Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፈረንሣይ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለላሊበላ ዕድሳት ቃል የገቡት ድጋፍ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል

  የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለላሊበላ ዕድሳት ቃል የገቡት ድጋፍ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል

  ቀን:

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፈረንሣይን በጎበኙበት ወቅት ፈረንሣይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳትና ጥገና ድጋፍ እንድታደርግ በመጠየቃቸው ምክንያት፣ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ድጋፍ እንደሚሰጡ በገቡት ቃል መሠረት ሳምንት በኋላ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት ይፋ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል ተባለ፡፡

  መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ እግረ መንገዳቸውን ላሊበላን እንደሚጎበኙ ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቀደም ብለው የተያዙ የጉብኝት ቀናት ሲለዋወጡና የቆይታ ጊዜያቸውም ከሁለት ቀናት ወደ አንድ ቀን ማጠሩንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁንና በጉብኝታቸው ፈረንሣይ ለላሊበላ ዕድሳት ቃል የገባችውን የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በፓሪሱ ስምምነት ወቅት ይፋ በተደረጉ ሦስት መሠረታዊ አጀንዳዎች አፈጻጸም ላይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡

  የፕሬዚዳንት ማክሮን ጉብኝት ለላሊበላ ቃል የተገባውን የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ሊደረግበት እንደሚችል ተስፋ ከመደረጉ በቀር፣ እስካሁን የተረጋገጠ ጉዳይ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለጉዳዩ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው፣ እስካሁን እንዲህ ያሉ መረጃዎች አለመጠናቀራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ለፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ሁለት ሳምታት ያህል ስለሚቀሩ በሒደት መረጃዎች ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ስለፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዝርዝር መረጃው ወደፊት እንደሚገልጽ የሚጠቁም ምላሽ ከመገኘቱ በቀር የተባለ ነገር የለም፡፡

  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የዓለም ቅርሶች አንዱ የሆኑት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ በተለይም ቤተ መድኃኔዓለምና ቤተ መርቆሪዎስ ከዝናብና ከፀሐይ እንዲከላከለው የተተከለለት ጊዜያዊ ከለላ ከሚገባው ጊዜ በላይ ሳይነሳ በመቆየቱ፣ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጫና በማሳደር አሳሳቢና ጉዳት ላይ ሊጥለው የሚችል ሥጋት በመፈጠሩ ምክንያት ለዕድሳት የሚውል ገንዘብ የማሰበሳብ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ 

  ከላሊበላ ድጋፍ ባሻገር በከተማ ልማት መስክ ብሎም በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት መስክ ፈረንሣይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ከተደረጉት ስምምነቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የበጀት ድጋፍ ልትሰጥ የምትችልበት አዝማሚያ እንዳለ ፕሬዚዳንት ማክሮን ፍንጭ ስለመስጠታቸው ተዘግቦ ነበር፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ የተደረጉ መረጃዎች እንደሳዩት፣ በፈረንሣይ በትልቅነቱ ሁለተኛው እንደሆነ የሚነገርለት ብሬድ ባንክ ፖፑላር የተሰኘው ባንክ፣ በኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር እየተዘጋጀ ነው፡፡

  ባንኩ ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳላት በማመኑ ኦፕሬሽን ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንዳለው የባንኩ ኃላፊ መግለጻቸውን ለስ ኤኮስ የተሰኘው የፈረንሣይ ዕለታዊ ጋዜጣ ያወጣውን ዘገባ በርካታ የዜና አውታሮች ተቀባብለውታል፡፡ ምንም እንኳ ባንኩ ይህንን ይበል እንጂ፣ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ መሰማራት እንደማይችሉ የአገሪቱ ሕግ ይደነግጋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img