Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲዘከር

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲዘከር

ቀን:

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለዕርቅና ለሰላም ግንባታ፣ ለዘላቂ ልማት ዕገዛና ለመሠረተ ትምህርት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ይገልጻል፡፡

ዩኔስኮ ይህንን ያስታወቀው 20ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን አስመልክቶ ለአባል አገሮች ባስተላለፈው መልዕክት ነው፡፡

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት እንደተገለጸው፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመሠረተ ትምህርት ውጤታማነት አራቱን የሒሳብ ሥሌቶች ደግሞ በቀላሉ ለማስጨበጥ ያስችላል፡፡

- Advertisement -

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብዝኃነትንና ማንነትን ከማጠናከር ባሻገር የዕውቀትና የአዳዲስ ሐሳቦች መፍለቂ ምንጭ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከዓለም ሕዝብ መካከል 40 ከመቶ ያህሉ ሊረዳው በሚችለው ወይም በሚገባው የአፍ መፍቻ ቋንቋው የመማር ዕድል አላጋጠመውም፡፡   

በዓለም ውስጥ 370 ሚሊዮን አገር በቀል ነዋሪዎች (ኢንዲጂነስ ፒፕል) እና 7,000 የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዳሉ፣ ከቋንቋዎቹም መካከል ስድስት ከመቶ ያህሉ እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወይም ከአጠቃላዩ ከዓለም ሕዝብ መካከል 94 ከመቶ የሚሆኑ ተናጋሪዎች አሏቸው፡፡

የአነስተኛ (ሕዳጣን) ጎሳዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፉ ሲሆን፣ ከመጥፋት ከዳኑት ቋንቋዎች መካከልም ግማሽ ያህሉ 10,000፣ ሩብ የሚሆኑት ደግሞ 1,000 ተናጋሪዎች እንዳላቸው፣ በ1980ዎቹ ውስጥ ብቻ በየሁለት ሳምንት አንድ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ይጠፋ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ፕሬዚዳንት ጽጌ ገብረ ማርያም (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመልካም ተግባቦትና ሕፃናት ባህላቸውንና ቅርሶቻቸውን አውቀው ዋጋ እንዲሰጡ የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በሥነ ቃልና በሕፃናት የትምህርት አቀባበል ላይም የተለየ ሚና ይኖረዋል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ80 በላይ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል ወደ 51 የሚጠጉት ቋንቋዎች በመጀመርያ ደረጃና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለሚሰጡ ትምህርቶች በመማርያነት እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱም ሕገ መንግሥት ለሁሉም የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ዕውቅና መስጠቱን ገልጸው፣ የክልል መንግሥታትና የዞን መስተዳድሮች የየአካባቢዎቻቸውን ቋንቋዎች ለሥራ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ፕሮፌሰር ጽጌ ተናግረዋል፡፡  

አካዴሚውም በእንግሊዝኛ የተጻፉ 12,000 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላትን ወደ አማርኛ የመተርጎሙን ሥራ እንደጀመረ የቃላቱ መተርጎም ለኮሌጆችና ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጠቀሜታ እንዳላቸው ፕሮፌሰሩ አክለዋል፡፡

አካዴሚው የትርጉሙን ሥራ እያከናወነ ያለው ከኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ከልማት አጋሮች ጋር በመተጋገዝ የትርጉም ተቋም የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው፣ ለዕቅዱም ከዓለም አቀፍ የቋንቋ ትርጉምና የዕውቀት ማዕከላት እንዲሁም በቋንቋ ስፔሻላይዝድ ካደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እንዳሰበ አስረድተዋል፡፡ ለሐሳቡም ስኬታማነት የልማት አጋሮች የዩኔስኮና የተለያዩ አገሮች የዲፕሎማቲክ አባላት ዕገዛና ትብብር እንዳይለየው ፕሮፌሰር ጽጌ ተማጽነዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሚስተር ሙኒር ኢስላም የአፍ መፍቻ ቋንቋ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዴት ለማግኘት እንደቻለ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ እንደ አምባሳደሩ፣ የባንግላዴሽ ሕዝብ፣ ‹‹ባንግላ›› ጎረቤት የሆነው የፓኪስታን ሕዝብ ‹‹ባንግላ›› እና ‹‹ኡርዱ›› ቋንቋዎች ተናጋሪ ናቸው፡፡ ከአጠቃላዩ የፓኪስታን ሕዝብ መካከል ደግሞ 56 ከመቶ በላይ የሆነውና በምሥራቅ ፓኪስታን የሚኖረው ሕዝብ ‹‹ባንግላ›› ተናጋሪ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፓኪስታን በ1939 ዓ.ም. ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ተላቅቃ ነፃ በወጣች ማግሥት የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ‹‹ኡርዱ›› እንዲሆን ተወሰነ፡፡

ይህንንም ውሳኔ የተቃወሙ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የካቲት 15 ቀን 1944 ዓ.ም. አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ገለጹ፡፡ በዚህም ተቃውሞ ላይ ‹‹ባንግላ›› ቋንቋ ‹‹ከኡርዱ›› ቋንቋ ጋር እኩል ተቀባይነት እንዲኖረውና ሁለቱም ቋንቋዎች የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋዎች እንዲሆኑ መጠየቃቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

አደባባይ የወጡትን ተማሪዎች ለመበተን ከፀጥታ ኃይሎች በተከፈተው ተኩስ በርካታ ተማሪዎች እንደተገደሉ፣ ይህም በዓለም ውስጥ ለአፍ መፍቻ ቋንቋ የተከፈለ የመጀመርያው መስዋዕትነት ሆኖ መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በባንግላዴሽ በየዓመቱ ይህ ቀን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ሆኖ ሲታሰብ እንደዋለ፣ በመካከሉም ዩኔስኮ ይህ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹ኢንተርናሽናል ማዘር ላንጉጅ ደይ›› (ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን) ሆኖ እንዲውል በ1991 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በውሳኔውም መሠረት ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ የካቲት 15 ቀን በመላው ዓለም እየታሰበ እንደሚውል፣ ቀኑም የሚታሰበው የሕዝቡን የሥነ ቃል፣ የባህል ብዝኃነትና የአፍ መፍቻ ቋንቋዎችን ግንዛቤ በማጎልበት መሆኑን አምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ዮሚኮ ዩከዚኪ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዩኔስኮ በመላው ዓለም የሚገኙ የቅድመ መደበኛና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሕፃናትን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲያስተምሩ ያበረታታል፤›› ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሰው (ዶ/ር) ‹‹የእያንዳንዱን ሰው ውስጣዊ ስሜት፣ ትክክለኛ ዕውነትና የራስን ማንነት ለመግለጽ የሚቻለው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአካዴሚው፣ በዩኔስኮ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ካፐሲቲ ቢዩልዲንግ ኢን አፍሪካና በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ ኤምባሲ ትብብር በተከናወነው በዚሁ ሥነ ሥርዓት የልዩ ልዩ አገሮች ባህላዊ ዘፈኖች፣ ውዝዋዜዎች፣ ግጥሞች መነባንቦችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቀርበው ታዳሚዎችን አዝናንተዋል፡፡

ዝግጅታቸውን ካቀረቡት መካከል በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የህንድ፣ የኢራን፣ የየመን፣ የባንግላዴሽ፣ የአዘርባጃን፣ የሩሲያ፣ የፖርቱጋል፣ የስፔን፣ የቻይናና የጃፓን ኮሙዩኒቴ አባላት ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...