Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየኦሮሚያ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣንን ይመለከታል

የኦሮሚያ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣንን ይመለከታል

ቀን:

ቀደም ባሉት ዓመታት ባለው አሠራር መሠረት ከክልል የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር ሕጋዊ የሆነ የመንጃ ፈቃድ አሠራር ተምረንና ሠልጥነን የመንጃ ፈቃድ ደብተር ተሰጥቶን ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ በክልሉ አሠራር የመንጃ ፈቃድ ደብተሩ በየሁለት ዓመት የሚታደስ በመሆኑ፣ የመታደሻው ወቅት ስለደረሰ ለማሳደስ ስንሄድ በተለይም በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የሚገኘው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት አዲስ አሠራር መጥቷልና የመንጃ ፈቃድ ደብተሩ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ካርድ መቀየር አለበት ተባለ፡፡

ለዕድሳት የሚያስፈልገውን አራት መቶ ብር፣ የደብተር መቀየሪያ ስምንት መቶ ብር፣ ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንድንከፍል ካስደረገን በኋላ፣ ዛሬ ነገ በማለት መንጃ ፈቃዳችን ሳይታደስ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይተናል፡፡ በየጊዜው ተመላልሰን ስንጠይቅም የሚሰጠን መልስ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ፕሪንተር ስለተበላሸ ጠብቁ ብቻ ነው፡፡ ለዚሁ ዕድሳት ከየቦታው በመመላለስ ጊዜያችንንና ገንዘባችንን ከማጣታችን ባሻገር፣ በሥራችን ላይ ዕንቅፋት በመሆን በየጊዜው ከትራፊክ ፖሊስ ጋር እሰጥ አገባ፣ ጭቅጭቅና የቅጣት ሰለባ እየሆንን እንገኛለን፡፡

አገራችን ብዙ በዘርፉ የሠለጠኑ የቴክኒክ ባለሙያዎች ባፈራችበት በዚህ ወቅት፣ ካልሆነ እንኳን ከእኛ በተሰበሰበው ገንዘብ ሌላ ፕሪንተር መግዛት እየተቻለ ለእንዲህ ዓይነት መልስ መሰጠቱ ለዜጋው ትኩረት አለመስጠትና የተሽከርካሪ አደጋውን ከማባባሱ ባሻገር፣ ፍትሕን ወደ ጎን ዞር አድርጎ የግድ የለሽ (የምን ቸገረኝ) አሠራርን መከተሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በአጽንኦት ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን፣ የእናንተ ጋዜጣ ደግሞ የሕዝብ ተደራሽ ድምፅ በመሆኑ በጋዜጣችሁ አማካይነት ይፋ እንዲሆንና ችግሩንም እንድትጠይቁልን ወደ ዝግጅት ክፍሉ ለመምጣት ተገደናል፡፡

(ተበዳዮች፣ ከአሰላ)

****

ስለተመድ ልማት ፕሮግራም የቀረበው ዘገባ ሐቅ ይጎድለዋል

      በየካቲት 24 ቀን 2011 እትም፣ ስለየተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ)፣ ሐቅመሠረት ያላደረገ ዘገባ በጋዜጣው መስተናገዱን አስተውለናል፡፡ ስለዚህም ለተከበሩ አንባቢያን እውነታውን ለማስገነዘብ እንፈልጋለን፡፡

      ዩንኤዲፒ በዓለም አቀፍ ደረጃ 170 አገሮች የአቅም ግንባታ ድጋፍ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ አገሮች የሚመሩበትን የልማት አጀንዳ ዕውን እንዲሆን የሚሠራ የተመድ አካል ነው፡፡ የአቅም ግንባታ ድጋፉ በተለይም የሰው ኃይል ክፍተትን ለመሙላት የመንግሥት ጥያቄንና የክህሎቱን አስፈላጊነት መሠረት በማድረግ የሚስተናገደው በዩኤንዲፒና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው አሠራር ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ይህም የአሠራር መርህ የሰው ኃይል ቅጥሮች ለሁሉም እኩል ዕድል እንዲሰጥ ግልጽ ማስታወቂያ ወጥቶለት ፍትሐዊና ሙያን መሠረት ያደረገ የግምገማ መሥፈርት ተከትሎ ቅድመ ማጣሪያውን ያለፉ አመልካቾችን አመዛዝኖ ለሥራው በብቃታቸው የላቁትን የሥራ ዕድል በመስጠት ነው፡፡

      ይህ አሠራር የኢትዮጵያ ዩኤንዲፒ ቢሮንም ጨምሮ በሁሉም የ170 አገሮች ባሉ ቢሮዎች እየተገበረ ነው፡፡ በጋዜጣችሁ ዕትም ላይ የጠቀሳችሁት በመንግሥት ጥያቄ በዩንኤዲፒ በኩል ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተፈጸመው ቅጥርም ከላይ የገለጽነውን አሠራር የተከተለና ለሁሉም ተወዳዳሪ በእኩል ደረጃ ክፍት የሆነና በምንም መልኩ አድሎአዊ አካሄድ ያልተከተለ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

      በዚሁ አጋጣሚ ዩኤንዲፒ የአሠራር ሒደቱን በየጊዜው በባለሙያዎች ኦዲት የሚያስደርግ መሆኑን እየገለጽን በጋዜጣችሁ ላይ እንደጠቀሰው ‹‹በዩኤንዲፒ ፕሮጀክት ድጋፍ አማካይነት የተፈጸሙ ቅጥሮች ተገግምግመው ተቀባይነት ያላገኙ ናቸው›› ብላችሁ የጻፋችሁት ዜና ከእውነታው የራቀ መሆኑን እንገለፃለን፡፡

(ዩኤንዲፒ)

****

በጫት ራስን መጉዳት?

በሐበሻ ወግ መጽሔት በቅጽ ሦስት ቁጥር 114 ጥር 2011 ዓ.ም. ዕትም የተጻፈውን ‹‹ጫትን ማገድ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም፤›› የሚለውን የቢቢሲና የዶ/ር ዘሪሁን መሐመድን ቃለ መጠይቅ አንብቤዋለሁ፡፡

ጫት ለአገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ የነበረውን ቡና እያደር በገቢ እየተገዳደረው መምጣቱ እንዲሁም አራት ሚሊዮን አምራቾች በምርቱ መሳተፋቸው አስገርሞኛል፡፡ ስለጫት ሱስ ሳስብ ሁለት አሳዛኝ ነገሮች ትዝ ይሉኛል፡፡ አንዱ ነገር በወጣትነት ዕድሜ የማውቀው የጫት ሱሰኛ የነበረ የሐረር ልጅ በሱስ ሲወላገድ ቆይቶ በለጋ ዕድሜው መቀጨቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር በጫት መቃም ባህል ላይ የተመሠረተው የየመን ማኅበረሰብ እያደር መንኮታኮቱና ሌላም ችግር እያሰባሰበ ለውድቀት መጋለጡ ነው፡፡

ስለየመን የጫት ባህል የተረዳሁት ከ20 ዓመታት በፊት በሥራ ምክንያት አልፎ አልፎ ወደ ሰንዓና ሌሎችም ከተሞች ስለምመላለስ ነበር፡፡ የተረዳሁት ነገር፣ ጫት ቃሚው ከረፋዱ ላይ ወደ ገበያና ሱቅ እየተቻኮለ ይሄድና ጫቱን ገዝቶ ከጓደኞቹ ጋር ሲቅም ይውላል፡፡ ከሰዓት አሥር ሰዓት ገደማ ሲሆን፣ ከመሥሪያ ቤቱ ብቅ ይልና ሥራውን እንደነገሩ ነካክቶ ወዲያው ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ይህን ሳስብ ምናልባት የመን በጫት ሱስ ምክንያት የተኮላሸች አገር እንዳትሆን ብዬ እሰጋ ነበር፡፡

የመን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ተራራማ አገር ነች፡፡ ከኢትዮጵያ የሚለያት በአብዛኛው የተራቆጠ አካባቢ የሚታይባት በመሆኗ ነው፡፡ እኛ ጋ ከሞላ ጎደል አብዛኛው አካባቢ ሳርና ቁጥቋጦ አይጠፋም፡፡ የየመንና የእኛ ሕዝብ በቅርፅና ቁመና ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ እኛ ተወልደንና ሳባን ከእኛ ትንሽ ቀላ ብለው ሰንአ ያገኘኋቸው መስሎኛል፡፡

በዝርያችንና በመሬት አቀማመጣጥችን በእጅጉ ከምንቀራረባቸው የመኖች ጋር ዕጣ ፈንታችንም ምናልባት ይመሳሰል ይሆን? ጫት መቃም ስሜት ያነቃቃል፡፡ ምርቃናው ያከንፋል፡፡ ሲለቅ ግን ያረግፋል ይባላል፡፡ የምግብ ፍላጎትን ያሳሳል፡፡ ፍቅር ያወላክፋል፡፡ ምርታማነትንም ያዳክማል፡፡  አፍ፣ ጉሮሮና ጨጓራ ያቆስላል፡፡ የጫት ሱስ በግልጽ የሰው ልጅ ህልውናን ይፈታተናል፡፡ ብርቱነቱንም ይሸረሽረዋል፡፡ በአጉል ሱስ ተጠምዶ መቆርቆዝ አንደኛ ደረጃ ግድፈት ይመስለኛል፡፡ በፈጣሪ ተመራጭ የሆነ ሰው ንፅሕናውን ጠብቆ መኖር አይገባውምን?

ሕይወት ምድር ላይ የፈለቀች ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ ነች፡፡ ፀሐይ ረዥም ዕድሜ ስላላት ለሕይወት መስረፅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላት ይነገራል፡፡ ሕይወት ለምግብ ውኃ ፍቅር አድናቆት ወዘተ. ስሜት ተፈጥሮዋዊ ግፊት አለባትም ይባላል፡፡ ስለሆነም እርካታ ወይ ዕጦት ደስታ ወይ ሐዘን በኑሮ ላይ ይንፀባረቃሉ፡፡ ይህም ማለት እንደ ፅድቅና ኩነኔ የመሰለ አንድ ወጥ ስሜት በፀሐይ ምድራዊ የሕይወት ዓለም ላይ ቦታ ያለው አይመስልም፡፡

ጥሩ ምግባር ያለው ሰው ሲሞት ነፍሱ ትፀድቃለች ይባላል፡፡ ነፍስ መንፈሳዊ መሆኗ ይነገራል፡፡

ሃይማኖት ያፀድቃል ወይም ይኮነናል የሚለን ነገር የፀሐይን ጨረር ይሆን? ስለ ኩነኔ ሲታሰብ ግን ቅጣቱ ድግግሞሽ ያለበት ይመስላል፡፡ ሕይወት የተፈጥሮ ልዩ ፀጋ ናት ሲባል ሽርፍርፍ ኑሮ እራሱን የቻለ ቅጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ኑሮ ሲጓደል ሐዘን እንጂ ደስታ አይገኝም፡፡ ሕመምም ስቃይ ነው፡፡ ሞት ደግሞ ሕይወት ስለሚቀጥል ዋናው ቅጣት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ ሰው በሕወት አንድ ጊዜ ስለኖረ ብቻ ለምን በተጨማሪ ይኮነናል? የኑሮው ውጣውረዱ ዕጦቱ እንግልቱ አይበቃውምን? የፅድቅ ተጠቃሚውስ ማነው? ሰው እንደሆነ ዘላቂ ደስታ አልለመደበትም፡፡ ደስታ ሲደጋገምበት ልክ እንደ ማር ቋቅ ይለዋል፡፡

የሚያዋጣው ነገር ህልውናን ይዞ መዝለቅ ነው፡፡ ያጠለቅነውን የሕይወት ሀብል ሳናወልቅ ማለት ነው፡፡ ህልውና ማለት የነፃነትና የእኩልነት እንዲሁም የሕዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት ተጣጥሞ የመዝለቃቸው ፍሬ ነው፡፡

(ከፍቅሩ አማረ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...