Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መርህ የሌለው ትውልድ ለአገር አደጋ ነው!

ከበድ የሚሉ ጊዜያትን በብልኃት ተሻግሮ ካሰቡበት ለመድረስ፣ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ መስማማት መቻል ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም ነገር ላይ መስማማት ባይቻል እንኳ፣ መሠረታዊ ልዩነቶችን ገታ በማድረግ በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና መግባባት ይቻላል፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከሌሎች በተሻለ ሥራቸውን የሚያቀላጥፉት በድርድር አማካይነት ነው፡፡ በሌሎችም መስኮች ሰዎች ካልተነጋገሩና ካልተደራደሩ፣ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ማስመዝገብ አይችሉም፡፡ ወደ ወቅታዊው የአገር ጉዳይ መለስ ስንል በእያንዳንዱ ዕለታዊ ጉዳይ ጽንፍ መያዝ እየተለመደ ነው፡፡ በተለይ ተምረናል የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል እንኳን ተነጋግሮ ለመደራደር ይቅርና መደማመጥ ያቃተው ይመስላል፡፡ አንዱ ይነሳና አዲስ አበባ የማን ናት ሲል፣ ለማሰብ ከሚከብዱ ስድቦችና ዘለፋዎች ጋር ምላሾች ይዥጎደጎዳሉ፡፡ ብሔራዊ ክብረ በዓላት የመግባቢያ አጋጣሚዎች መሆን ሲገባቸው፣ ታሪክና ተረት እየተደበላለቁ የቃላት ጦርነቱ በየገመገሙ ያስተጋባል፡፡ ትናንት ጭቆናን አምርረው በመቃወም ለነፃነት ታግለናል ያሉ፣ ዛሬ ተረኛ ጨቋኞች ለመሆን ጣራ ሲቧጥጡ ያድራሉ፡፡ ለሕዝቡም ሆነ ለአገሪቱ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ ያላበረከቱ፣ የግል ዝና አካብተው ከእኛ በላይ ጀግና ላሳር ይላሉ፡፡ በዚህ መሀል ግን መደመጥ ያለባቸው፣ ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ የሚያመነጩና ትምህርት መስጠት የሚችሉ ተዘንግተው አገር የግዴለሾችና የቧልተኞች መጫወቻ እየሆነች ነው፡፡ መርህ በሌለበት ትርፉ ይኸው ነው፡፡

ምክንያታዊ ሰዎች በስሜት አይመሩም፡፡ ሲወዱም ሆነ ሲጠሉ በምክንያት ነው፡፡ ከወራት በፊት ጭቆና አንገሸገሸን ያሉ የጭቆና ጠበቃ ሲሆኑ ያሳፍራል፡፡ ለሐሳብ ነፃነት ታግለናል ያሉ ሐሳብ ለማፈን ሲሯሯጡ ማየት ያስገርማል፡፡ ለፍትሕ እንቆማለን ያሉ ለኢፍትሐዊነት በአደባባይ ከበሮ ሲደልቁ ያማል፡፡ ትናንት የመንግሥትን ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች የተቃወሙ፣ ተመሳሳይ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መቃወም ካቃታቸው ችግር አለ፡፡ የመርህ ሰዎች ሲቃወሙም ሆነ ሲደግፉ ምክንያታዊ ሆነው ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም የግድ አደባባይ ወጥቶ ማውገዝ ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ የሰላ ሒስ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ በጨዋነት እየተነጋገሩ መተራረም የሚጠቅመው ሕዝብንና አገርን ነው፡፡ በጨዋነት መነጋገር ሲያቅት ነው በየሥፍራው ግጭት እየተቀሰቀሰ ንፁኃን ሰለባ የሚሆኑት፣ የአገር አንጡራ ሀብት የሚወድመው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ለተለዩ ሐሳቦችና ፍላጎቶች መደላድል ማመቻቸት የግድ የሚሆነው፣ ለፀብ የሚቸኩለው ጭምር እንዲገራ ነው፡፡ ሰዎች የብርቱ አሰላሳዮችን ምክርና ተግሳፅ ሲሰሙ ለፀፀት ከሚዳርግ ድርጊት ይቆጠባሉ፡፡ ለውይይትና ለድርድር ቅርብ ይሆናሉ፡፡

ወጣቱ ትውልድ ከስሜት ይልቅ ለምክንያታዊነት ቅርብ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው፣ ወሰን ከሌለው የትምህርት ማዕድ ዕውቀት ሲገበይ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ከማንበብና ከመጻፍ በተጨማሪ አስተዋይነት ሲታከልበት ደግሞ አካባቢውን በሚገባ ይረዳል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ዓለምን ማሰስ ይጀምራል፡፡ ነውጠኞች ለሚፈልጉት ዓላማ በቀላሉ አይሠለፍላቸውም፡፡ ይልቁንም ብርቱ ሆኖ ይሞግታቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውሳኔዎቹ የሚመሠረቱት በዕውቀት ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ቤተሰብ፣ ኅብረተሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና የሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በርትተው መሥራት ያለባቸው ወጣቶችን ለማብቃት ነው፡፡ ይኼንን ማድረግ ሲያቅት ወጣቱ የአጥፊዎች መጠቀሚያ ይሆናል፡፡ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትሕ ጭምብል ያጠለቁ ግለሰቦች መሣሪያ ከሆነ ደግሞ ሳያውቀው ከባድ ስህተት ይፈጽማል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ በመሸጉ ኃይሎች ምክንያት ምን እየደረሰ እንደሆነና ምን ሊደርስ እንደሚችል በግልጽ ይታወቃል፡፡ የአገር ሰላም አስተማማኝ ባልሆነበት በዚህ ጊዜ ሊመጣ የሚችለውን ጥፋት ገምቶ አለመዘጋጀት፣ የሚያስከትለው አደጋ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ ይህ ወቅት በመርህ የሚመሩ አስተዋዮችን ይሻል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሟትን ፈተናዎች ማለፍ የቻለችው በአስተዋይ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡ ለአገራቸው ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ይጨነቁ የነበሩ ብርቱዎቹ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለተተኪው ትውልድ በክብር ሰጥተው አልፈዋል፡፡ የእነሱን ታሪካዊ አደራ አክብሮ ኃላፊነትን መወጣት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት ግን ጨዋነትን፣ መከባበርንና በሰጥቶ መቀበል መርህ አብሮ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያን ታላቅ አገር ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ትጉኃን ያሉትን ያህል፣ ፍርክስክሷን አውጥተው የዘመነ መሳፍንት ዓይነት የተበታተነች መንደር ለማድረግ የሚያሴሩ አሉ፡፡ አርቆ አሳቢ ለሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ከአንድነት የበለጠ ምንም ነገር የለም፣ የአገሩ ህልውናም ለድርድር አይቀርብም፡፡ ዋናው ቁምነገር መሆን ያለበት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት አገር እንዴት ትገንባ የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በነፃነትና በእኩልነት የሚኖሩባት ፍትሐዊ አገር ለመገንባት መተባበር ሲገባ፣ ያገኙትን ነገር ሁሉ መጠፋፊያ ለማድረግ ግድግዳ ሲደበድቡ ማደር ተገቢ አይደለም፡፡ ከመርህ ሰዎች አይጠበቅም፡፡

ይህ ዘመን ጥራት ያለው ሐሳብ ይፈልጋል፡፡ ጥራት ያለው ሐሳብ ለማግኘት ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚወዳደሩበት ዓውድ መፍጠር ይጠበቃል፡፡ ይህ ዓውድ ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ መነጋገርና መደማመጥ በሌለበት ግን ይህ ዓይነቱ ሥልጡን መንገድ አይገኝም፡፡ ነባሩ ትውልድ አዲሱን ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን መወጣት አቅቶት አገር ችግር ውስጥ ከገባች በኋላ ጩኸት ማብዛት ያስተዛዝባል፡፡ ትውልዱን በዕውቀት እንዲበቃ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ሞጋች ሐሳብ ይዞ መቅረብ የሚቻለው ዕውቀት ሲኖር ነው፡፡ ትውልዱን በዕውቀት ማነፅ ተሳዳቢውን ለመቀነስና ሞጋቹን ለማበራከት ይረዳል፡፡ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም በተቋማት ላይ የሰላ ትችት ማቅረብ የሚቻለው የዳበረ ዕውቀት ሲኖር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ስድብና ብልግና ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ ሙያዎች ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ወገኖች ወጣቱን ትውልድ መርዳት አለባቸው፡፡ የአገር ተስፋ ወጣቱ ስለሆነ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ በርካታ ተስፋዎች አሉ፡፡ እነዚህን ተስፋዎች ለማግኘት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተባብሮ በብልኃት ማሳለፍ ይገባል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የዕዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሥራ አጥነት አፍጥጠው ባሉበት መተባበር አለመቻል የከፋ አደጋ ያመጣል፡፡ ይኼንን በአንክሮ አለመገንዘብና አገርን አለመታደግ መርህ አልባነት ነው፡፡ መርህ የሌለው ትውልድ ለአገር አደጋ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...