Monday, February 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአገሪቱ የሚጠበቀው ለውጥ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ዕድገት እንዲያመጣ በተጓዳኝ መሠራት አለበት

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

በዘመናችን አንድ አገር ራሱን ችሎ ሊጓዝ የሚችለው ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋሙ ጠንካራ ሲሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት የተሻገረና ጊዜውን የጠበቀ የመከላከያ ኃይል ስላላትና ካስፈለገም ሁሉም ሕዝብ ለአገሩ ሟች ስለሚሆን፣ የአገራችንን ድንበር አላስደፈርንም፡፡ እዚህ ላይ የአገሪቱ የደኅንነትና የመረጃ ተቋምም ጠንካራ መሆኑ አገሪቱ እንዳትደፈር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ሁሌም እየተፈታተኑን ያሉትና እስካሁን መፍትሔ ያላገኘንላቸው ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ናቸው፡፡ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ኢኮኖሚው በአንፃራዊነት እያደገ ሲመጣ፣ ፖለቲካው ባለመለወጡ፣ ብዙዎቻችን ቆይቶም ቢሆን ዕድገቷን ሊገታው እንደሚችል እናስብ ነበር፡፡ ፍርኃታችን አልቀረም አሁን እያጋጠመን ያለው ይኼው ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት፣ የሕዝብ ንቅናቄ በየቦታው እየተካሄደ ነው፡፡ የዚህም ንቅናቄ ግብ ይሆናል ብሎ አብዛኛው ሕዝብ የሚጠብቀው፣ አሁን ኢትዮጵያ በያዘችው ወሰን ላይ የሚገኙ ሕዝቦች ሙሉ የሰብዓዊ መብታቸው እንደሚጠበቅ፣ ማንኛውም ዜጋ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደ መጤ ሳይቆጠር፣ ዘሩና ሃይማኖቱ ሳይጠየቅ እንደሚኖር፣ መኖር፣ መሥራት፣ መነገድ፣ ንብረት ማፍራት፣ መመረጥ፣ መምረጥ፣ ወዘተ. ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ሥፍራ የሚችል መሆኑ፣ እንደሚረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት፣ ኢትዮጵያን በተለያዩ መደቦች ፊውዳል፣ ንዑስ ከበርቴ፣ ላብ አደር፣ ሠርቶ አደር፣ ወዘተ. በብሔር አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ ብሎ በመክፈሉ፣ ቀዳሚ የሆነችውን አገር፣ ከአገሮች በዕድገት ጭራ ሁና እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ይኼ መቀጠል የለበትም፡፡ አሁን የተጀመረውን ለውጥ በማጠናከር፣ ለአንዴም፣ ለሁሌም፣ አገሪቱ አስተማማኝ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንድትገባ፣ ሁሉም ሰው ለውጡን ደግፎ የሚችለውን ማበርከት አለበት፡፡

እዚህ ላይ እኔ በፖለቲካ ሥራ ላይ ገብቼ፣ ይኼንን አቋሜን አራምዳለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ በጥቅሉ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ እንደ አንድ ሕዝብ ግን ‹‹አገሪቱ በምንም ዓይነት እንደማትከፋፈል፣ ለመከፋፈል የሚሞክሩም ካሉ፣ የጥፋት ኃይሎች በመሆን ለጊዜው ሊያስቸግሩ ቢችሉም፣ ጠንካራ ሆኖ ያለው የሕዝቡ የመከላከያ የደኅንነትና የመረጃ ተቋም ጥምረት እንደሚያሸንፉ፣ ከአገራችን ነባሪያዊ ሁኔታ በመነሳት በሙሉ ልብነት ልናገር እችላለሁ፡፡ ይኼንን የምለው እንዲያው ሳይሆን፣ በደካማ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥምረት፣ የአገሪቷን ድንበር አስከብሮ፣ ከጥንት አገሮች አንዷ እንድትሆን ማስቻሉን ስለማውቅ ነው፡፡ ለዋቢም ያህል የጣሊያንን ጦር መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጣሊያን የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀል በዘመኑ አለ የሚባለውን ዘመናዊ መሣሪያ ጭኖ ከአርባ ዓመት በኋላ ተመልሶ መጣ፡፡ አውሮፕላን አይቶ በማያውቀው ሕዝብ ላይም መርዝና እሳት በመርጨት ፈጀው፡፡ ጦርነቱ ሲከፋ ንጉሡ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ አውሮፓ ሲሄዱ ሕዝቡ የጎበዝ አለቃ እንደ ራስ አበበ አረጋይ የመሳሰሉትን በየቦታው በመምረጥ እንዲመሩት በማድረግ ጦርነቱን በማቀጣጠል ጠላትን ያርበደብዱት ጀመር፡፡ ጣሊያንና አጋሮቹ የአትዮጵያ መንግሥት ወድቋል ጣሊያን ተቆጣጥሮታል ብለው ዲስኩር ሲናገሩ፣ እነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሲልቪያ ፓንክረስት ‹‹የጣሊያኖች ወሬ ውሸት ነው፣ የአገሪቷ ጥቂት ከተሞች በጣሊያን ቁጥጥር ቢገቡም የገጠሩ ክፍል ሙሉ በሙል በሚባል ሁኔታ በእነ ራስ አበበ ቁጥጥር ሥር ነው›› በማለት የጣሊያንን ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ ሲከላከሉ፣ ሕዝቡም በአገር ውስጥ ከአርበኞች ጋራ ቆሞ በመዋጋት ከአምስት ዓመት በኋላ ‹‹ነፃነቷን ከጣሊያን ወረራ ያስጠበቀች አገር›› እንድትባል አስችለው ወራሪውን በማባረር እነሆ ለዛሬ እስረክበውናል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የመከላከያ የደኅንነትና የመረጃ ተቋም አገሪቱን በአንድነት የማስቀጠል ብቃት አለው ብዬ ስለማስብና በአሁኑ ጊዜ የተጀመረው ንቅናቄ ለአንዴም ለሁሌም ለፖለቲካው መፍትሔ ይሰጣል ብዬ ስለማምን ወደ ቀረው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ልሸጋገር፡፡

ባለፉት ዘመናት አገራችን ያልተጠቀመችባቸው ብዙ በኢኮኖሚ የማደግ ዕድል አሳልፋለች፡፡ የታሪክ ምሁሮች የሚሉት ትክክል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኔ ከወላጆቼ በአፈ ታሪክ እንደ ሰማሁትና የራሴን ግንዛቤ እንደ ወሰድኩት፣ ወደ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመለወጥ የተጀመረው፣ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መጨረሻ ዘመን ሲሆን፣ ይኼም ሊሆን የቻለው የአፄ ምኒልክ መኳንንት አውሮፓን ተመልክተው ከተመለሱ በኋላ፣ የአውሮፓን ሥልጣኔ ለንጉሡ ስለነገሯቸው፣ ንጉሡም በመደነቅ ዘመናዊ የኢኮኖሚ አውታር ለመዘርጋት ዘመናዊ ትምህርት፣ ባቡር፣ ስልክ፣ ወዘተ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አገር አስገቡ፡፡ ንጉሡም የጀመሩትን ልማት እንዳያስቀጥሉ በሽታ ስለያዛቸው ጉዞው በአጭር ተቀጨ፡፡ ከአፄ ምኒልክ ሞት በኋላ ለዓመታት የሥልጣን ሹክቻ ተካሂዶ መቋጫ ያገኘው መሳፍንቱና መኳንንቱ መክረው በአፄ ምኒልክ የተጀመረውን ሥልጣኔ ለማስቀጠል ደጃዝማች ተፈሪ መኰንንን ራስ አልጋ ወራሽ አድርገው ንግሥት ዘውዲቱን አነገሡ፡፡ አልጋ ወራሹም በኋላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው ነግሠው ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመመሥረት ሰፋፊ መሠረተ ልማቶችን ዘረጉ፡፡ ብዛት ያላቸው ሚኒስትሮችን አቋቋሙ፡፡ ዘመናዊ ወታደር ለማቋቋም መሠረት አስቀመጡ፡፡ የትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ 17 እንዳደረሱ፣ የልማት ጉዞው በጣሊያን ወረራ ተቀጨ፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ አገሪቷን መልሶ ለማረጋጋት ጊዜ ወሰደ፡፡ ይኼም ቢሆን አብዛኛው በአሁኑ ጊዜ የምንጠቀምባቸው እንደ አየር መንገድ፣ አየር ኃይል፣ የፖሊስና የጦር አካዴሚ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውኃና ዩኒቨርሲቲ፣ ወዘተ በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረቱት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው፡፡ ፖለቲካውን ስንተወው የምናገኘው ‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥልጣኔና ኢኮኖሚ ፈር ቀዳጅ ሆነው ነው›› አፄ ኃይለ ሥላሴ በዕድሜም መግፋትም ሆነ፣ የመንግሥታቸው ባህሪ ፖለቲካውን ሊያሻሽሉ ባለመቻላቸው በተለይ በ1960ዎቹ መጀመርያ እየመጣ ያለውን የእርሻና የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ዕድገት ዕድል የሚያጨናግፍ የደርግ ዘመን መጣ፡፡

ከንጉሡ ዘመን በኋላ የመጣው ደርግ በዓለም አቀፍ ርዕዮተ ዓለም ተደፍቆ፣ የአምባገነን መንግሥት ለመመሥረት ተቃዋሚም ሆነ ገለልተኛውን ሕዝብ ካለ ርኅራኄ በመጨፍጨፍ ጊዜውን አባክኖ ምንም የኢኮኖሚ ዕድገት ሳያመጣ አገሪቷ አሁን ለገባችበት ችግር መነሻ በመሆን ሄደ፡፡ የኢሕአዴግ የመጀመርያው አሥር ዓመት ለሥልጣን ማደላደሊያ የተጠቀመበት ጊዜ ሲሆን፣ ከ15 ዓመታት ወዲህ ፊቱን ወደ ልማት በማዞር በጥቅሉ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ወገኖች በፖለቲካ ዓይን እየተመለከቱ ‹‹ምንም ዕድገት የለም›› የሚሉት የፖለቲካ ጨዋታ ነው ብንል፣ በተጨባጭ ግን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደ ነበረ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ጥያቄ የሚነሳው ‹‹የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፍትሐዊ ከመሆኑ ላይ ነው›› መልሱም አሁን የመጣው የሕዝብ ንቅናቄ ከምንጮቹ አንዱ ሊሆን ችሏል፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያ ላለፉት መቶ ሃያ ዓመታት ራሷን ችላ ዘመናዊ አገር በመሆን ለመጓዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚያስፈልጋት ብታውቅም፣ በዚህ ሁሉ ዓመታት ያልተሳካላት ምክንያቱ ምንድነው የሚሆነው? በተለይ እየጀመረች የማትጨርስበት ወይም በሌላ አነጋገር የኢኮኖሚ ዕድገቱ በቀጣይነት የማይዘልቅበት ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? የሚሉትን ነቅሰን አውጥተን አሁን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በአዲስ መልክ (Reform) ቃኝተን እንለውጣለን ባልንበት ሰዓት፣ ለኢኮኖሚው ማነቆ የሆኑትን በተጓዳኝ ጎን ለጎን መፍትሔ በማበጀት፣ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዘገብ ይችላል፡፡ ከመፍትሔዎችም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሀ) መንግሥት በመንግሥትነቱ ሊቀጥል የሚችለው ኢኮኖሚውን ሲያሳድግ መሆኑን መቀበል

የመንግሥት ድርሻ በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ የአንበሳ መሆኑን ምንም ጥያቄ አያስነሳም፡፡ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የሕዝቡን ኑሮ ማሳደግ ነው፡፡ ይኼም ሊሳካ የሚችለው ኢኮኖሚው ሲያድግ ነው፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚውን አሳድጎ፣ ሰላምንና መረጋጋትን ካላመጣ በሥልጣን ላይ የተቀመጠው ካለ ሕዝብ ፈቃድ እንደሆነና ሕዝብ ሲመቸው አሽቀንጥሮ ከቤተ መንግሥት እንደሚያስወጣው መገንዘብ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት የነበሩት መንግሥታት ‹‹ደርግን፣ ፓርቲን፣ ወዘተ ከያዝኩ መንግሥቴ አይወድቅም›› በማለት ለኢኮኖሚው ዕድገት ምንም ሳይጨነቁ በመጓዛቸው ቆይቶም ቢሆን ውድቀታቸው እንዳያምር ሆኗል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሕዝቡ ፍላጎት ለመቆየትም ሆነ፣ በታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን አገሪቷን በኢኮኖሚ ማሳደግ አለበት፡፡ አሁን እያደረግን ባለው ለውጥ ላይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ስናመጣ፣ ፓርቲዎች ለሥልጣን እርስ በራሳቸው በሚወዳደሩበት ጊዜ ዋናው አጀንዳቸው ኢኮኖሚውን በማሳደግና የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጡበት መንገድ አቀያየሳቸውን ማስረዳት መቻል አለባቸው፡፡ በሥራ ዘመናቸውም ቃል የገቡትን የኢኮኖሚ ዕድገት ማከናወናቸውን የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ካላመጡም ከመንግሥት ኃላፊነት ወርደው ለሌላ ፓርቲ የመንግሥቱን ሥልጣን እንደሚያስረክቡ መቀበል አለባቸው፡፡    

ለ) መንግሥት  ቢለወጥም ልማቱ እንዳይቆም ማድረግ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በአገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ከተናገሩት ውስጥ ‹‹ሁሉንም ነገር በዜሮ ማባዛትና አፍርሶ የመገንባት አባዜ አገራችንን ወደኋላ ሲጎትት እንጂ ወደፊት ሲያራምድ አላየንም፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ እሳቸው ሊናገሩ የፈለጉት መንግሥት በተቀየረ ጊዜ ሁሌም በአዲስ እንጀምር የሚል አባዜ ተጠናውቶናል፡፡ ይኼ መቅረት አለበት ነው፡፡ አገር ዘለዓለማዊ ብትሆንም በውስጧ ግን መንግሥታት ይቀያየራሉ፡፡ ይኼንን አውቆ አንዱ መንግሥት የጀመረውን ሥራ በሚለቅበት ጊዜ ሌላው አዲስ መንግሥት ተረክቦ በመጨረስ ለዘለዓለማዊ አገር ማስረከብ ግዴታው ነው፡፡ ይኼ ልምድ በአገራችን ከዚህ በፊት ሲተገበር አላየንም፡፡ ሁሌም የተለመደው አዲስ መንግሥት ሲመጣ የኢኮኖሚ ልማቱን በማስቆም በአዲስ ለማስጀመር መሞከር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ በኢኮኖሚ እንዳናድግ አድርጎናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለዘለዓለማዊ አገር የኢኮኖሚ ዕቅድ ሲወጣ ለሃያ ሠላሳ ዓመት ነው፡፡ እነዚህ በአምስት፣ አሥር ዓመታት እየተከፋፈሉ ይተገበራሉ፡፡ መንግሥት ሲቀያየር ሊደረስበት ለታለመው ኢኮኖሚ የሚያዋጣ ፖሊሲ ይቀይራል እንጂ ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የተጀመሩ፣ ወይም የታቀዱ ልማቶችን ቀይሮ በአዲስ ለመጀመር ማሰብ እብድነት ነው፡፡ አገር የሚለማው ዕቅዶች እየተደመሩ ሲሄዱ ነው እንጂ ሲቀነሱ አይደለም፡፡  

ሐ) የመንግሥት  ሹመኞች ዋና ሥራቸው ኢኮኖሚውን ማሳደግ መሆኑን አውቀው እንዲሠሩ ማስቻል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ለአምባሳደሮች በሰጠው ቀጭን ትዕዛዝ ‹‹አምባሳደርነት መጦሪያ አይደለም፣ የምትላኩት ምን ያህል ኢንቨስተሮች እንዳመጣችሁ ነው፡›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ በዚሁ አንፃር በአገር ውስጥ ያለ ተሿሚ ‹‹ለኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ተጠያቂ መሆኑን ማወቅ አለበት›› ባለፈው እንደታየው አዲስ ሹም ሲመጣ የነበረውን የልማት መዋቅር በማፍረስ፣ በአዲስ ለመጀመር መጣር ነው፡፡ ይኼም አንድ ሹም ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የልማት ጥናት ያስጠናል፡፡ እሱ ሥራውን ለማስጀመር ደፋ ቀና እያለ ሳለ፣ በድንገት ከሥራው ገበታ ሲነሳ፣ የሚመጣው ሹም የተጠናውን ጥናት ከማስቀጠል ይቅር፣ የራሴ የሚለው ሌላ ጥናት ይጀምራል፡፡ በእንደዚህ ያለ ተናቦ ያለ መሥራት ብዙ የልማት ጥናቶች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ከተጠናቀቁ በኋላ፣ በየሹሞች መደርደሪያ (ሸልፍ) ላይ አቧራ ለብሰውና ሸረሪት ደርቶባቸው ያሉ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ በጥናት የምንካፈል ባለሙያተኞች እንደዚህ ያለ ነገር የሚያጋጥመን ብዙ ገጠሜዎች አሉን፡፡ በቅርቡ ከገጠሙን አንዱ በመንግሥት  ፖሊሲ ጥናትና ምርምር እና በስኳር ኮርፖሬሽን ትብብር ያጠናነው ጥናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመልክዓ ምድሯ አቀማመጥ ከምድር ወለል በታችና ከምድር ወለል በላይ የሚገኝባት በመሆኗ የከፍተኛ ስብስብ ሕይወት (ባዮማስ) መገኛ አገር አድርጓታል፡፡ ይኼም ማለት እንደ ሸንኮራ አገዳ የመሳሰሉትን በሰፋፊ ወንዞችና መስኖዎች የማልማት ሰፊ ዕድል አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከሸንኮራ አገዳ ስኳር ለማምረት ከ50 ዓመት በፊት በወንጂና በመተሃራ ፋብሪካ በመክፈት እንቅስቃሴ ብትጀምርም ከቅርብ ዓመታት በፊት ከዚህ ኢንዱስትሪ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን በተለያዩ ቦታዎች ፕሮጀክት ነድፋ አዝጋሚ የሆነ አፈጻጸም እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ ይኼ እንደ ዕድሜው ያላደገውን ኢንዱስትሪ በእኔ መሪነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኬሚካልና በባዮ ምሕንድስና የትምህርት ክፍል ከሚገኙ በቂ ልምድ ካላቸው መምህራንና ከአንድ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ከሚገኝ ብዙ ልምድ ካለው መሐንዲስና ቴክኖሎጂስት ጋራ በመሆን እንድናጠና መንግሥት ኃላፊነቱን ሰጠን፡፡ እኛም ይኼ ኢንዱስትሪ አገሪቷን ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ ለመሸጋገር ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል በሚል በሙሉ ስሜት ሌት ተቀን ጥናት በማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ጥናት አቀረብን፡፡ ጥናቱም በጥቅሉ የሚያሳየው ለብዙ ሚሊዮኖች ወጣቶች የሥራ ዕድል ከገበሬነት እስከ የፋብሪካ ሠራተኛነት በሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ሊፈጥር እንደሚችል (እዚህ ላይ ህንድ እስከ 50 ሚሊዮን ዜጎቿ ከሸንኮራ አገዳ እርሻ እስከ ኢንዱስትሪ በሚገኙት ውስጥ በመሥራት ኑሯቸውን እየመሩ እንደሚገኙ መጥቀስ ይቻላል)፣ አሁን ያለው ስኳርን ብቻ ማምረት ጊዜው ያለፈበት እንደሆነና፣ ከስኳር የበለጡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን የስኳር ተረፈ ምርቶች ለማምረት የአገሪቷ የስኳር ኢንዱስትሪ መለወጥ እንዳለበት፣ ይኼንን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ አገሪቷ ውስጥ የአቅም ግንባታ ሥራ በአፋጣኝ እንዲሠራ ከ15 የማያነሱ ተረፈ ምርቶች መቼ፣ በምን ያህል ወጪ፣ የት እንደሚቋቋሙ የሚያሳይ ሰነድ አዘጋጀን፡፡ ይኼንኑ ሰነድ ለማዳበር በተናጠል ለአንድ ቀን ሴሚናር በቀጥታ ለሚመለከታቸው ለስኳር ኮረፖሬሽን ሠራተኞች፣ ኃላፊዎችና ለመንግሥት ልማት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ወደፊት ምርምር በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ እንዲያደርጉ ከ40 በላይ ለሚሆኑ በአገሪቱ ለሚገኙ በምክትል የምርምር ፕሬዚዳንት ለሚመራ ልዑካን ቡድን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  በመሩት ለሚኒስትሮችና ከጉዳዩ ጋራ አግባብነት ላላቸው ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በመጨረሻም ወደ መቐለ በመሄድ በክቡር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)  ሰብሳቢነት በክልሉ ለሚገኙ ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲ መሪዎች የጥናቱን ውጤት አቀረብን፡፡ ሁሉም ይኼ ጥናት በፍጥነት ባሉት የስኳር ኢንዱስትሪዎች ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በጀት በመያዝ መተግበር እንዲጀመር መግባባት ላይ ተደረሰ፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ከአገሪቱ ከፍተኛ ሹም ከሆኑት ከአንዱ ጋራ ስናወራ ‹‹ሁለት ከፍተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስናወጣ እንዴት ይኼንን ሳናውቅ ቀረን?›› የሚል ጥያቄ ቢጠይቁኝ፣ ‹‹የኢንዱስትሪ ዕውቀት ያለንን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስለኢንዱስትሪ አቅጣጫም ሆነ ዕድገት ማን ይጠይቀናል?›› በማለት ጥያቄውን መመለሴ ትዝ ይለኛል፡፡ የዚህ ጥናት የወደፊት ዕድል ምን ሊሆን እንደሚችል ለመናገር ጊዜው አጭር ቢሆንም፣ እንደ ሌሎቹ ጥናቶች መደርደሪያ ላይ እንደሚያርፍ ግን ምልክቶች አሉ፡፡ ይኼንን ለማለት የተገደድኩት በጥናቱ ውስጥ ከተቀመጡት አንዱ የሰው ኃይል ለማዘጋጀት ብቃት አለው ብለን የመረጥነውን ዩኒቨርሲቲ በመተው፣ ምንም አቅም ከሌለው ዩኒቨርሲቲ ጋር ኮርፖሬሽኑ ተፈራረመ ተብሎ ሲነገር፣ ጥናቱ መናድ መጀመሩ የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁን ልንተገብረው በፈለግነው የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ አንድ የመንግሥት ሹም ሥራውን በሚገባ ማከናወኑ የሚለካው መሥሪያ ቤቱ ያቀደውን ሥራ በመተግበሩ እንጂ፣ እሱ የፈለገውን በመሥራት እንዳልሆነ መለመድ አለበት፡፡

መ) በየቢሮው የሚገኙትን አመራሮች  ብቃት ማሳደግ

ለአንድ ሥራ ውጤታማነት የአመራሩ ብቃት ወሳኝ ነው፡፡ ብቃት ከትምህርትና ከልምድ ይመጣል፡፡ በሚሠራበት የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ያስቀመጥነው ኃላፊ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ከሌለው፣ ፕሮጀክቱን ወይም ተቋሙን ሊመራ አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት የአንድ ተቋም ኃላፊ ለመሆን የሚያስፈልገው የወንዜ ልጅ ወይም ለፓርቲው ታማኝነቱ ብቻ ነው፡፡ ይኼ አካሄድ ሥራውን የማያውቁ፣ ብቃት የሌላቸው ግለሰቦች በየኢኮኖሚው በመሰግሰጋቸው ኢኮኖሚው የሚፈለገውን ያህል እንዲያድግ አላስቻለውም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት እናመጣለን ብለን ከተነሳን፣ ለአንደዚህ ዓይነት ሰዎች ዕድል መስጠት የለብንም፡፡

ሠ) የሠራተኛውን ብቃት ማላቅ

ኢኮኖሚው በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ (ግሎባላይዜሽን) ሥርዓት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ይኼም ማለት ምርቶች ሁሉ ዋጋቸው ተመጣጣኝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሊትር ቤንዚን ወይም አንድ ኪሎ ቃሪያ ለማምረት የሚወጣበት ዋጋ አሜሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ወደ ፊት ተቀራራቢ ይሆናል (አሁን ያለው ልዩነት በአብዛኛው የሚመጣው ከሠራተኛ ብቃት መበላለጥ የተነሳ ነው)፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሮች የዋጋ ልዩነት እንዲኖር ድንበራቸውን በማጠር ለመከላከል ቢሞክሩም፣ ወደፊት ኢኮኖሚው አሸንፎ ድንበራቸውን ያስከፍታቸዋል፡፡ ይኼንን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ቃሪያ የሚያመርተው የጀርመን ገበሬ ጉልበት ውድ ስለሆነ፣ ቃሪያን ገበሬው በውድ ልሽጥ ቢል፣ የጀርመን ነጋዴ ቃሪያ ከፖርቱጋል በርካሽ በማምጣት የጀርመንን ገበሬ ዋጋ በመስበር ከገበያ ውጭ ሊያወጣው ይችላል፡፡ ይኼም በመሆኑ ነው በአብዛኛው የአውሮፓ አገሮች የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ተመሳሳይ የሆነው፡፡ እኛ አገርም የጫማ ማምረቻ ዋጋ ከፍ በማለቱ (የአምራች ብቃት ዝቅ በማለቱ) እና በአገር ውስጥ የመሸጫው ዋጋ ከፍ በማለቱ፣ ነጋዴዎች ከቻይና ጫማ አምጥተው በማራገፋቸው፣ በአገር ውስጥ አምራቾች ሲቸገሩ እናያለን፡፡ በተመሳሳይ በአሁኑ ጊዜ የመጓጓዣ ዋጋ ወድ መሆኑ ነው እንጂ፣ አንድ ኪሎ ቃሪያ እዚህ 60 ብር የሚሸጠውን፣ ከኬንያ በ20 ብር በማምጣት ዋጋውን ማስተካከል ይቻል ነበረ፡፡ ‹‹አገሮች በነፃ ገበያ መርህ ይመሩ›› እየተባለ ግፊት የሚደረገው ይኼንን ለማምጣት ነው፡፡

በአገሮች መካከል የምርት ዋጋ ልዩነት የሚመጣው በዋናነት ከአምራች ኃይል ብቃት ጋራ በተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ የቻይናው አምራች ኃይል በቀን ሦስት የቆዳ ኮት በአሁኑ ጊዜ እያወጣ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማራው የኢትዮጵያ አምራች በቀን ሊያወጣ የሚችለው የቆዳ ኮት አንድ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያዊው አምራች ብቃቱ ከቻይናው አምራች በአንድ ሦስተኛ ያንሳል፡፡ በተመሳሳይም የሚያገኙትን ገቢ በዚሁ ማወዳደር ይቻላል፡፡ ይኼም ከቻይናው አምራች ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ ድርጅት ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ እንግዲህ ኢኮኖሚው በዓለም አቀፍ ሕግ ነው የሚተዳደረው ስንል ‹‹አገሮች በነፃ ገበያ መርህ ይመራሉ›› ማለታችን ነው፡፡ በዚህም አሸናፊ ሆኖ ለመውጣትና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ አምራች ኃይሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን ብቃት እንዲኖረው ማስቻል አለብን፡፡  

ረ) የአገር ውስጥ አልሚዎችን ማበረታታት

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የሚመሠረተው በአገር ውስጥና ከውጭ በሚመጡ አልሚዎች ነው፡፡ ይኼም ቢሆን አገሪቷ ደሃ አገር ስለሆነች፣ ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው የአገር ውስጥ አልሚዎች በተለይ በታላላቅ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ለማግኘት ችግር ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት በመጀመርያዎች የዕድገት ዓመታት ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችን ራሱ በማልማት ለአገር ውስጥ አልሚዎች ከጊዜ በኋላ ማስተላለፍ ያለበት፡፡ ይኼም እየተካሄደ መነሻ ገንዘብ ያላቸውን የአገር ውስጥ ባለሀብት፣ በከፍተኛ ደረጃ ወለዱ አነስተኛ ገንዘብ ከባንክ እንዲያገኙ በማድረግ በጣም አናሳ በሆነ ዋጋ ለግብርናና ለኢንዱስትሪ ሰፋፊ መሬትን በማቅረብ፣ የግብር ዕፎይታ ጊዜን በማራዘም፣ ከቀረጥ ነፃ የማምረቻ መሣሪያ እንዲያስገቡ በማድረግ፣ ወዘተ ወደ ኢኮኖሚው ልማት እንዲገቡ ማበረታታት አለበት፡፡ በተጨማሪ አሁን በጥቃቅንና አነስተኛ ምርት ሥራ ላይ ለሚሠለፉ ወጣቶች ብድርና ቦታ በማመቻቸት ራሳቸውን በመቻል የአገሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያግዙ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡  

ሰ) የውጭ ኢንቨስተሮችን እንዲመጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር

በአሁኑ ጊዜ የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ሊፋጠን የሚችለው ከፍተኛ ሀብት ይዘው በሚመጡ የውጭ ኢንቨስተሮች ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች ሀብት ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂንም ይዘው ስለሚመጡ ሁሉም አገር በሚያስብል ሁኔታ ይፈልጓቸዋል፡፡ ለዚህም ኢንቨስተሮች ሊሄዱበት የሚችሉበት ብዙ አማራጭ አገሮች አሏቸው፡፡ ይኼም ስላላቸው ወደ አንድ አገር ለመሄድ ብዙ ለእነሱ የሚመች መሥፈርት ያስቀምጣሉ፡፡ ከዋናው መሥፈርታቸው መካከል ለሥራ ምቹ ቦታና ትርፍ ማግኘት ይገኝበታል፡፡ ትርፍ ደግሞ ከሚያገኙበት አንዱ የአምራች ሰው ኃይል ዋጋ ውድ አለመሆኑና ይኼም በቂ የሰው ኃይሉ በቂ ሆኖ ማግኘት ነው፡፡ ይኼንንም ፍለጋ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ኢንቨስተሮች ተነቃንቀዋል፡፡ የጎርቫቾቭን ለውጥ ተከትሎ ርካሽ ጉልበት ፍለጋ በ1990ዎቹ መጀመርያ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ኢንቨስትመንቱ ፈሰሰ፡፡ አሥር ዓመት በማይሞላው ጊዜ ውስጥ የምሥራቅ አውሮፓ ሠራተኛ ጉልበቴ አይበዘበዝም እንደ ምዕራብ አውሮፓውያኖቹ ይከፈለኝ ብሎ አስቸገራቸው፡፡ ጥያቄው እየበዛ ሲያስቸግራቸው ጠቅልለው ወደ እስያ ማለት ቬትናም፣ ካምቦዲያ፣ ወዘተ በተለይ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ አልባሳት ላይ የተሰማሩት ኢንቨስተሮች አመሩ፡፡ በዚህም ለምሳሌ ቬትናም 40 በመቶ የዓለም የቆዳ ጫማ አቅራቢ እንድትሆን አስቻላት፡፡ ኢንቨስተሮች በዚያም አልረኩም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀጣይ የፍልሰት ቦታቸው አፍሪካ እንደምትሆን ምልክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ከመጀመርያ ተመራጭ አገሮች አንዷ ልትሆን የምትችለው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለዚህም በቂ ምክንያት ለኢንቨስተሮቹ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ኢትዮጵያ፣ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ትልቅ አገር መሆኗ፣ የሚሠለጥን በቂ ወጣት ኃይል በአገሪቷ ውስጥ መኖሩ፣ ለአውሮፓም ሆነ ለእስያ ገበያ ቅርብ መሆኗ፣ የውጭ ገበያ እንኳ ቢጠፋ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ካደገ በቂ ገበያ በአገሪቱ ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችል (ምሳሌ የመቶ ሚሊዮን ጫማ ገበያ ሊኖር እንደሚችል) ይገኙበታል፡፡

አገራችንም የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ አቅሟ የፈቀደውን የተሟላ እንኳ ባይሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሳይቀር በመገንባት ጥረት ታደርጋለች፡፡ ግን ይኼ ሁሉ ተደርጎ ኢንቨስተሮች በብዛት መጥተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በአንድ ወቅት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በምሠራበት ጊዜ ለምን ቬትናሞች ከእኛ የበለጠ ኢንቨስተሮችን ሳቡ? ብዬ ለማጥናት ተነሳሁ፡፡ ለዚህም እንዲረዳኝ የቬትናምን ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ፖሊሲና አሠራር ጽሕፈት ቤቱ ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው ድጋፍ፣ ወዘተ አጠናሁ፡፡ በተጓዳኝም የእኛንም አጠናሁ፡፡ ከጽሑፎቹ እንደተረዳሁት በፖሊሲውም ሆነ በድጋፉ ዓይነት ብዙም ለውጥ የለም፡፡ ልዩነት ያለው አተገባበሩ ላይ ነው፡፡ ቬትናሞች የጻፉትን ከላይ እስከ ታች ያሉት አስተግባሪ አካላት በትክክል ይፈጽሙታል፡፡ እኛጋ በሚመጣበት ጊዜ ሹሙ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ሌላው ሠራተኛ ወይም ያለውን ፖሊሲና ድጋፍ አያውቀውም፣ ቢያውቀውም ፖሊሲውንና ድጋፉን ለመፈጸም ኢንቨስተሩን ያንገላታል ወይም ጉቦ ይፈልጋል፡፡ ይኼም አሠራራቸው ነው የፈለግነውን ያህል ኢንቨስተሮችን ልናገኝ ያልቻልነው፡፡ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው ማደግ እንደ ሞተር ልንጠቀምባቸው የምንችለውን የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ ጋሬጣዎቹን በማንሳት  ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡

ሸ) ሰላም በአገሪቱ ማስፈን

ፖለቲካና ኢኮኖሚ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የምንለው፣ ሁለቱ የተቆራኙ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ በአገሪቱ ፍፁም ዴሞክራሲ ከሰፈነ የአኮኖሚ ዕድገት ሊከተል ይችላል የሚለውን እንደ መርህ ብንወስድ፣ በሌላ በኩል አንዳንድ አምባገነኖች በአንዳንድ አገሮች ካለዴሞክራሲ ኢኮኖሚ እንዳሳደጉ ይታወቃል፡፡ እዚህ ላይ አንዱ ችግር ፍፁም ዴሞክራሲ ስንል ምን ማለታችን ነው? መቼስ ነው የሚመጣው? አገሮችስ ይደርሱበታል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይኼነው የሚለውን መሥፈርት ላይ አለመስማማታችን ነው፡፡ አሜሪካ የዴሞክራሲ አገር ነኝ ካለች 200 ዓመት አልፏታል፡፡ ዴሞክራሲንም የማስጠብቅ አገር ነኝ ብላ ስትናገር፣ በሌላ በኩል ግን አሁንም የፍፁም ዴሞክራሲ ደረጃ እንዳልደረሰች መሪዎቿ ሳይቀሩ ይመሰክራሉ፡፡ እያንዳንዱ አገር በራሱ መሥፈርት እየወሰደ፣ መንግሥቴ ዴሞክራሲዊ ነው ይላል፡፡ ከላይ ያየነው ዕድገት ያመጣው አምባገነንም በአገሬ ዴሞክራሲ አለ ይላል፡፡ አንድ ነገር ሊያስማማን የሚችለው ዴሞክራሲን ለማሳደግ የመንግሥቱ ሥርዓትና የሕዝብ ዕውቀት ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ በኩል ዴሞክራሲና ኢኮኖሚ ጎን ለጎን መሄዳቸው፣ አንድን አገር ወደ አስተማማኝ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ የዴሞክራሲ መጎልበት ደግሞ ዞሮ ማቀንቀኛው ሰላም ነው፡፡ በአውሮፓ ከ70 ዓመታት በፊት በየአገሩ ጦርነት ብቻ ነበር፡፡ ሁለት የዓለም ጦርነቶች ተካሂዶባቸዋል፡፡ ከሰባ ዓመት ወዲህ ኢኮኖሚውን ስላሳደጉ፣ ሰላም በሁሉም አገር ሰፈነ፡፡ ኢኮኖሚው በመተሳሰሩ አንዱ ጋ ጦርነት ቢጫር ሌላው ጋ ሰላም አሳጥቶ ኢኮኖሚውን ሊያናጋ ስለሚችል፣ ሁሉም ተባብሮ ኢኮኖሚውን ለማስጠበቅ ሰላሙን ይሻል፡፡ ወደ አገራችን መለስ ስንል፣ ሕዝብ ለሕዝበ አይጣላም እንላለን፡፡ አባባሉ ትክክል የሚሆነው እስካልተራበ ድረስ ነው፡፡ ድህነት እስካለ ድረስ አንዱ ለመቀማት፣ ሌላው እንዳይቀማ፣ ወይም ለእኔ አይበቃኝም፣ ከአካባቢዬ ተነስ፣ ወዘተ የሚሉት ይመጣሉ፡፡ ሁሉም ተርፎት ጠግቦ የሚያድር ከሆነ ወይም ሁሉም የራሴ የሚለው ሥራ ካለው ማንም ከማንም አይጣላም፡፡ እንግዲህ ላለፉት አራት ዓመታት በአገራችን ሰላም የታጣው ዋናው ምክንያት ምንጩ ድህነት ወይም ሁሉንም የሚያሳትፍ የኢኮኖሚ ዕድገት አለመኖሩ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር ሰላም ይፈልጋል፡፡ ሰላም በመታጣቱ አገሪቷ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ እየደረሰባት ነው፡፡ ስለዚህ አስተማማኝ ኢንቨስተሮች መጥተው ኢኮኖሚው እንዲያድግ በአገሪቱ ሰላም መኖሩ ከሁሉም በላይ ግዴታ ነው፡፡

ማጠቃለያ

አንድን አገር ለማስቀጠል የአራት መሠረታዊ ነገሮች ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋሙ ጥምረት አስፈላጊ ነው፡፡ ከእነዚህ ጥምረቶች አንዳቸው ከጎደሉ አገሪቷ የመቀጠሏ አስተማማኝነት ሁል ጊዜ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በምንመጣበት ጊዜ የሕዝቡ የመከላከያና የደኅንነት ተቋሙ ጥምረት፣ ዘመን የፈጀ ስለሆነ ይኼንኑ ጥምረት በማስቀጠል የአገራችንን ህልውና ካለን ነባራዊ ሁኔታ አደጋ ይደረስበታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ፖለቲካውም ፍፁም ዴሞክራሲ የነገሠበት፣ የሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ ሁሉም የአገሪቷ ዜጎች እኩል መብታቸው የሚረጋገጥበት፣ እኩል የምርጫ ካርድ የሚይዙበት ለማድረግ እልህ አስጨራሽ ትግል እየተካሄደ ስለሆነ ይኼም በድል ይጠናቀቃል የሚል ግንዛቤ በመውሰድ ቀሪው አገርን በተደላደለ ለማስቀጠል አስፈላጊ የሆነውን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ ከፖለቲካው ትግል ጋራ በተጓዳኝ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የኢኮኖሚ  ዕድገት ለማምጣት ችግሮቹን ነቅሰን አውጥተን መፍትሔ መፈለግ አለብን፡፡ ከችግሮቹም በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል፣ መንግሥት ስለኢኮኖሚው ማደግ ደንታ ቢስ መሆን፣ መንግሥት  በተለወጠ ቁጥር ኢኮኖሚውን በአዲስ ለመጀመር መሞከር፣ የመንግሥት ሹመኞች ዋና ሥራቸው ኢኮኖሚውን ማሳደግ መሆኑን አለማወቅ፣ በየቢሮው የሚገኙት አመራሮችና ሠራተኞች  ብቃት አናሳ መሆን፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን በበቂ ሁኔታ አለማበረታታት፣ የሰላም ዕጦት፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ችግሮች በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ በዳሰሳው ለይ የቀረበውን አክለንበት በማስተካከል አሁን ከሚካሄደው የፖለቲካ ለውጥ ጋራ በመደረብ ከሠራን በኢኮኖሚ የምታድግ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ልንመሠርት እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ (/ር፣ ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bela[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles