Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአቪዬሽን ገበያ ለመክፈት የቀረበው ረቂቅ ሕግ ተቃውሞ ገጠመው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶችንና አየር መንገድን ውህደት መንግሥት በድጋሚ እንደሚያጤነው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአገር ውስጥ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ያረቀቀው የአቪዬሽን ሕግ፣ ከባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

ባለሥልጣኑ መንግሥት እየተገበረ ካለው የኢኮኖሚ ለውጥ ጋር የሚሄድና የአገሪቱን የአቪዬሽን ዘርፍ ለማሳደግ ይረዳሉ ያላቸውን፣ የኤርፖርቶች ግንባታና አስተዳደር አዋጅና የአየር ትራንስፖርት ማስፋፊያ ደንብ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል፡፡ ሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው የውይይት መድረክ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በኤርፖርት ልማት ዘርፍ መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ዓሊ መሐመድ በሰጡት ማብራሪያ ባለሀብቶች አነስተኛ ኤርፖርቶች፣ የአነስተኛ አውሮፕላኖች የማረፊያ ሜዳ፣ የሔሊኮፕተር ማረፊያዎች መገንባትና ማስተዳደር ይችላሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና መሥራት እንደሚችሉ አቶ ዓሊ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ የአቪዬሽን ኩባንያ ላይ እስከ 49 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ረቂቅ አዋጁ ይፈቅዳል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) ረቂቅ አዋጁ የግሉ ዘርፍ በኤርፖርት ግንባታና ማስተዳዳር ዘርፍ መሰማራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወይም ከመንግሥት ጋር በመተባበር ኤርፖርት ሊያለሙ እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በኤርፖርት ግንባታ ማካሄድ የሚችለው የፌዴራል መንግሥት ብቻ እንደነበር ገልጸው፣ ረቂቅ ሕጉ ግን ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የራሳቸውን አነስተኛ ኤርፖርት እንዲገነቡ እንደሚፈቅድ አስረድተዋል፡፡

የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተከለለ የሥራ ዘርፍ እንደነበር ጠቅሰው፣ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቶች ወደፊት ኤርፖርት እንዲያስተዳድሩ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ የአቪዬሽን ሥራ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በግል ባለሀብቶችም ቢካሄድ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሟሉ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት በቀረበው ረቂቅ ሕግ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ባለሀብቱም ሆነ የክልል መንግሥታት የኤርፖርት ግንባታ ልምድ ስለሌላቸው፣ በአንድ ጊዜ ከፍቶ መስጠቱ ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ምን ዓይነት ኤርፖርት ነው እንዲገነቡ የሚፈቀድላቸው? አነስተኛ አውሮፕላኖች ማረፊያ የሚለው አንድ ነገር ነው፡፡ ኤርፖርት የሚለው ግን በየቦታው ሲገነቡ የበረራ ደኅንነትና የፀጥታ ሥጋት ይፈጥራል፡፡ በበረራ ደኅንነት፣ በፀጥታና በጥራት ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች ስላሉ፣ በግል ባለሀብቶችና በክልሎች የሚገነቡ ኤርፖርቶች ደረጃ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ተብሎ ስያሜ ቢወጣላቸው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ በሕገ መንግሥቱ ላይ የኤርፖርት ግንባታ ማካሄድ የሚችለው የፌዴራል መንግሥት እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ፣ የተረቀቀው ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ሊጋጭ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ ባለሥልጣኑ የሕግ ባለሙያዎች እንዳማከረ ገልጸው፣ የፌዴራል መንግሥት ካለው ሥልጣን ላይ ለክልሎች በውክልና ማስተላለፍ እንደሚችልና ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣረስ ተናግረዋል፡፡ በግል ባለሀብቶች፣ በክልል መንግሥታትና በከተማ አስተዳደሮች ሊገነቡ ስለሚችሉ ኤርፖርቶች ደረጃ በመንግሥት እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኤርፖርት ልማት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ነገ ባለሀብቶች ትልቅ ኤርፖርት ይሠራሉ የሚል እምነት የለንም፡፡ የምናስበው ከ10 እስከ 15 ዓመት በኋላ ሊከናወኑ ስለሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ነው፤›› ብለዋል፡፡

የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበራ ለሚ (ካፒቴን) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርፖርቶችን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የኤርፖርቶቹ ባለቤትነት በአየር መንገዱ እንደሆነ ይቀጥላል ወይስ የሚለወጥ ነገር እንደሚኖር ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አሁን በኤርፖርት አገልግሎት ዙሪያ ስላሉብን ችግሮች ለምን አንወያይም?›› ብለዋል፡፡

የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሚር አብደልሃብ በኤርፖርት አገልግሎት ዙሪያ በርካታ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፣ ስለኤርፖርት ፕራይቬታይዜሽን መነጋገር ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የተሳሳቱ ውሳኔዎች ሳይስተካከሉ በአዲስ አዋጅ ላይ መነጋገር በተበላሸ መሠረት ላይ ሕንፃ እንደ መሥራት ይቆጠራል፤›› ያሉት አቶ አሚር፣ የግል አየር መንገዶች ተገቢውን የኤርፖርት አገልግሎት እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የግል አየር መንገዶች የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋር ለመገንባት ቦታ ሲጠይቁ፣ ብሔራዊ አየር መንገዱ ለወደፊት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስለምፈልገው አልሰጥም ይላል፡፡ የመንግሥት ኤርፖርት ውስጥ እንዲህ ዓይነት አድሎአዊ አሠራር እያለ የግል ባለሀብቶች ኤርፖርት ሲገነቡ ምን እንጠብቅ?›› ብለዋል፡፡

የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሰለሞን ግዛው (ካፒቴን) ባሉት ኤርፖርቶች ላይ አንዳንድ መሠረተ ልማቶች ለምን እንደማይገነቡ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ለአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ላለፉት ረዥም ዓመታት የጥገና ሃንጋር ለመገንባት ቦታ እንዲሰጠን ጥያቄ ስናቀርብ ብንቆይም እስካሁን አልተሳካልንም፡፡ በዚህም ምክንያት ሜካኒኮች ቢኖሩንም አውሮፕላኖቻችንን የምናስጠግነው ኬንያ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመክፈል ነው፡፡ ያለፈውን ሳምንት ደረሰኝ እንኳን ባሳያችሁ 76,000 ዶላር ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ መንግሥት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶችን ከኢትዮጵያ አቪዬሽን ቡድን ጋር የቀላቀለው የአየር መንገዱን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል፣ አየር መንገዱ በረዥም ዓመት ያካበተው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለኤርፖርቶች በማካፈል ኤርፖርቱን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል እንደሆነ ገልጸው፣ በኤርፖርቶች አገልግሎት ዙሪያ ቅሬታዎች ካሉ በሌላ መድረክ በግልጽ መወያየት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ትራንስፖርት ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ይገዙ፣ የኤርፖርቶችና የአየር መንገድን ውህደት አስመልክቶ መንግሥት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኤርፖርት ባለቤትነት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም የሚለው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥናት አካሂዶበት ለውሳኔ ለመንግሥት የሚያቀርብ በመሆኑ፣ ይህ አሁን ሊያከራክረን አይገባም፡፡ በሚኒስቴሩ በኩል የተያዘ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች አንዱ የሆነው የአኳሪየስ አቪዬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ተሰማ በበኩላቸው፣ የአነስተኛ አውሮፕላኖች ማረፊያዎች በክልሎች ቢገነቡ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸው አኳሪየስ አቪዬሽን የአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ጥረት ቢያደርግም ትብብር ባለማግኘቱ ሊሳካለት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ላንጋኖ ላይ ነባር ሜዳ ጠግኖ ለመጠቀም ወይም አዲስ ሜዳ ለመገንባት ያቀረብነው ጥያቄ የሚመለከተው እንኳ ባለማግኘቱ ልንገነባ አልቻልንም፤›› ብለዋል፡፡ በነቀምት፣ በአዳማ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በደብረ ማርቆስና በኤርታሌ አካባቢ የአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ሜዳዎች ቢገነቡ ባለሀብቶችንና ቱሪስቶችን ለመሳብና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹በግለሰቦች ከሚገነባ ይልቅ ክልሎች ሐሳቡን ተቀብለው የአነስተኛ አውሮፕላኖች ማረፊያ ሜዳ ቢገነቡ ደስተኞች ነን፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተሰነዘረውን የሰላ ትችት የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሰው አስተባብለዋል፡፡ አቶ መስፍን መንግሥት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ቡድን ሥር እንዲተዳደሩ የወሰነው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኤርፖርት አገልግሎት በመስጠት አየር መንገዱ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያደርገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጂ፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና አየር መንገድ የተቀላቀሉት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት እንደነበር አስታውሰው፣ የጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍ ደግሞ ለአሠርት ዓመታት ሲንቀሳቀስ እንደነበር በመጥቀስ በኤርፖርት ዘርፍ ላሉ ችግሮች የአየር መንገዱን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰው የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ የሚለው ረቂቅ ደንብ ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነትና ማስፋፊያ ደንብ የውጭ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ አየር መንገዶች ላይ እስከ 49 በመቶ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይፈቅዳል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አየር መንገድ፣ የአቪዬሽን ትምህርት ቤት፣ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከልና የአቪዬሽን አማካሪ ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉ ይጠቅሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ረቂቅ ደንቡን በፅኑ ተቃውመውታል፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፕራይቬታይዝ ሳያደርግ የቆየው አየር መንገዱ ብሔራዊ ተልዕኮዎች ይዞ የሚንቀሳቀስ ስትራቴጂካዊ ተቋም በመሆኑ እንደሆነ የገለጹት አቶ መስፍን፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ አየር መንገዱ በመንግሥታቸው ከፍተኛ ድጋፍ ከሚደረግላቸው እንደ የኤምሬትስ፣ የኳታር፣ የኢቲሃድና የቱርክ አየር መንገዶች ጋር ከፍተኛ ፉክክር እየገጠመው እንደሆነ የተናገሩት አቶ መስፍን፣ ከእነዚህ አየር መንገዶች ጋር መንገደኛ ለማንሳት ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የውጭ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ አየር መንገዶች ላይ 49 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው መፍቀድ፣ ብሔራዊ አየር መንገዱን ለአደጋ ማጋለጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ ከተፈቀደ እንደ ኤምሬትስ ያሉ ግዙፍ አየር መንገዶች 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይዘው፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንዲፎካከሩ መፍቀድ አየር መንገዱን መግደል ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ አየር መንገዱ እስከ መቼ በከለላ ሥር ይኖራል?›› ብለው የጠየቁት አቶ አሚር፣ መንግሥት ኢኮኖሚውን እየከፈተ በመሆኑ ስለከለላ ከማውራት የሚመጣውን ጠንካራ ፉክክር እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ማሰብ እንደሚበጅ ተናግረዋል፡፡

ሰለሞን (ካፒቴን) የአገር ውስጥ የአቪዬሽን ገበያ ለውጭ ባለሀብቶች መክፈት ወቅቱ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የቁጥጥር አቅሙን መገንባት አለበት፡፡ የሁላችንም ኩራት የሆነውን ብሔራዊ አየር መንገድ ያለ ቅድመ ሁኔታ ገበያውን ከፍቶ ማጋለጡ ጊዜው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አበራ (ካፒቴን) የግል አየር መንገዶች ላለፉት ዓመታት ሲያነሱት የነበረው ተቀዳሚ ጥያቄ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲፈቀድ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ህልውና ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ስንጠይቅ የኖርነው የተጣሉብን ክልከላዎች እንዲነሱልን ነው፡፡ የአውሮፕላን መቀመጫ ገደብና መጠቀም የምንችለው አውሮፕላን ዓይነት ገደብ እንዲነሳልን፣ መደበኛ የመንገደኛና የካርጎ በረራዎች እንዲፈቀዱልን እንጂ ብሔራዊ አየር መንገዳችን እንዲጎዳ አንፈልግም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መስፍን ከአገር በቀል የግል አየር መንገዶች ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚቻል ገልጸው፣ አንዳንድ አስተያየቶች የሚሰነዘሩት ስለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በጥልቀት ካለመረዳት እንጂ ሁሉም አገሮች የበለፀጉት ሳይቀሩ ለብሔራዊ አየር መንገዳቸው ከለላ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንዳንታለል›› ያሉት አቶ መስፍን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረቂቅ ሕጉና ደንቡ ላይ ያሉትን አስተያየቶች በጽሑፍ አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ገነነው አሰፋ፣ ይህን አዋጅና ደንብ ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መነሻው ሕጋዊ መሠረቱ ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መነሻችሁ ምንድነው? እዚህ የምንነጋገረው ስለባለቤትነት መዋቅርና ትልልቅ የፖሊሲ ጉዳዮች ነውና እንዴት እንደዚህ በቀላሉ ታየ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ወሰንየለህ (ኮሎኔል) በሰጡት ምላሽ የባለሥልጣኑ መነሻ የሲቪል አቪዬሽን አዋጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኦፕሬተር ነው፡፡ የአቪዬሽን ሕግ የማርቀቅ ሥልጣን የተሰጠው ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ነው፤›› ብለው፣ የባለሥልጣኑ  ኃላፊነት ረቂቅ ማቅረብ እንደሆነ፣ መንግሥት የሚቀበለውን አሳልፎ የማይቀበለውን ውድቅ እንደሚያደርግ፣ የቀረበ ሁሉ ይፀድቃል ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ ሕግና ደንቡ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚቀርብ፣ በመቀጠል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ደንቡ እንደሚፀድቅ፣ ረቂቅ ሕጉ ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች እንደሚላክ ወሰንየለህ (ኮሎኔል) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች