Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለጠለፋ መድን ኩባንያ ዳግም በተመረጡት ኃላፊ ላይ የጥቅም ግጭት ስለመኖሩ እንዲጣራለት ማዘዙ ተሰማ  

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የጠለፋ መድን ኩባንያን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩትና በቅርቡ ዳግም ለቦታው ተመርጠው የነበሩት የአቶ ኃይለ ሚካኤል ኩምሳ በድጋሚ የተመረጡበት አግባብ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጥቅም ግጭት መፈጠሩን የሚያሳይ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰማ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያን በቦርድ ሰብሳቢነት ለመምራት በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ አቶ ኃይለ ሚካኤል፣ በቦርዱ ውስጥ በድጋሚ መመረጣቸው ጥያቄ ያስነሳው በተመሳሳይ ኩባንያ ውስጥ በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የአዲሶቹን ቦርድ ተመራጮች ሹመት ከማፅደቁ በፊት በአቶ ኃይለ ሚካኤል ላይ የተነሳውን ጥያቄ የምርጫ አስፈጻሚው ማብራሪያ እንዲሰጥበት ባለፈው ሳምንት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ማብራሪያ የተጠየቀበት ደብዳቤም ለጠለፉ መድን ኩባንያው እንደደረሰው ታውቋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በአንድ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ በቦርድ አባልነት የሚያገለግል ግለሰብ በሌላ ተመሳሳይ ተቋም ውስጥ ማገለግል ስለማይችል፣ አቶ ኃይለ ሚካኤልም ‹‹አፍሪካ ሪ›› በተባለ ተፎካካሪ ኩባንያ ውስጥ በቦርድ አባልነት እያገለገሉ እንደሚገኙ የቀረበለትን መረጃ በመያዝ ብሔራዊ ባንክ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከአንድ ወር በፊት ባካሄደው የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ መሠረት፣ የአዲሶቹ ተመራጮች ሹመት ብሔራዊ ባንክ ያፀድቅለት ዘንድ ጥያቄ በማቅረብ ውጤቱን እየተጠባበቀ በሚገኝበት ወቅት ነው ገዥው ባንክ የማጣራት ጥያቄ ያቀረበበት፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከቀረቡለት ተመራጮች ውስጥ የአቶ ኃይለ ሚካኤልን ጉዳይ በመነጠል የእርሳቸው መመረጥ ጥያቄ የሚያስነሳ ስለመሆኑ በመጥቀስ አስመራጭ ኮሚቴው ማብራያ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሊሰጥ ችሏል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በተደረገው ምርጫ ኩባንያውን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ተመርጠው ሹመታቸው እንዲፀድቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ስማቸው ከተላለፈው ውስጥ ከተለያዩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡

በሕጉ መሠረት የጠለፋ ኩባንያው ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአቶ ኃይለ ሚካኤል ጉዳ የሚሰጠው ምላሽ በአፍሪካ ሪ ውስጥ በቦርድ አባልነት እያለገሉ መሆናቸውን የሚገልጽ ከሆነ፣ በሕጉ መሠረት በኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ውስጥ በቦርድ አባልነትም ሆነ በሊቀመንበርነት ለማገልገል እንደማያስችላቸው ታውቋል፡፡ ሌላው አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ ግን አቶ ኃይለ ሚካኤል ቀድሞም በአፍሪካ ሪ ውስጥ ማገልገላቸው እየታወቀ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድንን በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዴት ሊመሩ ቻሉ የሚለው ነው፡፡

 አቶ አቶ ኃይለ ሚካኤል ኩምሳ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ረዥም ዓመት በመገልገል የሚታወቁ ጉምቱ ባለሙያ ሲሆኑ፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያን በቦርድ ሊቀመንበርነት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ከሦስት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረና አገሪቷ እስከዛሬ ለጠለፋ መድን ለውጭ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ የሚከፈለውን ወጪ ለመቀነስና አገራዊ የጠለፋ መድን ኩባንያ እንዲኖር ታስቦ በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ነው፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ለውጭ የጠለፋ መድን ኩባንያዎች የሚያወጡት ወጪ በአረቦን ከሚሰበሰቡት እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ያክላል፡፡ ኩባንያው በ2010 በሒሳብ ዓመት ከ665 ሚሊዮን ብር በላይ አረቦን መሰብሰቡም ይታወቃል፡፡ በዚህ ኩባንያው ውስጥ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የተለያዩ ባንኮች ባለአክሲዮን ሆነው የመሠረቱት ሲሆን፣ ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ኩባንያው የተፈረመ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል አለው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ኩባንያ አደራጆች መሆናቸው የተጠቀሱ ግለሰቦች ለአደራጅነት ሊከፈለን ይገባናል ያሉትን ክፍያ በብሔራዊ ባንክ ውድቅ ተደርጎ፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት በማምረት ክርክር ይደረግበት የነበረው ክስ አሁንም አለመቋጨቱ ተገለጸ፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ኩባንያውን ለማቋቋም በአደረጃጀት ሲያገለግሉ የነበሩ አምስት ባለሙያዎች ለአደራጅነታችን ሊከፈለን ይገባል ያሉትን ክፍያ በብሔራዊ ባንክ አወንታዊ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ከዚህ ከብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በኋላ ክፍያ ሊፈጸምልን ይገባል ያሉት አምስቱ በአደራጅነት የተሳተፉ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች (በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ በኃላፊነት የሚሠሩት) ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው የተከራከሩበት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ክፍያው መፈጸም የለበትም በማለት ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡ ባለጉዳዮቹ በይግባኝ እንዲታይላቸው በማመልከታቸው ክርክሩ እስካሁን በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

እንደ ምንጮች ከሆነ፣ ክፍያ የጠየቁት አምስት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል ሊከፈላቸው ይገባል ተብሎ የተጠቀሰው ገንዘብ 1.6 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ይህንን የአደራጆች ክፍያ የአክሲዮን ማኅበሩ በጠቅላላ ጉባዔ ያፀደቀላቸው ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄውን ሁለት ጊዜ ውድቅ እንዳደረገው ታውቋል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አነጋጋሪ የሆነው ክስተት፣ በፍርድ ቤት ጥያቄ ያቀረቡት አካላት በኩባንያው ውስጥ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው፡፡ ከጠያቂዎቹ መካከል በአዲሱ የቦርድ ኃላፊነት ምርጫ ውስጥም የተካተቱ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች