ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ቦሌ የሚያመራው ታክሲ ውስጥ ከጥቂት ተሳፋሪዎች ጋር ተቀምጠናል፡፡ ወያላው ‹‹ቦሌ! ቦሌ!›› እያለ ተጨማሪ ተሳፋሪዎች ሲጣራ፣ በዚህ መሀል ቁመተ ረዥምና ትከሻ ሰፊ ጎረምሳ ከአንዲት ቆንጆ ወጣት ጋር ገብተው ቦታቸውን ያዙ፡፡ ወጣቷ እሱ ላይ ጥብቅ ስላለች እሱ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ ገብተው እንደተቀመጡ ጎረምሳው አንዳች የሚያህል የሞባይል ስልኩን ያወጣና መነጋገር ይጀምራል፡፡ እኔ በ40 ዓመት ዕድሜዬ እንዲህ ዓይነት ሥርዓት አልበኛና ጋጠወጥ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ንግግሩ በሙሉ በአፀያፊ የብልግና ቃላትና በስድብ የተሞላ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እየጮኸ ስለሚነጋገር የታክሲውን ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል አሸማቆናል፡፡ ከንግግሩ መሀል፣ ‹‹መጣውልህ አንተ ቆሻሻ!›› እና ‹‹እደፋሃለሁ!›› የሚሉት ደግሞ በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቆንጅዬዋ ወጣት ምንም እንዳልተፈጠረ እየተፍነከነከች ትስቃለች፡፡
ታክሲያችን ከሥምሪቱ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስቀል አደባባይን ስናቋርጥ የሾፌሩ ረዳት፣ ‹‹ወንድም ድምፅህን ቀንስ ወይም በጨዋነት ተነጋገር፤›› የሚል ማሳሰቢያ ጣል አደረገለት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ወጠምሻ ጎረምሳ ንግግሩን ገታ አድርጎ፣ ‹‹አንተ ምን አልክ?›› ብሎ ለዱላ ከመቀመጫው ሲነሳ ረዳቱ ከወንበር ሥር የብረት ዘነዘና የመሰለ ነገር አወጣ፡፡ ረዳቱ በዓይን ሲገመገም ይህንን አንዳች የሚያህል ወጠምሻ ለመመከት አቅም ባይኖረውም፣ ለክፉ ጊዜ ያዘጋጀው የብረት ዘነዘና ወጠምሻውን ወደነበረበት እንዲመለስ አስችሎታል፡፡ ታክሲው ፍላሚንጎን አልፎ ወደ ኦሊምፒያ ሲቃረብ በብልግና ቃላት እየተጠቀመ ሲያደነቁረን የነበረው ጎረምሳ ስልኩን ኪሱ ከተተ፡፡ ከዚያም ረዳቱን በነገር መውጋት ጀመረ፡፡ ረዳቱም፣ ‹‹ሰማህ? ብትከበር ይሻልሃል፡፡ ያለበለዚያ አናትህን ብዬ እገላግልሃለሁ፤›› ሲለው ሌሎች ተሳፋሪዎች ‹ተው! ተው!›› እያሉ አበረዱት፡፡
በዚህ መሀል ከወጠምሻው ጋር ያለችው ቆንጆ፣ ‹‹አንተ አታፍርም? ቢይዝህ እኮ አንድ ጉርሻ ነው የሚያደርግህ . . .›› እያለች ነገሯን ስታደራ አንዲት እናት፣ ‹‹ምነው ልጄ? ነገር ማብረድ ሲገባሽ ታባብሻለሽ? በይ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ንግግር ከአንቺ አፍ አይውጣ፤›› አሏት፡፡ ከመልክ በስተቀር ምግባር የጎደላት ይህችው ወጣት፣ ‹‹እማማ በማይመለከትዎት ነገር ጣልቃ አይገቡ፤›› ስትላቸው፣ ‹‹ልጄ እኔ ጤነኛ መስለሽኝ እንጂ የአማኑኤል ምልስ መሆንሽን መቼ አውቄ?›› ብለው ሲገረምሟት ረዳቱና የተወሰኑ ተሳፋሪዎች ሳቁ፡፡
ያ ደረቱ እንደ ጃንሜዳ የሰፋው ብልሹ ጎረምሳ፤ ‹‹ተያቸው ይሳቁ፡፡ ቦሌ ስንደርስ ምን እንዳሳቃቸው ቃላቸውን እንቀበላለን . . . ከዚያም አይቀጡ ቅጣት እንቀጣቸዋለን . . .›› እያለ ሲመፃደቅ በሞባይል ስልኩ ጽሑፍ ሲያነብ የነበረ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹አንተ ስድ አደግ አይበቃህም? ማንን ነው የምትመረምረው? አንተ ማን ሆነህ ነው የምትቀጣው? ሕግ አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ የሆንከው ማን ስለሆንክ ነው? ይህንን በአስቸኳይ ካልነገርከኝ እኔ ራሴ እዚሁ ምርመራ እጀምርብሃለሁ፤›› ሲለው ወጠምሻው በድንጋጤ ይሁን በመገረም ዓይኑ ፈጠጠ፡፡ ያቺ ቅልብልብ የምትለው ጠፍቷት አንዴ ውጭ ውጩን ሌላ ጊዜ ደግሞ የታክሲውን ጣሪያ በዓይኖቿ መዳሰስ ጀመረች፡፡
በዚህ ውጥረት ውስጥ ተሳፋሪዎች ‹‹ወቸው ጉድ . . .›› እያሉ እርስ በርስ ማውራት ሲጀምሩ አንዲት ረጋ ያለች ሴት፣ ‹‹ፈረንጆች ጨዋነት ሲያከትም ብልግና ይነግሳል እንደሚሉት፣ ይሉኝታና ኃፍረት ጠፍቶ በባለጌ እንወረር?›› በማለት አጠገቧ ካለው ወጣት ጋር ወሬ ጀመሩ፡፡ የሁለቱ ርዕስ ከሌሎች ሹክሹክታዎች በላይ ስለገነነ እኛም ተደባለቅናቸው፡፡ ይህች ሴት የዘመኑን ብልግናና ይሉኝታ ቢስነት እያነሳች ወጉን ስታሰፋው፣ ‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› በሚል በወሬ ተጠመድን፡፡ በዚህ መሀል ያ ወጠምሻ ጎረምሳና ልጅቷ ድምፃቸውን እንዳጠፉ ፍሬንድሺፕ አካባቢ ሹልክ ብለው ሲወርዱ ግርማ ሞገሳቸው ጠፍቶ ነበር፡፡ ማንም ከመጤፍ ሳይቆጥራቸው ሹክክ እንዳሉ ተለዩን፡፡
ከሴትዮዋ አጠገብ የተቀመጠ ወጣት እንዲህ አለን፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ራስ ወዳድነት በመንሰራፋቱ ይሉኝታና ህሊና የሚባሉ ጠቃሚ ነገሮች እየጠፉ ናቸው፡፡ ህሊና ሳይኖር ሲቀር ብልግና ይበረታል፡፡ ራስ ወዳድነት ጣሪያ ሲነካ ብልግናና ሌብነት ኩራት ይሆናሉ፡፡ ድሮ በአገራችን ጨዋነት፣ ሥነ ምግባርና ኩራት የደህና ሰው መገለጫ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ኩራት እራት ነው፣ ከፍትፍቱ ፊቱ . . .› እየተባለ ብዙ አልባሌ ነገሮች ይናቃሉ፡፡ አሁን ግን ዘረኝነት፣ የገዛ ወገንን ማፈናቀል፣ መግደል፣ ማመናጨቅ፣ ጥላቻ መዝራት፣ ዝርፊያ፣ ሐሜትና ስግብግብነት በርክተዋል፡፡ የዘመኑ ሰው ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ› የሚባለውን ዕድሜ ጠገብ ብሂል ገልብጦት ‹ፍትፍቱን በልተህ ጥፋ ከፊቱ› እያለ ይሳለቃል፡፡ ይኼ ደግሞ የሞራል ውድቀትን ያሳያል . . .›› እያለ ሲነግረን አስደመመን፡፡ ወጣቱ የበሰለ መሆኑ ያስታውቃል፡፡
እኔ በበኩሌ ‹‹ድሮ ቀረ›› በሚባለው አባባል የማምን ባልሆንም፣ በዚህ ዘመን የማያቸው አሳዛኝ ድርጊቶች ግን ያበሳጩኛል፡፡ ብልግናና ራስ ወዳድነት ከመጠን በላይ ሆኖ በየቦታው ‹እኛ . . .እናንተ . . .› ሲባል፣ በየቦታው ክፉዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሕዝቡን ሲያምሱ፣ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ የቡድን መጠቃቀሚያ ሲሆን በጣም ያበግነኛል፡፡ ይህንን እያሰላሰልኩ ሳለሁ ቦሌ ጫፍ ደርሰን ከታክሲ ወረድን፡፡ አንዳንዴ አጋጣሚ አይጠፋም አይደል? ቦሌ ጫፍ ላይ ያለው ኖክ ማደያ አጠገብ በከፍተኛ ድምፅ የሚናገር ሰው ቀልቤን ያዘው፡፡ ይህ ንክ የሚመስል ነገር ግን ልባም ሰው፣ ‹‹አቤቱ ፈጣሪ ሆይ! ኢትዮጵያን ከዘረኞች፣ ከምግባረ ብልሹዎች፣ ከህሊና ቢሶችና ከራስ ወዳዶች ጠብቃት!›› እያለ በተደጋጋሚ ሲማፀን መልዕክቱ ለሁላችንም መሰለኝ፡፡
የሰውየው ተማፅኖ ያለንበትን ጊዜ ሲያስታውሰኝ ልቤ ተነካ፡፡ ምድረ ዕብሪተኛ በገዛ አገራችን መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጣን እንዴት ዝም ይባላል? የሰሞኑን አገር በሪሞት ኮንትሮል የሚያስተዳድሩ የሚመስሉ ጥጋበኞችን ከልክ ያለፈ ጥጋብ ‹ልብ ያለው ልብ ይበል› የሚያሰኝ ነው፡፡ ባለ ጊዜ ነን ብለው ደሃ የሚያፈናቅሉ፣ አፈናቃዮችን በርቱ የሚሉ፣ ሁሉም ቦታ ውስጥ ተሰግስገው ተረኛ አስገባሪ ለመሆን የሚጋጋጡ፣ ላቡን ጠብ አድርጎ ለፍቶ ለዓመታት እየቆጠበ የኮንዶሚኒየም ተራ ሲጠብቅ የኖረ ምስኪን ደረሰኝ ብሎ ሲደሰት አገር የሚያሸብር ማስፈራሪያ እያሰሙ ቀውስ የሚፈጥሩ፣ አገራችን ያገኘችውን መልካም አጋጣሚ አበላሽተው ተስፋችንን የሚያመክኑና በመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የመጣውን ለውጥ ለራሳቸው መሰሪ ዓላማ ለመጥለፍ የተነሱ እኩዮችን ሳስብ አቤቱ ጌታ ሆይ አንተ ጉልበት ሁነን ማለት ጀምሬያለሁ፡፡ ሌላ ምን ይባላል?
(ወንድወሰን ተስፋ፣ ከልደታ)