ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ መርከቦች የኤርትራ ጭነቶችን ወደ ቻይና በማጓጓዝ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ሰሞኑንም ሰመራ የተሰኘችው የኢትዮጵያ መርከብ ለመጀመርያ ጊዜ ከቻይና ያጓጓዘቻቸውን ጭነቶች ወደ ሴኔጋል ማድረሷን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው ከሆነ፣ በዚህ ዓመት በአፍሪካ ባልተለመደ መልኩ የአፍሪካ አገሮችን በንግድ የማስተሳሰር ሥራን የኤርትራ ጭነቶችን ወደ ቻይና በማመላለስ የጀመረውን አገልግሎት ወደ ሴኔጋል አሻግሯል፡፡ የሴነጋልን ጭነቶች ከቻይና በመጫን ወደ ዋና ከተማዋ ‹‹ዳካር በማድረስ አፍሪካን ከሌላ አኅጉር በንግድ ያገናኘ የመጀመርያው አፍሪካዊ የመርከብ ኩባንያ ሆኗል›› በማለት ድርጅቱ ስለራሱ ያሰፈረው መረጃ ይጠቅሳል፡፡ ይሁንና ምን ያህል ጭነት እንደተጓጓዘ አልተገለጸም፡፡ ከዚህ ቀደም ከቻይና ወደ ኤርትራ፣ ከኤርትራም ወደ ቻይና በኢትዮጵያ መርከብ አማካይነት ጭነት መጓጓዝ እንደጀመረ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
የጭነት አገልግሎቱን ሰመራ በተባለችው ብሔራዊ መርከብ አማካይነት በማጓጓዝ፣ ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ዳካር ወደብ ጭነቷን ለማራገፍ መግባቷን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባሰፈረው ጽሑፍ መሠረት፣ የአፍሪካ ኅብረት ያወጣውን ‹‹አጀንዳ 2063›› ማለትም የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስርና የፓን አፍሪካ የመርከብ ኩባንያ ለመመሥረት የተወጠነውን ዕቅድ መገለጫ የሆነውን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መርከቦች ከወዲሁ በጥቂቱ እንደጀመሩት ገልጿል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ በ50 ዓመታት ጉዞው እንዲህ ያለውን ድንበር ዘለል አገልግሎት ማቅረቡ ካካበተው ልምድና ከዕድሜው አኳያ አንዳንዶቹ በድርጅቱ ድረ ገጽ ባሰፈሩት ሐሳብ መሠረት ከዚህም በላይ ማድረግና ማደግ የሚጠበቅበት ተቋም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በድርጅቱ መግለጫ ላይ ከተሰጡ ሐሳቦች መካከል አንድ የድረ ገጹ ጎብኚ ‹‹ገና ሁለት አገሮችን አስተሳስሮ የበርካታ ደረጃ ላይ መድረስ የለበትም፡፡ የመርከቦቹን ደረጃ ማሻሻል አለበት፡፡ ድርጅቱ ቢያንስ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁና በሁሉም የአውሮፓ አገሮች ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉ ኢንተርናሽናል መርከቦች ሊኖሩት ይገባል። አሁን ያሉት መርከቦች ካላቸው ደረጃ አንፃር በሁሉም የዓለም ክፍል ተዘዋውረው መሥራት ባለመቻላቸው፣ እንደ ድርጅትም እንደ አገርም መገኘት የነበረበት ገቢ አልተገኘም፤›› በማለት ሐሳባቸውን አስፍረዋል፡፡ ድርጅቱም እንደ ሰሞንኛው የመንግሥት ተቋማት ፋሽን በሚዲያ በኩል መግለጫውን ከመስጠትና ለሚቀርቡለት የሚዲያ ጥያቄዎች ከሚሰጠው ምላሽ በፈጠነ መንገድ፣ ለእኚሁ አስተያየት ሰጪ ምላሹን አስፍሯል፡፡
ሪፖርተር ስለዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከሚመለከታቸው የተቋሙ የመረጃ ምንጮች በስልክ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ባይሳካም፣ ድርጅቱ በድረ ገጹ ለቀረበት የአስተያየት ሰጪው ጥያቄ ግን እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአሥራ አንድ መርከቦች ባለቤት ሲሆን፣ ዘጠኙ የደረቅ ጭነት፣ ሁለቱ ደግሞ ነዳጅ ጫኝ ናቸው፡፡››
እንደ ድርጅቱ ምላሽ ከሆነ ከ11 መርከቦች ውስጥ ዘጠኙ በክልል ከተሞች ስም መነሻነት ስያሜያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡ ሸበሌ ደረቅ ጭነት፣ ጊቤ ደረቅ ጭነት፣ ባህር ዳር ነዳጅ ጫኝ፣ ሐዋሳ ነዳጅ ጫኝ፣ ፊንፊኔ ደረቅ ጭነት፣ መቐለ ደረቅ ጭነት፣ ሐረር ደረቅ ጭነት፣ ሰመራ ደረቅ ጭነት፣ ጅግጅጋ ደረቅ ጭነት፣ አሶሳ ደረቅ ጭነት፣ እንዲሁም ጋምቤላ ደረቅ ጭነት የተባሉ መርከቦችን በማሰማራት የገቢና ወጪ ንግዱን እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ በባህር ትራንስፖርት መስክ በአፍሪካ ቀዳሚ ታሪክ አላት፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገሮች ፖለቲካዊ ነፃነታቸውን ቢያውጁም ኢኮኖሚያዊ ነፃነታቸውን ማረጋገጥ ግን ፈታኝ ጉዳይ እንደነበር አስታውሶ የአብዛኞቹ ትኩረት ብሔራዊ የመርከብ ኩባንያዎችን በማቋቋም ለኢኮኖሚያቸው ዘላቂና አስተማማኝ የድጋፍ ማገር ማበጀት እንደነበር፣ ነገር ግን እንደሌሎቹ የፖለቲካም የኢኮኖሚም ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ያልወደቀችው ኢትዮጵያ፣ ብሔራዊ የመርከብ ኩባንያ ዕውን ካደረጉ አገሮች መካከል አንዷና ቀዳሚዋ አገር እንደሆነች ድርጅቱ አስፍሯል፡፡
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረ ጉዞ በዘርፉ ባለው ከፍተኛ የውድድር ወጀብ ክፉኛ እየተመቱ አብዛኞቹ ከዘርፉ ሲወጡ አገራችን ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረትና ድጋፍ ብሔራዊ የንግድ መርከባችን ከአፍሪካ ብቸኛው የአገርን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ (National Flag Carrier) አገልግሎቱን እያቀረበ ይገኛል፡፡