Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየደኢሕዴን ስብሰባ በሲዳማ ዞን አመራሮች ተቃውሞ ምክንያት ተቋረጠ

የደኢሕዴን ስብሰባ በሲዳማ ዞን አመራሮች ተቃውሞ ምክንያት ተቋረጠ

ቀን:

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ስብሰባ በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን ተወካዮች ምክንያት ተቋረጠ፡፡ ለስብሰባው መቋረጥ ምክንያት የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በስብሰባው ተንኳስሶ ቀርቧል በሚል ሲሆን፣ ስብሰባው በተጀመረ በሁለተኛ ቀኑ ተወካዮቹ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሊያካሂደው ያቀደውን ስብሰባ በሐዋሳ ለአንድ ቀን ካደረገ በኋላ፣ በሁለተኛ ቀኑ ዓርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በሲዳማ ዞን አመራሮች ጥያቄ ምክንያት ሊቋረጥ ችሏል፡፡

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ከወራት በፊት ቀርቦ፣ ምክር ቤቱም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሪፈረንደም እንዲካሄድ በጽሑፍ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ በምላሹ መዘግየት ምክንያት በሐዋሳ ከተማ ሪፈረንደሙ በፍጥነት እንዲካሄድ በቅርቡ ሠልፍ ተካሂዶ ነበር፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፣ ምርጫ ቦርድ አሁን ሌላ ሥራ ላይ በማተኮሩ ሪፈረንደሙን በቅርቡ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረው ነበር፡፡

ይሁንና የሪፈረንደሙን አለመደረግ ምክንያት በማድረግ ደኢሕዴን በሚያደርገው ስብሰባ ላይ እኛም እንሳተፋለን በማለት የሲዳማ ‹‹ኤጄቶ›› የሚባሉ ወጣቶች የስብሰባው አዳራሽ ገብተው እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሀል ስብሰባው እንዲቀጥል ቢደረግም የሲዳማ ዞን የደኢሕዴን አመራሮች ጥያቄቸው ከሌሎች አዳዲስ ጥያቄዎች ጋር እኩል መታየት የለበትም ሲሉ እንደ ተቃወሙም ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ውስጥ የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን ለማጥናት የተቋቋመው ቡድን ‹የእኛን ጉዳይ መመልከት የለበትም› በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ሌሎች አባላት በቀደመና ባልቀደመ ሳይሆን፣ ምክንያታዊ ጥያቄ በማቅረብና ባለማቅረብ መመዘን አለበት በማለት፣ የሁሉም ጥያቄ በአጥኚ ቡድኑ ግኝት ምላሽ ያግኝ ሲሉ መከራከራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከስብሰባው ውጪ በሐዋሳ ከተማ በተለያዩ ሥፍራዎች ‹‹ኤጄቶ›› በመባል የሚታወቁት የዞኑ ወጣቶች በተለያዩ አደባባዮችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ሲያወርዱ ታይተዋል፡፡

የድርጅቱ ስብሰባ በዘጠኝ ቡድኖች ተከፍሎ ሲካሄድ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ ስብሰባው የተቋረጠበት ሰዓት እንደ ቡድኑ መለያየቱንና የተወሰኑት ቡድኖች ግን የቀኑን ስብሰባቸውን ሊያጠናቅቁ ሲሉ መቋረጡን አክለዋል፡፡

የተለያዩ የክልልነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ሕጋዊ አግባብ ያለው መሆኑን ሁሉም የድርጅቱ አባላት እንደሚስማሙ የተናገሩት ምንጮች፣ የክልልነት ጥያቄ የቀበሌነት ጥያቄን ያህል እንኳን የመተግበር ክብደት ስለሌለው በአጥኚ ቡድኑ የሚቀርበውን ምክረ ሐሳብ መጠበቅ እንደሚገባ መተማመንም አለ ብለዋል፡፡

የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ዞኖች በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት እየተመደበላቸው እነሱ ግን አመንጭተው ሩብ ያህሉን እንኳ እንደማይሸፍኑ፣ በዞን አደረጃጀት መቀየር ምክንያት ካሁን ቀደም ወደማያባራ ብጥብጥ የገቡ አካባቢዎችን እያዩ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባ በርካቶች ያሳስባሉ፡፡

ስብሰባው ሲቋረጥ ከዘጠኙ ቡድኖች በአንዱ የወላይታ ዞን የድርጅት አመራሮች ቡድን ከውጭ ከገቡ ግለሰቦች ጋር በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ስብሰባው ሲጀመር መደበኛ የፀጥታ አስከባሪዎች በሥፍራው እንደነበሩ የገለጹት ምንጮች፣ ዓርብ ከቀትር በኋላ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በሥፍራው መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...