፡ ምንም ይሁን ምን የታሪካቸው አካል ነውና እንግሊዞች ለንጉሥ የሚገባውን ክብር አልነፈጉትም፡፡ ከ530 ዓመታት በፊት ለሞተ ሰው መጨነቅ ሞኝነት ይመስላል፡፡ ታሪካቸውን ማክበራቸው አሁን ላለውና ለሚመጣው ትውልድ የሚሰጠውን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡

ሩቅ ሳንሄድ አፍሪካዊቱ አገር ጋና ለክዋሜ ንክሩማህ ካደረገችው ብዙ የምንቀስማቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ፡፡ ንክሩማህ ጋናን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ያላቀቀ፣ የመጀመርያው የነፃይቱ ጋና ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት የነበረ ታላቅ ሰው ነው፡፡ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባቶች አንዱም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1966 ግን ያልታሰበ ነገር በጋና ተከሰተ፡፡ በቂ ለውጥ ለጋና አላመጣም ተብሎ በመንግሥት ሠራተኞች ድጋፍ በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ንክሩማህ ከሥልጣን ተባረረ፡፡ ለጉብኝት ውጭ አገር ስለነበረ ነው እንጂ ቢያገኙት ሊገድሉትም ይችሉ ነበር፡፡ በጎረቤት አገር ጊኒ የስደት ኑሮ ለመግፋት ተገደደ፡፡ የለፋላት አገሩንም ሁለተኛ ሳያያት እ.ኤ.አ. በ1972 በዚያው ሞተ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 ግን ሌላ አዲስና ያልተጠበቀ ዜና በዚያው በጋና ተሰማ፡፡ ወደ ሥልጣን የመጡት አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተደረገውን አውግዘው የንክሩማህን ታሪክ ከወደቀበት አነሱት፡፡ የጋና መሥራች አባት እንዲባል ከመወሰናቸውም በላይ፣ የልደት ቀኑ የአገሪቱ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አወጁ፡፡ ንክሩማህ ዛሬ በጋናም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ የሚታወቀው አጠፋ በሚባለው ጥፋት ሳይሆን በሠራው በጎ ሥራ ነው፡፡ አክራ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሰፊ ቦታ ላይ አስደናቂ ሐውልትና ልዩ የቀብር ቤት (Mausoleum) ተሠርቶለት በርካታ ሕዝብ ሲጎበኘው ይውላል፡፡ በአፍሪካ ኅብረትም ሐውልት እንደቆመለት ይታወቃል፡፡

ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በትዕቢት ተወጥረው መልካሙን ነገር በማጣመምና በማበላሸት ዘመናቸውን የሚጨርሱ መሪዎች እንዳሉ ሁሉ የተጣመመውን የሚያቃኑ፣ የወደቁትን የሚያነሱ፣ ያዘኑትን የሚያፅናኑ፣ ያለቀሱትን ዕንባ የሚጠርጉ መሪዎች ደግሞ መኖራቸውን ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ከሁለተኛው ጎራ የሚመደቡ ናቸው ብዬ አምናሁ፡፡  አንዳንድ ለውጦችን ማየት የጀመርነው እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የተመረቀው ሐውልት አፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ቢሆንም፣ ያለ መንግሥት ፈቃድ ለመሥራት የሚያዳግት ይመስለኛል፡፡ ወጪውንም ሙሉ በሙሉ መንግሥት መሸፈኑ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ በሐውልቱ ምርቃት ቀን ዶ/ር ዓብይ በሁኔታው መደሰታቸውን ከቃላቸው በላይ ፊታቸው ይመሰክር ነበር፡፡ ይህን ማድረጋቸው እሳቸውንም ሆነ መንግሥታቸውን ያስመሰግናቸዋል፡፡ ሌሎችን የሚያከብር ደግሞ ራሱም ይከበራል፡፡ በእርግጥ በዚህ የሚከፉ እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡ ቢሆንም እውነትን ተናግሮ በመሸበት ማደር ይሻላል፡፡

ማጠቃለያ

ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳንና የታሰበው ዕርቀ ሰላም የተሟላና የተሳካ እንዲሆን ቁልፍ ችግሮቻችንን ሁሉ ሊዳሰሱ ይገባልና የሚከተሉትን ሐሳቦች ለዶ/ር ዓብይና ለኮሚሽኑ በትኅትና አቀርባለሁ፡፡

 1. መንግሥት የጃንሆይንና የባለሥልጣኖቻቸውን ጉዳይ በዝምታ ከማለፍና ከማድበስበስ ወጥቶ የተደረገውን ጭፍጨፋ በይፋ እንዲያወግዝና ይቅርታ እንዲጠይቅ፣
 2. የንጉሡ አፅም ከተጣለበት ተነስቶ በተዘጋጀለት ቦታ ማረፉ ባይካድም መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ግን ተነፍጎታል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ናቸው ብቻቸውን አልቅሰው የቀበሯቸው፡፡ ስለዚህ ለንጉሥ የሚገባ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲደረግላቸው፣
 3. በተለይ እስካሁን ድረስ ስማቸው ከሕዝቡ ልብ ሊወጡ ያልቻሉትን እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፣ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት፣ ልዕልት ዘነበ ወርቅ ሆስፒታልና የመሳሰሉት ደርግ ያወጣላቸው ስሞች ተወግደው በቀድሞ ስሞቻቸው እንዲጠሩ እንዲደረግ፣
 4. የአፍሪካ ኅብረት ለጃንሆይ ሐውልት ማሠራቱ የሚያስደስት ቢሆንም፣ ሐውልቱ ለመሪዎችና እዚያ መግባት ለሚችሉ እንጂ ከአብዛኛው ሕዝብ ዕይታ የተሰወረ መሆኑ አይካድም፡፡ የቆመላቸውም ለኅብረቱ ላደረጉት ድጋፍ መታሰቢያ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ሌላ ደረጃውን የጠበቀ ሐውልት እንድታሠራላቸው እንዲደረግ (ይህ ዕውን እንዲሆን ሟቹ ፕሬዚዳንት ግርማና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ብዙ ሲደክሙ እንደነበር ይታወቃል)፣
 5. ጃንሆይን የሚያዋርዱና ጥላሸት የሚቀቡ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆሙ እንዲደረግና በተለይ በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም ውስጥ ተሰቅሎ የሚገኘው ደርግ ‹‹የወሎ ሕዝብ እየተራበ ንጉሡ የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖሩ ነበር›› ለማስባልና ለማስጠላት ይጠቀምበት የነበረው ጃንሆይ ኬክ ሲቆርሱ የሚያሳየው ፎቶ ግራፍ እንዲወገድ፡፡

በእውነት ኢትዮጵያ ልብ ብትገዛና ይህን ብታደርግ ሰበር ዜና ሆኖ በዓለም ዙሪያ ሁሉ በተነገረ ነበር፡፡ ፈጣሪ ከቁጣው በተመለሰና አገራችን ሙሉ ፈውስ ባገኘች ነበር፡፡ ቸር ያሰማን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...