በአንዳርጋቸው አሰግድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕለት በስዊዘርላንድ ዴቮስ በየዓመቱ በሚካሄደው የመሪዎችና የከፍተኛ ባለሀብቶች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ መደመር “የታደሰው የኢትዮጵያ ራዕይ” (Renewed Ethiopian Vision) እንደሆነ አስታወቁ:: “የታደሰውን ራዕይ” “ፍልስፍና”፣ “ሪፎርም” እያሉ ገልጸውታል። አስተዳደራቸው “ሕዝብ ተኮር” (Peoples Centered) አመራር የሚሰጥ እንደሚሆንም አያይዘው አስምረዋል። ይሁንና ቀጥለው አንዳንድ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ እንደሚዛወሩ ሲዘረዝሩና ስለየ ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የጎራ ለውጥ (Strategic Repositioning) ጣል ሲያደርጉ፣ 85 በመቶውን ሕዝብ ለሚመለከተው የግብርና ዘርፍ ስለሚሰጡት “ሕዝብ ተኮር” አመራር ሳይነሱ አልፈዋል። በካፒታልና በኢንዱስትሪ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ስለመረጡ ይሆናል።
ለማንኛውም፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) “የታደሰው የኢትዮጵያ ራዕይ” ያሉትንና የአስተዳደራቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂካዊ ጎራ ለውጥ ጉዳይ ራሱን “የዓለም ማኅበረሰብ” እያለ ከሚጠራው የሀብታም አገሮች መሪዎችና የዓለም ከፍተኛ ባለሀብቶች ፊት ለማወጅ መምረጣቸው በራሱ አስደማሚ ነው። ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በእነዚህ የዲቮስ ታዳሚዎች ፊት ስትራቴጂካዊ የጎራ ለውጥ በማለት ጣል ያደረጉትን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጥር 21 ቀን ለምክር ቤቱ ባደረጉት ገለጻ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ አሁንም በገለልተኝነት መርህ እንደሚመራ፤›› አስረግጠው ባያሳውቁ ኑሮም አዲስ ርዕስ በተከፈተ ነበር።
ለማንኛውም በዛሬው የካፒታሊስትና የሶሻሊስት ጎራዎች የሚባሉ በሌሉበትና የፋይናንስ ካፒታልና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ገዥ በሆኑበት ዓለም ውስጥ፣ የስትራቴጂካዊ ጎራ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳበት ምክንያት የለም። ወይም ለደሃ አገሮች ዛሬ ያለው ምርጫ ብሔራዊ ነፃነታቸውን ባስጠበቀና ባረጋገጠ ፖሊሲ ከማንም ጋራ መወዳጀትና ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅ መሟሟት ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕና የአሜሪካ “ዓለም አቀፍ” የገንዘብ ድረጅቶች አገሮች በእሳቸው በአሜሪካንና በቻይና መካከል ምርጫ እንዲያደርጉ መጫናቸው፣ ይኼንን ለደሃ አገሮች የህልውና ጥያቄ የሆነ ጉዳይ ሊያስለውጥ አይችልም። የአሜሪካ አገሮች የሚባሉትን የምዕራብ አውሮፓ አገሮችን ጨምሮ በርካታ ሌሎች አገሮች በተቃራኒው ያቀኑትም፣ ከቻይና ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ማጠናከር ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‘እንደዚህ ከሆነማ’ በማለት ይመስላል፣ ትኩረታቸውን ‘ደሃ አገሮች የግዳቸውን ይቀበላሉ’ ብለው ወዳሰቧቸው የአፍሪካ አገሮች አዞሩ። በመጋቢት 2010 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሬክስ ቲለርሰንን ወደ ኢትዮጵያ፣ ቻድ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያና ናይጄሪያ ልከው፣ ስለተንኮለኛዋና ክፉዋ ቻይና አሰብኩ። ቲለርሰን ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ተሰናብተው ጉዳዩ ለጊዜው በዚሁ ቆመ። ቲለርሰን በአዲስ አበባ በጉብኝታቸው ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ ያፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ 567 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበርና የቻይናው 15 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሳያነሱ ነበር፡፡ ቻይና ስለምትፈጽምብን “በደልና ግፍ” አጥተው የተመለሱት። እንደዚሁም፣ ‹‹ኢትዮጵያ የአሜሪካ ፀረ ሽብር ትግል ስትራቴጂክ ወዳጅ፤›› እንደሆነች ሳትታክት የምታስታውቀው አሜሪካ፣ ከኢትዮጵያ ጋራ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከጀመረችበት ከ1895 ዓ.ም. ጀምሮ ለ124 ዓመታት ያልገነባችውን መሠረተ ልማትና ኢንዱስትሪዎች ቻይና በ10 ዓመታት ውስጥ እንደገነባች አላነሱም።
ነገሩ ሊዌንግራፍ ‹‹አፍሪካን ለመቀራመት አዲሱ የኃያልን እሽቅድድም›› በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ እንዳለው፣ አፍሪካን ለሁለተኛ ጊዜ ለመቀራመት የሚካሄድ ሩጫ ነበር (Lee Wengraf፣ Extracting Profit: Imperialism, Neoliberalism and The New Scramble for Africa፣ 2016)። የ19’ኛውን ክፍለ ዘመን እሽቅድድም በጉንደት፣ ጉራና በዓድዋ ሕዝባዊ ድሎቿ የሸኘችው ኢትዮጵያ፣ እኛን አፍሪካዊያንን ‹‹ለመብላት፣ ለማሳረርና ለመገዳደል የሚተጉ ሰነፍ ደደቦች፤›› (“Lazy Fools Only Good at Eating, Lovemaking and Thuggery”) ብሎ ለዘለፈው ለትራምፕ አስተዳደር የምትንበረከክ መሆን የለባትም። የመቅደላው ቴዎድሮስ ‹‹እንኳንስ ሕዝቡና ምድሪቱ ለወራሪ እንዳትገዛ!›› በማለት በ1860 ዓ.ም. ያቆመው ብሔራዊ አደራ፣ ዛሬም በኢትዮጵያ ተራሮችና ሸለቆዎች ከፍ ብሎ እንዲስተጋባና እንዲጠበቅ ይገባል።
ዶ/ር ወርቅነህ የኢትዮጵያ በ1994 ዓ.ም. (2002 ዓ.ም.) የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ፀጥታ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመከለስ ላይ እንደሚገኝ በጥር 21 ቀን ንግግራቸው ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል። የረጅም ጊዜው ዲፕሎማት ተከዳ ዓለሙ (ዶ/ር) ‹‹የ1994 ዓ.ም. ሰነድ የመነሻ ትኩረት የአገሪቱ ውስጣዊ ሁኔታ ነበር››፡፡ ያሉትን መሠረታዊ የስትራቴጂና የፖሊሲ ጉዳይ መነሻቸው እንደሚያደርጉ ተስፋ ይደረጋል (Dr. Tekeda Alemu፣ The Conundrum of Present Ethiopian Foreign Policy፣ Cdrc፣ January 2019፣ Vol.4 No 1)።
ይኼ መሠረታዊ ጉዳይ በዚሁ ይቆይና ዶ/ር ዓብይ በዴቮሱ ንግግራቸው “የመደመር ሦስት ምሰሳዎች” በማለት ከዘረዘሯቸው የሪፎርም አጀንዳዎች መካከል አብዝተው ትኩረትን የሚስቡት ጉዳዮች በአንድ በኩል “የታደሰው የኢትዮጵያ ራዕይ” በማለት ያሳወቁት ራዕይ፣ ዴሞክራሲና ቀጣናዊ ንግድ በሚል የጠቀሷቸው ጉዳዮች ናቸው። በሌላው ወገን፣ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ ስለማዛወር ያነሷቸው ጉዳዮች ናቸው። ከእንግዲህም፣ በእነዚህ የመጭይቱን ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ኢኮኖሚ በሚወስኑ የለውጥ ጉዳዮች ላይ ግልጽና የተለያዩ ባለሙያዎች ሥርዓት በያዘ መንገድ የሚሳተፉበት የአደባባይ ውይይቶች መካሄድና መመራት ይገባቸዋል። በሌላ አገላለጽ ውይይቱ ከእንግዲህ የቡና ቤት ጓደኞች ጭውውት በሚመስሉት የቴሌቪዥን ወግ ትርዒቶች (Talk Shows) ዓይነት ብቻ ሊቀጥል አይገባም። የቴሌቪዥኑ፣ አስተናጋጆቹ ራሳቸው “ትርዒት” (Show) ብለው በትክክል እንደሰየሙት ትርዒት ነው።
የተመለከተው የአደባባይ ውይይት በተለይም በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሕዝብ ንብረት ለውጭ የካፒታል አፍሳሾች ለማዛወር በሚተጉት የውጭ ካፒታል አስተናጋጅ ኢትዮጵያዊያንና የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎችና ተጨባጭ አቅም እንዲስተዋሉ በሚመክሩት ኢትዮጵያዊያን መካከል እንደሚሆን ከወዲሁ ለማመልከት ይቻላል። እዚሁ ላይ ግን፣ ይኼ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ወቅት በዶ/ር ዓብይ የሚመራውን የኢሕአዴግ ጆሮ ያማለለው ፊና የኢትዮጵያ የውጭ ካፒታል አስተናጋጆች፣ የአሜሪካው “ዓለም አቀፍ” የገንዘብ ድርጅቶችና የሁነት አጋፋሪዎቹ (Event Managers) ስብጥር እንደሆነ አበክሮ መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህም ከነዚህ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጡንቻቸው ከደነደነው ኃይሎች ጋራ የሚደረገው ግብ ግብ ቀላል እንደማይሆን አምኖ መጀመሩ የሚሻለው ነው።
በዚሁ ወደ ርዕሱ ለመመለስ፣ ከዶ/ር ዓብይ የዴቮስ ሦስት ምሰሶዎች መካከል ስትራቴጂካዊ የጎራ ለውጥ ያሉት ጉዳይ ለአሁኑ ብዙ የሚያመላልስ አይመስለኝም። ዶ/ር ዓብይ ስለራዕይ፣ ዴሞክራሲ፣ ቀጣናዊ ንግድና ውህደት የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ ስለማዛወር ያሳወቋቸው ጉዳዮች ግን፣ በአንድ በኩል የመረጃዎችን ይፋ መሆንና ተደራሽነት ይጠይቃሉ። በሌላው በኩል፣ ግልጽና በዝርዝር መረጃ ላይ የተደገፉ የአደባባይ ውይይቶች መደረጋቸውንና ብሔራዊ/አገራዊ መግባባትን ማረጋገጥ ይጠይቃሉ። አስተዳደራቸው እንደዚህ ዓይነቱን ክንዋኔ እንደሚያስችል ተስፋ ይደረጋል።
የራዕይ ህዳሴና የዴሞክራሲ ግንባታ
“መደመር” ፍልስፍና ስለመሆን አለመሆኑ መመራመር የፈላስፋዎች ጉዳይ ነው። ጉዳዩ የራዕይ ከሆነ ግን፣ የመለስ ኢሕአዴግ ‹‹በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት፤›› በማለት በሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው አገራዊ ራዕይ ምንም የሚወጣለትና መለወጥ የሚያሻው አይመስለኝም። እንደ ሌሎቹ የመለስ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት አንቀጾች ሁሉ ይህም በተግባር አለመዋሉ በራሱ ምክንያት አይደለም። መለወጥ ካስፈለገ ደግሞ፣ በዶ/ር ዓብይ የሚመራው ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥር 11 ቀን ‹‹አንዲት ዴሞክራሲያዊትና ጠንካራ ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት፤›› በማለት ያሳለፈው ውሳኔ ሸጋ ራዕይ ነው። በእኔ ዕይታ ስለዚህም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዶ/ር ዓብይ ቢሻቸው በሕገ መንግሥቱ ያለዚያም እሳቸው በሚመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አሰፈጻሚ ውሳኔ መሠረት የብሔራዊ/አገራዊ ራዕይ ግንባታን በተግባር ማዋል እንጂ፣ አዲስ ራዕይ ለማፈላለግ መድከም የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
የዴሞክራሲ ግንባታ በአንድ ወቅት ውሳኔና ዕርምጃ የማይጠናቀቅ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዶ/ር ዓብይ በኋላ ለብዙ ዘመን ሳይቋርጥ መስፋት፣ መደርጀትና መበልፀግ ያለበት መሠረታዊ የማኅበራዊ ፖለቲካ ጥያቄ እንደሆነም የዚያኑ ያህል ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በዛሬው ወቅት መሬት ሊይዝ የሚችለው በዛሬው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችና ሁኔታ ልክ ተቀዶ ሲሰፋ ነው። ዶ/ር ዓብይም ይኼንን ብዙዎች ደጋግመው ያመለከቱትን ጉዳይ ለማስታወስ በመሻት ይመስላል፡፡ በጥር 25 ከተቃዋሚዎች ጋራ ሲወያዩ ‹‹የሚገነባው ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መሆን እንዳለበት፤›› አመልክተው ነበር።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችና አንዳንዴም የሃይማኖት ጥያቄዎች የሆኑባት አገር ናት። በሌላው በኩል በተለይም የፖለቲካ መሪዎቿና ተዋናዮቿ የዴሞክራሲያዊ ድርድር ሥርዓት አረዳድና የሰጥቶ መቀበል ሲቪክ ባህል እጅግ ደካማ የሆነባት አገር ናት። ተዓማኒ የመንግሥታዊ አስተዳደርና የዴሞክራሲ ማስተናገጃ ተቋሞቿን “ሀ” ብላ መገንባት ያለባት አገር ናት። ተዓማኒ የሕዝብ አገልጋይ ባለሥልጣኖችንና የሚዲያ አስተናጋጆችን ማፈላለግ፣ “ሀ” ብላ ማሠልጠንና ማሠማራት ያለባት አገር ናት። ነገር ግን የአዲስ ፎርቹን አዘጋጅ አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት ወግ ላይ በትክክል እንዳሉት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥትና የግል ሚዲያ የሚባሉት ድርጅቶች ምንም ዓይነት ተቋማዊ ጡንቻ የሌላቸው አገር ናት። የግል ሚዲያ ድርጅቶች በተለይ፣ ተቋማዊ ጡንቻቸውን ገና ገና በብዙ የመገንባትና የማደራጀት ሥራ አለባቸው። ተቋማዊ ጡንቻው የደነደነውን ያህል ነው፣ አራተኛው ሥልጣን የሚሆኑት። የመጣ አስተዳደር ሁሉ መሣሪያ የሚያደርጋቸው። እንዳሻው የማይገፈታትራቸው።
ይህ በእንደዚህ እንዳለ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ የሚባሉትና አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከክላሽን የማይተናነሱ የቅስቀሳና የመታገያ/ማታገያ መሣሪያዎች በሆኑበት በዛሬው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ከቶም ቀላል ተግዳሮት አይደለም። በነዚህ መሣሪያዎች “ዜናና፣ መረጃ” እየተባሉ ከውጭም ከውስጥም ለ24 ሰዓታት የሚለቀቁት በሬ ወለደ ወሬዎች የአብዛኛው ሕዝብ የንባብ አቅም ባላዳበራት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው ይዳረሳሉ። ይደመጣሉ። ይቀባበላሉ። ይባስና፣ የመንግሥት የዜና ተቋሞች ተዓማኒነት ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ጭምር ይታመናሉ። በተለይም ወጣቱን ባልሆኑ መንገዶች ለመቀስቀስና ለማነሳሳት እየዋሉ ግጭቶችን ይጭራሉ። ዶ/ር ዓብይ ጥር 24 ቀን ለምክር ቤቱ በትክክል እንደገለጹት፣ ‹‹የክልል ዜና ማሠራጫዎች አገራዊ ዕይታ የሌላቸው መሆኑ፤›› ሲታከልበት ደግሞ፣ ተግዳሮቱ ይወሳሰባል። ጥር 25 ዕለት ከተቃዋሚ ወገኖች ጋራ ሲወያዩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጤነኛ የሚባል ሚዲያ የለም። ያለው ሚዲያ ተነስ፣ ታጠቅ የሚል ነው፤›› ያሉትም፣ በእጅጉ እውነት ነው። የመንግሥት ሚዲያ የሚባለው “ከአወዳሽ አንጋሽ” ማንነቱ ለመላቀቅ የተቸገረ ሚዲያ እንደሆነ ቢያክሉ ኑሮ፣ ገለጻቸው የተሟላ ይሆን ነበር።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ስለዚህም፣ በአሜሪካና በሌላ ሌላ እንደሚሆነው በሚል “በቁረጥ ለጥፍ” አሠራር ሊሆን አይችልም። የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ጭብጥ የፖለቲካና የባህል ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን መጣር ያስፈልጋል። በሌላ አገላለጽ፣ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ መገንባት ለዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚመጥንንና የሚስማማን ዴሞክራሲ መገንባት ማለት ምን ማለት ነው? ብሎ መጠየቅ፣ መወያየትና ማስተማር ለግንባታው መሳለጥና መሳካት ተጨባጭ መልሶችን የሚያስገኝ ሊሆን ይችላል። እንዲያም ሲል፣ ለብሔራዊ/አገራዊ መግባባትና ግንባታ የሚያግዝና የሚጠቅም ይሆናል።
ለዚህም በአንድ በኩል የራሳችን ከሆኑት የተለያዩ የሕዝባችን የመወያየት፣ የመስማማት፣ በተስማሙበት የመታሰርና በሥርዓት አብሮ የመኖር ባህላዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ሞራላዊና አብሮ የመኖር ዘዴ ዕሴቶች መካከል ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ የሚበጁትን መመርመርና በብሔራዊ/አገራዊ ደረጃ መጠቀም ያስፈልጋል። ከእየ ቀበሌው አዛውንት እስከ የማኅበራዊና የፖለቲካ ሳይንስና የሕግና የታሪክ ባለሙያ ድረስ ያሉት ሊቃውንቶቻችን በብዙ ሊረዱ ይችላሉ። በሌላም በኩል፣ በኢትዮጵያ የተወሰነ ዴሞክራሲ የፈነጠቀባቸውን የፖለቲካ ታሪክ ወቅቶች መለስ ብሎ በመቃኘት አንዳንድ ጉዳዮችን ማስታወስና ትምህርቶችን መቅሰም ይጠቅማል። በዚህም ረገድ፣ ቢያንስ አራት የከሸፉ ወቅቶችን ለመለየት የሚቻል ይመስለኛል።
የመጀመሪያው አፄ ኃይለ ሥላሴ ራስ ተፈሪ በነበሩበት የ1920’ዎቹ ብርሃንና ሰላም አዕምሮ የተባሉት ጋዜጦች የነበሩበት ዘመን ነው። ጋዜጦቹን ዛሬ ተመልሶ የሚያገላብጣቸው አንባቢ ይካሄድ በነበረው ህያው ውይይት ይመሰጣል። ራስ ተፈሪ ወደ አፄነት ባደረጉት ጉዞና ከ1928 ዓ.ም. የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ሒደት ጋር በተያያዘ ተዳፈነው አበቁ። ሁለተኛው፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋራ ከመቀላቀሏ በፊት በአስመራ የነበሩት ጋዜጦችና የዴሞክራሲ አየር ነበር። የኤርትራ መቀላቀል ሲፈጸም፣ በአፄያዊው አዲስ ዘመን ሥርዓትና አያያዝ ገብተው አከተሙ። ሦስተኛው፣ በ1960’ዎቹ ማብቂያ ላይ የተከፈቱት የመወያያ መድረኮች (የውይይት ክበቦችና ለአደባባይ ውይይት የተከፈቱት የመንግሥት ጋዜጦች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን. . .) ነበሩ። በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መንገድ ተጨማሪ የጥላቻና የግጭት ማራመጃ መሣሪያዎች ጭምር ሆኑ። ደርጉም ይህንኑ አሳቦ ጠረቀማቸው። ይሁንና ደግሞ፣ እንዲወያዩ የተጠሩት የወቅቱ ተዋናዮች በውል ሳይጠቀሙበት ያባከኑት አጋጣሚና ለመክሰሙ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱለት ጥርቀማም እንደ ነበር ላለማስታወስ አይቻልም። አራተኛው፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ሽው ያለው የዴሞክራሲ አየር ነበር።
በመለስ ኢሕአዴግና በወቅቱ ተዋናዮች የይዋጣልን ክንድ ተደቁሶ እንደ ሦስተኛው አጋጣሚ ተጠረቀመ። የዶ/ር ዓብይ ኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ጥሪ በዚሁ አምስተኛው የታሪክ አጋጣሚ ይሆናል። የዛሬው የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ሊያባክኑት የማይገባቸው አምስተኛው የታሪክ አጋጣሚ ነው።
በመጨረሻም ደግሞ ግን፣ ስንቱ የአፍሪካ መሪ የዴሞክራሲን ሰንደቅ ለስንት ጊዜ እያውለበለበ እንደመጣና ለስንት ጊዜ ሕዝብን አስጨብጭቦ ለስንት ጊዜ ከአምባገነን አገዛዞች ጫማ ሥር እንደደፈቀው ይታወቃል። ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነቱ መንሸራተት “ባለፀጋ” እንዳትሆን ነቅቶ መጠበቅና መታገል የማይቀረው ዕጣዋ ሆኖ እንደሚቀጥል የሚያሳስብ እውነታ ነው። እዚህም ላይ ዶ/ር ዓብይ ታኅሳስ 23 ቀን ከመምህራን ጋራ ሲወያዩ ‹‹የሚያስፈልገን የጭንቅላት ክላሽ ነው፣ ልምምድ የለንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አምባገነን ለመሆን ጫፍ ላይ ያለ መንግሥት ነው። ይኼ ግፊት አያስፈልገንም፤›› ብለው እንደነበርም እንዲታወስ ይገባል።
ቀጣናዊ ንግድና ውህደት
ቀጣናዊ ንግድን ማበርታትና ማሳደግ በተለይም የወደብ አልባ ለሆነችውና የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ መሠረታዊ፣ አስፈላጊና ለህልውናዋ የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከውጭ ያስገባችው 14.7 ቢሊዮን የነበረ መሆኑ ብቻ የቀጣናዊ ንግዷ ማደግ ለኢኮኖሚዋና ለብሔራዊ ነፃነቷ መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያመለክታል። ቀጣናዊ ንግድ የዚያኑ ያህል ግን ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋራ እንደተደረገው ግብዓታዊና ሥርዓተ አልባ “የኢኮኖሚ ንግድ” ዓይነት ሊሆን አንደማይገባውና እንደማይችል ጠንክሮ መነገር ያለበት ጉዳይ ነው። በሕጋዊ ውሎችና በዓለም አቀፋዊ ሥርዓት መሠረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀው ልክ እየተመዘነ በሥራ መዋል ያለበት ጉዳይ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ግን የባለሙያዎች ሥራ ሊሆን ይገባል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጥር 21 ቀን ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ፊት ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋራ የሚደረጉትን ግንኙነቶች በሕጋዊ መሠረት ላይ ለማቆምና ሥርዓት ለማሲያዝ የሚሠራ ኮሚቴ እንዳለ ገልጸዋል። ፊርማ ከመቀመጡ በፊት ረቂቁ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተስፋ ይደረጋል። ከዚህም በተያያዘ፣ ለኢትዮጵያ የአገር ውስጥና የውጭ የፖለቲካ ድረጅቶችና ተዋናዮች በሩንና መድረኮችን የከፈተው የዶ/ር ዓብይ ኢሕአዴግ፣ የኢሳያስ አምባገነን አገዛዝ ተቃዋሚ ኤርትራዊያንን ማሳሰቢያዎችና ጥሪዎች ለማድመጥ ጭምርም መጣር አለበት።
የቀጣናዊ ውህደት አስተሳሰብ በተረፈ፣ በኢትዮጵያ የቀጣና ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የተነሳው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። የመጀመሪያው ምናልባት፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊነት ባለቤት የነበረው ደርግ በታኅሳስ 1967 ዓ.ም. ስለ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረት አኅጉር መመሥረት አስፈላጊነት፤›› ያደረገው ጥሪ ነበር። ከዚያም በ1969 ዓ.ም. ያንሰራራውን የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነትን ለመግታት ፊዴል ካስትሮና የምሥራቅ አገሮች በኮንፌዴሬሽን ሥርዓት ለማስማማት ያደረጉት ጥረት ነበር። በ1980 ዓ.ም. ደግሞ፣ የኢትዮ ኤርትራን ቀጣናዊ ትብብር ለማስቻል በርካታ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ ዕርምጃዎች በአቶ መለስ ኢሕአዴግ ተወስደው ነበር። ይሁንና ሁሉም ጥረቶች ከሸፉ። የከሸፉት ግን፣ በዋናነትና እስከዚህም በውጭዎቹ ምክንያት አልነበረም።
የሶማሌው፣ በተለይም የሶማሊያ መሪዎች ኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም. አብዮት ሒደት ተዳክማለች ብለው በማሰብ በጦርነት ለመቦጨቅ የሚችሉትን በመቦጨቅ ሕልማቸው ስለከቸቹ ነበር። ይህንኑም የአሜሪካ አስተዳደር የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ሳይቀር በ20/3/2012 (11/7/2004) ዕገዳውን ባነሳለት (Declassify) “የኦጋዴን ሁኔታ” ሪፖርቱ ውስጥ ‹‹የሶማሊያ የሐምሌ 1969 ዓ.ም. በአብዮቱ ተከፋፍላ የተዳከመችውን ኢትዮጵያ ሁኔታ ለመጠቀም በሶማሊያ መሪዎች የተደረገ ሙከራ ነበር፤›› በማለት አትቶበታል (Somali’s Invasion Of The Ogaden in July 1977 Was an Attempt To Capitalize On The Weaknesses Of The Revolution Torn Ethiopia CIA፣ The Ogaden Situation፣ 2012)። ኢሳያስ የ1990 ዓ.ም. ጦርነቱን የከፈተውም የመለስ ኢሕአዴግ የነበረውን ዝቅተኛ ተቀባይነት ደምሮና ቀንሶ የሶማሌው ዚያድ ባሬን “አጋጣሚውን የመጠቀም” ሥሌት ስለተከተለና እሱም ለመቦጨቅ የሚችለውን በመቦጨቅ ሕልሙ ስለከቸቸ ነበር። ሊቀሰሙ የሚገባቸው ትምህርቶች ግልጽ ይመስሉኛል።
አንደኛ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላም፣ ውህደትና ጥንካሬ በተዳከመ ቁጥር የኢትዮጵያ የቅርብና የሩቅ ጎረቤቶች ጦራቸውን ሰብቀው ይጎርፋሉ። ሁለተኛ ኢትዮጵያን የቅርብና የሩቅ ጠላቶች በወረሯት ቁጥር ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ ቆመውና የተከፈለውን መስዋዕትነት ከፍለው ነፃነቷን ያስከብራሉ። ሦስተኛ ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላምን ተጎናፅፋ ወደ ውህደቷ፣ ዕድገቷን ወደ ማስቻልና ጥንካሬዋን ወደ ማጎልበት በምታቀናበት ወቅት ሁሉ፣ የቅርብና የሩቆቹ በተለያዩ መንገዶች ይፈታተኗታል። አራተኛ፣ የአንፃራዊው ሰላም ወቅት አካሄዳቸው ከግልጽ ወረራው ወቅት የሚለየው፣ በአንፃራዊው ሰላም ወቅት አንዳንድ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ተጠቅመውና አሠልፈው የሚሠሩ በመሆኑ ብቻ ነው።
አምስተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ወራሪዎችን መክተውና ጨቋኝ ገዥዎችን አስወግደው ወደ ሰላምና ዕደገት በሚያቀኑበት ወቅት ሁሉ ኢትዮጵያ መልሳ ወደ መታመስ የምትገባው ግን አንድም፣ ገዥዎቿ ውሎ አድሮ በአንድ ወገን፣ የነፃነት ታጋዮቿንና የለውጥ አራማጆቿን እያገለሉና እያጠፉ፣ በሌላውም ወገን ለግል ጥቅማቸው ብቻ የሚያድሩ “እሺ ጌታዬዎችን” እያጋበሱ አምባገነን አገዛዝን ወደ ማስፈን ስለሚያቀኑ ነው። በዚህ ረገድ ዮፍታሔ ንጉሤ ገና ጠላት እንደወጣ ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ. . .›› በማለት የተቀኘው ስንኝ በመጀመሪያ ረድፍ ይታወሳል። ከዚያም ደርጉ አንድ አገር ወዳድና ታጋይ ትውልድን ጨርሶ የኢሠፓን አምባገነንነት አሰፈነ። የመለስ ኢሕአዴግ በበኩሉ የትግል ጓዶቹን ሳይቀር አግልሎና አጥፍቶ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አምባገነን አገዛዙን አሰፈነ። ከእነዚህ ተደጋጋሚ እውነታዎች ሊደረስበትና ሊያዝ የሚችለው መደምደሚያ አንድና አንድ ብቻ እንደሆነ በዚሁ ግልጽ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊም ሆነ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ የድርድር መድረኮች ላይ በልበ ሙሉነት ልትቀርብና ልትደራደር የምትችለው በውስጣዊ ሰላሟ፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነቷና ጥንካሬዋ ልክ ብቻ ነው። ለቀጣናዊ ውህደት ከሁሉም ነገር በፊትና ከሁሉም ነገር በላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ስለዚህም፣ በውስጣዊ ሰላምና ፀጥታ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እኩልነቷና አንድነቷ ላይና በጋራ ብልፅግና ጥንካሬዋ ላይ የቆመ አገዛዝ ነው። ይህንን በማንኛውም መስክ ሳይገነቡ፣ ሳያደራጁና ሳያጠናክሩ በፊት ወደ ቀጣናዊ ውህደት ዕርምጃዎች ማቅናት ውስብስብ ችግሮችን ለመጋበዝ መጣደፍ ይሆናል። ሌላም፣ ደረጃ በደረጃና ተከታታይነት ባለው መንገድ መመራት፣ መከናወንና መፈጸም ያለበት ጉዳይ ነው።
ከዚህ ጋራ በተያያዘ አንድ የቅርብ ጊዜ ሁኔታን እንደ ተጨማሪ አመልካች ብንወስድ፣ በርካታ አገሮች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ አንድም ሳትጠየቅና ሳትማከር ከኤርትራ እስከ ሶማሊያ የቀይ ባህር ወደቦች ድረስ የጦር ሠፈሮችን ለመገንባት ደፍረዋል። ይኼ የሆነው የጎረቤት አገሮቹና የሩቅና የቅርብ መንግሥታቱ ጉዳዩ ኢትዮጵያን በቅርብ እንደሚመለከት ስላጡት አልነበረም። የኢትዮጵያን ውስጣዊ ውህደትና ጥንካሬ መዝነውና “ደካማ” በሚል ስለገመገሙት ነው። የዛሬው ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ለውስጣዊ ሰላም፣ ዴሞክራሲያዊ ውህደትና ጥንካሬ ተገቢውን ትኩረት እስካልሰጡ ድረስና በአንድነት እስካልቆሙ ድረስ፣ የኢትዮጵያ የቅርብና የሩቅ ተቀናቃኞች ሴራ አይሟሽሽም።
ነገር ግን፣ ቀጣናዊ ትብብር/ኅብረት/ውህደት የሚባሉት ጉዳዮች የመልከዓ ምድር አቀማመጥ፣ የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆኑም ከግንዛቤ እንዲገባ ያስፈልጋል። ከታሪካቸው እንደሚታየው አገሮች ቀጣናዊ ትብብር/ኅብረት/ውህደትን የገነቡት በነዚህ ምክንያቶች ብቻ አይደለም። ይልቁኑ፣ በአንድና ሁለት ጠንካራ አገሮች ዙሪያ ነው። ለምሳሌም፣ በምዕራብ አፍሪካ በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካና በአውሮፓም በጀርመንና በፈረንሣይ ዙሪያ ነው የተገነቡት። በሌላ በኩል ቻይና የቢሊዮን ሕዝብ ባለቤትና በቆዳ ስፋቷ ከዓለም ሦስተኛዋ አገር ብትሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለትብብር/ኅብረት/ውህደት የምትፈለግ አገር አልነበረችም። ውስጣዊ ሰላሟን፣ ውህደቷንና ጥንካሬዋን ያደረጀችውን ያህል ግን፣ ተፈላጊ ሆነች። የኤዢያን አገሮች በተለያዩ መንገዶች ወደ ማቀፍ አቀናች። የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሊቃውንቶች በዚህም አኳይ ስለዚህም፣ ዶ/ር ዓብይ “ቀጣናዊ ውህደት” ያሉት አጀንዳ እንደ ኢትዮጵያ በራሱና ለራሱ “አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብን በጋራ” ላልገነባና ላላደረጀ አገርና በራሱና ለራሱ የተዋሀደ ኢኮኖሚ ለሌለው አገር ምን ማለት? እንደሆነ ሊያስረዱን ይገባል። በእኔ ዕይታ ይኼ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሌሎቹ ጉዳዮችም ግልጽና አሳታፊ የሆነን የነፃ ባለሙያዎች ውይይት ይጠይቃል።
ወደ ግል ይዞታ ስለሚዛወሩት የመንግሥት ይዞታዎች
ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን በመጡ ጥቂት ቀናት ውስጥ (ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም.) ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ከፊሉ ለውጭና ለአገራዊ ባለሀብቶች እንደሚሸጥ አውጀው ነበር። የመንግሥት ይዞታ ድረጅቶች ካፒታል አይደግ፣ አመራርና አስተዳደራቸው አይሻሻል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አይስተዋወቅ፣ የግንኙነትና የንግድ አድማሶች አይስፉ፣ የሥራ መስኮች አይከፈቱ. . . የሚሉ አስተያየቶች የሉም። ይሁንና አንዳንድ ወገኖች አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን በማስታወስ ወዲያውኑና በተከታታይ ቢያንስ አየር መንገዱ በመንግሥት ይዞታ እንዲቆይ የሚጠይቁ ጥሪዎችን አሰምተው ነበር። አንደኛው፣ አየር መንገዱን ለሰባት ዓመት (ከ1996 እስከ 2003 ዓ.ም.) የመሩትና የድርጅቱ የ2025 ራዕይ አባት የሆኑት አቶ ግርማ ዋቄ የለገሱት የሚከተለው ምክረ ሐሳብ ነበር፡፡
‹‹የአጭር ጊዜ ፍላጎት የረዥም ጊዜ ተስፋችንን እንደ ማያጨልም ተስፋ አደርጋለሁ። ተመሳሳይ ዕርምጃ ከወሰዱ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች ተሞክሮና ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል። የኬንያ አየር መንገድ በከፊል ወደ ግል እንዲዛወር መደረጉ ብዙም አልጠቀመውም። የኬንያ አየር መንገድ አሁንም ኪሳራ ውስጥ ነው የሚገኘው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ነው። ከአየር መንገዱ ትርፍ የተወሰነውን መንግሥት ለሌሎች ፕሮጀክቶች መደገፊያ ሊጠቀምበት ይችላል። ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የግል ንብረት አድርጉ ብለው አያውቁም፣ በንግድ መርሆች እስከተዳደረ ድረስ፤›› (ሪፖርተር፣ ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም.)።
በአየር መንገዱ ላይ ከአቶ ግርማ ዋቄ ምክረ ሐሳብ የላቀ አስተያየት ለመስጠት አይቻልም። ዶ/ር ዓብይ ወደ ግል የማዛወር ውሳኔያቸውን ጥር 11 ዕለት ለዴቮሱ ስብሰባ ሲያሰሙ ግን፣ የብዙዎቹ ምክረ ሐሳብ እንዳልተደመጠ ግልጽ ሆነ። ዶ/ር ዓብይ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሎጂስቲክ፣ ቴሌ፣ ባቡርና መብራት ኃይል ወደ ግል ይዞታ እንደሚዛወሩ ለዴቮሱ ታዳሚዎች አሰምተዋል። ከአየር መንገዱ በኋላ ተረኛው የኢትዮ ቴሌኮም እንደሚሆን በማተትም ሪፖርተር እንደሚከተለው ዘግቦ ነበር። ‹‹በተለይ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል በመሸጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ፣ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለው የትራንዛክሽን አማካሪ እንዲሰይሙ የሚፈቅድ መሆኑ ታውቋል፤›› (ሪፖርተር፣ ጥር 12)። የሎጂስቲኩ ክፍል ቀደም ሲል በ51 ከመቶ ለአገራዊ ባለሀብቶችና በ49 ከመቶ ለውጭዎቹ በሚል ሥሌት ለሽያጭ እንደቀረበ ይታወሳል።
ወደ ግል ይዞታ ስለሚዛወሩት የመንግሥት ይዞታዎች የሚቀርቡት ጥያቄዎች በርካታ ናቸው። ለጥያቄዎቹ እንደሚገኙት መልሶች፣ በዶ/ር ዓብይ የሚመራው ኢሕአዴግ የሚሄድበትን መንገድ በተሻለ ለመረዳት ይቻላል። ዋናና መሠረታዊዎቹን ለማስታወስ ያህል አንደኛ፣ ውሳኔው የተመሠረተባቸው የኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ጥናቶች (ከ1987 አስከ 1994 ወደ ግል ከዞሩት 223 ድርጅቶች የተቀሰመውን ተሞክሮ ጨምሮ) የትኞቹና ምንድናቸው? ሁለተኛ፣ ከፊሉ ለአገራዊ ባለሀብቶች ይሸጣሉ መባሉ መልካም ሲሆን፣ የአገራዊ ባለሀብቶቹ የካፒታልም ሆነ የአስተዳደር ክህሎትና ተሳትፎ ተጨባጭ አቅምና ብቃት ዝቅተኛ እንደሆነ ለአዋጭነቱ የሚሞግቱት ክፍሎች ሳይቀሩ ያስታውሳሉ። ስለኢትዮጵያ ባለህብቶች አመርቂ ተሳትፎ የተደረጉት ጥናቶች የትኞቹና ምንድናቸው?
የምዕራብ አገሮች ብሔራዊ ንብረቶችን ለግል ባለሀብቶች ስለማዛወር ቢናገሩ፣ የናጠጡ ባለሀብቶች ባለቤቶች ስለሆኑ በመሆኑ ሊያዋጣቸው ይችል ይሆናል። የአንዳንዶቹ የግል ባለሀብቶቻቸውና የፈይናንስ ድርጅቶቻቸው የግል ካፒታልም እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም. ያስመዘገበችውን 80 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ አገራዊ ምርት በብዙ እጅ ያጣፋል። ስለኢትዮጵያ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን፣ የግል ባንኮች ጠቅላላ ካፒታል ለምሳሌ ያህል ከአንድ ቢሊዮን ዶላር የማይበልጥ ነው። ሌላም፣ ከ1984 እስከ 2009 ባለው የ25 ዓመት ዘመን 17,519 ኢትዮጵያዊያን መዋዕለ ንዋያቸውን በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማፍሰስ ቢመዘገቡም፣ ወደ ሥራ የገቡት 1,837 (10 ከመቶ) ብቻ ናቸው። በዚህ ሁኔታ የሚገኙት አገራዊ ባለሀብቶች በዚህ ወይም በዚህ ከመቶ ይሳተፋሉ ስለተባለ ብቻ፣ በተግባር ውሎ የሚታይ ይሆናል ወይ? ሦስተኛ፣ እነሱ ወደ ግል ያዞሯቸው ድርጅቶች ቢከስሩም፣ በ2008 ዓ.ም. (በ2000) እንዳደረጉት በቢሊዮን ደጉመው ነፍስ ይዘሩባቸዋል። የኢትዮጵያ አቅም እስከ ምን ድረስ ነው? አራተኛ፣ የመንግሥት ይዞታዎች ለውጭና ለአገራዊ የግል ባለሀብቶች እንዲዛወሩ አጠንክረው የሚቀሰቅሱት ወገኖች በየቴሌቪዥን መስኮቱ እየቀረቡ በተለይም ኬንያን፣ በምሳሌነት ደጋግመው ይጠቅሳሉ። በዚህስ አኳያ ሰፊው ሕዘብ ስላገኝው ትርፍና ጥቅም የተደረጉት ጥናቶችና የተቀሰሙት ተመክሮዎች ምንድናቸው?
የኬንያውን በሚመለከተው ለምሳሌ፣ ከላይ የተጠቀሱት አቶ ግርማ ዋቄ ‹‹የኬንያ አየር መንገድ በከፊል ወደ ግል እንዲዛወር መደረጉ ብዙም አልጠቀመውም። እንደሚታወቀው የኬንያ አየር መንገድ አሁንም ኪሳራ ውስጥ ነው የሚገኘው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ነው፤›› በማለት አመልክተው ነበር። የድረጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳስታወቁትም፣ የአየር መንገዱ የ2010 ዓ.ም. ገቢ የ43 በመቶ ዕድገት በማሳየት 89.1 ቢሊዮን ብር (3.7 ቢሊዮን ዶላር) ደርሶ ነበር። 6.8 ቢሊዮን ብር (233 ሚሊዮን ዶላር) የተጣራ ትርፍ አግኝቶም ነበር። የኢትዮ ቴሌኮም ትርፋማ እንደሆነም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራህማን አህመድ ‹‹ድርጅቱ በ2010 ዓ.ም. የባጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 18.4 ቢሊዮን ብር (564 ሚሊዮን ዶላር) ገቢ እንደሰበሰበና ከ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋራ ሲነፃፀር የ18 በመቶ ጭማሪ እንዳስገኘ፤›› አስታውቀው ነበር (ሪፖርተር፣ የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም.)። እውነታው ይኼ ሆኖ ሳለ፣ ወደ ግል የሚዛወሩበት ምክንያት ምንድነው? በሌላ በኩል፣ ‹‹ቢሆንም፣ ብዙ ዕዳ አለባቸው እኮ!›› የሚል አስተያየት ይሰጣል። ባላቸው ገቢና ትርፍ ዕዳቸውን ለመክፈል ስለማይችሉበት ምክንያት የሚሰጥ አሳማኝ ነገር ግን የለም።
አምስተኛ፣ ቴክኖሎጂ ያስተዋውቃሉ ይባላል። የተዘረዘሩትን ብሔራዊ ንብረቶች አክሲዮኖች ለመግዛት የሚመጡት ኩባንያዎች ግን፣ በሚገዙት የአክሲዮን ልክ ለማትረፍ የሚመጡ የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ኩባንያዎች (Investment Companies) እንጂ፣ መሠረተ ልማት ገንቢዎችና አምራች ኩባንያዎች (Operational Businesses) አይደሉም። የሚመጡት ለተጨማሪ ትርፍና የአክሲዮን ድርሻ ገቢያቸውን ለማሳደግ ስለሆነም፣ ትኩረታቸው ይኼውና ይኼው ብቻ ነው። የሠራተኛ መብት፣ ደኅንነት፣ ጤንነትና የአካባቢ ተፈጥሮ እንክብካቤ የሚባሉትን ጉዳዮች የትርፋቸው ተሻሚ አድርገው ስለሚመለከቱ አያተኩሩባቸውም።
የብዙ አገሮች ተመክሮ (ለምሳሌ ናይጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሴራ ሊዮን፣ ኮንጎ፣ ዛምቢያ) እንደሚመሰክረው እንደውም፣ የሠራተኞችን መቀነስና የአካባቢ ተፈጥሮ እንክብካቤ ሕጎችንና ደንቦችን ማላላት፣ ቅድመ ሁኔታ ጭምር እስከ ማድረግ ይሄዳሉ። ሌላም ጊዜ፣ ሕጎችንና ደንቦችን እስከ መጣስ ይደፍራሉ። የተጠቀሱት አግሮች “የጨረቃ ምድር” (Moon Landscape) የሚባሉ አካባቢዎችን ብቻ አቅፈው እንደቀሩም፣ ተደጋግሞ ይነገራል። በመጨረሻም፣ ወደ ግል ይዛወሩ የሚባሉት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ብሔራዊ ማንነትና ኩራት ጭምር የሚገለጡባቸው ብሔራዊ ንብረቶች ናቸው። በእጅጉም ደግሞ፣ ከብሔራዊ ደኅንነትና ነፃነት ጋራ በጥብቅ የሚያያዙ ናቸው። በዚህም ረገድ በአፍሪካ፣ ኤዢያና በደቡብ አሜሪካ ቀርቶ፣ በኖርዌይ፣ ስዊድንና በአሜሪካ ጭምር ከፍትኛ ክርክሮች ተካሂደው እንደነበርም ይታወሳል። የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር አመለካከት ምንድነው?
በመንግሥት ይዞታ የሚገኙትን ንብረቶች ወደ ግል ይዞት አዛውሩ የሚለው ጫና በደሃ አገሮች መንግሥታት ላይ እየከበደ የመጣው ከ80’ዎቹ ዘመን ጀምሮ ነው። አንዳንድ ተመራማሪዎችም፣ እንቅስቃሴው የተጀመረው ‹‹አትገተር፣ ይልቁኑ የሆነን ነገር አወላልቅ›› (“Don’t Just Stand There, Undo Something”) በሚለው የፕሬዚዳንት ሪገን አስተዳደር መፈክር ዘመን እንደሆነ ያሰምራሉ። ከ80’ዎቹ በፊት ግን፣ ራሱን አሜሪካንና የምዕራብ አውሮፓ አገሮችን ጨምሮ የአብዛኞቹ ያደጉ አገሮች መሠረታዊ ኢንዱስትሪዎች፣ የትራንስፖርትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና አገልግሎቶች. . . ወዘተ. የመንግሥት ይዞታዎች ወይም በመንግሥት የሚዶገሙ ነበሩ።
የማኅበራዊ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን ጉዳይ ወደ ጎን እንተወውና፣ እነሱ ከ80’ዎቹ ዘመን ጀምሮ የመንግሥት ይዞታዎችን ወደ ግል ይዞት ወደ ማዞር ያቀኑት የዴሞክራሲያዊና የሕግ የበላይነት አስተዳደር ሥርዓታቸውን ገንብተው፣ ሲቪክ ባህላቸውን አዳብረው፣ የኢንዱስትሪና የካፒታል አቅማቸውን፣ የአገራዊና የገበያ መረጃዎቻቸውን፣ የካፒታል ገበያቸውንና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን ለስንት ዘመን ካጎለበቱ በኋላ ነው። የማኅብራዊ ደኅንነት ጥበቃ ተቋሞቻቸውንና ሥርዓታቸውን ካደራጁና ካጎለበቱ በኋላና የሕዝቦቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች አትረፍርፈው ካሟሉ በኋላ ነው። እንደዚሁም፣ የተፈጥሮ እንክብካቤ ተቋሞቻቸውንና ሥርዓታቸውን ጥበቃ ካደራጁና ካጎለበቱ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ በዋናነት እየተገፋች የምትገኘው በውጭ ገንዘብ እጥረትና በውጭ ዕዳ ጫና ምክንያቶች ነው። ይኼንን ችግር አገሪቱ ያሏትን አትራፊ ብሔራዊ ንብረቶች ወደ ግል ይዞት በማዞር ለመወጣት ስለመቻሏ ግን፣ ምንም ማስተማመኛ የለም። በአፍሪካ፣ በእዚያና በደቡብ አሜሪካ የተደረጉ ወደ ግል ይዞታ የማዞር ዕርምጃዎቸ ስላስከተሏቸው የማኅበራዊ ፖለቲካ መዘዞች በርካታ ጥናቶች ተደርሰዋል። ብዙዎችም የሚስማሙት፣ የኋላ ኋላ ብዙ የሚያስከፍል ዕርምጃ እንደሆነ ነው። አቶ ሄበን መሀሪ በዚህ አኳያም የዶ/ር ዓብይንና የጆርጅ ሶሮስን በጂኔቫ መገናኘት አስታውሰውና የታይላንድን ምሳሌ አንተርሰው ለአዲስ ፎርቹን በጥር 23 ባቀረቡት ጽሑፍ የጉዳዩን አሳሳቢነት በአጭሩና በጥሩ አብራርተዋል (Addis Fortune፣ Feb.1፣ 2019፣ Vol19፣ No979)።
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ቀርቶ፣ አስተማማኝ አገራዊ የስታቲስቲክ መረጃ እንኳን የላትም። የደረጁ የማኅብራዊ ደኅንነት ጥበቃ ተቋሞችና ሥርዓት ባለቤት አገር አይደለችም። የደረጁ የተፈጥሮ እንክብካቤ ተቋሞችና ሥርዓት አገር አይደለችም። ከቁም የሚገባ የካፒታል ስልቻ ያለው የከበርቴ መደብ ክፍል የላትም። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ከሆነ፣ አቅሙ ያላቸው ምናልባት በሥልጣን ብልግና የከበሩት ክፍሎች ናችው። በእኔ ዕይታ ስለዚህም፣ ታኅሳስ 25 ቀን “ዴሞክራሲም ከሆነ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ” ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ ወደ ግል የማዞር ከሆነም የኢትዮጵያ በሚለውና የሀብት ምንጩ ተጣርቶ በታወቀ ኢትዮጵያዊ በሚለው ቢመሩ የሚጠቅም ይሆናል። አሁንና ለአሁኑ ወቅት የሚበጀው አካሄድም ይልቁኑ፣ ከ15 ወራት በኋላ ከብሔራዊ ምርጫ ፊት ለምትቆመዋ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የቅድሚያ ቅድሚያ ጉዳዮች በቅድሚያ ለመመለስ መጣር ይመስለኛል።
ቅድሚያ ለቅድሚያ ቅድሚያ ጉዳዮች
ኢትዮጵያ ዛሬ በምትገኝበት አጠቃላይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ አነሰ ቢባልና በተለይም እስከ 2012 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ የቅርብ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። አንዳንዶቹ አገራዊ ፀጥታና ሰላም፣ ብሔራዊ መግባባት፣ የሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሻሻል፣ መዋቅራዊና የአሠራር ለውጦች፣ የተጀመሩት ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች ከፍጻሜ መድረስ፣ ሙስናን መዋጋት፣ የኢሕአዴግን ካድሬ “ሙያተኞች” በሃቀኛና የየመስኩ ባለሙያዎች መተካት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ መድረሱና መቋቋማቸው፣ ሥራ ለሥራ አጡ ወጣት መቅረብ፣ የዴሞክራሲያዊ መድረኮች መስፋትና የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት. . . ናቸው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ ግን መንግሥት የሚባለው ድረጅት ከቀበሌ እስከ ስታትስቲክስ ቢሮው ድረስ ተዓማኒነትን ያጣባት መንግሥት አገር ስለሆነች፣ የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ፉክክር ከመከፈቱ በፊት ይኼንን ጉድለት ለማከምና ለማደስ ብዙ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
በዶ/ር ዓብይ የሚመራው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ የለውጥ ዕርምጃዎችን በተከታታይ ወስዷል። በሌላ በኩል ግን፣ ከዛሬይቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሪፎርም አጀንዳዎች አንፃር ሊተኮርባቸው በማያስፈልጉ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጊዜና ሐሳብ ሲባክኑ ይስተዋላል። አንደኛው ከላይ ያነሳሁት የመንግሥት ይዞታዎች ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ጉዳይ ነው። ሌላው፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ምክንያት በሚልና የአፍሪካዊ ቱሪስቶችን ጉብኝት ለማቃለል በሚል የተለቀቀው የቪዛ አሰጣጥ ነው። ሌላውም፣ “የስደተኞች ጉዳይ” በሚል የፀደቀው አዋጅ ነው።
ከላይ እንደ ተመለከተው የመንግሥት ይዞታዎች ወደ ግል ይዞታ የሚዛወሩበት ዋና ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥርት ነው። ይሁንና፣ በቅድሚያ በሕገ ወጥ መንገዶች የሚወጣውን ገንዘብ ለመቆጣጠር ጥብቅ ዕርምጃዎች ቢወሰዱ አትራፊ ድርጅቶችን መሸጥ ላያስፈልግ ይችላል። በዚህ ረገድ ባልፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ብቻ ሃያ ቢሊዮን ዶላር በሕገ ወጥ መንገዶች ከአገሪቱ እንደ ወጣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በየካቲት አምስት ባወጣው ሪፖርት አስታውቆ ነበር (ሪፖርተር፣ የካቲት 6)። ይህም በየዓመቱ 2.2 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገዶች ወጥቷል ማለት ነው። ይሁንና፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሪፖርት የሚያደርገው በገቢና በወጪ ንግድ ደረሰኞች የሚጭበረበረውን ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። በሌሎች መንገዶች የሚወጣው ተጨምሮ ቢታሰብ፣ በ2009 ዓ.ም. ከውጭ ንግድ ተገኘ ከተባለው የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በላይ ይሆናል።
የቪዛውን በሚመለከተው፣ ኒዮርክም ሆነ ጄኔቫና ብራስልስ ተመሳሳይ የጉባዔዎች አስተናጋጅ መዲናዎች ናቸው። ስለሆኑም ግን፣ የቪዛ ግዴታዎችን አላነሱም። ሽብርተኝነት፣ የአደንዛዥ ዕፆች ገበያና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በሆኑበት በዛሬው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ እንደውም፣ የቪዛ ሥርዓቶቻቸውን አጠናክረዋል። በኅብረት ስም ከሆነም፣ የአውሮፓ ኅብረት በቪዛ አልጀመረም። ለአባል አገሮች ብቻ የሚሠራው ሼንገን በ1985 (1977) የተፈቀደው የአውሮፓ የጋራ ገበያ በ1957 (1949) ከተመሠረተና ለ30 ዓመታት ከተገነባ በኋላ ነው።
በሌላው በኩል ደግሞ ግን፣ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ ወደ አፍሪካ አገሮች ያለቪዛ መሄድ ስለመቻላቸው ከየአገሪቱ ጋራ ስለተደረገ ስምምነት አይታወቅም። ከአፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚጎርፉት አፍሪካዊ ቱሪስቶችና ከቱሪዝም ስለሚገኘው የገቢ መጠን የተባለው በምን ተጨባጭ ጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደቆመም አይታወቅም. . . ለማንኛውም የዛሬው ጊዜ የኢትዮጵያዊያን የቅድሚያ ጥያቄ የአፍሪካዊያን ወደ ኢትዮጵያ መጉረፍ/አለመጉረፍ አይደለም። ይልቁኑ፣ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ምድር እንደ ዜጋ ተዘዋውረውና አፍርተው ለመኖር መቻል/አለመቻላቸው ነው። በመጨረሻም ደግሞ ግን፣ ኢትዮጵያ ሌላዋ የአፍሪካ ጋምቢያና ሌላዋ የኤዢያ ታይላንድ ሆና እንዳታበቃም ሊታሰብበት ይገባል።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጥር 9 ቀን “የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ” የተባለውን አዋጅ ያፀደቀው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመስከረም 2016 ዓ.ም. (2008) የወሰነውን የስደተኞች ጉዳይ ጥያቄ (Comprehensive Refugee Response Framework CRRF) ተከትሎ እንደሆነ ይታወቃል። ውሳኔው እንደሚታወሰው፣ ስደተኞች በየተሰደዱበት አገር ያላቸውን ለመደራጀት፣ ለመዘዋወር፣ ለመማር፣ በግብርናና በንግድ ለመሠማራት፣ ለእነሱ በተወሰኑና የተመቻቹ የሥራ መስኮች ለመቀጠር፣ ንብረት ለማፍራትና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብቶች ይደነግጋል። ያደጉ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጭምር አሳውቀው ውሳኔውን የገፉት እየጎረፈባቸው ያለውን ስደተኛና ሥራ ፈላጊ ለመግታት በማሥላት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ኢትዮጵያ የድረጅቱ አባል እንደመሆኗ ውሳኔውን ማክበር ይጠበቅባታል። ይሁንና፣ ሒሳቡ ቀላልና ግልጽ ይደረጋል ስለሆነው የገንዘብ ድጋፍም ልዩ ጥናት አያስፈልግም። ሃንሰን እንዳለው ለምሳሌ ‹‹በአሜሪካ አንድን ስደተኛ አስፍሮ ለማቋቋም እስከ 8,000 ዶላር ሲያስፈልግ፣ በደሃ አገሮች በእጅግ አነስተኛ ይሆናል፤›› (Randall Hansen፣ The Comprehensive Refugee Response Framework፣ June 2018)።
የሆነው ይሁንና፣ ኢትዮጵያ ዛሬ በምትገኝበት ባልተረጋጋ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥና የሚሊዮን ተፈናቃዮቿና ሥራ አጦች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረትን በሚጠይቁበት ሁኔታ ውስጥ የተመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ አጣዳፊ ብሔራዊ ጉዳይ የሆነበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። በሌላም በኩል፣ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋራ እንኳን ውይይትና ምክክር ባለመደረጉ፣ የጋምቤላ ተወላጆች የተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ተገደዱ። ከበቂ በላይ አጣዳፊ ጉዳዮች ያሉበት የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር ለአንዳንድ ዛሬና ዛሬ አስቸኳይ ያልሆኑ ጉዳዮች ጊዜውንና ሐሳቡን ማሻማት ያለበት አይመስለኝም። በተለይም ተቃውሞዎችን ለመቀስቀስ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድሞ በውል መመዘን የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ውስጣዊ ውስብስብ ችግሮች በውጭዎቹ ደስታና ሙገሳ የሚፈቱ እንዳልሆኑ ተጨማሪ ማስታወሻ አያስፈልገውም።
ከዶ/ር ዓብይ አስተዳደር ፊት ያለው አንደኛው አስቸኳይና ከባድ የቤት ሥራ፣ የኢሕአዴግን ካድሬ “ሙያተኞች” በእውነተኛና ሃቀኛ የየመስኩ ባለሙያዎች መተካት ነው። ይኼ የቤት ሥራ ምናልባትም፣ ከባዱና የሪፎርሙን መሳካት/አለመሳካት የሚወስን ነው። ከታሪካችን ለማስታወስ አፄ ኃይለ ሥላሴ የራሳቸው ምክንያቶች የነበራቸው ቢሆንም፣ ከጠላት ወረራ መልስ ባንዳዎችንም ለመሾም ተገደው ነበር። በወቀቱ የተሰጠው ምክንያት፣ ‘ዘመናዊነትን ተላብሰው የተገኙት ባንዳዎቹ ናቸው’ የሚል ቢሆንም ቅሬታውና ተቃውሞው እስከ ዘመናቸው መጨረሻ ድረስ ያላባራ ቢሆንም፣ ውሳኔያቸው ለ1930 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን ነበር ለማለት ይቻላል።
ለ1967 ዓ.ም. የመሬት አዋጅ እወጃ ዝግጅት ሲደረግ፣ አርቃቂዎቹ አዋጁን በንጉሠ ነገሥቱ ቢሮክራሲ ወደ ሥራ ለመተርጎም እንደማይቻል አሳውቀው ለውጥ እንዲደረግ ጠየቁ። ደርጉ የገበሬ ማኅብራትን መቋቋም፣ የንዑስ ደርጎችን መበተንና የነባር አስተዳዳሪዎችን መተካት ተቀበለ። ነባር አስተዳዳሪዎቹ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ይቀርባሉ ተብለው በተገመቱ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት፣ የግብርናና የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞችና በመምህራን ተተክተውና በዘማቾች ተደግፈው የገበሬ ማኅበራትን ወደ ማቋቋምና አዋጁን ወደ ማስፈጸም ሥራ ተገባ። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ የሚካሄዱት ለውጦች በተመሳሳይና በግልጽ የሙያ ብቃትና የአገልጋይነት ቁመና መሥፈርቶች መሠረት ቢፈጸሙ፣ ለብሔራዊ ፀጥትና ሰላም መጎልበትና ለአስተዳደር አገልግሎት መሻሻል የሚጠቅም ይሆናል።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በአንድ በኩል የማዕከሉ የጋራና የክልሎች ራስን በራስ አስተዳደር ባልተጣጣሙበት “ሥርዓት” ሥር የምትስተዳደር አገር ናት። ክልሎችና ከተሞች በዚህ ላይ በሕዝባዊ መሰል (Populist) ድርጅቶችና ቀስቃሾች የተሞሉበት አገር ናት። ይህ በራሱ የተወሳሰቡ ሁኔታዎችን ማስፈኑ ሳያንስ፣ ኢሕአዴግ ራሱ በሌላው በኩል በአንድ ረድፍ ባለማቆሙ፣ ሁኔታዎች በባሰ ተወሳስበዋል። የኢሕአዴግ ውስጥ ፍትጊያና ሽኩቻ በኢሕአዴግ ውስጥ መደረግ ባለበት መሠረታዊ ሪፎርም የተፈታውን ያህልና ተቃዋሚ ድርጅቶች ለጋራ ብሔራዊ ዕይታና ኃላፊነት የበቁትን ያህል፣ የሪፎርሙ የመሳካት ዕድል ይጎለብታል። በሌላ አገላለጽ ኢትዮጵያ ዛሬ ከምትገኝበት አገራዊ ቀውስ ውስጥ ወጥታ ልትፈካ የምትችለው፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ወደ ፊት ተመልካች የሆኑትን ያህልና በቅድሚያ ቅድሚያ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩትን ያህል ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡