Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስኪ እንነጋገር የኢኮኖሚውን ነገር

ኢኮኖሚያችን መላ ያስፈልገዋል፡፡ በተለይ ኢኮኖሚውን በሚገባ ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ አሠራሮች በቶሎ መተግበር አለባቸው፡፡ ወትሮም በርካታ ችግሮችን ተሸክሞ አሁን ላይ የደረሰው የአገራችን ኢኮኖሚ በበርካታ ችግሮች ተከቦ የሚገኝ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህ ሊፈጸሙ ይችላሉ የተባሉ አንዳንድ ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎች ተስፋ ሰጪ የመሆናቸውን ያህል፣ በፍጥነት ወደ መሬት ለማውረድ ጊዜ እየጠየቁ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና በተሻለ ለማራመድ የታሰቡ ጉዳዮች በእርግጥም ጊዜ የሚጠይቁ ቢሆኑም፣ በፍጥነት መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ግን ማዝገም ተገቢ አይደለም፡፡

ለምሳሌ ስለአገር ኢኮኖሚ ሲወራ እንደ ችግር ከምናነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ ይህ ችግር ሥር የሰደደና ዛሬም የአገር ችግር ሆኖ ስለመዝለቁ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ችግሩ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ለዓመታት እየተንከባለለ የመጣ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ለችግሩ የሚሆን መፍትሔ ያለመበጀቱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ተስፋ የተጣለበት የወጪ ንግዱ በተያዘለት ግብ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ ይንደፋደፋል፡፡ በኮንትሮባንድ ተጠልፎም ከዕድገቱ ይልቅ የኋሊት ጉዞው ጎልቶ ወጥቷል፡፡ አንዳንዶችም በወጪ ንግድ ስም እንዳሻቸው የሚሆኑበት ዘርፍ እንዲሆን የተለቀቀ እስኪመስል ድረስ መቆየቱ ችግሩን አብሷል፡፡ መንግሥት ራሱ ከዚህ ረገድ የተፍታታ ፖሊሲ ያለማቅረቡ የውጭ ምንዛሪ ችግር አብሶታል፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡

ይህንን የአፈጻጸም ችግር የቀድሞ ታሪክ ነው ብለን እናስበው፡፡ አሁንስ የወጪ ንግዱን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪውን ከፍ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው? ካልን የሚያጠግብ መልስ አናገኝም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ እየተሠራ ነው የሚባለውም ነገር ብዙ የሚቀረው ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አንደበት ያደመጥነውም ቢሆን፣ ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ፈጣን የሆኑ መፍትሔዎች አለመበጀታቸውን ነው፡፡ በአንፃሩ ግን አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለል ባንካቸው እየወሰደ ስላለው ዕርምጃ ጥናት እየተደረገ መሆን ከመግለጽ የዘለለ አለመሆኑ፣ ለእኔ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት ተጨባጭ ሥራ አለመሠራቱን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ አማራጮች ላይ እየተሠራ አይደለም፡፡

ከለውጡ ወዲህ አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቻቸው ባደረጉት ጥረት የተገኘው የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ጊዜያዊ ችግሮችን ፈትቷል፡፡ እንዲህ እየተደረገ ግን አይዘልቅም፡፡ አጭር ጊዜ ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማጎልበት ያስችላሉ የተባሉ ምን ዓይነት አፋጣኝ ፖሊሲዎች በብሔራዊ ባንክ ቀረቡ? ካልን ምንም የለም፡፡ ጥናት አጥንተናል የሚል ብቻ ነው፡፡ በተግባር የሚታይ መሆን ካልቻለ ዋጋ የለውም፡፡

ከገዥው መረዳት የሚቻለው የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለመባባሱ ዋናው ምክንያት የወጪ ንግድ መቀዛቀዙ ነው፡፡ አዎ ልክ ነው፡፡ ወጪ ንግዱ ተቀዛቅዟል፡፡ የሚፈለውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት ተስኖታል፡፡ የሚጠበቅበትንም እያስገኘ ባለመሆኑ በየጊዜው እያደገ የሄደውን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለመሸፈን አላስቻለም፡፡ እንዲያውም ዓመታዊ የአገሪቱን የነዳጅ ግዥ የሚሸፍን አልሆነም፡፡ ገዥውም ከዚህ ችግር ለመውጣት አሁንም ወጪ ንግዱ ላይ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ ይህም ሐሳባቸው ያስማማናል፡፡ ችግሩ ግን የውጭ ምንዛሪ ችግሩን በአንድ ወጪ ንግድ ላይ በመርኮዝ ለማቃለል መሞከር ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡ አሁን አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ታገኝባቸዋለች ተብለው ከሚጠቀሱ ምንጮች የሚሻገር ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም ላይ ናቸው ሲባል አንዱ ሲጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ የሚለወጡ ፖሊሲዎችን ጭምር ነበር፡፡ ምክንያቱም ወጪ ንግዱ የሚነገርለት ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሥራዎች ላይ መድከም የግድ ይላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አገሪቱ የተቆላለፈ የፋይናንስ ሕግጋቶቿን ማስተካከል የግድ ቢሆንም ይህ እየታየ አይደለም፡፡

የውጭ ንግዱን ካሳደግን የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማቃለል ይቻላል የሚለው እምነት እውነት ቢሆንም ተግባር ላይ መታየት አልቻለም፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እንዲሁ እየተባለ የወጪ ንግዱ ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ በመሆን ፈቅ ማለት እንዳልቻለ በመገንዘብ አማራቾችን መመልከት ለምን ተፈራ?

ጭራሽ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢን ከፍ በማድረግ ለዓመታት የጎላ አስተዋጽኦ የነበራቸው የወጪ ንግድ ምርቶች የቁልቁለት ጉዞ ላይ የመሆናቸው ነገር፣ ችግሩን እያባሰው በመሆኑ መፍትሔ ሊበጅ ይገባ ነበር፡፡ ለምሳሌ የቁልቁለት ጉዞ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥው የ2006 ዓ.ም. የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ በምሳሌነት ጠቅሰው፣ በወቅቱ የተገኘው 430 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ ገቢ 32 ሚሊዮን ዶላር ማዘቅዘቁ በእጃችን ያለውንም እያጣን መሆኑን ያሳያል፡፡ በነገራችን ላይ በ2005 ዓ.ም. አገሪቱ ከወርቅ ወጪ ንግድ ተገኝቶ የነበረው 630 ሚሊዮን ዶላር ስለነበር፣ አሁን ከወርቅ ተገኘ የተባለው የውጭ ምንዛሪ በምን ያህል ደረጃ እያሽቆለቆለ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡

ይህ የቁልቁለት ጉዞ መታየት ከጀመረ ረዘም ያሉ ዓመታት እንደሆነ እየታወቀ፣ ለምን እንዲህ ሆነ? ብሎ በ2006 ዓ.ም. ባይቻል በ2007 ዓ.ም. እንዲስተካከል ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ሰፊ ጊዜ የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ያለው ባለመኖሩ ችግሩ ብሶ ተገኝቷል፡፡ አሁን ደግሞ የለውጥ ሒደቱ እንዲህ ያለውን ነገር ለማረም ጊዜ መስጠቱ ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህ አሁንም የችግሩን ምንጭ አይተን እርምት እንወስዳለን ማለቱን ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡

በእርግጥም የወጪ ንግዱን ገቢ በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ከተቻለ እሰየው ነው፡፡ ችግሩ ግን ይህንን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው? የሚለው ጥያቄ ስለእውነት መመለስ አለበት፡፡ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ አማራጮች ይታዩ ከሚባልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ቢያንስ በእጃችን ያለ የወጪ ንግድ ምርቶችን በትክክለኛው ገበያ እንዲራመዱ ለማድረግ ዘንድሮም ጥናት የሚያስፈልገው አለመሆኑ ነው፡፡ የሚሻው ቁርጠኛ ተግባር ነው፡፡ ሕግ ማስከበርና ያለመታከት በመሥራት ብቻ ቢያንስ የወርቅን፣ የቀንድ ከብትን፣ የቡናን ገቢ ወደ ነበረበት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የዓመታት ጉዞው ነገም እምነት እንዳይጣልበት አድርጓልና ወጪ ንግዱን ወደፊት ለማራመድ ይወሰዳሉ የተባሉ ዕርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ ለገባንበት ችግር መፍትሔ የሚሆኑ ሌሎች አማራጮች ግን ጊዜ ሊሰጣቸው አይገባም ነበር፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ዕድገት ይበጀው የተባሉ አዳዲስ አሠራሮች እየተቀረጹ ነው ቢባልም፣ እነዚህ አዳዲስ ጉዳዮችም ቢሆኑ በቶሎ ሥራ ላይ እንዲውሉ አለመደረጉም ሌላው ችግር ነው፡፡

ለምሳሌ እንደ ለገደንቢ ያሉ ወርቅ ማምረቻዎች መዝጋት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ማሳጣታቸው ታውቆ፣ የሕዝብ ጥያቁ በአግባቡ እንዲመለስ በማድረግ የተጎዳውን ኢኮኖሚያዊ በትንሹ መጠገን ይቻል ነበር፡፡ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ ያቀርቡ የነበረው ወርቅ መቀነሱ ዕርምጃም ይሻል፡፡

ስለዚህ አሁን ያለበትን ችግር ለመወጣት የሚያስችሉ በአፋጣኝ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ብቻ ሳይሆን የእስከዛሬው ፖሊሲ አዋጭ አይደለምና ፖሊሲውን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ይህንን እየመከሩ ነውና አማራቾችን በመጠቀም ችግሩን የመፍታት ሥራ ይሠራ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት