Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉውስጣችን የማያምንበትን ነገር መቀበል ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ

ውስጣችን የማያምንበትን ነገር መቀበል ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

በአብዛኛው ሰዎች ሐሳባቸውን ለማሳካት ሲፈልጉ በቅድሚያ ያለውን ችግር ይፈታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ነባሩን ችግር በመፍታት ሳይሆን፣ ኃይልን በመጠቀም ሌላ ተጨማሪ ችግር በመፍጠር ከግባቸው ለመድረስ ይጥራሉ፡፡ ‹ነገር ከሥሩ ምንጭ ከጥሩ› የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ካልደፈረሰ አይጠራም ባዮችም በርካቶች ናቸው፡፡

በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮችን እየፈጠርን ነው፡፡ ነገሮች ተሰባሰቡ ስንል ውሉ የጠፋበት ልቃቂት ሆነው እየተተበተቡና እየተወሳሰቡ ይሄዳሉ፡፡ ለመፍትሔ የማይመቹ፣ ለዕርቅ የማይሆኑና ለመስማት እንኳን የማይጥሙ ሆነዋል፡፡ ፖለቲከኞች የግል ጥቅማቸውንና ሥልጣናቸውን፣ እንዲሁም የድርጅታቸውን ፍላጎት ብቻ ማዕከል አድርገው የቅራኔ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ ወጣቶች ደግሞ ትክክለኛውን የአገር ፍቅር የሚያሳያቸው መሪ ስለሌላቸው፣ በለጋ አዕምሮአቸው ትክክል የሚመስላቸውን የተዘበራረቀ አቋም ይይዛሉ፡፡ ሚዲያዎቹ ይጥማል ብለው በሚያስቡት መልክ ችግራችንን በማቅረባቸው፣ ሕዝብና ሕዝብ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልላዊ መንግሥትና በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል መሀል የተፈጠረው አደገኛ አዝማሚያ ከላይ ከተጠቀሱት ወገኖች የሚመነጭ ነው፡፡ የአገራችን ባለሥልጣናት ካለፈው መማር የማይችሉና የፊት የፊታቸውን ጥቅም ብቻ የሚያዩ በመሆናቸው፣ ይኼው እንደምናየውና እንደምንሰማው ለጦርነት የክተት አዋጅ አውጀዋል፡፡ ከሩቅና ከጎረቤት ሳይሆን ኢትዮጵያ በሕወሓት አመራር ሥር እያለች የፈጸምነውን ስህተት በአንድ ትውልድ ውስጥ ልንደግመው ነው፡፡

ከኤርትራ ጋር እንዴት እንደተለያየን እናስብ፡፡ እኛ ከኤርትራ፣ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ እንዴት እንወጡ እናስብ፡፡ በመለያየት ሒደቱ ውስጥ ምን ያህል ግለሰቦችና መንግሥት ምን ያህል ንብረት እንዳጡና እንደወደመ እናስብ፡፡ ተለያይተን በኖርንባቸው ዓመታት በአገሮቹ ላይ የደረሰውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እናስብ፡፡ ይኼ ጦርነት በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ የፈጠረውን ጠባሳና ቀጣናዊ ቀውስ እንዲህ በቀላሉ ምንም ሳንማርበት ከአዕምሮአችን የሚጠፋ አይመስልም ነበር፡፡ ጦርነቱ ታሪክ የሌለው፣ ምክንያት የሌለው በጀብደኞች ውሳኔ የተደረገ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ምንም እንዳልተፈጠረ ያለ አስታራቂና ያለ ድርድር ድንገት በተፈጠረው ዕርቅ፣ በሕዝብ ውስጥ የተፈጠረውን የደስታና የቁጭት ስሜት እናስብ፡፡ ስላላስብነው ግን ምንም አልተማርንበትም፡፡ ስላልተማርንበትም ይኼን አሳፋሪና ትርጉም አልባ ጦርነት ዛሬ በትግራይና በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል መሀል ለመድገም የመጨረሻውን ፊሽካ እየጠበቀን ይመስላል፡፡

ለዚህ ጦርነት እያዘጋጁን ያሉት የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት እንዲካሄድ የወሰኑና የመሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ መሪዎች አሸናፊነታቸውንም ሆነ ተሸናፊነታቸውን በውል የማያውቁና አምነው ያልተቀበሉ ነባር አመራሮች ናቸው፡፡ ከዚህ ስህተት ያልተማርን ከየትና ከምን እንማር? ምንጊዜም የእርስ በርስ ጦርነት መነሻው ጀብደኝነትና የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ የእነዚህ ዓይነት ጦርነቶች መነሻቸው በብሔርና በሃይማኖት ጉዳይ ስለሚሸፈን፣ ኪሳራው ከየትኛውም መደበኛ ጦርነት በእጅጉ እንደሚበልጥ ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ትንሿ ሩዋንዳ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝቧን ጭዳ ለማድረግ ቀናት ብቻ ነው የፈጀባት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ከዓድዋ ድል በኋላ 20 ዓመት ቆይቶ የተከሰተውን የሰገሌ ጦርነት እናስብ፡፡ የሰገሌ ጦርነት ለነፃነት የተደረገ ጦርነት ሳይሆን፣ የወቅቱ ገዥዎች የወሎው ንጉሥ ሚካኤልና የሸዋው ተፈሪ መኮንን (ኃይለ ሥላሴ) የአፄ ምኒልክን ሥልጣን ለመውረስ ሲባል የወሎና የሸዋ ሕዝብ የተጨራረሰበት ነው፡፡ ይኼ ጦርነት ሰገሌ ላይ ከተደረገው የመጨረሻው ጦርነት ቀደም ብሎ መንገድ ላይ በሚኤሶ፣ በቶራ መልስ በአንኮበርና በሌሎችም ሥፍራዎች ግጭቶች ተፈጥረው በርካታ ሕዝብ አልቋል፡፡ በመጨረሻ ሰገሌ ላይ በተደረገ ጦርነት ብቻ የሞተው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥር 15 ሺሕ ሲሆን፣ የቆሰለው ደግሞ 20 ሺሕ መሆኑን መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ ገልጸዋል፡፡

ይኼ ጦርነት ተገቢነት የሌለው፣ በታሪክም ቦታ ያልተሰጠው፣ አሸናፊውም ተሸናፊውም ያልተደሰቱበት፣ ሕዝብና ወታደሩ የተቆጩበት መሆኑን ይኼው ታሪክ ያስረዳናል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ የኢጣልያ ጋዜጠኛ በወቅቱ የሸዋን ጦር መርተው ድል ያስገኙትን ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን ስለሰገሌ ጦርነት እንዲያስረዱት ጠይቋቸው ነበር፡፡ ጦርነቱ ተገቢ እንዳልነበረ የሚያውቁት የጦር መሪ ወንድሞቼን ወግቼ አሸነፍኩ ማለት አሳፍሯቸው የሰጡት መልስ፣ ‹‹የሰገሌው ጦርነት በወንድማማቾች መሀል የተደረገ ግጭት ነው፡፡ ይልቅስ ስለዓድዋው ጦርነት ጠይቀኝና ላስረዳህ›› ብለው የጦርነቱን ታሪክ አልባነት ነገሩት፡፡ ከዚህ ጦርነት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ አንዱ ቤት ለቅሶ ሌላው ቤት ዕልልታ ይሰማ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ይኼ የሆነው የሟችም የገዳይም ወገን አብረው ስለሚኖሩ ነው፡፡ የታሪኩ ጸሐፊም ይህ ጦርነት ለታሪክ የሚበቃ እንዳልሆነና መጻፍም የማይገባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን የወደፊቱ ትውልድ እንዲማርበት ብለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ በጦርነት ታሪኳ እጅግ የምትኮራበት የዓለምንም ሕዝብ ያስደመመ፣ ለሰው ልጆች ነፃነትና ለዓለም ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ የፈጠረው የዓድዋ ጦርነት ነው፡፡ የዓድዋ ጦርነት መሪዎች የተወደሱበት፣ ሕዝቡ አንድነቱንና አይበገሬነቱን ያሳየበት፣ ተገቢና በዓለም ታሪክ ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ ያገኘ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 7,500፣ የቆሰሉት ደግሞ 10,000 እንደሆኑ ታሪክ ያስረዳል፡፡ የታሪክ ሚዛኑን ትተን ያለቀውን ሕዝብ ከውስጥ ግጭቶቻችን ጋር እንመዝነው፡፡ ሰገሌ ላይ የሞተው ሕዝብ 15,000፣ የቆሰለው 20,000 ነው፡፡ ከዓድዋ ጉዳት በዕጥፍ የበለጠ ነው፡፡  በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በድምሩ ከመቶ ሺሕ ሠራዊት በላይ እንደሞተ ይነገራል፡፡ ከዓድዋው በ15 ዕጥፍ ይበልጣል፡፡ ሕወሓት ከደርግ ጋር ባደረገው ጦርነት ከእነሱ ወገን ብቻ 60,000 ወጣቶቹ እንደተገደሉ ገልጿል፡፡ ከዓድዋው ጋር ሲነፃፀር ስምንት ዕጥፍ ነው፡፡

ከዚህ መረዳት የምንችለው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪኩ ትንሽ ዕልቂቱና ኪሳራው ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ነው፡፡ እኛ ግን ይኼን ሁሉ ረስተን ከኢትዮ ኤርትራ ዕልቂት ወዲህ በተፈጠሩት ታዳጊዎች የሞት ድግስ እያሰናዳንላቸው ነው፡፡ አሁን ለመቀስቀስ ጥረት በምናደርገው ጦርነት የትግራይ ልጆች ድል ከቀናቸው ‹‹ዘራፍ አማራ ገዳይ፣ ኦሮሞ ገዳይ . . .›› ብለው ሌሎች ደግሞ ሲቀናቸው፣ ‹‹ዘራፍ ትግሬ ገዳይ›› ብለው እንዲፎክሩ ነው ጥረታችን፡፡ ወጣቶቹ አንገት ላይ የጦረኛ ምልክት ብለው ያመኑበትን ፎጣ ጠምጥመው ክላሽ አስጨብጠው በቴሌቪዥን ብቃትን ለማሳየት መሞከር ነውር ነው፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ሕዝባችን የደረሰበት ሰብዓዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ እሴቶቻችንና ሰብዓዊ ክብራችን ሁሉ ነው የጠፋው፡፡ መንፈስ ልልነት፣ አድርባይነት፣ ስግብግብነትና ቁሳዊ ፍላጎታችን ነው በየጊዜው እያደገ የሚሄደው፡፡ በአግባቡ ለመመራት ያልተዘጋጀ ጋጠወጥ ሁሉ ያለ ችሎታው አገርን ካልመራሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ነው፡፡

ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በትግራይና በሌሎች መሀል ለጦርነት የሚያበቃ ምን ምክንያት አለ? ወይስ እንደ ሰገሌው ጦርነት የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄን በሌላ ለመሸፈን ነው? እንደ ሕወሓት ገለጻ ከሆነ ለጦርነት ምክንያት ይሆናል ብሎ ከሚናገረው አንዱ የሕገ መንግሥት መጣስ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ከወጣበት ዕለት ጀምሮ አንድ ቀን ያልተጣለበት ጊዜ እንደሌለ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ አንድ ፖሊስ አንድን ዜጋ ሲመረምር በጥፊ እንኳ ከመታው ሕገ መንግሥቱን መጣሱ መታወቅ አለበት ይኼና ከዚህ የገዘፉ ጥሰቶች ናቸው የነበሩት፡፡ ያኔ ይፈጸም የነበረ ጥሰት መደገም አለበት፡፡ ማለት ስህተት ቢሆንም፣ ስህተቱን በጦርነት ለማረም መዘጋጀት የሞራል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እኛ ስንፈጽመው የኖርነውን በሌሎች ሲፈጸም መታገልና ማረም የሚገባ ቢሆንም፣ ሌላ ምክንያት ከሌለ ለጦርነት የሚያበቃ አይደለም፡፡ ይህ ጦርነት ከተጀመረ ልክ እንደ ሰገሌው፣ እንደ ኢትዮ ኤርትራና እንደ ደርግ ጦርነት ታሪክ አልባ፣ ግብ የሌለው፣ ውጤቱና ጥቅሙ የማይታወቅ ዕልቂት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራም መለያየታችን አይቀርም፡፡ ልክ እንደነዚህ አገሮች መፀፀታችን አይቀርም፡፡ ልክ አንደ ኢትዮ ኤርትራ ከረዥም የመከራ ዘመናት በኋላ ኬላ ጥሰን፣ ምሽግ ደርምሰን ተከዜና አላማጣ ላይ ተንጋግተን እየተላቀስን መገኘታችን አይቀርም፡፡ በዚያን ወቅት አሁን ይኼንን ጦርነት በጥብቅ የሚፈልጉ ሰዎች ስለማይኖሩ አፅማቸውን የሚወቅስ ሌላ ትውልድ ይፈጠራል፡፡

ጉዳያችን ብዙ ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት እኛን ለማጨራረስ የተሞከረው ሁሉ፣ በተፈለገው መጠንና ዓይነት ሊሳካ አልቻለም፡፡ አሁን ሌላው በአማራጭነት ለመሞከር እየታሰበ ያለው ሁከቶቹን ወደ ከተማ ማዛወር ነው፡፡ በለገጣፎ፣ በአዲስ አበባ፣ በጎንደርና በሌሎችም እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ቀደም ሲል ከነበረው የተለየ ሁኔታ ሳይኖር የጥፋት ፕሮፓጋንዳ እየተካሄደ ነው፡፡

ሰሞኑን በለገጣፎ ከተማ የዜጎች መኖርያ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተፈጸመ ነው፡፡ ሕገወጥ ቤቶች ተሠርተው ሕገወጥ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ የአሁኑ የማፍረስ ውሳኔ ትክክለኛ ስለመሆን አለመሆኑ በችኮላ ባንናገር ይመረጣል፡፡ መንግሥትን የሚያስተቸው ነገር ቢኖር አሁን አገሪቱ ሰላም ባጣችበትና እንቅስቃሴው ሁሉ ሰላምን የሚፈጥርና ሕዝብን የሚያቅፍ መሆን ሲገባው ወደዚህ የጭካኔ ተግባር ለምን ገባ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሕገወጥነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ጊዜ ቢሰጣቸው ምን ጉዳት አለው? ታዲያ ዛሬ ይኼ የተለመደ ተደጋጋሚ ችግር ለምን ግነቱ ከልክ አለፈ?

በሌላ በኩል ደግሞ ስናየው በመጀመርያ ደረጃ ሥፍራው ሕገወጥ ነው፡፡ በመቀጠል እስከ ዛሬ ድረስ ሲደረግ እንደነበረው አሁንም መንግሥት ሁሉን ነገር ይቅር ብሎ ወደ ሕጋዊነት ቢያስገባቸው፣ ተመሳሳይ የመሬት ወረራ መጨረሻውና ማቆሚያው የት ነው? በዚህ ዓይነት ሕጋዊነትን ለማግኘት ሕገወጥ መሆን ሊያስፈልግ ነው፡፡ ወረራው አሁንም በያለበት ቀጥሏል፡፡ መሬትን ያህል ንብረት ባለቤት እስከሌለው ድረስ ይኼ ወንጀል ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ ሌላው በጥልቀት ሊታሰብበት የሚገባው እነዚህ ሕገወጦች በዘፈቀደ ሄደው የሚሠፍሩበት ቦታ ከቀድሞ ጀምሮ ጠፍ የነበሩ ቢሆኑም ባለቤት አልባ አልነበሩም፡፡ እነዚህ ሁሉ ቦታዎች ቀደም ሲል ባለመብት የነበሩ ነዋሪዎች የነበሩበት፣ መንግሥት እነሱንም ኃይል ተጠቅሞ ያነሳቸውና ሜዳ ላይ የተበተኑ ናቸው፡፡ ታዲያ እነሱ ከሕጋዊ ይዞታቸው ተነቅለው ሌሎች ሕገወጦች ሲተከሉ የሚያየው ነባር ሕዝብስ ምን ይበል? አሁን ስለፈረሱት ቤቶች የሚያንገበግባቸው ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች የነባሮቹ ነዋሪዎች ቤቶች ሲፈርሱ ምነው ዝምታን መረጡ? አንዱን ተቃውመን ተመሳሳዩን ለምን ረሳን?

መቃወም መብት ሆኖ ለነገሮች የሚሰጡዋቸው ፍቺዎች ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ ናቸው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ትንሽ እንኳ ሳያቅማማ በአደባባይ ሕገወጦችን መደገፍ ነውር ነው፡፡ አንድ የኢሳት ጋዜጠኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን ባስተላለፈው መልዕክት፣ መንግሥት ቤቶቹን የሚያፈርሰው ሰፋሪዎቹን አስነስቶ ቀደም ሲል ለነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች መሬቱን ለመመለስ ነው ብሏል፡፡ ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመርያው ምክንያት በቅርቡ በሚካሄደው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ የኦሮሞን ሕዝብ ቁጥር ለመጨመር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመጪው ምርጫ ተጨማሪ ድምፅ ለማግኘት ነው ብሎ በድፍረት ተናግሯል፡፡ ለዚህ ዘገባው ምንጩን አልጠቀሰም፡፡ በምን አመክንዮ እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡

ቀደም ሲል ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ሰዎች በሕይወት እስካሉ ድረስ የትም ቢሄዱ መቆጠራቸው ስለማይቀር፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የቁጥር ለውጥ ማምጣት አይችሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች ተፈናቅለው የሚኖሩት በዚያው አካባቢ ስለሆነና አገር ለቀው ያልሄዱ በመሆናቸው፣ እንዴት ነው ተጨማሪ ሕዝብ ሆነው ምርጫው ላይ ልዩነት የሚፈጥሩት? እንደነዚህ ያሉ አደገኛ የፈጠራ ወሬዎችና የተንኮል ጥንስሶች በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መሀል እተጠናከረ የመጣውን የአንድነት መንፈስ ለማላላትና ለማጋጨት መንገድ እንደ መጥረግ ይቆጠራል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ይችን ያህል እንኳን ትንፋሽ ያገኘነው በሁለቱ ብሔሮች መሀል በተፈጠረ አዲስ ልባዊ ግንኙነት መሆኑን አንርሳ፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን የለገጣፎ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ቤታቸውን በላያቸው ላይ ማፍረስ ቀደም ሲል በነባሮቹ ላይ የተፈጸመውን የጭካኔ ተግባር መድገም ስለሚሆን፣ ለጊዜው ባሉበት ቆይተው ለዘለቄታው ግን ሌላ መፍትሔ ቢፈለግላቸው የተሻለ ይሆናል፡፡ በአገሪቱ ላይ የሚሸረበው ሴራ ለገጣፎን አልፎ አዲስ አበባ እንዲገባ ሴረኞች የተቻለውን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡

ዛሬ አዲስ አበባ መልስ የማይገኝለት ጥያቄ እየተጠየቀች ነው፡፡ አዲስ አበባ የማናት የሚለው ጥያቄ ዛሬ ለምን እንደተነሳና ማን ሊመልሰው እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ይህን ጥያቄ ያነሱ ብዙ ወገኖች ናቸው፡፡ የእነዚህ ጠያቂዎች ዓላማቸው ምን አንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ይኼ አደገኛ ጥያቄና አካሄድ አዲስ አበባ ከዓለም አገሮች ዋና ከተሞች ሁሉ የተለየች ሆና ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ አገሪቱን በፍጥነት ለማፍረስ የተጠነሰሰ ሴራ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በፊትና በኋላ የተፈጠሩት እነ ዋሽግተን፣ ለንደን፣ ሮምና ሞስኮ የማን ናቸው? እዚህ በቅርባችን ያሉት ዋና ከተሞች ናይሮቢ፣ ካርቱም፣ ካይሮና ሌሎች የማን ናቸው? እነዚህ ሁሉ ከተሞች ዓለም ሲፈጠር የነበሩ ሳይሆኑ፣ ልክ እንደ አዲስ አበባ የገጠሬዎች መኖርያ የነበሩና በሒደት ባለአገሮቹ (Indigenous) ነዋሪዎቹ በሌሎች ተውጠው ወይም ለቀዋቸው የተመሠረቱ ከተሞች ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ከተሞች የእኔ ናቸው ይመለሱልኝ የሚል በሌለበት ዓለም እንዴት እኛ ብቻ ተለይተን የተለየ ጥያቄ እናነሳለን? እነዚህ የውጭ አገር ተሞክሮዎችስ ለእኛ የሚያስተምሩን ነገር የለም? ምንስ ቢሆን እኛ ኢትጵያውያን እንደ እነዚህ ያሉ ለዓለም እንግዳ የሆኑ ትርክቶች እየፈጠርን ግምት ውስጥ መግባት የሚገባን ሕዝቦች ነን? በዚህ ጉዳይ ጦር የምንማዘዝ ነን? አሁን እኮ የፖለቲካችን ጡዘት ሄዶ ሄዶ አዲስ አበባ የሚል ክልልና አዲስ አበቤ የሚል አዲስ ብሔር ለመፍጠር እየዳዳው ነው፡፡ አሁን የአዲስ አበባ የኦሮሞ ወጣቶች ማኅበር ተቋቁሟል፡፡ ነገ የአማራ፣ የወላይታ፣ የትግሬ . . . የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር የሚል ላለመቋቋሙ መተማመኛ የለንም፡፡ የመደራጀት መብት እንኳ ቢኖር አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ መግባት ነበረበት፡፡ ይኼ አደረጃጀት አዲስ አበባን ለማፅዳት፣ መሠረተ ትምህርትን ለማስተማር፣ ለልማት ሥራ ወይም የአዲስ አበባን ሰላም ለማስከበር አይደለም፡፡ የፖለቲከኞችን አቋም ተደራጅተው እንዲደግፉና እንዲያሳኩ ብቻ ነው፡፡

ተወደደም ተጠላ አዲስ አበባ በኦሮሚያ እንብርት ላይ የተፈጠረች የብሔር ብሔረሰቦች ከተማና መኖርያ ነች፡፡ ኅብረ ብሔራዊነቷና ዓለም አቀፋዊነቷ እንደ ሌሎች ተመሳሳይ የዓለም ከተሞች ራሷን ችላ በራሷ የምትተዳደር የፌዴራል ዋና ከተማ ያደርጋታል፡፡ የኦሮሚያም ዋና ከተማ ናት፡፡ ሁሉም በሕጋዊነትና በእኩልነት ሊኖርባት ይገባል፡፡ ሌላ ተሞክሮ ካለ ምሁሮቻችን የት ናችሁ? ለመቼስ ልትሆኑን ነው? በአሁኑ አያያዛችን ከቀጠልን እስቲ የከርሞ ሰው ይበለንና በምርጫው ወቅት ምን እንደምንደራረግና ምን እንደምንባባል ለማየት ያብቃን፡፡ እንዲህ ዓይነት በሴረኞች የሚፈጠር የመሳሳብ ፖለቲካ አንዱ ሲከሽፍ በሌላ የሚሞከር መጨረሻ የሌለው ነው፡፡ ትልቅ ሕዝቦች ነን፡፡ የትልቅ አገር ባለቤትና ባለአደራ ነን፡፡ ለትልቁም ለትንሹም ነገር ቸኩለን አተካራ አንፍጠር፡፡ ለልጆቻችን ማስተማር የሚገባንን በጎ በጎ ነገር ትተን አዕምሮአቸውን በጥላቻና በበቀል አንተብትበው፡፡

የብሔር ፖለቲካን አጠቃቀሙን ባለማወቃችን ያሳደረብን አሉታዊ ንቃተ ኅሊና ወደ አደጋ እየመራን ነው፡፡ አሁን ያለን አማራጭ ለጊዜውም ቢሆን ይኼ ብቻ መሆኑ ግልጽ እየሆነ ስለመጣ፣ አወቃቀሩንና አደረጃጀቱን እንደገና መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ ኦዴፓ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ፓርቲው ወደፊት የሚከተለው የብሔር ፌዴራሊዝምን እንደሆነ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ለድርድር የማይቀርብ ነገር መሆኑ አልገባን አለ እንጂ፣ ይዞት የቆየውን አቋም ማስቀጠሉ አዲስ ነገር አይሆንብንም፡፡ የቲም ለማን አቋም ስንገመግመው ነገሩ ግር የሚለን አንጠፋም፡፡ ምንጮቹ አንዳንዴ ይፈታተናሉ፡፡ ውስጣችን የሌለን ነገር መቀበል ግድ የሚሆንበትም ጊዜ አለ፡፡ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፣ አንድ አጥባቂ የኦርቶዶክስ አማኝ መንገድ ሲሄድ እጅግ ይርበውና የሚበላ ነገር መፈለግ ይጀምራል፡፡ ምንም ሰው በሌለበት አካባቢ ወደ አንድ ቤት ጎራ ብሎ የሚቀመስ ነገር ይለምናል፡፡ የቤቱ ባለቤት ጆሮዋ የማይሰማና የማትናገር ስለሆነች፣ በግራ እጁ ሆዱን እያሻሸ በቀኝ እጁ የጉርሻ ምልክት እያሳየ ይለምናታል፡፡ ሐሳቡ የገባት ሴትም ቶሎ ብላ በአንድ ሳህን የተከሸነ የሥጋ ወጥ፣ በሌላ ሳህን እንደ ነገሩ የሆነ ሽሮ ከጭልፋ ጋር የታጠፈ እንጀራ ጎን አስቀምጣለት ወጣች፡፡ ሰውየውም በሥጋው ወጥ ተደስቶ ሊበላው አሰበና ቀኑ ረብዕ ይሁን ሐሙስ አልመጣለት አለ፡፡ ለማስታወስ ቢሞክርም አቃተው፡፡ የሥጋ ወጡን ቢበላ የመሳሳት ዕድል መኖሩን አሰበና ቢመገበው ምንም ችግር የሌለውን ሽሮ ተመገበ፡፡ ትክክለኛ አማኝ ስለሆነም የሚፈልገውን ነገር ትቶ ያልፈለገውን፣ ነገር ግን ለመምረጥ ግድ የሆነውን መረጠ፡፡

 በብሔር ላይ የተመሠረተውን ፌዴራሊዝም ሕዝቡ አውቆት፣ ተወያይቶበትና ፈቅዶ የተቀበለው አይደለም፡፡ የአንድ ወቅት የፖለቲካ አየራችን ወልዶ እዚያ ላይ ጥሎናል፡፡ ነገር ግን የተቀበልነው አስተሳሰብ በውድም ይሁን በግድ ሕዝቡ ውስጥ ሥር ስለሰደደ፣ በአሁኑ ጊዜ እንዲህ በቀላሉ የምናስወግደው አይደለም፡፡ በተለይም በኦሮሚያና በትግራይ፣ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ውስጥ የአዲሱ ትውልድ መሠረታዊ እምነት ስለሆነ በአገራችን እንደ አንድ ዋነኛ አማራጭ የሚታይ ነው፡፡ ሌላው በሕዝብ ዘንድ በተለይም በምሑራን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያለው የዜጋ ፖለቲካ የሚባል ነው፡፡ ይኼ አማራጭ በአሸናፊነት መውጣት የሚችለው ምሁራኑ አዲሱን ትውልድ አስተምረው በማሳመን ተቀባይነት እንዲያገኝ ካደረጉ ብቻ ነው፡፡ አብዛኞቹ ምሁራን ግን ከወጣቱ ጋር ትግል ገጥመው ለመመለስ የማይሞክሩ ብቻ ሳይሆን ባያምኑበትም ወጣቱን ተከትለው እየነጎዱ ነው፡፡

እንግዲህ ኦዴፓ በፍስግ ቀንም በፆም ቀንም ሊመገበው የሚችለውን የፆም ምግብ መርጧል፡፡ ይኼን የሽግግር ጊዜ በሰላም ለማለፍና ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድም የወሰደው አቋም ትክክል ነው፡፡ መንግሥታችን በበጎ መንፈስ ተነሳስቶ እየሄደበት ያለው አቅጣጫ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን ካሉብን ችግሮች ብዛትና ዓይነት የተነሳ ያለ በቂ አማካሪ የሚወጣው አይደለም፡፡ አማካሪ ስንል የግድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዶክተርና ፕሮፌሰር ማለት አይደለም፡፡ ለአገራቸው ሰፊ ራዕይ ያላቸው የሕዝብን ታሪክና ባህል ጠልቀው የሚያውቁ፣  ካለፈው ተሞክሯቸው የወደፊቱን የሚተነብዩ በርካታ ዜጎች አሉን፡፡ የመንግሥት መሪ የግድ አዋቂ አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ መሠረቱ የራስ ሆኖ የሰው ምክርን መስማትም ተገቢ ነው፡፡ ያለበለዚያ አሁንም በምንጓዝበት መንገድ ሩቅ ልንሄድ አንችልም፡፡

ፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያችንም ያለበትንም ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ለልማቷና ለሰላሟ ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ለግለሰቦችና ለቡድኞች ጥቅም ነው፡፡ አገሪቱ መድኃኒት መግዣ አጥታ ከቱሪስቶችና ከግለሰቦች የተለቃቀመ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በጆንያ እየተጫነ በየቀኑ ከአገር ይወጣል፡፡ ወደ ውጭ የተላኩ ጥሬ ዕቃዎች ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ማስገባት አልቻሉም፡፡ በሌቦች መረብ ተጠልፈው እዚያው ይቀራሉ፡፡ በአጋጣሚ ወደ አገር ውስጥ የገባችው የውጭ ምንዛሪም ሌቦች ባሰማሩዋቸው ግለሰቦች ከገበያ እየተለቀመች በጓሮ በኩል ትወጣለች፡፡ ወጣቶቻችን ሥራ አጥተው ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ሾልከው ይሰደዳሉ፡፡ አገራችን ደግሞ የሌሎች አገር ስደተኞችን ያለገደብ አስገብታ መሬትና ሥራ ልትሰጣቸው ሕግ አውጥታለች፡፡ ምዕራባውያን የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞች ትልቅ ራስ ምታት ስለሆኑባቸው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰምጠው እንዲቀሩ አሳምነውናል፡፡ አሁን የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ . . . ወዘተ ስደተኞች በየቀኑ ወደ እኛ እየጎረፉ ነው፡፡ መታወቂያም በቀላሉ እየታደላቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ ብቻ አምላክ የሚበጀንን ያምጣልን፡፡ እኛማ አልቻልነውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...