Saturday, February 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክረቂቁ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ

ረቂቁ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

አሁን አሁን በአገራችን ስለሕገወጥ የጦር መሣሪያ መያዝ መስማት የዘወትር ዜና ሆኗል፡፡ በተለያዩ አቅጣጫዎችና በተለያዩ ዘዴዎች መሣሪያ መግባታቸው እየቀነሰ ቢመጣ ዜናው አይበዛም ነበር፡፡ አገራችን አሁን ያለችበት የፀጥታ ሥጋት ላይ እዚህ ግባ የማይባል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ሲታከልበት የጦር መሣሪያ አስተዳደር ሁኔታውን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባል ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጦር መሣሪያ አስተዳደርን የሚገዛ ሕግ እየተረቀቀ እንደሆነ በተለያዩ ዘዴዎችና ጊዜያት ለሕዝብ አሳውቀዋል፡፡ እንደተነገረውም ሕግ ተረቋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ የምንገመግመውም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተረቀቀውን አዋጅ ነው፡፡ ትኩረት የተደረገውም ይሻሻሉ ዘንድ ከእንደገና በአጽንኦት መታየት ያለባቸው ነጥቦችን ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ አሁን ባለበት ደረጃም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ከሆነም ምክር ቤቱ ውሳኔ በአንክሮ እንዲያያቸው ለመጠየቅ ነው፡፡

1952 .ም. የመሣሪያ ደንብ

ስለጦር መሣሪያ መያዝ፣ በሥራ ላይ ያለውና ተፈጻሚነት ያለው ዋናው ሕግ በ1952 ዓ.ም. በወቅቱ የአገር ግዛት ሚኒስቴር በመባል ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት ያወጣው፣ የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 229/1952 ወይም ‹‹የ1952 ዓ.ም. የመሣሪያ ደንብ›› ተብሎ የሚጠቀሰው ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ በዋናነት የተኩስ መሣሪያ ያላቸው ሰዎች በአካባቢያቸው በሚገኙ በስም ተለይተው በተገለጹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲያስመዘግቡ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ የመሣሪያ ዓይነት (አነስተኛም ይሁን ቀላል፣ አውቶማቲክም ቢሆንም ባይሆንም) ሳይለይና ገደብ ሳይጥል፣ ከአንድ በላይም መያዝን የፈቀደ ነው፡፡ መሣሪያ ይዞ የማይገባባቸውን ቦታዎችም ለይቷል፡፡ የሚያሰክር መጠጥ የሚሸጥበት ማናቸውም ቦታ፣ ሕዝብ የሚሰበሰብበትና የሃይማኖት በዓላት የሚከበርባቸው ቦታዎች፣ እንዲሁም ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች፣ ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ውስጥ  ይዞ መዘዋወርን ከልክሏል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የጦር መሣሪያ መያዝ የሚችለው ሰው ማሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታዎች አላስቀመጠም፡፡ ግቡም በእጃቸው ያለውን መሣሪያ እንዲያስመዘግቡ እንጂ ማን መያዝ ይችላል ወይም አይችልም የሚለው በመለየት ቁጥጥር ማድረግ አይደለም፡፡

ይኸው ሕግ፣ የጦር መሣሪያ ከአገር ውጭ ለማስገባትም ሆነ ለማስወጣት እንዲሁም ለመነገድ የሚቻልበትን ሁኔታም እንዲሁ አስቀምጧል፡፡ የንግድ ፈቃድም ሲወጣም መሟላት ያለበትን ለባለፈቃዱ የሚሰጠውን የፈቃድ ወረቀት ሳይቀር አካትቶ አውጥቷል፡፡

ምንም እንኳን ይህ ሕግ ግለሰቦች በሕጋዊ መንገድ የጦር መሣሪያ መሸጥ መለወጥ ውስጥ በመሰማራት የንግድ ሥራ እንዲያከናውኑ ቢፈቀድም አሁን ላይ በይፋና በሕጋዊ መልኩ፣ ሱቅና መደብራቸውን ሕዝብ አውቆት የሚነግዱ ሰዎች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ሕጉ እስካልተሻረ ድረስ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ይህ ማለት ግን አገሪቱ ውስጥ የጦር መሣሪያም ሆነ ተተኳሾች የሚሸጡበትና የሚገዙበት ቦታዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡

ሽያጭና ግዥ ስለተንሰራፋ ነው የጦር መሣሪያ ያላቸው ሰዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሄዱ፡፡ ግብይቱ ግን ደንቡ ባስቀመጠው የንግድ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወን ስላልሆነ ሕጋዊነት ይጎድለዋል፡፡ መንግሥትም ሕገወጥ ግብይቱ እንደሚጧጧፍ ሳይጠፋው ሥርዓት እንዲሰፍን የማድረግ ግዴታውን ዘንግቶታል ወይም ትቶታል፡፡

አሁን ላይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያረቀቀው አዋጅ ሲጸድቅ ይህንን የሕግ ክፍል ማስታወቂያ እንደሚሽረው ግልጽ ነው፡፡ በረቂቁ አዋጁ አንቀጽ 31 ላይ ተቀምጧል፡፡ ረቂቅ አዋጁ፣ የጦር መሣሪያ ሲለሚሸጥበትና ስለሚገዛበት ወይም የጦር መሣሪያ ንግድን በሚመለከት ሥርዓት መዘርጋትን በመተው የቀድሞውን ደንብ ለመሻር ፈልጓል፡፡

ረቂቅ አዋጁ

ወደፊት ይህንን ረቂቅ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ካላሻሻለው በስተቀር (በጸሐፊው እጅ ከገባ በኋላ ተሻሻሎም ካልሆነ በቀር) ሠላሳ ሁለት አንቀጾች አሉት፡፡ እነዚህ አንቀጾችም ወደ ስድስት ክፍል ተሸጋሽገው ተከፋፍለዋል፡፡ ጠቅላላ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምን በሚመለከት ክልከላዎች የተዘረዘሩበትን አራት አንቀጾች የያዘ አንድ ክፍል አለው፡፡ አሥራ አራት አንቀጾች ያሉት ደግሞ የጦር መሣሪያ ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደርን የሚመለከት ሰፋ ያለ ክፍል አለው፡፡ አምስተኛው ክፍል የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ፍቃድ ሰጭ በመሆን የተቆጣጣሪነት ተግባር የተሰጠውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን የሚመለከት ነው፡፡ የመጨረሻው ክፍል ደግሞ የወንጀል ተጠያቂነትና የቅጣት ዝርዝሮች፣ የመተባበር ግዴታና ያለመተባበር  የሚያስከትለውን ቅጣትና ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ሥልጣንና ክልሎች

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(1)(ሸ) ላይ እንደተገለጸው የጦር መሣሪያ አያያዝን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ረቂቁም በዚሁ መነሻነት ነው የተዘጋጀው፡፡ ሕጉ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል የጦር መሣሪያን ጉዳይ የማስተዳደር ሥልጣኑን (በመከላከያ ሠራዊቱ እጅ የሚገኘውን ሳይጨምር) ለፌዴራል ፖሊስ አድርጎታል፡፡ ተቆጣጣሪ ተቋም የሚል ሥያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ፈቃዱን የማገድ ሥልጣን አለው፡፡ ሊሰርዝም ይችላል፡፡ ይኼ ሥልጣኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም የክልል መንግሥታትንም ይጨምራል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው ክልሎች በወሰናቸው ውስጥ ያለውን ፀጥታ ለማስፈን ፖሊስና ሚሊሻ የማቋቋም ሥልጣን ቢኖራቸውም ሊያስታጥቋቸው የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛት፣ አቅርቦትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚወስንላቸው ግን የፌዴራሉ መንግሥት ነው ማለት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ይህንን ሥልጣኑን ለሰላም ሚኒስቴር እንዲያስፈጽም፣ ማለትም መመርያ በማውጣት እያንዳንዱ የፀጥታ ተቋም የሚፈቀድለትን የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት ይወስናል፡፡ ይኼንን ተግባራዊ በማድረግ የማስፈጸምና የመቆጣጠር ሥልጣኑ ደግሞ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡

የክልል መንግሥታት በሚሊሻና በፖሊስ እንዲሁም በግል የፀጥታና ጥበቃ ድርጅቶች አማካይነት የክልላቸውን ፀጥታ ለማስከበር የሚያስፈልጋቸውን መጠንና ዓይነት በፌዴራል መንግሥት አማካይነት በማዕከል እንዲታወቅና እንዲወሰን መደረጉ ተገቢ ቢሆንም የክልሎቹን ነባራዊ ሁኔታ፣ የፀጥታ ሥጋትና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲሁም ከውገና የፀዳ አሠራር መዘርጋት ፈተና ሊሆን እንደሚችል በማሰብ እነዚህን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተቋማዊ አሠራር ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ የቅሬታና ይግባኝ ሥርዓትንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በግለሰብም ሆነ በድርጅቶች እጅ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶችን የሚመዘግብበትና የሚያስተዳድርበት ብሔራዊ የጦር መሣሪያ መቆጣጠሪያ ክፍል (National Firearms Register) እንዲያቋቁም ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የግል የጥበቃና የደኅንነት ድርጅቶች የሚይዟቸውን መሣሪያዎችም መመዝገብና መቆጣጠርም የመንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ የናይሮቢው ፕሮቶኮል ያሳስባል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ፣ እነዚህን ግዴታዎች ለመወጣት ቃል ብትገባም ወይም ፕሮቶኮሉን ብታጸድቅም የተጣሉባትን ግዴታዎች መወጣት የሚያስችሏትን የሕግ ማዕቀፎች ስላልነበራት ይህ አዋጅ ለፕሮቶኮሉ ምላሽም እየሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፌዴራል ፖሊስ የጦር መሣሪያ ፍቃድ ሲከለክል፣ ሲያግድ፣ ሲሰርዝ አዲስ ፈቃድ ጠያቂዎችም ሆኑ ዕድሳት የሚፈልጉ ሰዎች ቅሬታ ቢኖራቸው ይግባኝ የሚሉበትም ሆኑ አቤቱታ የሚያቀርቡት ሥርዓት ረቂቁ ውስጥ የለም፡፡ ከታች እንደምንመለስበት ለፈቃድ መስጠትና ማድስ በመስፈርትነት የተቀመጡት ፖሊስን እንዳሻው እንዲወስን የሚያደርጉ ሆነው ሳለ የቅሬታ፣ የአቤቱታና ይግባኝ ሥርዓትን መዝለል ዳፋው ብዙ ነው፡፡

ለመያዝ ነው ፈቃድ ወይስ ከያዙ በኋላ?

እስካሁን ባለው አሠራር የጦር የመሣሪያ ፈቃድ መሰጠት ያለበት ከያዙ በኋላ ሳይሆን ለመያዝ ነው፡፡ በአገራችን፣ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ መሸጫ ስለሌለ ማንም እንዳሻው ካገኘበት ይገዛል፡፡ ከዚያም የሚያስገድድ ሁኔታ ካጋጠመው ከሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ወይም ደግሞ ከፖሊስ ጣቢያ (እንደ ክልሎቹ ስለሚለያይ) ፈቃድ ያወጣሉ፡፡

ኢትዮጵያ፣ በታላላቅ ሐይቆችና በአፍሪካ ቀንድ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን ክልከላ፣ ቁጥጥርና ቅነሳ የሚመለከተውን የናይሮቢ ፕሮቶኮል ፈራሚ ናት፡፡ በዚህ ፕሮቶኮል መሠረት ደግሞ ፈቃድ ሳይኖር በእጅ የገቡ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪዎችን በመውረስ የማስወገድ ግዴታ አለባት፡፡

አሁንም ቢሆን፣ ግለሰቦችን በሚመለከት ረቂቅ አዋጁ የጦር መሣሪያን በእጅ ካደረጉ በኋላ ማስመዝገብን እንጂ፣ መሣሪያ ለመያዝ (ለመግዛት) አስቀድሞ ፈቃድ ማውጣትን አልመረጠም፡፡ ይኼ ደግሞ ግለሰቦች ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ከገዙ በኋላ ፈቃድ ባላገኝስ፣ ባይሰጠኝስ በማለት ላያስመዘግቡ ይችላሉ፡፡ ፈቃድ ካልተሰጣቸው መሣሪያው እንደሚወረስ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል፡፡

ስለሆነም፣ የተወሰነ የመሸጋገሪያ ጊዜ ተዘርግቶ፣ በእጃቸው መሣሪያ ያላቸው ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ መሣሪያ መያዝ የሚፈልግ ሰው ፈቃድ ሊሰጠው የሚገባው ለመግዛት እንጂ ከገዛ በኋላ መሆን የለበትም፡፡ ለመግዛት አስፈቅዶ፣ ከዚያ ከገዛ በኋላ መሣሪያው ማስመዝገብ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች አሠራርም እንዲሁ ነው፡፡

ስለጦር መሣሪያ አጠቃቀም ዕውቀትና ክህሎት 

አንድ ሰው የጦር መሣሪያ ፈቃድ ለማውጣት ሲፈልግ ከሚኖሩት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ስለመሣሪያ ዕውቀትና ልምድ ያለው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሌሎች አገሮችም ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ ሰዎች ስለሚይዙት የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ዕውቀት ሊኖራው ይገባል፡፡ ፈቃድ ሲሰጥም፣ ልክ እንደ መንጃ ፈቃድ ንድፈ ሐሳባዊ፣ ባሕርያዊና ተግባራዊ ችሎታዎች መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመችውና ያፀደቀችው የናይሮቢ ፕሮቶኮልም ይኼንኑ  ይጠይቃል፡፡ ዜጎችም የሚለማመዱበት ቦታና የሚያሠለጥኑ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል፡፡

በርካታ አገሮች ዜጎች የጦር መሣሪያ አተኳኮስና አጠቃቀም የሚሠለጥኑባቸው ተቋማት አሏቸው፡፡ ዜጎች መሣሪያ መያዛቸው ካልቀረ ስለሚይዙት መሣሪያ ባሕርይ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ከአያያዝ ጉድለትና ከጥንቃቄ ማነስ የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ ልምምድ የግድ ይላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ፕሮቶኮልም ይህ እንዲሆን ግዴታ ይጥላል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ረቂቅ አዋጁ ላይ ‹‹የጦር መሣሪያ አጠቃቀም እንዲሁም በዚህ አዋጅ መሠረት ያለበትን ግዴታ ግንዛቤ ያለው ወይም ትምህርት የሚወስድ ለመሆኑ በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት›› ከሆነ በሚል የተድበሰበሰ አገላለጽ ያልፈዋል፡፡

 ፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት ፈቃድ የሚጠይቀው ሰው፣ ፈቃድ ስለሚጠይቅበት መሣሪያ አያያዝ፣ አቀማመጥና አጠቃቀም አስቀድሞ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ አገሮች (ለምሳሌ እንግሊዝ) የፈቃድ ጠያቂውን መኖሪያና መሣሪያ እንዴት ሊያስቀምጥ እንደሚችል ቤቱን አስቀድመው ይጎበኛሉ፡፡ የቤት ሁኔታን ማረጋገጥና መጎብኘት ቢቀር እንኳን ስለመሣሪያው ያለውን ዕውቀት ለማረጋገጥ የሚያስችል መለኪያ (ለምሳሌ የተግባር ፈተና በመስጠትና በማረጋገጥ) መኖር አለበት፡፡ ‹‹የታመነበት›› በሚል ለሙስናና ለሌሎች አግባብ ላልሆኑ አካሄዶች በር ማበጀትም ነው፡፡ 

ቀላል የጦር መሣሪያና ቦንቦች መያዝ ይፈቀዳልን?

ረቂቅ አዋጁ የጦር መሣሪያ የሚባሉትን ምን እንደሆኑ ወጥ ብያኔ አስቀምጧል፡፡ ‹‹በሚፈነዳ ኃይል አማካይነት ተተኩሶ ጥይት ወይም አሩር የሚያወጣ መሣሪያ…›› ነው  ይላል፡፡ ይኼ ትርጉም ፈንጅና ቦንቦችን ይይዛል ማለት አይቻልም፡፡ የፈንጅም የቦንብም ሥሪት ከትርጉሙ ጋር አይሄድም፡፡ ስለሆነም የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚጠይቅ ሰው በተለይ ቦንብ (በግለሰቦች እጅ እንደሚገኝም ስለሚታወቅ) በፈቃድ ሊያዝ እንደሚቻል ወይም እንደማይቻል መገለጽ ነበረበት፡፡

ሌላው በዚሁ የትርጓሜ አንቀጽ ላይም ሆነ ሌላ ቦታ የጦር መሣሪያዎች አውቶማቲክ የሆኑና ያልሆኑ እንዲሁም በከፊል አውቶማቲክ የሆኑ በሚል በሦስት ከመክፍል ባለፈ አነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያ (small arms and light weapons) በሚል አልከፋፈላቸውም፡፡

እንደሚታወቀው ‹‹አነስተኛ የጦር መሣሪያ›› በመባል የሚታወቁት አንድ ሰው ከቦታ ቦታ ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችሉትን ሲሆን፣ በበርካታ ሰዎች ተሳትፎ ከቦታ ቦታ ሊዘዋወሩ የሚችሉት ደግሞ ‹‹ቀላል የጦር መሣሪያ›› ይባላሉ፡፡ አገሮች በሕጋዊ መንገድ ለዜጎች የሚፈቅዱት አነስተኛ የጦር መሣሪያዎችን ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ የሆኑትን የሚከለክሉ አሉ፡፡

ረቂቅ አዋጁ በዚህ መልኩ ስላልከፋፈላቸው ቀላል የጦር መሣሪዎችን በመያዝ ፈቃድ ማውጣት ስለመቻል ወይም መከልከሉ አልተገለጸም፡፡ የናይሮቢው ፕሮቶኮል ላይ፣ ቀላልና አውቶማቲክ  የጦር መሣሪያዎች በዜጎች እጅ መግባት እንደሌለባቸው ተደንግጓል፡፡

ንብረት ነውን?

በረቂቅ አዋጁ መረዳት እንደሚቻለው የጦር መሣሪያ ባለቤትነት (ግለሰቦች በግዥ ያገኙት ቢሆንም እንኳን) የባለፈቃዱ አይመስልም፡፡ ረቂቁ አንድ ግለሰብ መያዝ የሚፈቀድለት አንድ መሣሪያ እንደሆነ አንቀጽ 7(1) አስቀምጧል፡፡ ከአሁን በፊት ሁለትና ከዚያ በላይ ቢኖረው አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ይህ ሁኔታ ይቀራል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ከግንዛቤ መግባት ያለበት ብዙ ከቦታ ወደ ቦታ በሚዘዋወርበት ጊዜ ሽጉጥ መያዝን ቢመርጥም፣ ለቤቱ ደግሞ ክላሽንኮቭና ሌላ አነስተኛ መሣሪያ መያዝን መምረጡ ነው፡፡ ይህን ዓይነት ሁኔታ ከግምት ሳያስገቡ በአንድ መሣሪያ ብቻ መወሰኑ አፈጻጸም ላይ ሕዝባዊ ቅሬታን ሊፈጥር ስለሚችል እንዲሁም የመሣሪያዎቹን ዓይነት ከግምት ያስገባ ቁጥር መወሰንን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ፣ አንድ ሰው ምን ያህል መሣሪያ መያዝ እንዳለበት ቁጥጥር የማድረግ ግዴታን ፕሮቶኮሉ አስቀምጧል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የጦር መሣሪያን የንብረትነት ሁኔታ ምን እንደሆነ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ለምሳሌ በግዥ የተገኘ ቢሆን ገዥው የባለቤትነት መብት ነው ያለው የይዞታ ነው በአንድ በኩል ባለመሣሪያው ሲሞት ፈቃድ ማግኘት የሚችልና መሥፈርቱን የሚያሟላ ሰው ወራሽ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ያም ሆኖ ግን በውርስም ቢሆን ፈቃድ ሊኖረው ለሚችልና መሥፈርቶቹን ለሚያሟላ እንጂ እንደማንኛውም ንብረት የውርስ አካል ሆኖ ክፍፍል ውስጥ አይገባም፡፡

ረቂቁ ላይ መሣሪያን በግል መሸጥና ማስተላለፍ በግልጽ አልፈቀደም፡፡ ይሁን እንጂ ፈቃድ እንደማይታደስለት ያወቀ ወይም የገመተ ሰው መሣሪያው ለሌላ ፈቃድ ማግኘት ለሚችል ሰው ማስተላለፍ እንደሚችል ስለተፈቀደ ያው መሸጥን ዕውቅና ሰጥቷል ማለት ይቻላል፡፡

ዜጎች በጥረታቸው ያገኙትን ማንኛውም ንብረት የመጠቀም፣ የመሸጥ፣ የመለወጥና የማስተላለፍ መብት እንዳለቸው ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) ላይ በግልጽ አስፍሯል፡፡ የጦር መሣሪያም ቢሆን በራስ ጥረት የተገኘ እስከሆነ ድረስ የንብረት አካል እንዳይሆን የሚያግድ ሕግ የለም፡፡ ግን በሚሸጥበትና ስመ ንብረቱ (ፈቃዱ) ለማዞርና ወደ ሌላ ሰው ለማስተላለፍ የሚቻለው ፈቃድ ሊያገኙ ለሚችሉና የሕጋዊ መንገድ የጦር መሣሪያ ለሚነግዱ ቢሆን ይመረጣል፡፡  

የጦር መሣሪያ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ነው ወይስ የግል (ፈቃድ ያለው) ነው ለመግዛት ከጋራ ንብረት ወጭ ከሆነ በፍች ጊዜ የንብረት ክፍፍል ውስጥ ይገባልን የማይገባ ከሆነ ንብረት የማሸሻ ስልትም ሊሆን ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

የፌዴራል መንግሥትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር...

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...