Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመምህራንና የትምህርት አመራር ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

የመምህራንና የትምህርት አመራር ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

ቀን:

ለመምህራን ሥልጠና የሚመለመሉት 12ኛ ክፍል የጨረሱ ብቻ ይሆናሉ

የመምህራንን መብት ለማስጠበቅም ሆነ በመማር ማስተማሩ ሥርዓት ላይ ያሉ ግድፈቶችን ነቅሶ በማውጣትና ለመንግሥት በማሳወቅ ረገድ የነበረውን የተንዛዛ ምልልስ ያስቀራል የተባለ የመምህራንና የትምህርት አመራር ኮሚሽን ሊቋቋም ነው፡፡

የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እያከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ‹‹የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን›› እንዲቋቋም መንግሥትን መጠየቁን ተከትሎ፣ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ የመምህራንና የትምህርት አመራር ኮሚሽን እንደሚቋቋም የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ባለፉት ዓመታት በመማር ማስተማሩ ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ምክረ ሐሳብ የሰጠ ሲሆን፣  በምክረ ሐሳቡም የመምህራን ኮሚሽን መቋቋም ለመማር ማስተማሩ ሒደት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አሳይቷል፡፡

ዶ/ር ጥላዬ እንዳሉት፣ የመምህራንና ትምህርት አመራር ኮሚሽን ለማቋቋም አስተዳደራዊ ሥራው በሚኒስቴሩ በኩል እየተከናወነ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ሲገባም የመምህራንን ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ ከመምህራን ምልመላ እስከ ስንብት ያለውን የሚሠራ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር 30ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት፣ ማኅበሩ የአደረጃጀትና የመደራደር አቅምን አስመልክቶ ባሳለፈው ውሳኔ፣ የአባላቱን መብትና ጥቅማ ጥቅም ለማስከበርና ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሲሠራ መቆየቱን አስታውሷል፡፡

እንደየዘመኑ ሁኔታና እንደ ሚኒስቴሩ አመራሮች አድማጭነት በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራት መፈጸሙን፣ ነገር ግን በመምህራን ጥቅማ ጥቅሞች ዙሪያ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መግባባት ላይ የደረሰበት አጀንዳ ለሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት ሲቀርብ አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች በሲቪል ሰርቪስ በኩል እየተቀነሱ ለአስፈጻሚ የሚቀርቡበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡

ይህ ሁኔታ እንደማያስኬድ የገለጹት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ በንቲ፣ በምሳሌነትም የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የደረጃ ከፍታ ዘጠኝ ሆኖ ሳለ መምህራን የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ቢሆኑም የደረጃ ዕድገታቸው እስከ ስድስት ብቻ ተገድቦ መቆየቱን፣ እንደሌሎች ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ሁሉ ደረጃቸው እስከ ዘጠኝ ከፍ እንዲል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በ2003 ዓ.ም. ቢስማሙም፣ በወቅቱ አጠራር የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም. አንድ ደረጃ ብቻ ከፍ በማድረግ ለመንግሥት አቅርቦ እንዲፀድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ይኼን ቅሬታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቀርቦና በወቅቱ ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ደግፈውት የመምህራን ደረጃ ከአምስት ዓመት በኋላ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ወደ ደረጃ ዘጠኝ ሊያድግ ቢችልም፣ ጥር 2009 ዓ.ም. የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ መምህራኑን ያላሳተፈ ነበር፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ የመምህሩን ጉዳይ በቀጥታ ለካቢኔ የሚያቀርብ አካል መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና በሌሎችም አገሮች “Teachers’ Service Commission” የሚል ስያሜ ያለው ከመምህራን ማኅበር ጋር በመደራደር የድርድሩን ውጤት ለካቢኔ እንዲቋቋም፣ የሚያቀርብ መንግሥታዊ ተቋም አላቸው፡፡

የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ተቋም በኢትዮጵያ የመምህርነትን ሙያና ልዩ ባህሪ የሚገነዘብ፣ የመምህራንን ቅጥር የሚያፀድቅ፣ የሚያሰናብት፣ ደረጃ የሚያወጣና በአጠቃላይ የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤትን ተግባር የሚያከናውን የመምህራን አገልግሎት ኮሚሽን (ኤጀንሲ) እንዲቋቋምና ማኅበሩም በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት የመደራደር መብት እንዲኖረው እንዲደረግም ምክር ቤቱ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

ይህ ጥያቄ መልስ ማግኘቱን ዶ/ር ጥላዬ ሲገልጹ፣ በሦስት ወር ውስጥ ይቋቋማል የተባለው ኮሚሽን የመምህራንን ችግር እንደሚፈታ፣ የማኅበሩም የመደራደር አቅም እንደሚጠናከር፣ ከዚህ ቀደም ዓመታት ይፈጁ የነበሩ ጉዳዮችም በጥቂት ጊዜ እንዲያልቁ እንደሚረዳ ደግሞ አቶ ዮሐንስ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም፣ ከዚህ ቀደም ሲተችና ማኅበሩም ሲቃወመው የከረመውን የመምህራን ትምህርት ምልመላ ከ10ኛ ክፍል መሆንና ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ወደሙያው መመደባቸውን በተመለከተ፣ ከዚህ በኋላ ይህ አሠራር እንደሚቀር ዶ/ር ጥላዬ አስታውቀዋል፡፡

ለትምህርት ጥራት መውደቅ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል የተባለው የቀደመው የመምህራን ምልመላ፣ ከ12ኛ ክፍል እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

ተማሪዎች 18 ዓመት እስኪሆናቸው በመደበኛ ትምህርት እንዲቆዩ፣ 12ኛ ከጨረሱ በኋላም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚገቡ፣ ወደ መምህርነት ትምህርት ዘርፍ የሚገቡትም ከተመረቁ በኋላ በሥራ ዓለም ላይም በየጊዜው ሥልጠና እንደሚኖር ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ