አትክልትና ፍራፍሬ አቀናባሪዎች ማኅበሩን ተቀላቅለዋል
ከስድስት ወራት በፊት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝቶ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃና የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ለአካባቢ ብክለት መንስዔ የሆነውን የመጠጦች አንገት ላይ የሚታሸገውን የፕላስቲክ ሽፋን ለማንሳት ወሰነ፡፡
ማኅበሩ ሐሙስ፣ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከውሳኔ ላይ የደረሰው ለገበያ በሚቀርቡት ምርቶች የአንገት ሽፋን ሳቢያ አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ብክለት ከመቆጣጠር አንፃር ፋይዳ እንዳለው በማመኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ክዳን ላይ የሚጠቀለለውን ሽፋኑን ማስቀረት ሕገወጥ የውኃ አቅርቦትን ለመቆጣጠር ያስችላል ብለው በማመናቸው፣ የማኅበሩ አባላት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃና የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲና የጥራት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ የምግብ ጥራትና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ ከተስማሙ በኋላ የማኅበሩ አባላት እንዲወያዩበት ተደርጎ ውሳኔው እንደተላለፈ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
መጠጥ አምራቾቹ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸውን ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለማቅረብ ስለማቀዳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም እንዲረዳ ታስቦ ማኅበሩ መቋቋሙ ተጠቅሷል፡፡ አብዛኞቹ አምራቾች በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያዎች ለማቅረብ ግን ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ተጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት 65 የታሸጉ ውኃ አምራቾች፣ 11 የማዕድን ውኃና፣ ሁለት የለስላሳ መጠጥ አምራቾች በምርት ሥራ ላይ ሲሆኑ፣ አሥር ኩባንያዎችም በዘርፉ ለመሰማራት በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት ተሳታፊዎች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የኤክሳይስ ታክስ ጉዳይና ሌሎችም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩባቸው እንደሚገኙ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት የታክስ ጫና፣ ቅጣትና ወለድ ፈታኝ እንደሆኑባቸውም ገልጸዋል፡፡ ኤክሳይስ ታክስን በተመለከተ የወጣውን አዋጅ 307/1995 ምንም ዓይነት የአፈጻጸም ደንብና መመርያ የሌለውና ክፍተት እንዳለበት የዋን ውኃ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንየው ዘለቀ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
‹‹ደንቡና መመርያው ስለማይታወቅ ኤክሳይስ ታክሱ ለእኛ ነው የሚገባው በማለት በአካባቢው ማኅብረሰብም፣ ገቢዎች ሚኒስቴርም ታክሱን መሰብሰብ ያለብን እኛ ነን በማለታቸው ያልተጣሩ አስቸጋሪ ጉዳዮች ችግር እየፈጠሩ ነው፤›› በማለት አቶ እንየው ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች በታሸጉ ውኃዎች ላይ የሚነሱት የጥራት ጉድለት ጥያቄዎችን በተመለከተም የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና አስተዳደር፣ ክብካቤና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ ተስማሚነትና የጥራት ምዘና ተቋማት ፈትሸው ያረጋገጧቸው ምርቶች ለገበያ እንደሚቀርቡና በጥራት ረገድ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ሥጋት እንደሌለባቸው አምራቾቹ ይናገራሉ፡፡
የታሸገ ውኃ ክዳን ሽፋን ውሳኔን በተመለከተ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ብቸኛ ተቃውሞ ያቀረበው ዋን ውኃ ሲሆን፣ የክዳን ሽፋኑ ኖሮም ውኃው በተለያየ አቧራና ብናኝ መበከሉ አይቀርም በማለት ውሳኔውን ተቃውመዋል፡፡
በአንፃሩ የአንገት ክዳን ሽፋኑ በማንኛውም ግለሰብ በቀላል ዋጋ ተመሳስሎ ማምረት ስለሚቻል፣ ከዚህ ይልቅ ሽፋኑን በጠንካራ ክዳን መተካት ሕገወጥ አምራቾችን እንዲታቀቡ ለማድረግ ተመራጭ ዘዴ እንደሚያደርገው አምራቾቹ አስቀምጠዋል፡፡
በሌላ በኩል የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ከማኅበሩ ጋር መዋሃዱን በዕለቱ በጉባዔው ፀድቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የምግብና አስተዳደር እንዲሁም የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መሠረታዊ የሆነ ጥራትን መሠረት ያደረጉ ትምህርት ተኮር ሥልጠናቸውን አቅርበዋል፡፡