Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየለገጣፎ ተፈናቃዮች መውደቂያ አጥተናል እያሉ ነው

የለገጣፎ ተፈናቃዮች መውደቂያ አጥተናል እያሉ ነው

ቀን:

የለገጣፎ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የመጠለያ ችግር እንዳጋጠማቸው ገለጹ፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከማስተር ፕላን ውጪ ተገንብተዋል ተብለው በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ከፈረሱ በኋላ፣ ተፈናቃዮች መውደቂያ አጥተናል እያሉ ነው፡፡ መኖርያ ቤታቸው የፈረሰባቸው አባወራዎች በየዘመድና በቤተ እምነቶች ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸውን፣ ሜዳ ላይ ድንኳን ጥለው እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

150 ሰዎች ያድሩበታል የተባለው የዕድር ድንኳን ደግሞ ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ በላያቸው መፍረሱን ለደኅንነታቸው ሲባል ማንነታቸው ያልተገለጸ የተፈናቃዮቹ ተወካይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተኛንበት ነው መጥተው ያፈረሱብን፡፡ አሁን ቤተሰቦቻችንና ንብረታችን ዝናብ ላይ ተበትነዋል፤›› የሚሉት ተወካይ፣ ድንኳኑን ያፈረሱት የዕድሩ አባል የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ጥያቄያችን ሕገወጥ ተብለው የፈረሱት ቤቶች ሕጋዊና የአየር ካርታ ያላቸው በመሆናቸው ወደ ቦታችን መልሱን የሚል ነው፤›› ያሉት ተወካዩ፣ የተፈናቃዮቹን ድምፅ ለማሰማት የተለያዩ ተቋማትን በር እያንኳኩ ባሉበት ወቅት እንዲህ ያለ ችግር መፈጠሩ ነገሮችን ውስብስብ አድርጓል ብለዋል፡፡ ጊዜያዊ የመጠለያ ድንኳን ለማግኘትም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከኦሮሚያ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ደብዳቤ አጽፋችሁ አምጡ እንደተባሉም አስረድተዋል፡፡

‹‹በትክክል ተፈናቃይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ካሉበት አካባቢ እንዲያመጡ የምንጠይቀው በተፈናቃይ መልክ የሚገቡ ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ነው፤›› ያሉት፣ በአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ የምሥራቅ ዞን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘውዲቱ ካሳሁን ናቸው፡፡ አያይዘውም በአካባቢው በሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ተፈናቃዮችን እንጂ፣ ሌላ አካባቢ የሚኖሩ ተፈናቃዮችን እንዳላነጋገሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታ ጥሪ ለጽሕፈት ቤቱ የደረሰው ሐሙስ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊዋ፣ በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተግኝተው ተፈናቃዮቹ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ከተመለከቱ በኋላ አስፈላጊውን ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኑን ጉብኝት ወቅት 913 ሕፃናትን የያዙ 540 ተፈናቃይ አባ ወራዎች ተጠልለው ማየታቸውን፣ በቤተ ክርስቲያኑ እንዲጠለሉበት የተሰጣቸው አንድ ድንኳን ሁሉንም ማስጠለል ባለመቻሉ፣ ብዙዎቹ ሜዳ ላይ ይተኙ እንደነበር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈናቃዮቹ በእርሱ ሥር ስለመገኘታቸው የሚያረጋግጥ ባለ ማኅተም ደብዳቤ ለጽሕፈት ቤቱ ከሰጠ በኋላም፣ አስፈላጊው ድጋፍ እንደተደረገ ወ/ሮ ዘውዲቱ አክለዋል፡፡ ‹‹ብርድ ልብስ፣ ምንጣፍ፣ ድንኳን፣ ሰሃን፣ ኩባያና ሳሙና ነው ያደልናቸው፡፡ ተፈናቃዮቹ ግን ምግብና ደህና መጠለያ ነው የሚስፈልጋቸው፤›› ሲሉም ጽሕፈት ቤቱ በእጁ ላይ የነበረውን አንስቶ ቢሰጥም አንገብጋቢው ጉዳይ ሌላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ በየቦታው የተበታተኑና በድንኳን የተጠለሉ ተፈናቃዮች መኖራቸውን፣ የሚያስፈልጋቸው ነገር ከተጠናም በኋላ በቀጣይ ድጋፍ እንደሚያረግላቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኃላፊዋ እስካሁን በማኅበረሰቡና በጽሕፈት ቤቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ካለው ችግር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የቤት ቁጥር፣ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የአየር ካርታ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ነዋሪነታቸውን የሚመሰክሩ ሌሎች እንደ ኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎት እንደገባላቸው፣ ሕገወጥ ተብለው እንዲፈናቀሉ የተደረገው በግፍ ነው የሚሉት የተፈናቃዮቹ ተወካይ፣ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የሚያደርጉት ትግል አይቋረጥም ብለዋል፡፡

ጠበቃ ቀጥረው ለመከራከር እያሰቡ መሆኑን ጠቁመው፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያለውን ችግር ማስረዳታቸውንና ኮሚሽኑም ‹‹ድምፃችሁን እናሰማለን፤›› የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ያነሱትን ጥያቄ በተመለከተ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደርን ለማግኘት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...