Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባለህበት እርገጥ አይሰለችም ወይ?

ሰላም! ሰላም! ምን ሰላም አለ ነገር እያሻቀበ? አትሉኝም። ባለፈው እህል ቅጠል የማይል ፍርፍር ማንጠግቦሽ ሠርታ ብታቀርብልኝ ማላመጥ እንኳ እስኪያቅተኝ አፌ ውስጥ ሳንገዋልለው ነበር። ማንጠግቦሽ ዓይታኝ፣ ‹‹እንግዲህ ቻለው! ቲማቲሙም የባለሀብት መሬቱም የመንግሥት ሆኗል!›› አለችኝ። የቲማቲሙ ገብቶኛል የመሬቱ ግን ግር ስላለኝ፣ ‹‹የመንግሥት ስትይ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?›› አልኩና ጠየቅኳት። ‹‹እንደ ድሮው ቢሆን ጓሮ ኖሮን ቲማቲሙን ቤታችን ባበቀልነው ነበር። አሁን ሊዝ ከመጣ ወዲህ እንኳ ለቲማቲም ለሰው የሚበቃ ምን ቦታ ተረፈ ብዬ ነዋ?›› አለችኝ። በሌላ አባባል ለጓሮ አትክልት መትከያ መሬት በሊዝ መግዛት ይጠበቅብሀል ነው ነገሩ። ‘የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት’ ማለት ይኼ አይደል ታዲያ? ተደራጅተን ቆጥ ላይ መኖር አቅቶናል ማንጠግቦሽ ሆዬ ጭራሽ ስለጓሮ እርሻ ታስባለች። እኛ እኮ ኮንዶሚኒየም ብርቅ ሆኖብን ኩሽና መኖር የሰለቸን ምንዱባን ነን፡፡ ነገረኛው ደግሞ ይህችም ብርቅ ሆናበት ይዛበትብናል፣ ያቀሳስረናል፡፡

እንግዲህ ይህን ሁሉ የሚያስወራን የቲማቲም ዋጋ ከሞባይል ካርድ እኩል መሆን አይደል? (ካርዱንስ ኔትወርክ የሚባል  ስለሌለ ባትሞሉት ግድ የለም፣ ሆድ ግን እንዴት?) ምን አሉ መሰላችሁ አንዲት በጡረታ ገንዘባቸው የሚተዳደሩ ሴት አዛውንት። ‹‹እስኪ አንድ ኪሎ ቲማቲም መዝንልኝ?›› ይሉታል አሉ ባለአትክልት ቤቱን። ‹‹ዋጋውን ሰምተዋል አይደል?›› ይላቸዋል ኋላ ሁለቴ እንዳይደክም ፈርቶ። አዛውንቷም፣ ‹‹የዘመኑ ሥራ ግሽበት ነው! ያው ጨምሯል ልትለኝ አይደል? በልማ መዝንልኝ፤›› አሉት ቆጣ ብለው። ‹‹እሺ! ለማንኛውም 25 ብር ሆኗል፤›› ሲላቸው ያን ያህል ጭማሪ ስላልጠበቁ በተዘበራረቀ ስሜት አካባቢውን በዕልልታ አቀለጡት። “ምን ተገኘ?” ሲሏቸው፣ ‹‹የሞት መድኃኒት ተገኘ!’ ብዬ ነዋ!›› አይሉ መሰላችሁ? ይህንን እንደ ሰማሁ የሳቅኩትን ያህል እየቆየሁ ከቲማቲም ዋጋ መናር አንፃር የአዛውንቷን ግነታዊ ማነፃፀሪያ ሳብላላው ሳግ አነቀኝ። ኧረ! ኧረ! እስከ መቼ ይሆን እንዲህ በኑሮ እያሾፍን ሳንኖር ሞት የሚቀድመን?!

አዎ! ስለኑሮ ሸክም አወራለሁ ብዬ ሌላ ሸክም ቁለላ ውስጥ ተደነጎርኩ። መቼስ ወግ አይደል። ወግ ደግሞ በዓይን ይገባል። አሁን እንኳ በቴክስት፣ በቫይበር፣ በፌስቡክና በትዊተርም እየገባ ነው። ማን ዓይን ለዓይን ይተያያል? እውነቴን ነው። ስንተያይም የራሳችንን ምሰሶ ሳንነቅል የሰው ጉድፍ ካላወጣን እያልን አገር ይያዝልን ሆኗል ሙያችን። ይኼው ያልነው አልቀረልንም፡፡ እማማ ኢትዮጵያ ይህቺ የሆሜር ድርሰት አድማቂ፣ የሦስት ሺሕ ዓመት ተጀምረው ያልተጨረሱ ሥልጣኔዎች ባለቤት፣ እርስ በርስ በመነቋቆርና በመጠዛጠዝ ግርግር ተይዛልን አረፍነው። እሰየው አይባል አገር፣ እንቢ አይባል ፍቅር ነስቶን በ‘ምን አባህ! የት አባሽ! ምን ታመጣለህ?! ምን ታመጫለሽ?!’ ግልምጫ ማን አለብኝነታችን ፋፋ። ‹‹ምነው ግን በልጅነታችን የበላነው ፋፋ ደግ ደጉ ባህላችን ላይ አላፋፋን አለ?›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ከጥያቄህ በፊት የሚቀድመው ‘ስንት ፐርሰንቷ ኢትዮጵያ ናት ይኼን ምግብ እኩል ተመግባ የፋፋችው?’ የሚል ጥያቄ አለ፤›› ብሎኝ አረፈው። እሱ ደግሞ እንዴትም እንዴትም ብሎ ‘ፐርሰንት’ እና ‘ዕድገት’ የሚባሉ ቃላት ንግግሩ መሀል መደንጎር ይወዳል። ኤድያ!

እኔም ቆርጦ አይቆርጥልኝ ዞሬ ዞሬ ለእሱው ነው የሆዴን የማጫውተው። ሆዴ ከሞላና ጨዋታ ‘ኤክስፖርት’ የማድረግ አቅም ካለው ነው ታዲያ። ለነገሩ ተመስገን ነው! እኛ እኛ ምንም አንልም። ለእነሱ ለእነሱም በልማታዊ ብልፅግና ጎርፍ በሥልትና በጥበብ (ጥበብ የሚለው የፀደቀ ስለመሰለኝ አቋራጭ ማለቱን ትቻለሁ) ተሽለው ለሚታዩትም አገሩ አማን ነው። ግን ደግሞ አሉ ወዲያ። ከአደባባዩ ባሻገር፣ ፍሳሽ እያስመለሰ ከተማችንን ከፊል ጎርፋማ ከሚያደርገው ፉካ ሥር የሚያድሩ። መጠለያና ንፁህ ምግብ ማግኘት፣ መንግሥተ ሰማይ ‘ቪአይፒ’ ቦታ ከማግኘት እኩል የሆነባቸው ደግሞ አሉ። ‘እንዴት ይረሳል?’ እንዳለው የትዝታው ንጉሥ!

ታዲያ በቁሜ የማየው የዚህች ዓለም ትዕይንት በሐዘን እያፈዘዘኝ በቁሜ ላንኮራፋ ‘ሲንግል ዲጂት’ የሮሮ ዕድገት ሲቀረኝ እባንንና እጄ ላይ ያሉትን ሥራዎች ለመጨራረስ እቃብዛለሁ። እዚያ የሚከራይ ቤት አለኝ። ወዲህ አንዳች የሚያህል  ቪላ ቤት ተከራይና ገዥ የሚፈልጉ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችን አልቆጥርላችሁም። ግን መምረጥ ይከብደኛል። ‘የቱን ቅድሚያ ልስጥ? ማን ደውሎልኝ ነበር? ምን ፈልጎ?’ ስል የሚታዘበኝ አንድ የሙያ ባልደረባዬ፣ ‹‹አይ አንበርብር ኢኮኖሚው በተቀዛቀዘበት በዚህ ብርዳም ጊዜ አንተም እንደ ሰፊው ሕዝብ ግራ ተጋባህ?›› ይለኛል። እንደምታውቁት ባልተጻፈው የጠቅ ጠቅ ፎርሙላችን እገዛ መናገር የምንፈልገውን ቀጥታ ተናግረን አናውቅም። መናገሩን ትታችሁትን መንገድም ቀጥ ብለን አንራመድም። ለምሳሌ ከቤት ወጥተን ጎረቤት ቤት ገብተን፣ ከጎረቤት አውርተን ደግሞ ዕቃ ረሳን ብለን ቤታችን ተመልሰን ገብተን፣ ከዚያ ተመልሰን የሠፈራችን ሱቅ ወይም ከአንድ ባለሻይ ቤት ወዳጅ ጋር አቶክቱከን፣ ከዚያ ነው ሊመሽ አካባቢ ሠፈር የምንለቀው እንጂ፣ ከፈረንጅ እኩል 24 ሰዓት ተሰጥቶን ይኼን ያህል የኑሮና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዴት ይመጣል? ደግሞ ይኼን ልናጣራ ነው ብላችሁ ዙሩን አክሩት አሉዋችሁ። ሆሆ!

አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ መግዛት የሚፈልግ ደንበኛዬን አንጋግሬ ሳበቃ ሳይውል ሳያድር ላሳየው ቀጠርኩት። ያው እንደምታውቁት በአገራችን መቅጠር እንጂ መድረስ ከባድ ነው። ማቀድ እንጂ ማሳካት ህልም ነው። መውቀስ እንጂ ሠርቶ ማሳየት እንዴት ጭንቅ እንደሆነ ለኖረ አይነገረውም። ‹‹. . . ዳሩ ትናንትን ዛሬ እያሰከረው ብዙ ነገር የገባን መስሎን ሳይገባን እየዘለለን ነው። ከታሪካችን አስታውሰን ልንማርበት የሚገባንን ሁሉ እንደምንዘለው ለጤናችን አስበን ገመድ እንኳ አንዘልም፤›› ይሉኛል ባሻዬ የሰሞኑን መጣሁ ሄድኩ የሚለው ዝናብ ያመጣው ብርድ ቁርጥማት ጨምድዶ ቤት እያስቀመጣቸው ልጠይቃቸው ስሄድ። መቼም እሳቸውን ታውቋቸዋላችሁ። ሲያመሩም ሲቀልዱም ወግ ይችሉበታል። ደግሞ መቼ ዕለት ነው፣ ‹‹አንተ ተው እንጂ? ምነው ወጣት ካልተሆነ በረደኝ ተብሎ ሚስት አይፈለግም እንዴ? እስኪ ሚስት ፈልግልኝ፤›› አሉኝ።

‹‹አይ ባሻዬ በፍለጋ ቢሆን ንፋስ እስከ ዛሬ ስንት ሚስቶች ይኖሩት ነበር?›› ስላቸው ከት ብለው እየሳቁ፣ ‹‹እኔ እኮ ገለባ ስለማንገዋልል አልጠየቅኩህም? ከአጨዳና ከጉልጓሎ የቱ እንደሚቀድም የተምታታበት ትውልድ በ‘ኢንተርኔት’ የትዳር አጋር ሲጎለጉል ይውላል ሲባል ስለሰማሁ ለምን ይቅርብኝ ብዬ እንጂ። በላ ምን ይጎድለኛል?›› ብለው ሳቃቸውን እስኪጨርሱ አጀብኳቸው። ባሻዬ ለቀልድ ነገሩን አነሱት እንጂ፣ እንኳን ትዳር ወገባችንን ታጥቀን የተያያዝነው የአገር ልማት በጎደለ ተሞልቶም አልሞላ ብሏል። እናላችሁ ከሕዝብ ተቀላቅዬ ወደ ደንበኛዬ ስገሰግስ አንዱ፣ ‹‹በቅርቡ ሳተላይት እናመጥቃለን የሚሉን መጀመርያ መቼ ምድር ለምድር መጠቅን? የታለ ራዕያችን? ወሬ ከመደራረብ ምናለበት ከሥር ከሥሩ ጫና ብናቀልና የዋልንበትን አረም ባይበላው?›› እያለ ሰውን ሲያስጨንቀው ሰማሁ። ተጨንቆ አስጨናቂ ብቻ ይሙላው መንገዱን?!

በሉ እንሰነባበት። ሆድ ስለባሰኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አንድ አንድ ስንል አመሸን። የሰሞኑ የኮንዶሚኒየም ወሬ በአጥንት ይገባል። ከየፌስቡኩ የተለቃቀመ ወሬ ግሮሰሪ ደርሶ ሰውን በነገር ያናጅሰዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ደግሞ በሁሉም ነገር አትግባቡ ያለን ሰይጣን ከየት ይሆን የመጣው?›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ይኼን ሲል አንዱ ከሩቅ ሰምቶት፣ ‹‹ሰይጣን ምን አለን? ከሕግ በላይ የሚወበራውና አላስቆም አላስቀምጥ ያለን ነገረኛና አሻጥረኛ አይብስም?›› አለው። “ነገር መጣልህ!” አልኩና የካፖርቴን ኮሌታ ወደ ላይ ቀስቼ ጠንቀቅ ብዬ ተቀመጥኩ። ተጠንቅቀንም መዳናችንን እርግጠኛ አይደለንም እንዳትሉ ብቻ። ወይ እናንተ!

“እና ምን ይሻላል?” አለው አንዱ ተናግሮ አናጋሪ ከወዲያ በኩል የተቀመጠ። ‹‹ማጥራት ነዋ። ማፅዳት ነው መፍትሔው። ሳይታክቱ መጥረግ፤›› አለው። እኔ ወሬውን አልቻልኩም። የባሻዬን ልጅ ተሰናብቼ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ስደርስ ቤቱ ተተራምሷል። “ምንድነው እሱ?” ስላት ማንጠግቦሽን፣ “ቤት እያፀዳሁ!” አለችኝ። ወገቧ እስኪቆረጥ ጎንበስ ቀና ትላለች። ‹‹በዚህ በሌሊት እንደ ዕብድ? ደግሞስ ከላይ ከላይ አፅድተሽ ሲነጋ በደንብ አታፀጂም?›› ብላት ‹‹‘ሱፐርፊሺያል’ ፅዳትና ሥራ ነው አንድ ወደፊት አስኪዶ ሦስት ወደ ኋላ እየሳበ ያስቸገረን፤›› ብላኝ እርፍ። ብርዱ ላይ የማንጠግቦሽ እንግሊዝኛ አጠቃቀም ሲጨመርበት አዞረኝ። ዘልዬ አልጋዬ ላይ ወጣሁ። ለማለት የፈለገችው ግን ገብቶኛል። ጥልቀትና ጥራት የሌለው፣ የታይታ፣ ከአንገት በላይ ፅዳት በዛ ማለቷ ነው፡፡ ዛሬ ከትናንት እንደማይሻል ሁሉ አንገት እያስደፋን እባቡን፣ ጊንጡን፣ አይጡንና ምስጡን አደላድሎ አስተኝቶብናል። እኮ እስከ መቼ በታይታ ሥራና በአገም ጠቀም አካሄድ እንታሻለን? እስከ መቼ ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ተረኛ ሆኖ ይጨፍርብናል? ለመሆኑ ትናንትን ንቀን ዛሬን የመረጥነው ተረኛ ጨፋሪ ለማስደነስ ነው ወይ? ማን ነው ተረኛ እየተባባልን ባለህበት እርገጥ አይሰለችም ወይ? በጣም ይሰለቻል፡፡ መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት