Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአሜሪካ በዚምባቡዌ ላይ የጣለችው ማዕቀብ መራዘም

አሜሪካ በዚምባቡዌ ላይ የጣለችው ማዕቀብ መራዘም

ቀን:

የዚምባቡዌ ኢኮኖሚ ተዳክሟል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሕዝቡ ለችግር መጋለጡ ይነገራል፡፡ አገሪቱ ባለፈው አሥር ዓመት ከነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ በከፋ ሁኔታ ውስጥም ትገኛለች፡፡ በአገሪቱ በቂ መጠባበቂያ ገንዘብ የለም፡፡ የነዳጅ እጥረትም ሕዝቡን ፈትኖታል፡፡ የነዳጅን እጥረት ለማርገብ በነዳጅ ላይ ዋጋ መጨመርን እንደ አማራጭ የወሰደው የዚምባቡዌ መንግሥትም፣ ባለፈው ወር ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

ለ38 ዓመታት ዚምባቡዌን የመሯት ሮበርት ሙጋቤ፣ የነጮችን የእርሻ መሬት ባለቤትነት በመሻር ለጥቁር አርሶ አደሮች ካስተላለፉ በኋላ፣ አሜሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተቃውሞ የገጠማት ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብም አገሪቷን ቀስ በቀስ አንኮታኩቷታል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመታደግ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ሲረል ራማፎዛን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎች በዚምባቡዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ይህ ተስፋ ሆኖ ቀርቷል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ከሙጋቤ መውረድ በኋላ የአገሪቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ኤመርሰን ማንጋጋዋ የአሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ቢሠሩም፣ እስካሁን አልተሳካላቸውም፡፡ ይነሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የኢኮኖሚ ማዕቀብም፣ አሜሪካ ለአንድ ዓመት አራዝሜዋለሁ ስትል የዚምባቡዌን የኢኮኖሚ ተስፋ አጨልማዋለች፡፡

​​አሜሪካ በዚምባቡዌ ላይ የጣለችው ማዕቀብ መራዘም

 

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትላንት በስቲያ እንዳስታወቁት አሜሪካ ዚምባቡዌ ላይ የጣለችውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለአንድ ዓመት አራዝማለች፡፡

‹‹የዚህ ሰው [ኤመርሰን ማንጋጋዋ] ድርጊትና የአገሪቱ ፖሊሲዎች በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ሥጋት መሆናቸው እንደቀጠለ ነው›› ሲሉም የማዕቀቡን መራዘም ባስታወቁበት ወቅት ትራምፕ ተናግረዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናትም፣ ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋ በዚምባቡዌ ጋዜጠኞችን የሚገድበውን ሕግ እስኪያሻሽሉ፣ የጋዜጠኞች ነፃነት እስኪረጋገጥና ዜጎች ሰላማዊ ሠልፍ መውጣት እስኪፈቀድላቸው ድረስ ማዕቀቡ እንደማይነሳ አሳውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋን፣ ሮበርት ሙጋቤንና ሌሎች ግለሰቦችንና ቁሳቁሶችን ጨምሮ በ141 ዓይነቶች ላይ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ፣ ማዕቀቧን አንድታነሳ ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋም ጠይቀው ነበር፡፡

በፕሬዚዳንት ሙጋቤ ዘመን የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥሰት አለ በሚል በከፍተኛ የመንግሥትና የመከላከያ አመራሮች እንዲሁም የመንግሥት ድርጅቶች ላይ የተጣለው ገደብ በማንጋጋዋ ዘመን ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይገባም አሳውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በመስከረም 2018 ከቪኦኤ ጋር ቆይታ የነበራቸው በዚምባቡዌ የአሜሪካ አምባሳደር ብሬን ኒኮላስ፣ ዚምባቡዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ፣ ማንጋጋዋ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ቃል የገቡዋቸውን የፖሊሲ ማሻሻያዎች መፈጸም አለባቸው ብለው ነበር፡፡

ማንጋጋዋ ቃል የገቡትን ከፈጸሙ አሜሪካ ማዕቀቡን ለማንሳት ዝግጁ ናት ያሉት ሚስተር ኒኮላስ፣ ከዚምባቡዌ ፕሬዚዳንትም ሆነ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አሳውቀው ነበር፡፡

ሚስተር ኒኮላስ ይህን ይበሉ እንጂ፣ በዚምባቡዌ ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያ አልተደረገም፡፡ በመሆኑም ማዕቀቡ ዳግመኛ ለዓመት ተራዝሟል፡፡ ይህም ፕሬዚዳንቱን ማንጋጋዋን ጨምሮ የአገሪቱን ባለሥልጣናት አስደንግጧል፡፡

አሜሪካ በዚምባቡዌ ላይ የጣለችው ማዕቀብ መራዘም

 

የዚምባቡዌ የኢኮኖሚ አቅም

ዚምባቡዌ በተለይ የቱሪዝም፣ የግብርናና የማዕድን ሀብት ባለፀጋ ናት፡፡ አገሪቷ በዓለም ቆንጆ ከሚባሉ አገሮች አንዷ ስትሆን፣ የቱሪዝም ሀብቷም ብዙዎችን የሚያማልል ነው፡፡

የግብርና ዘርፍም ቢሆን በተለይ ሙጋቤ እ.ኤ.አ. በ2000 ነጭ የሰፋፊ እርሻ ገበሬዎችን አግደው ለጥቁሮች ከስጠታቸው በፊት የበለፀገ ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ ጊዜ አንስቶ አገሪቷ ከውጭ በገጠማት ተቃውሞና እርሻውን የተረከቡት አርሶ አደሮች የሰፋፊ እርሻ አስተዳደር ልምድ ማነስ ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ማሽቆልቆል ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሆኖም የዚምባቡዌ ግብርና ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡

ማዕድን የዚምባቡዌ ሌላ ፀጋ ነው፡፡ በአገሪቱ 40 የተለያዩና ውድ ዋጋ ያላቸው ማዕድናት ይገኛሉ፡፡ ይህ በአግባቡ ቢተዳደር ለዚምባቡዌ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ ሆኖም ዚምባቡዌ ፀጋዋን በአግባቡ ለመጠቀም አልቻለችም፡፡ በተለይ በአገሪቱ ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ አገሪቱን አንኮታኩቷታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ማንጋጋዋም ቃል የገቡትን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ መታደግ አልቻሉም፡፡ ባለፈው ወር በነዳጅ ላይ የተጣለው የ150 በመቶ ጭማሪም ነዋሪውን አስቆጥቶ ለተቃውሞ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...