የጠራ ተቋማዊ አደረጃጀት ሳይኖረው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የምሥረታ ዕድሜ ካላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ እንደ አለመታደል ሆኖ ከእነ ችግሮቹ ዛሬም በእኔነት ስሜት የሚብሰለሰሉለት ተመልካቾች አላጣም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የክልል ከተሞች በክብረ በዓል መልክ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ዓመታዊ ዝግጅት ተከትሎ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድየሞች መገንባታቸው ለእግር ኳሱ ተደራሽነት የጎላ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩ አሉ፡፡ ይሁንና የስፖርቱን ፋይዳ ያገናዘበ፣ ወቅትና ጊዜውን የጠበቀ የአሠራር ሥርዓት ስላልተበጀለት ከእግር ኳሳዊ ባህሪ ይልቅ የማንነት መገለጫ ሆኖ የግጭት ዓውድማ እየሆነ ይገኛል፡፡
እግር ኳሱን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየደረጃው ባዋቀረው የሊግ አደረጃት መሠረት ውድድሮችን እያከናወነ ቢገኝም፣ አገሪቱን በአኅጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ሊወክል የሚችል ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት ግን አልቻለም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀርበው፣ ተቋሙ እንደ ብሔራዊ ተቋም የሚያወጣቸው መመሪያና ደንቦች በየደረጃው ደርሰው የተፈጻሚነት አቅማቸው ውስንና እንዲያውም የ”ማንነህ አንተ” ዓይነት ትርጉም ስለሚሰጠው እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡
ከታላላቆቹ አገሮች ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው፣ እግር ኳስ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሚያበረክተው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ “ተደራሽ ሆኗል” በሚል ብቻ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም፡፡ ከተደራሽነቱ ጎን ለጎን በየደረጃው እስከ ክልልና ወረዳ ድረስ ያለው እግር ኳሳዊ አደረጃጀት ምን እንደሚመስል ገምግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኑን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ደረጃ ሲታይ ገና ብዙ እንደሚቀረው የሚያመላክቱ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ለአንድ አገር እግር ኳስ ዓይነተኛ ሚና ከሚጫወቱ ተቋማዊ አደረጃጀቶች መካከል፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዲፓርትመንት ዋናው ነው፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ለእግር ኳስ ልማት በሚል ከፍተኛውን በጀት የሚያውለው ለዚህ ዲፓርትመንት መሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ፊፋ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ለሴቶችና ለታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ልማት በሚል በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው ወቅት ከሚያቀርበው የፋይናንስ ሪፖርቱ መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዲፓርትመንት ከመርሁ አኳያ ምን እያከናወነ ነው? የሚለውን እንድንፈትሽ ግድ ይለናል፡፡ የዲፓርትመንቱ ዳይሬክተር አቶ መኰንን ኩሩ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ልማት ሁሉን አቀፍ የሆነ የአሠራር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ለትግበራ በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በአጠቃላይ 21 ነጥቦችን የያዘ ማዕቀፍ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡ ከነጥቦቹ መካከል የማዕቀፉ ፋይዳ፣ ይህን ለመተግበር መከተል ስለሚገባው ስትራቴጂና ተግዳሮቶቹ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከተመረጡት ነጥቦች ምን ያህሉ እውነታ አላቸው፣ ስለተግባራዊነታቸውስ? የሚለውን ለመለየት የሚያስችሉ አሠራሮች የተቀመጠለት መሆኑን ጭምር የሚናገሩ ዳይሬክተሩ፣ ፊፋ በእግር ኳስ ልማት ላይ ከሚከተለው ስትራቴጂክ ዕቅድ አንፃር ተገምግሞ የቀረበ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡
በማዕቀፉ መሠረት የእግር ኳስ ፕሮግራም ማስተግበር፣ የማሠልጠን ፈቃድ በተለይ በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ከማኑዋል ዝግጅት ጀምሮ በራስ አቅም ሙያተኞችን ማፍራት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በአገር ውስጥ “የራሴ ፍልስፍና አለኝ” የሚሉትን ጨምሮ ብሔራዊ የሆነ ሥልጠናን ማስተግበሪያ መመሪያ ማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም በተለይ የአሠልጣኞችን ቅጥርና ስንብት ላይ ያለውን የአሠራር ክፍተት የሚያስተካክል መሥፈርት እንዲኖር፣ ከተጨዋቾች ምልመላና የጤና ሁኔታን በሚመለከት በግምት ካልሆነ በኢትዮጵያ ተጨዋቾች ከክለብ ወደ ክለብ በሚዘዋወሩበት ወቅት የተሟላ የጤና ምርመራ ስለማይደረግላቸው የሚስተካከልበትን ሥርዓት መፈለግ እንደሚገባም ያምናሉ፡፡
በቅድሚያ ግን በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ የግንዛቤ ሥራ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ መኰንን፣ የማስፈጸሚያ ሰነድ ማዘጋጀትና ለዚህም ሲባል 130 ሰዎች በዲፓርትመንቱ አማካይነት እንዲዘጋጁ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ቡድኑም የሥልጠና ማኑዋሎችን፣ የስትራቴጂ ሰነዶችን ማዘጋጀት የሚጠበቅበት ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡ በመጨረሻም ግብረ ኃይሉ መድረኮችን በማመቻቸት ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝ ግብዓት ከወሰደ በኋላ ከዝርዝር መመሪያና ደንብ ጋር ለሚመለከታቸው እንዲሰጥ፣ ከዚያም አተገባበሩን በሚመለከት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የተቋም ድርሻ እንደሚሆን ነው ያስረዱት፡፡
እንደ ኃላፊው ከሆነ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወድቋል ብቻውን መፍትሔ ስለማይሆን ዝርዝር የአሠራር ሥርዓቱ ወደ መሬት እንዲወርድና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ባለድርሻ ነው፡፡ ሌላው በዲፓርትመንቱ እየተዘጋጀ የሚገኘው የብሔራዊ ቡድኖች ፎረም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሁኑ ወቅት ለአንድ አሠልጣኝ ሙሉ ኃላፊነት ከሰጠ በኋላ የሌሎች ድጋፍ ሲደረግለት አይስተዋልም፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር እንደማያስኬድ ያምናሉ፡፡
ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ዳይሬክተሩ፣ የብሔራዊ ቡድኑ እያንዳንዱ ተጨዋች የሚመጣው ከክለብ በመሆኑ፣ ስለተጨዋቾቹ ጥራትም ሆነ ብቃት የተሻለ እውቀት የሚኖራቸው የክለብ አሠልጣኞች እንደመሆናቸው ለብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ የሚሰጡት ግብዓት አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ሲሉ የፎረሙን አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር ይህን ቢሉም በሌላ በኩል ባለው ሁኔታ ሁሉን አቀፍ የሆነው የቴክኒክ ዲፓርትመንቱ ዕቅድ ከወረቀት እንደማያልፍ፣ ለዚህ ደግሞ ከዚህ በፊት በርካታ ተመሳሳይ ጥናቶች የምርምር ውጤቶች ተዘጋጅተው የፌዴሬሽኑ ሸልፍ ማሞቂያ ሆነው እንደሚገኙ የሚናገሩ አሉ፡፡ አቶ መኰንን ግን በዚህ አይስማሙም፣ ምክንያት የሚሉት ደግሞ ቀደም ባሉት ዓመታት ብዙ ነገሮች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር አለመቀየራቸው እንደ ክፍተት ተወስዶ ለዚህኛው መማሪያ ሆኖ እሳቸው ከሚመሩት ዲፓርትመንት ጀምሮ ለተግባራዊነቱ መትጋት የሁሉም እንደሚሆነው ነው የሚናገሩት፡፡
የዲፓርትመንቱ ሌላው ትልቁ ድርሻና ኃላፊነት የሚሉት ባለሙያው፣ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጀምሮ ክልሎችና ክለቦች አሁን ከያዙት አሠራር ጎን ለጎን ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት በማድረግ የእግር ኳስ ልማት ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እስከ ዛሬ በነበረው ታዳጊዎቹን ሰብስቦ ሁለትና ሦስት ኳስ በመወርወር በታዳጊ ወጣት ላይ እየሠራን ነው ከሚለው የውሸት አካሄድና ትክክለኛውን አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግ ጭምር ፅኑ እምነት አላቸው፡፡ እዚህ ላይ በእሳቸው የሚመራው ቴክኒክ ዲፓርትመንት ከባድ ኃላፊነት ይጠበቅበታል፡፡
ቴክኒክ ዲፓርትመንቱ በእግር ኳሱ ላይ የግል አልሚዎች መምጣት እንዳለባቸው ቢያምኑም፣ በክልሎችና ክለቦች የሚስተዋለው በተቃራኒው ነው፡፡ በአገሪቱ ሁሉም ክለቦች ለጊዜያዊ ውጤት ካልሆነ እንደሚሉት ታዳጊ ወጣቶች ላይ የመሥራት አዝማሚያ ቀርቶ ፍላጎት እንኳን ያላቸው አይመስሉም፡፡ ከሁለት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ አሠልጣኞች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ሲዘዋወሩ ለእነሱ አጨዋወት የሚያመቻቸውን ተጨዋቾች ይዞ መዞር ልምድ ካደረጉ ውለው አድረዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት ቴክኒክ ዲፓርትመንቱ ያዘጋጀውን ሁሉን አቀፍ የእግር ኳስ ልማት ማስተግበሪያ ሰነድ ወደ ተግባር ለመቀየር አያስቸግርም ወይ? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ መኰንን፣ “እንደ ዲፓርትመንት ለእግር ኳስ ልማት የሚያስፈልጉ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ተፈጻሚነቱ እስከ ምን ድረስ ይሆናል በሒደት የሚታይ ሆኖ፣ ግን ደግሞ እግር ኳሱ መለወጥ አለበት የምንል ከሆነ እግር ኳሱ የሚፈልገውን መፈጸም ግድ ነው፤” ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ትንሣኤ እውን ለማድረግ እንደ ቴክኒክ ዲፓርትመንት እስከ ስድስት የሚደርሱ ብሔራዊ ቡድኖችን ማዋቀር ያስፈልጋል፣ እየተሠራበትም እንደሆነ ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ መኰንን በክልል ደረጃ ሳይቀር አካባቢውን የሚወክል ጠንካራ ቡድን በማቋቋም አንዱ ከሌላው ጋር እርስ በእርስ እንዲጫወቱ በማድረግ ከነዚያ ውስጥ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር እንደሚቻል፣ ይኼንኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገሩበት ጭምር ይናገራሉ፡፡
የተግባራዊነቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አካሔዱ በተለይ ለክልል ታዳጊዎች ዕድል በመፍጠር ረገድ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን የሚያክሉት አቶ መኰንን፣ ይህ ግን በእያንዳንዱ ክልልና የክለብ አመራር መልካም ፍላጎት ላይ የሚወሰን መሆኑ ግን ሥጋታቸው ነው፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሪሚየር ሊጉ የአንደኛውን ዙር የጨዋታ መርሐ ግብር አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ. ም በጁፒተር ሆቴል ግምገማ አድርጓል፡፡ በዕለቱ የሁሉም የፕሪሚየር ልግ ከለቦች ተወካዮች በተገኙበት በተደረገው የአንደኛው ዙር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ፣ ጠንካራ ጎን ተብሎ የቀረበው በትግራይና በአማራ ክለቦች መካከል የነበረው አለመግባባት ተፈቶ ሁለቱም ክልሎች በመርሐ ግብሩ መሠረት ውድድራቸውን እንዲያደረጉ መደረጉ ነው፡፡
በአንደኛው ዙር ከቀይና ቢጫ ካርዶች ውጪ፣ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር የዘንድሮ ካለፈው ዓመት በንጽጽር የተሻለ መሆኑ ተነስቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ በውድድር ዓመቱ ክፍተት ብሎ የተነሳው ደግሞ፣ በአገሪቱ ባለው ወቅታዊ ችግር የውድድር ዳኞችን በወቅቱና በሰዓቱ አለመመደብ፣ በቂ የጸጥታ ኃይል እጥረት፣ ለዳኞችና ለታዛቢ ዳኞች ዋስትና ማጣት፣ በዚህም በጨዋታ ሪፖርቶች ለታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች የተሟላ ማብራሪያ እንዳይቀርብ መንስኤ መሆኑ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ሌላው በግምገማው የቀረበው የውጪ ተጨዋቾችን የተመለከተ ሲሆን፣ የውድድር ዓመቱ እንደተጠናቀቀ በአጠቃላይ የተጨዋቾች ዝውውር እንዴት ይመራ በሚለው ላይ መነጋገር እንደሚያስፈልግ መድረኩ መግባባት ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መድረኩን ከማመቻቸት ባለፈ በዋናነት ጉዳዩ የክለቦች መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በመጨረሻም ሁለተኛው ዙር መርሐ ግብር መጋቢት 7 ቀን ተጀምሮ ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ እቅድ የተያዘ ስለመሆኑ ጭምር ተነግሯል፡፡