የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በሚያደርገው ድጋፍ አማካይነት የዴሞክራሲና የአስተዳደር ዘርፎችን በሙያ ክህሎታቸው እንዲያግዙ በከፍተኛ የመንግሥት አማካሪነት እየተቀጠሩ የሚገኙ ሙያተኞች የቅጥር ሒደት፣ በውድድርና ግልጽነት የተመራ አይደለም የሚል ቅሬታ ተነሳበት።
የዩኤንዲፒ የአስተዳደርና የዴሞክራሲ ተቋማት የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት፣ የመንግሥትን የአቅም ውስንነት ለመሙላት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል። ይኼንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፕሮጀክት ድጋፍ በመጠቀም የላቀ የትምህርትና የሙያ ብቃታ አላቸው የተባሉ፣ በተለይም በውጭ አገሮች የተማሩና የሠሩ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የመንግሥት አማካሪነት እየተቀጠሩ ነው፡፡
ዩኤንዲፒ በኢትዮጵያ ቢሮው በኩል ለሚቀጠሩት ግለሰቦች ከፍተኛ ወርኃዊ የደመወዝ ወጪ በጀት መድቦ ክፍያውን በመፈጸም ላይ ይገኛል። በዚህ መሠረትም በርካታ ግለሰቦች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በአማካሪነት ተቀጥረው በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትም በተመሳሳይ መቀጠራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ ዩኤንዲፒ የሚያደርገውን የደመወዝ ድጋፍ ተጠቃሚ በመሆን ቅጥር ከፈጸሙ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይገኝበታል። የቅጥር ሒደቱ ትውውቅን መሠረት ያደረገና ግልጽነትን በተከተለ ውድድር እየተፈጸመ አለመሆኑን የሚገልጽ ቅሬታ ለዩኤንዲፒ መቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል።
ይኼንንም ተከትሎ ዩኤንዲፒ የዚህን ፕሮጀክት አፈጻጸም በተመለከተ ሰሞኑን ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተባባሪ የውጭ መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር በመሆን መገምገሙን ምንጮች ገልጸዋል። በግምገማውም ዩኤንዲፒ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት የተመድ መርህን ባልተከተለ፣ ግልጽነቱ በተጓደለና ውድድርን መሠረት ባላደረገ ሒደት ቅጥር የተደረገባቸው 15 መደቦችን እንደማይቀበል በመወሰን፣ ይኼንኑ ለመንግሥት እንዳሳወቀ ምንጮች አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በተወሰኑ የሥራ መደቦች ላይ ቅሬታ እንደቀረበ፣ ከእነዚህም መካከል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሸፈኑ የማማከር የሥራ መደቦች እንደሚገኙበት ምንጮች አክለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ በተለይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተፈጸመ ቅጥር ላይ ቀረበ ስለተባለው ቅሬታ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ምዕራፍ ሞገስ፣ በተቋማቸው የሚፈጸሙ ቅጥሮች የተመድ መሠረታዊ መርህ የሆኑት ግልጽነት፣ ውድድርና ታማኝነትን በተከተለና በይፋ ማስታወቂያ ጥሪ አማካይነት የሚመጡ ማመልከቻዎችን በጥልቅ በመገምገም እንደተፈጸሙ ገልጸዋል። ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማካሪነት ቅጥርም የተፈጸመው በዚሁ አግባብ መሆኑን አስረድተዋል።