Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፍጥነት መንገድ ላይ የተደረገው የታሪፍ ለውጥ በዚህ ሳምንት ይተገበራል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የሚያስተዳድረው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ያፀደቀው አዲስ የአገልግሎት ክፍያ በዚህ ሳምንት ወደ ተግባር እንደሚገባ አስታወቀ፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጭማሪ የተደረገበትን የአገልግሎት ታሪፍ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር ያስታወቀው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር፡፡ አዲሱ ታሪፍ ከመጪው ዓርብ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባዊ እንደሚደረግ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በአዲሱ የዋጋ ታሪፍ መሠረት በአንድ ጉዞ ዝቅተኛ ጭማሪ የተደረገው አምስት ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው አሥር ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ለአነስተኛ ተሽከርካሪዎች በአንድ ኪሎ ሜትር ይከፈል የነበረው 66 ሳንቲም፣ በአዲሱ ተመን መሠረት ወደ 76 ሳንቲም ከፍ መደረጉን ያመለክታል፡፡ በኪሎ ሜትር 62 ሳንቲም ይከፍሉ የነበሩ ተሽከርካሪዎችም በአዲሱ ታሪፍ መሠረት 1.05 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በታሪፉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው በጉዞ አሥር ብር ያህል ሲሆን፣ እንደ ተሽከርካሪው ዓይነት በአንድ ጉዞ አምስት ብር ጭማሪ በማከል እስከ አሥር ብር እንዲደርስ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰውም እስካሁን 70 ብር ይከፍሉ የነበሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአዲሱ ታሪፍ 80 ብር ይከፍላሉ፡፡ 

ድርጅቱ ይህንን የታሪፍ ለውጥ ያደረገበት ምክንያት ለፍጥነት መንገዱ ግንባታ የዋለውን ብድር ከመክፈል ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ የፍጥነት መንገዱ ግንባታ ከአሥራ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ለግንባታ የዋለው ገንዘብም ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ የዋጋ ማስተካከያ ስለመደረጉ በሚጠቅሰው የድርጅቱ መግለጫ ላይ፣ ‹‹ድርጅቱ የተመሠረተበትን ዓላማ ለማሳካትና ተቋሙ ያለበትን ብድር ከመክፈል አንፃር ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል በመታሰቡ ይህ የዋጋ ለውጥ ተደርጓል፤›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡  

ከዚህም ባሻገር ለዋጋ ጭማሪው ምክንያት የተባሉ ሌሎች ጉዳዮችንም ጠቅሷል፡፡ ከዋጋ ለውጡም በፊት ድርጀቱ ገቢውን እያሳደገ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የፍጥነት መንገዱ ተገልጋዮች ቁጥርና ዕለታዊ ገቢው በየዓመቱ እያደገ መምጣቱም ታይቷል፡፡

የ2011 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በማስመልከት ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ በስድስት ወራት ውስጥ ያገኘው ገቢ 131.2 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ግማሽ ዓመት አኳያ የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው አማካይ የቀን ገቢው 677,057 ብር እንደነበረም አስታውቋል፡፡ የቀን ገቢው ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ከ2007 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ ዕለታዊ ገቢው በዕጥፍ መጨመሩንና በየዕለቱ በመንገዱ የሚስተናገዱ ተሽከርካሪዎችም ከዕጥፍ በላይ መጨመሩን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. በፍጥነት መንገዱ በአማካይ በየቀኑ የተመዘገበው የተሽከርካሪዎች ፍሰት 12 ሺሕ ሲሆን፣ ዕለታዊ ገቢውም 331,494 ብር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሽከርካሪ ፍሰቱ በቀን በአማካይ ከ22 ሺሕ በላይ ሲሆን፣ የቀን አማካይ ገቢውም ወደ 677,057 ብር አድጓል፡፡

አዲሱ የዋጋ ታሪፍም እያደገ የመጣውን ዕለታዊ ገቢ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል፡፡ በክፍያ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት አዳዲስ የክፍያ መንገዶች ወደ ሥራ ሲገቡም ከፍጥነት መንገዶች የሚገኘው ገቢ ይበልጡን እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል፡፡ በመንግሥት እየተገነቡ ከሚገኙት ባሻገር ሦስት የፍጥነት የክፍያ መንገዶችን በግሉና በመንግሥት አጋርነት ለማስገንባት የአዋጭነት ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች