Wednesday, June 12, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለማደግ ሰዓት ያለማከበር ጎጂ ልማዳችንን እናስወግድ

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብን ‹‹እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን፣ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም፣ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም›› ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ይኼ ቀጭን ትዕዛዝ የታዘዘው ምናልባትም 600 ኪሎ ሜትር ተጉዞ እንዲመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ መቼ መነሳት እንዳለበት ምኒልክ ግድ የላቸውም፡፡ ተጓዡ የሚደርስበትን ራሱ አቅዶ በተባለው ቀን ወረኢሉ መገኘት አለበት፡፡ በዚያን ቀን ካልተገኘ፣ ምኒልክ ያሰቀመጡትን ቅጣት መቀበል ግዴታው ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየን ጥንት ቀጠሮ በኢትዮጵያውያን ዘንድ መከበር እንዳለበት ነው፡፡ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ግን ቀጠሮ አለማክበር እንደ ባህላችን ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በዚህም ይመስላል ታላቁ ዘፋኛችን ጥላሁን ገሠሠ፣ ቢቸግረው ‹‹ቀጠሮ ይከበር ብሎ ያቀነቀነው››፡፡ እንግዲህ ጥንት የነበረው ቀጠሮ ማክበር ጥሩ ባህላችን እንዴት ጠፋ? መቼ ነው ቀጠሮ ያለማክበር የተጀመረው? የሚለውን  የሚመለከታችሁ ጥናት ካላችሁ አንድ ብትሉን ደስ ይለናል፡፡

በዘመናዊ አነጋገር አንዱ የቀጠሮ አገላለጽ በሰዓት ስለሆነ፣ ቀጠሮን በሰዓት ብተካው ብዙም ስለማልሳሳት ወደዚሁ ልቀይር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ሰዓት አክብሮ የሚገኝ፣ ከኅብረተሰቡ የወጣ አስተሳሰብ እንዳለው ሆኖ እየተቆጠረ ነው፡፡ ይኼ ቀጠሮ ያለማክበር መጥፎ ልማድ ከልጅ እስከ አዋቂው፣ በትምህርት ቤት፣ በዩኒቨርሲቲ፣ በቢሮው፣ በፍርድ ቤት፣ በፓርላማ፣ በቤተ መንግሥት፣ በአውሮፕላን ጣቢያ፣ በሠርግ ቤት፣ በሐዘን ቤት፣ በፍቅረኞች መካከል ወዘተ የተለመደ ሆኗል፡፡ ይኼም ስለሆነ የውጭ ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያውያን ሰዓት የማያከብሩ ናቸው፤›› በማለት መታወቂያ ሰጥተውናል፡፡ በጅምላ ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ ሁኖ አብረን ተደመርን እንጂ ከኢትዮጵያዊያን እኔን ጨምሮ ቀጠሮ አክባሪዎች አለን፡፡ ግን አብዛኛው ሰው ሰዓት ስለማያከብር የሚያከብሩት ጥቂቶች ስለሆኑ የጋራ እሴት አድርጎ መቀበል ግድ ይላል፡፡

በአብዛኛው ጊዜ ለሠርግ ምሣ እንድንበላ በሰባት ሰዓት ታድመን የሄድንበት ሙሽራው የሚመጣው በዘጠኝ ሰዓት ነው፡፡ ይኼንን የተቀበለችው ባለቤቴ ከቤት ምሣችንን በልተን እንሂድ ብላ እየወተወተቺኝ አልበላም ብዬ ሄጄ ረሃብ ሲበዛብኝ አቅራቢያው ባለው ሆቴል ገብቼ በገንዘቤ የበላሁት ወይም ካላመቸ ሠርጉን ጥዬ የሄድኩት ብዙ ነው፡፡ የሚገርመው በሰባት ሰዓት ምሣ ሊያበሉን የጠሩን ጋባዦች ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ‹‹ሠርገኛ ማርፈድ ልማዱ ነው፡፡ ትንሽ ታገሡን›› እያሉ ሲናገሩ ሰዓት ባለመከበሩ አያፍሩም፡፡ ለእነሱ ሰዓት ያለማከበር  የተለመደ ነው፡፡ ሰዓት ያለማከበር በትምህርት ቤትም ተለመደ ነው፡፡ እኔ የማስተምራቸውን ልጆች በመጀመሪያው ቀን በስንት ሰዓት ክፍል እንደምንጀመር እንስማማለን፡፡ ዩኒቨርሲቲው ክፍል የሚጀመረው በሁለት ሰዓት ነው ቢልም በመጓጓዣ ወዘተ ምክንያት ልትደርሱ አትችሉም በማለት በመስማማት ሁለት ሰዓት ተኩል እንደምንጀምርና እኔ ክፍል በሠዓቱ ገብቼ ከጀመርኩ በኋላ መግባት እንደማይቻል ተስማምተን ወደ ሥራችን ከገባን በኋላ በሳምንቱ የተወሰኑ ልጆች አርፍደው መጥተው አስገቡኝ የሚል ንትርክ ውስጥ መግባት የተለመደ ነው፡፡ ልጆቹ ወደው ሣይሆን ከኅብረተሰቡ የወረሱት ‹‹ሰዓት ያለማክበር ልምድ ነው፡፡››  የትምህርት ጥራት አንዱ መለኪያው (አንድ ክፍለ ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 16 ሳምንት ነው) በክፍለ ትምህርት ጊዜው መሰጠት የሚገባውን ትምህርቶች ማጠናቀቅ ሲገባ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎ የራሱ የጊዜ ሰሌዳ ያወጣል፡፡ ሴሚስቴሩ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ ትምህርት ሚኒስቴር ይመጣና 15 ቀን የመምህራን ስብሰባ፣ 15 ቀን የተማሪዎች ስብሰባ፣ ወዘተ በማለት የትምህርት ክፍለ ጊዜውን አስከ 12 ሳምንት ያወርደዋል፡፡ መምህራኑም ከሚያስተምሩት ትምህርት በጊዜው ሁኔታ ይቀንሱታል፡፡ የማይማሩት ትምህርት አለ ማለት ነው፡፡ በዚህም የትምህርት ጥራት መውደቅ ሲያስከትል ቆይቷል፡፡ ከዚሁ ከዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፣ ተማሪው በመጀመርያ ክፍለ ትምህርት ወደ ክፍል የሚመጣው የትምህርት መጀመሪያ ቀን ሳይሆን ከሳምንት በኋላ ነው፡፡ ይኼንን ለማስቀረት የዩኒቨርሲቲው አመራር ‹‹ትምህርት የሚጀመረው በመጀመሪያ ቀን ነው›› ብሎ መምህራኑም ተማሪዎችም እንዲያከብሩ ማስታወቂያ ያዥጎደጎዳል፡፡ የሚመጡት ተማሪዎች ግን ከሁለት በመቶ አይዘሉም፡፡ ለምንድነው ቢባል ‹‹ሰዓት አለማክበር ባህላችን መሆኑ ነው፡፡›› 

ሰዓት ያለማከበር ፓርላማም ጋ አለ፡፡ ነገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሦስት ሰዓት ለፓርላማ መግለጫ ስለሚሰጡ፣ ሕዝቡ በቴሌቪዢንና በሬዲዮ እንዲከታተል ተብሎ ይታወጃል፡፡ ሕዝቡም ሥራውን ፈትቶ በተባለው ሰዓት ይጠባበቃል፡፡ ቴሌቪዥንና ሬዲዮም በሦስት ሰዓት ዘፈን ለቅቆ ይጠፋል፡፡ ከሰዓት ማርፈድ በኋለ የተባለው ዝግጅት ይቀጥላል፡፡ ሆስፒታልም እንደዚሁ ነው፡፡ ሐኪም ቤት ቀጠሮ በዘጠኝ ሰዓት አስይዞ ሐኪሙን የሚያገኘው በ12 ሰዓት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም አሠራራችንን አሻሽለናል ብለው ባለጉዳይን የሚያስተናግዱበት የቀጠሮ ሰዓት ይለጠፋል፡፡ ግን አንዴም አይከበርም፡፡ አንድ የሆነ ጉዳይ ለምሳሌ ብጠቅስ ወጣቱ ለመኪናው የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ውጭ በመሄዱ ሳያድስ ይቀራል፡፡ ተመልሶ መኪና ሲያሽከረከር ትራፊክ ይይዘዋል፡፡ የትራፊክ ቅጣቱን ከከፈለ በኋላ ቆይቶ በወንጀል ‹‹ካለኢንሹራንስ በማሽከርከሩ›› ፍርድ ቤት በስንት ሰዓት እንዲቀርብ መጥሪያ ይደርሰዋል፡፡ ወንጀሉ እሰከ 3,500 ብር ስለሚያስቀጣ ወጣቱ ገንዘቡን ይዞ ከተባለው ሰዓት ቀድሞ ችሎት የሚቻልበት ቦታ ገብቶ ይቀመጣል፡፡ ለስምንት ሰዓት የተቀጠረው በ11 ሰዓት ይጠራል፡፡ ዳኛው ተከሳሽን ካስቀረበ በኋላ፣ ፖሊስ በመጥራት ‹‹ተከሳሽን ወስደህ ፖሊስ ጣቢያ አሳድረህ ነገ ጠዋት አምጣልኝ›› ይላል፡፡ ባለጉዳዩ ሲጮህ ‹‹የዳኛ ትዕዛዝ አልቀበልም ነው የምትለው›› ብሎ ዳኛው ፍርድ ሲገመድል ሌላ የባሰ እንዳይከተል ሲል ወጣቱ ዝም አለ፡፡ ፖሊስም የብረት ካቴና ልክ ከባድ ወንጀል እንደ ሠራ በእጁ ላይ አስገብቶ እንደሚታረድ በሬ ይዞት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ፡፡ በማግስቱም ወጣቱን እጁን በካቴና ይዞ ዳኛው ጋ አቀረበ፡፡ ዳኛውም 3,000 በር እንዲከፍል ፈረደበት፡፡ ዳኛው ሰዓት ባለማክበሩ ለእሥር የተዳረገበት ሁኔታ እያንገበገበው፣ ወጣቱ ‹‹አይ አንቺ አገር!›› ብሎ ለራሱ መልስ ሳያገኝ ዝም አለ፡፡ ሰዓት ባለመከበሩ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ሚኒስቴሮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ወዘተ ብቻ የትም ሂዱ ሁሉም ቦታ የኢትዮጵያ ዜጋ እየተሰቃየ ነው፡፡ ቆሞም ብቻ ሳይበቃ ሲቀበርም በሰዓት ማርፈድ አስከሬኑ ይንገላታል፡፡

ሰዓት ሲደመር ቀን ይሆናል፤ ቀን ወራትን፣ ወራት ዓመትን፣ ዓመት 5፣ 10፣ 20፣ 50፣ ምዕት ዓመት፣ አምአት (ሚሌኒየም) እያለ ይቆጠራል፡፡ አንድን ሥራ ለማከናወን የአምስት ዓመት ቀጠሮ ወይም በሰዓት ተደምሮ ልንይዝ እንችላለን፡፡ ለእያንዳንዱ ተግባር መርሐ ግብር ልንነድፍ እንችላለን፡፡ የዚህን ዓይነት የቀጠሮ ጥቅል አሠራር፣ በዘመናዊ አኗኗር ዕቅድ ልንለው እንችላለን፡፡ ወርኃዊ፣ ዓመታዊ፣ ብሎም የ5፣ የ10፣ የ20፣ የ30፣ የ50 ዓመት እየተባለ ሰዓትን በመደመር የአንድ አገር ዕቅድ ይነደፋል፡፡ በንጉሡ ጊዜም፣ በደርግም፣ በኋላም በኢሕአዴግ መንግሥት የአምስት ዓመት ዕቅድ እየወጣ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል የሚለውን ለመዳሰስ ጊዜዬን አላጠፋም፡፡ ያው ኢትዮጵያን የተጠናወታት መጥፎ ባህል ‹‹ሰዓት/ቀጠሮ/ዕቅድ ያለማከበር›› በመኖሩ ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዳልተሳካ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ዕቅዱ ባለመሳካቱም አገሪቷ በኢኮኖሚ ዕድገት ምንም ፈቀቅ እንዳላለች የምናየው ነው፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት መቀጠል እንደማትችል በመረዳት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት በመተማመን ወደ ለውጥ ገብተናል፡፡ በኢኮኖሚው በኩል የሚጠበቀው ለውጥ ፈጣን ዕድገት በማምጣት ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ ለዜጋው ፍላጎቱ ተሟልቶለት በተረጋጋ አገር እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ ይኼንን ለማድረግ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፈን ኢኮኖሚውን ማሳደግ አለብን፡፡ እኛ ደግሞ ሰዓት/ዕቅድ እንደማናከብር ከላይ አይተናል፡፡ ይኼንን ባህል ይዘን ኢኮኖሚያችንን እንደምናሳድግ ምንም ማስተማመኛ የለንም፡፡ ልንተማመን የምንችለው ይኼንን መጥፎ ባህል አውልቀን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ዕቅድ የማስፈጸም ብቃታችን ስናሳድግ ብቻ ነው፡፡

ለትምህርትና ለእርመት እንዲሆን ባለፉት 15 ዓመታት በኢኮኖሚ ጉዟችን ላይ በዕቅድ አፈፃፀም በኩል የታዩ ምክንያታዊ ድክመቶችን እንደሚከተሉት ማንሳት ይቻላል፡፡

ሀ) ዕቅድን ለመፈጸም ሥነ ሥርዓት አለመኖር

አንድን ዕቅድ ለማዘጋጀትም ሆነ ለመፈፀም በመጀመሪያ ሥነ ሥርዓት (discipline) ያስፈልጋል፡፡ ሥነ ሥርዓቱም የተመሠረተው በተቀመጠው መሠረት ለመፈጸም ቁርጠኝነት መኖሩ ላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ተሰዓት በኋላ ባለው አምስት ሰዓት ውስጥ ገበያ ሄዶ መሸመት፣ ጓደኛውን ከአውቶቡስ ተራ መቀበል፣ አባቱን ሐኪም ቤት ሄዶ መጠየቅ፣ ልጅን ከትምህርት ቤት ማምጣት፣ ምግብ መብላትና ወደ ማታ ትምህርት ቤት መሄድ እንዳለበት ዕቅድ ካወጣ እነዚህን ለመፈጸም ለእያንዳንዱ ሰዓት መድቦ ባስቀመጠው ሰዓት መሠረት በሥነ ሥርዓት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ አባቱ ጋ ባስቀመጠው ሰዓት ጠይቆ ካልወጣ፣ የሌላውን ክንውን ይደናቅፍበታል፡፡ ገበያ ለመሸመት በዋጋ በመከራከር በማማረጥ ወዘተ. ከመደበው በላይ ከወሰደ ሌሎቹን ክንውኖች በተለይም የማታ ትምህርትን መሰረዝ ሊገደድ ይችላል፡፡ በዚህም ትምህርቱን የማቋረጥ ሁኔታው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር ምናልባት ሰውዬው በዕቅድ ለመንቀሳቀስ ሥነ ሥርዓት ይጎድለው ይሆናል፡፡ እንዲያው ኑሮው ቧል ፈሰስ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ይኼ ሰው ዝርከርክ ነው ማለት ነው፡፡ ኑሮውን በዕቅድ ሊመራ አይችልም፡፡ በዚህም ኑሮው ከዓመት ዓመት አይቀየርም ዕድገት የሚባል አይጎበኘውም፡፡

ወደ ኢኮኖሚው ስንመጣም ዕቅድ በሥነ ሥርዓት የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ሰው ከባንክ ገንዘብ ተበድሮ ቤት ገንብቶ በዕቅዱ መሠረት ቤቱን አከራይቶ ከሚያገኘው ገንዘብ የባንክ ዕዳውን ከነወለዱ ለመክፈል በዕቅድ ቢያዝ ዲዛይንና ፈቃድ ለማውጣት፣ ዕቃ ለማቅረብ፣ መሠረት ለማውጣት፣ ምሰሶና አግዳሚ ለመገንባት፣ ብሎኬት ለመደርደር፣ ቆርቆሮ ለመምታት፣ መስኮትና መዝጊያ ለመግጠም፣ ቀለም ለመቀባት፣ ወዘተ ያሉት ሒደቶች ነቅሶ የጊዜ ቀመር በትክክል ሊያወጣላቸው ይገባል፡፡ በአንዱ ላይ መዘግየት ካጋጠመው ቤቱ የሚያልቅበት ጊዜ ይራዘማል፡፡ ይኼ ማለት የባንክ ዕዳውን በተባለው ጊዜ ሊከፍል አይችልም፡፡ ያሰበው ምኞት ሊጨናገፍበት ይችላል፡፡ ይኼ እንዳይሆን በሥነ ሥርዓት የዕቅዱን ሠሌዳ መከተል አለበት፡፡ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ፍኖተ ካርታ፣ ስትራቴጂክ ዕቅድ ወዘተ ሹም ሁሉ ሲመጣ መሥራት እንደ ፋሽን ሆኗል፡፡ እነዚህ ነገሮች ይሠራሉ፡፡ መሥሪያ ቤታችን እነዚህን ለመሥራት ይኼን ያህል ጊዜ ይወስዳል፡፡ ሲጠናቀቁም መሥሪያ ቤታችን እዚህ ቦታ ይደረሳል ይባላል፡፡ እነዚህ ግን ተዘጋጅተው መደርደሪያ ላይ ይቀመጣሉ እንጂ በትክክል ሲተገበሩ አይታዩም፡፡ ዕቅድ ወጥቶላቸው ቢወጣላቸውም ለትግበራው ክትትል አይደረግም፡፡ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ብዙ ዕቅዶች አውጥታ አንዳንዶቹ የውኃ ሽታ ሲሆኑ፣ የተቀሩት በሥነ ሥርዓት ስላልተገበሩ፣ የጊዜ መጓተት ስላጋጠማቸው አገሪቱን ለኪሳራ ዳርገዋታል፡፡

ለ) ዕቅዱን የሚፈጽሙ ሹሞች ብቃት አናሳ መሆን

ዕቅድን ለመፈጸም ሥነ ሥርዓት ያስፈልጋል እንዳልነው በተለይ ሥራው ውስበስብና የተያያዙ የብዙ ክንውኖች ውጤት ተደምረው በዕቅድ ከተያዙ፣ ይኼንን ለማስፈጸም ከፍተኛ በትምህርትም ሆነ በልምድ ብቃት ያለው መሪ ያስፈልጋል፡፡ ለፓርቲ (ለመንግሥት) ታማኝ ብቻ መሆን ዕውቀት ካልተጨመረበት ዕቅዱ ሊከናወን አይችልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ምሳሌዎች ዕቅዱ ሳይፈጸም ያልተሠሩ ወይም የአገርን ሀብት እያባከኑ ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በተለይ ሜጋ ፕሮጀክቶች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ አገራችን ዕድገቷን ለማፋጠን በአምስት ዓመት የሚተገበር የዕድገትና የመሸጋገሪያ ዕቅድ (የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ – ዕትዕ) ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. የመጀመሪያውን አወጣች፡፡ ብዙዎቻችን ዕቅዱን ተመልክተን በጣም ደስ አለን፡፡ በተለይ በእኔ ሙያ ውስጥ ካሉት የፋብሪካ ኢንዱስትሪ አንዱ በሆነው ላይ አምስት የማዳበሪያ ፋብሪካ በዕቅዱ መሠረት እንገነባለን ሲባል፣ ማዳበሪያ ለአገሪቱ እስትንፋስ መሆኑን ስለማውቅና በሙያዬ ከ20 ዓመት በላይ በመንግሥት በተቋቋመው የማዳበሪያ ልማት ቦርድ  ሳገለግል ስለነበርኩ ተጨባጭ አንድ ተጨማሪ ሥራ ለአገሬ ላበረክት ነው በሚል ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡ ይኼ ደስታ ግን ብዙም አልቀጠለም፡፡ ሜቴክ ነው የሚሠራው ሲባል፣  ሜቴክ በብቃት ምክንያት እንደማይሠራው ስለማውቅ (ገንዘብ ያባክናል የሚባለውን ብሰማም፣ በዓይኔ እስካላየሁ አልተቀበልኩም ነበር፡፡) ከጅምሩ ተስፋ ቆረጥሁ፡፡ ቦርዱ ውስጥ እኔ ስለሆንኩ ቴክኒኩን የምመራው ጩኸቴን ለቦርዱ አቅርቤ ቦርዱም ተቀብሎ አብረን ብንጮህ የሚሰማ የበላይ አካል ጠፋ፡፡ የዕድገትና የመሸጋገሪያ ዕቅድ (ዕመዕ)  አንድ ሲጠናቀቅ አምስት ማዳበሪያ ፋብሪካ እገነባለሁ ያለው ሜቴክ ያደረሰው አንድ የያዩ ፋብሪካ ብቻ ግንባታ 30 በመቶ ነው፡፡ የዕድገትና የመሸጋገሪያ ዕቅድ አንድ አልቆ የዕቅዱን አፈጻጸም ለመገምገምና ለሁለተኛው ዕቅድ አዲስ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚገኙበት ስብሰባ ተዘጋጀ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በአጠቃላይ የአገሪቱ የዕመዕ አንድ ዕቅድ አፈጻጸም በአማካይ ከ40 በመቶ አይዘልም ነበር፡፡ ምክንያቱ ሲሰጥ ‹‹ዕቅዱ ተለጥጦ ነበር የተዘጋጀው›› የሚል ሆነ፡፡ እውነታው ግን ፕሮጀክቶችን የሚያስፈጽሙት ሹማምንቶች ብቃት አናሳ መሆን ነበር፡፡ ዕቅድ የመፈጸም ብቃት ባለው ሙያተኛ ከተሠራ፣ ከአቅም በላይ ችግር ካጋጠመ፣ ወይም እነሱ እንዳሉት የተለጠጠ ከሆነ፤ 70/ 80 በመቶ አፈጻጸም ይመዘገባል እንጂ 40 በመቶ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የዕቅድን ሳይንስ አለማወቅ ነው፡፡ የሚገርመው በዚሁ ስብሰባ ላይ የሁለተኛው ዕመዕ ሲቀርብ ፕሮጀክቶቹን ሊመሩት የቀረቡት ዕመዕ አንድ ላይ ፕሮጀክቶችን መርተው ውጤት ያላስመዘገቡት እነዚያው ሹማምንቶች ነበሩ፡፡ ከታዳሚዎች አንዳንዶቹም፣ ‹‹እነዚህ ፕሮጀክቶችን ውድቀት ላይ ያደረሱ ሹሞች እንዴት እንደገና ይቀጥላሉ? እነዚሁ ሰዎች ሁለተኛውን ዕመዕ ማሳካታቸው ምን ማረጋገጫ አለ?›› የሚሉትን ጥያቄዎች አቀረቡ፡፡ ስብሰባውን ያዘጋጁት ‹‹ለኢሕአዴግ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ስለሆኑ ነው›› የሚል ዓይነት አጥጋቢ መልስ ሳይሰጡ ስብሰባውን በተኑት፡፡

ሐ) የወጣውን ዕቅድ አፈጻጸም በጊዜ አለመከታተልና ዕርማት ያለመውሰድ

ከላይ እንዳየነው አንድን ሥራ በፕሮጀከት ወይም በሌላ ለመሥራት ዕቅድ በጊዜ ተተምኖ ይቀመጣል፡፡ በዋናነት በሦስት ዓይነት ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ለዕቅዱ የሚያስፈልግ ንዋይ ቁሳቁስና የሚያስፈጽም የሰው ኃይል ቀድሞ መዘጋጀት ወይም በሒደት የሚዘጋጅ መሆኑን በዕቅዱ የጊዜ ቀመር ውስጥ መታየት አለበት፡፡ በባለሙያ የታቀደ ዕቅድ በአንዳንድ ቀድሞ ባልታየ ምክንያት የአሥር በመቶ የዕቅድ አተገባበር ወደ ላይና ወደ ታች ሊዋዥቅ ይችላል፡፡ ለዚህም መጠባበቂያ በዋጋም ሆነ በጊዜ በዕቅዱ አዘገጃጀት ጊዜ ሊቀመጥ ይቻላል፡፡ ዕቅድን ለማስፈጸም ሥነ ሥርዓት ዋና አስፈላጊ ነው፡፡ የዕቅዱ ቅደም ተከተል መዛነፍ የለበትም፡፡ በግምገማ ጊዜ በዕቅዱ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መተግበሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ካልሆነ ወዲያው የጊዜ ማካካሻ መቀየስ አለበት፡፡ በአገራችን በፕሮጀከት አተገባበር ላይ ይኼ ባለመተግበሩ ብዙ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ለምሳሌ የያዩን ማደበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እንውሰድ፡፡ ፕሮጀክቱን በአሥር ቢሊዮን ብር አካባቢ ሜቴክ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማስረከብ ወሰደ፡፡ ከዓመታት በኋላ በእሱ ቀመር 30 በመቶ ሲደርስ የፋብሪካው ግንባታ ከ20 ቢሊዮን ብር ሊሻገር እንደሚችል አስታወቀ፡፡ ፋብሪካው ቢጠናቀቅ የት እንደሚደርስ ሜቴክ ራሱ አያውቀውም ነበር፡፡ የርብ ግድብ ፕሮጀከትን በሦስት ቢሊዮን ብር ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለታል ተብሎ የተጠናቀቀው ከሦስት እጥፍ በዘለለ ብር ነው፡፡ ለምን እንደዚህ የዋጋ ንረት አስከተለ ሲባል አንዱ የሚቀርበው የዲዘይን ለውጥ በመደረጉ የፕሮጀክቱ ዋጋ በእጥፍ ወይም ከዚያ በላይ አድጓል የሚለውን መስማት የተለመደ ነው፡፡ መልሱ ግን ሌቦች በየፕሮጀክቶቹ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ፕሮጀክቶቹ የዕቅድ ሥነ ሥርዓት በሚያዘው የጊዜ ተመን መሄዱን አለመከታተልና የገጠመም ችግር ካለ በጊዜ ባለመታረሙ ምክንያት ነው፡፡

መ) ዕቅድ ሳይፈጸም በቆየ ቁጥር ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል አለማወቅ

ፕሮጀክቶች እየተራዘሙ በሄደ ቁጥር ከአዋጭነት ወደ አላዋጭነት ይሸጋገራሉ፡፡ የወጣባቸውን ገንዘብ ለመመለስ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለኪሣራ ይዳርጋሉ፡፡ የታለመለትን ግብ ሳይመታ ፕሮጀክቱ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ለታዳጊ አገር ደግሞ ዕድገቱን ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ በእኛ አገር የታየውም ይኼው ነው፡፡ አገራችን በምግብ ራሷን አንድ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን ከአሥር በላይ ተመሳሳይ የማዳበሪያ ፋብሪካ ያስፈልጋታል፡፡ በሌለ ገንዘብ ላይ ለያዩ ከሚያስፈልገው በላይ ሦስት እጥፍ ከከፈልን ሌሎች የሚያስፈልጉንን ማዳበሪያ ፋብሪካ ልንሠራ አንችልም፡፡ ውጤቱም በምግብ ራሳችንን አንችልም፡፡ ሦስት ግድብ ሠርተን በብዛት ገበሬዎችን ለማስፈር የያዝነው ዕቅድ ከተበላሸብን አንድ ርብ ግድብን ብቻ ከሠራን ረሀብ ቀን ይሰጣል ወይ በማለት ስንዴ ልመና ወደ ዓለም እድንጓዝ ያደርገናል፡፡

አገራችን ህልውናዋን ለማስጠበቅ ካለችበት የድህነት አረንቋ በቶሎ መውጣት አንዳለባት በመታመኑ ለአገር ዕደገት ተብሎ የተለያዩ ፕሮጀከቶች የዕድገትና የመሸጋገሪያ ዕቅድ በሦስት ከፍላ ለ15 ዓመታት በማውጣት እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ እነዚህን ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ለማስኬድ የገንዘብ ምንጭ የሆነው በአንድ በኩል የአገር ውስጥ ሀብትን አሟጦ መጠቀም በሌላ በኩል ከውጭ ብድር መውሰድ ነው፡፡ በተለይ ለሁለተኛና ለሦስተኛው ዕመዕ ፕሮጀክቶች ከፊል ማስፈጸሚያ የታቀደው በመጀመሪያው ዕመዕ የተያዙትን ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ፋብሪካዎቹን ወደ ምርት በማስገባትና ምርቶቹን ወደ ውጭ በመሸጥ ከሚያስገኙት የውጪ ምንዛሪ ዶላር ነበር፡፡ ለምሳሌ የስኳር ፋብሪካዎችን በዕመዕ አንድ በማጠናቀቅ ስኳርን ለውጪ አገር መሸጥ የህዳሴ ግድብን በመጨረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ነበር፡፡ የያዩን ማዳበሪያ ፋብሪካንም በማጠናቀቅ ለማዳበሪያ የሚወጣውን ብዙ መቶ ሚሊዮኖች ዶላር በማስቀረት ለዕዳ ክፍያ ይውላል ተብሎ ነበር፡፡ ሁሉም ነፋስ ሆኖ በኖ ጠፋ፡፡ የቀረው የትም የማይሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕዳ ታቅፎ ቀረ፡፡

ዕቅድ በሚገባው ባለመፈጸማችን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው፡፡ ሰዓት ያለ ማክበር መጥፎ ልማዳችንን በአገራችንም ልማት ላይ መጥቶ በዓለም ላይ ማፈሪያ ሊያደርገን እየተግደረደረ ነው፡፡ ዕውቀት ያለውን በመናቅ ‹‹ታማኝነት ብቻ ነው አገሪቷን የሚያሳድጋት›› ተብሎ የተደሰኮረባት አገር ታማኞቹ ወንዝ ሳያሻግሩ ፕሮጀክቶቹን ሁሉ ይዘው ጠፉ፡፡

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት ድክመቶች ተስፋ ሳይቆጥር ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት፣ ‹‹አገርን ማልማት በሜዳ ላይ መሄድ አይደለም፡፡ ላመጣ ላሰብኩት የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈታተኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህንም ለማሸነፍ ዘወትር መጣር አለብኝ የሚለውን ነው፡፡›› በዚህም ስሜት በመነሳት፣ ዓለምን ያስገረመው የህዳሴ ግድባችንን ለአንድ ቀን እንኳ ማቆም የለብንም፡፡ እንደገናም ቢሆን ደመወዛችንንም አዋጥተን በማስጨረስ የአገራችንን ክብር ለወዳጆቻችንም ሆነ ለጠላቶቻችን ማሳየት አለብን፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችንም ሆነ አዳዲሶች የሚያስከፍሉን ዋጋ እንደ ሬት ቢመርም አጠናቀን ከድህነት በቶሎ መውጣት አለብን፡፡ አገር የምታድገው በቅብብሎሽ ነው፡፡ ይኼ ትውልድ የሚሠራው ለቀጣዩ ትውልድ ነው፡፡ አባቶቻችን ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተከላክለው ብዙ ደም አፍስሰው በነፃነቷ የተከበረች ኩሩ ኢትዮጵያን ከነ ባህሏ አስረክበውናል፡፡ እኛም ለነገው ትውልድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዕድገት ለአገራችን በማምጣት የሚቀጥለው ትውልድ የማያፍርባት ኢትዮጵያን ለማስረከብ ሌት ተቀን ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ከምንሠራቸው አንዱ የተጠናወተንን ሰዓት ያለማክበር ከአገራችን ማጥፋት አለብን፡፡ በአገሪቱ ሰዓት (ዕቅድ) ባለመከበሩ ብቻ ቢሊዮን ዶላሮች እየጠፉ ነው፡፡ ይኼም የኢኮኖሚ ዕድገታችንን አዘግይቶብናል ወይም እንዳንደርስ አድርጎናል፡፡ በግለሰብም ደረጃ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በሰዓት ባለመሥራቱ አያውቀውም እንጂ ሊደርስበት ከሚችለው አዘግይቶታል/አስቀርቶታል፡፡ ሰዓት ያለ ማክበር እንደ ባህል በተቆጠረበት ኅብረተሰብ ውስጥ ይኼንን ጎጂ ልማድ ለማስቀረት የብዙ ኅብረተሰብ ክፍሎች ንቅናቄን ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያው መስፈርት የሚሆነው፣ የመንግሥት፣ የሃይማኖት፣ ሕዝባዊ ማኅበራት፣ ልዩ ልዩ ተቋማት ወዘተ. ቁርጠኝነት ነው፡፡ እነዚህ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናኖቻቸው ሰዓት ያለማክበር በፈጣሪም የማይደገፍ መሆኑንና መተው እንዳለበት ማስተማርና ማዘዝ አለባቸው፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ሰዓት ያለማክበር መቅረት እንዳለበት በየደረጃው ለተማሪዎች ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡ ሁሉም ኅብረተስብ ከሰዓት ጋራ በተያያዘ ሰዓት ማክበሩን ማሳየት አለበት፡፡ በየስብሰባው፣ በየመርሐ ግብሩ፣ በየሥራ ቦታው ወዘተ. በሁሉም ሰው ጋ ሰዓት ተከብሮ መታየት አለበት፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ፣ ሥራ በሰዓቱ እንዲጀመር ለአሠሪዎች ጥብቅ ትዕዛዝ በመንግሥት የሚመለከታቸው አካላት መሰጠት አለባቸው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ሰዓት ያለማከበር ያልሠለጠነ ሰው ምልክት ነው ብለው ሰዓት ያለ ማክበር ማጥላላት አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ሰዓት ያለማክበር ጎጂ ልማድ ሆኖ ተቆጥሮ ከአገሪቱ እንዲጠፋ ዘመቻ የሚያስጀምር አንደ ሪፖርተር ጋዜጣ ያሉ ኃላፊነቱን ወስደው ቢያቀጣጥሉት ጥሩ ውጤት ሊመጣ ይቻላል፡፡ መንግሥትም ይኼንን ጎጂ ልማድ ልክ እንደ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች (እንደ ሴት ልጅ ግርዛት የመሳሰሉት) ባሉት የሥራ ክፍሎች አማካይነት ለማጥፋት የራሱን ቤት ሥራ መውሰድ አለበት፡፡

ከአዘጋጁፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ (/ር፣ ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ   የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles