Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየምርጫ ቦርድን ትኩረት የሚሻው ሌላው ዓብይ ጉዳይ

የምርጫ ቦርድን ትኩረት የሚሻው ሌላው ዓብይ ጉዳይ

ቀን:

በተስፋዬ ጎይቴ

አገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ከልባችን የምንደግፈውና ልናግዝ በፅናት የተነሳሳነው በውስጡ ምንም ዓይነት ችግር ስለሌለው አይደለም። አባጣ ጎርባጣ፣ ውጣ ውረድ፣ መውደቅ መነሳት፣ ሕይወትና ሞት የተቀላቀሉበትና ስንክሳር የበዛበት መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ነገር ግን በማናቸውም መሥፈርት ቢለካ አንድ፣ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ፣ በጆሮ የሚሰሙ ብቻ ሳይሆኑ በዓይን የሚታዩ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች በየቀኑ ህያው እየሆኑ መጥተዋል። ማንም በፈለገው መንገድ ሊተረጉመው ይችላል። ይሁንና ከህሊናው ጋር ያልተጣላ ሁሉ በማሳያ ሊገለጥለት የቻለ መሠረታዊ ለውጥ አለ። በኢትዮጵያ ሰማይ ጥላ ሥር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ወዘተ. ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ሁለንተናዊ ለውጥ በየቀኑ ይታያል። ጉዳዩ ግን ለውጡ በየቀኑና በየሰዓቱ፣ በየክልሉና በየብሔረሰቡ እንደ ኩይሳ በርካታ ችግሮች እየሰፈሩበት፣ ሺሕ ጋሬጣዎች እየተጋረጡበት፣ ቀፍድደው ይዘው አላራምድ ያሉ ተውሳኮች እየበዙበት መጥቷል። ይህም ሆኖ ግን ምልዓተ ሕዝቡ የደገፈው ለውጥ ስለሆነ ግስጋሴው ለአፍታም አልተገታም። የለውጥ መሠረት እየተጣለላቸው ካሉት ዓበይት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው መጪው ምርጫ ስለሆነ፣ አንዳንድ ትኩረት የሚሹ መሠረታዊ ጉዳዮችን መጠቆሙ ወቅታዊና ተገቢም ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

መጪው ምርጫ እንደከዚህ በፊቶቹ ከቃላት ባለፈ ፍፁም ተዓማኒ፣ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ፈርጀ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታያል። አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መሠረታዊ ልዩነቶቻቸውና ፕሮግራሞቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው ቢያንስ የጋራ አገራችንን ወደ ተሻለ ዓውድ እንዴት እናሸጋግር በሚለው ዓብይ ጉዳይ ላይ በበቂ ሁኔታ ተቀራርበው መነጋገር ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። መነጋገር ብቻ አይደለም። በተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ መቀራረብም ይታያል። ይህ አበረታች ጅምር ነው። ጅምር ግን ፍፃሜ አይደለም። ብዙዎቹ ፓርቲዎች ውጤት ሲርቃቸው በምርጫ ቦርድና በገዢው ፓርቲ ከማሳበብ ወይም ያልሆነ ሰበብ ከመፍጠር ለሩጫው እኩል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በሌላ ማላከክ ከእንግዲህ መቆም አለበት። እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የመሮጫው ሜዳ የበለጠ ፍትሐዊና ምቹ እንዲሆንም በጋራ መታገል ያስፈልጋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገር አቀፍም ሆነ በየደረጃው በሚከናወኑ የምክር ቤቶች ምርጫዎች ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓትን እንከተል? አሳታፊነትን እንዴት እናጎልብት? ተዓማኒነትን ልናረጋግጥ የምንችለው በምን መንገድ ነው? የሚሉ አንኳር ጉዳዮች እየተነሱ እየተንሸራሸሩ ናቸው። በየመድረኮቹ ሁሉም ዘንድ የሚታዩት የፖለቲካ ብልጣ ብልጥነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው። ምንስ ቢሆን የፖለቲካ ሥልጣን አይደል? ብልጣ ብልጥነት አይኖርም ተብሎ እንዴት ይጠበቃል? ምንም ይሁን ምን ግን ትልቁ ጉዳይ በደንብ እየተሄደበት ይመስለኛል።

ይሁንና የተከበረውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን፣ የፍትሕ መዋቅሩን (በምርጫ ሒደት ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን የሚያዩት መደበኛ ፍርድ ቤቶች ስለሆኑ ማለት ነው)፣ መገናኛ ብዙኃንን (በምርጫ ሥርዓቱ አካሄድ ላይ ተኪ የሌለው ሚና ስላላቸው)፣ ዋናው ባለቤት የሆነውን የምርጫ ቦርዱን ጨምሮ በዚህ ወቅት ትልቅ ትኩረት የሚሻው ሌላው ጉዳይ ግን የተቋማዊ አደረጃጀቱና አሠራሩ ጉዳይ ነው። አደረጃጀት ሲባል የምርጫ ዝግጅት ሲጀመር የሚፈጠረውን ረጅም ሰንሰለት ያለው ጊዜያዊ አደረጃጀት፣ በቋሚነት እየሠራ ያለውን መዋቅርና የሰው ኃይል ማለት ነው። የሚፈጠረው የአሠራር ሥርዓት ከድምፅ መስጫ ጣቢያዎች (Polling Stations) ጀምሮ፣ የእያንዳንዱ ተመራጭ ውክልና የሚገለጽባቸው የምርጫ ክልሎች (Constituencies) በመላ አገሪቱ ሲመሠረቱ ተዓማኒ፣ ነፃና ገለልተኛ የሚለው የምርጫ መርህ ከዚህ መጀመር አለበት። ዋናው የምርጫ ቦርድ ወይም አገር አቀፉ ጽሕፈት ቤት በእንዶድ እንደታጠበ ሸማ ሺሕ ጊዜ ታጥቦ ንፁህ ቢሆን ይህ ብቻውን ፋይዳ የለውም። ምርጫው የጋራ የቤት ሥራ ውጤት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት (በደርግም በኢሕአዴግም) የተካሄዱት አገር አቀፍና የክልል ምርጫዎች ሰፋፊ ነገሮችን አስተምረውን አልፈዋል። በየደረጃው የተመደቡት በርካታ የምርጫ አስተባባሪዎች ገለልተኛ ናቸው እየተባለ ተመልምለው ከተመደቡ በኋላ፣ ምን ሲሠሩ እንደቆዩ በምርጫዎቹ ሒደት ውስጥ በአስፈጻሚነት ተሳትፈን በቅርብ ያየነው እናውቀዋለን። ገዥው ፓርቲ በተፎካካሪዎቹ በራሳቸው የስትራቴጂ ስህተት የተነሳ ንቋቸውም ይሁን ፈርቷቸው ጢቢጢቢ ሲጫወትባቸው ቆይቷል። በመጪው ምርጫ ይህ የቆሸሸ አካሄድ በፍፁም ሊታይ አይገባው፣ ሊሞከርም አይችልም። አስቀያሚው ድርጊት ከተፈጸመ ደግሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አበቃለት፣ ዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመሩትም ለውጥ ዶጋ አመድ ሆነ፣ አገራችንም ተመልሳ አደጋ ላይ ወደቀች ማለት ነው። ከዚህ ይሰውረን።

በተለይ በምርጫ 97 ከኢሕአዴግ በተሻለ መራጩን ማርከውት የነበሩና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የነበራቸው የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግንባር ቢፈጥሩ ኖሮ በርካታ (የበለጡ) መቀመጫዎችን ከገዥው ፓርቲ መዳፍ መንጠቅ፣ የውጤቱን አኪር ወደ ራሳቸው ማዞር ይችሉ ነበር። ኢሕአዴግ የቀመመላቸውን መርዝ ቀምሰው እንደ አይጥ ወዲህና ወዲያ ሲቅበዘበዙና በራሳቸው ግማሽ ሜዳ ላይ እርስ በእርሳቸው ግብግብ ገጥመው፣ ሁሉም ፓርቲዎች ለገዥው ፓርቲ ሜዳውን በቀላሉ ለቀውለት ወጡ። ለኢሕአዴግ ሠርግና ምላሽ ሆነለት። ለሕዝባችን ደግሞ መከራ ተረፈው። ከዚህ የተነሳ የስትራቴጂ ስህተቶቹ ለነገው ምርጫ ብዙ ነገር አስተምረውናል ብዬ አስባለሁ። የተመለከትነው ዓይነት ክስተት የተፈጠረው በኢሕአዴግ የሥልጣን ስግብግብነትና ንፉግነት የተነሳ ብቻ ሳይሆን፣ በተፎካካሪዎቹ ድክመት ጭምር መሆኑ አይካድም። ከሌሎች ውድቀት መማር ካልተቻለ ከራስ ኪሳራ መማር ደግሞ የግድ ነው። አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲም ጋር ይሁን እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት ፉክክርና ውድድር አሁን አሁን ጨዋታው በደንብ እየገባቸው የመጣ ይመስለኛል። የበለጠ ሊገባቸው ግን ይገባል።

የዚህ ጽሑፍ አንዱና ዋነኛው አትኩሮት ደግሞ የምርጫ አፈጻጸም ሥርዓቱ ትልቁ ክፍተት ያለው ታችኛው መዋቅር ላይ መሆኑን ማሳየት ነው። በየደረጃው ተመልምሎ በሚመደበው የምርጫ አስፈጻሚ ሠራዊት ገለልተኝነት ላይ እንዴት ሊኬድበት ታስቧል? አስፈጻሚዎቹ በገዥው ወይም በአጋር ፓርቲዎች ተመልምለው፣ ፓርቲው እንደ መንግሥት ሆኖ በጠራው “የሕዝብ” ስብሰባ ተገምግመዋል ተብለው በመራጩ ሕዝብ “ዓመኔታ” ያገኙ እንደሆኑ በማስመሰል፣ የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚነት ሎቲ ተንጠልጥሎላቸው ለዓመታት በዴሞክራሲ ሥርዓቱ ላይ አክሳሪ ቁማር ሲጫወቱ ኖረዋል። ያኔ “እኔን ምርጫ ያድርገኝ . . . እኔን ይቦርድደኝ . . .” እየተባለ የነበረውን ስላቅ እናስታውስ።

ውድ አንባቢያን! የሚገርማችሁ ነገር የእገሌ ክልል ወይም ዞን የምርጫ ኃላፊ ገለልተኛ ያለመሆኑ ተረጋገጠ ተብሎ ተጨባጭ ማስረጃ እንኳን ቢቀርብበት ማን ሊቀበል? ውዝግቡ በጣም ከባሰም ሽፋን የሚሰጥለት የፖለቲካ ድርጅት ስላለ ከምርጫ ቦርድ መዋቅር ተነስቶ ዕንቁ የሆነ የፓርቲ/የመንግሥት ሥልጣን ምን ከመሰለ መኪናና ቤት ጋር ይሰጠዋል። ትናንት የፓርቲ ሹመኛ የነበረን ሰው ወደ ምርጫ ቦርድ መዋቅር አምጥቶ ሳይሳካ ሲቀር፣ ለእኛ ብለህ መስዋዕትነት ከፍለሃልና ሜዳ ላይ ወድቀህ አትቀርም ተብሎ ሌላ ሹመትና ሽልማት ይሰጠዋል። ምርጫው ተጭበርብሯል፣ ኮሮጆ ተገልብጧል፣ ድምፅ ተሰርቋል ቢባል ማን ሊሰማ? ያው የተለመደው የተቃዋሚዎች የሽንፈት ጩኸትና ማላዘን ነው ተብሎ ይታለፋል። ከአዲስ አበባችን ተነስተን ወደ አራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ብንጓዝ ይህ ትዕይንት ነበረ። አንዱ ክልል ከሌላኛው የከፋ ቢሆንም ችግሩ ያልነበረበት ክልል እንደሌለ በዚህ ተውኔት ውስጥ ያለፍነው ሁሉ እናውቀዋለን። ኃጢያትን መናዘዝ ደግሞ ለሰማይም ለምድርም ይጠቅማል። እንዲያውም አንዳንዴ ታችኞቹ የፈጸሙትን ጥፋት ላይኞቹ ለማረም ከአቅማቸው በላይ የሚሆንበት ጊዜ ነበረ። የማስረጃ ደብዛ በማጥፋት ከኢሕአዴጎች የሚፈጥን እንደሌለ ተምረናል።

በዚህ ጽሑፍ የምርጫ ቴአትሮቻችን ደራሲና ዳይሬክተር የነበረው ገዥ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ የተዘረጋውን ሥርዓት በመጠቀምና የምርጫ አስፈጻሚዎቹን የቴአትሩ ተዋናይ በማድረግ፣ በየደረጃው ባሉት መዋቅሮቹ የሠራቸውን ህፀፆች በእዚህ ቀን እዚህ ቦታ በማለት ለአብነት ያህል ብጠቅሳቸው ደስ ባለኝ። ግን ጥሩ አይመጣም። ከሥነ ምግባርም ውጪ ነው። ለተቋሙ ክብርና ታሪክም አይመጥንም። በዚህ ላይ ደግሞ ያኔ በመዋቅሩ ላይ የነበሩትና በምርጫዎቹ መዛባት ቀዳሚውን ሚና ሲጫወቱ የኖሩት በየደረጃው የተሰለፉ ብዙዎቹ አመራሮች ዛሬ ስለሌሉ “ሙት ወቃሽ” መሆን አልፈልግም። ነገር ግን ድምፅ ልትሰጡ ወደ ምርጫ ጣቢያ ስትሄዱ አስመራጮቹ ይኼ ንብ፣ ይኼ ምናምን ነው ብለው የምርጫ ምልክቶቹን ሲያሳዩዋችሁ ምን ምን ያደርጉ እንደነበረ በመራጭነት የተሳተፋችሁ ሁሉ ህያው ምስክሮች ናችሁ። የዚያን ዓይነቱ የተዛባ አካሄድ ከዚህ በኋላ በዚህች የተቀደሰች ምድር ላይ ከቶም አይደገምም። በዚህ ዴሞክራሲ ፈላጊ ምስኪን ሕዝብ፣ በእውነት፣ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ይኖራል ብለው የለውጡን አካሄድ አምነው ከውጪ ወደ አገራቸው በገቡ ወይም አገር ውስጥ በነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በጭራሽ አይጫንም።

ሌላው ከፍተኛ ለውጥ ሊደረግበት የሚገባው አሠራር በምርጫ ወቅት የመንግሥት ንብረትና ገንዘብ ፍትሐዊ አጠቃቀም ጉዳይ ነው። ኢሕአዴግና አጋሮቹ ከ500 በላይ በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ሲወዳደሩ (ውድድር ከተባለ) ከ500 በላይ የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን ለራሳቸው መገልገያነት አሰማርተው ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የመኪና፣ የነዳጅ፣ የማተሚያ ቤት፣ የውሎ አበል፣ የመሳሰለው ችግር ሰንጎ ይዟቸው ኢሕአዴጋውያኑ ግን በመንግሥት ገንዘብ፣ ተሽከርካሪ፣ ነዳጅ፣ ማተሚያ ቤት፣ ወዘተ. ተጠቅመው የምርጫ ዘመቻቸውን (Election Campaign) እያደረጉ የመሮጫ ሜዳው ፍትሐዊ ነበር ብለው ይነግሩናል። ጎምቱ ባለሥልጣናቱና አጃቢዎቻቸው ጭምር ከአዲስ አበባ ተነስተው በምርጫ መወዳደሪያ ክልላቸው ተገኝተው ለቀናት ድርጅታዊ ሥራቸውን ሲሠሩ የአውሮፕላን ቲኬት ክፍያ፣ በትልልቅ ሆቴሎች የማረፊያና የመስተንግዶ ወጪ፣ የመሳሰለው ሁሉ ከፓርቲው ካዝና ሳይሆን የሚሸፈነው ከሚመሩት ተቋም የመንግሥት በጀት ነው። ያለበለዚያ ደግሞ ለፓርቲዎች በመንግሥት ከሚመደበው በጀት ውጪ መጠቀም ከተፈቀደ የመንግሥት ንብረት ለሁሉም በፍትሐዊነት በጥቅም ላይ መዋል አለበት። ታዲያ እዚህ ላይ ቦርዱ “አይቻልም” የማለት ክንዱን ማፈርጠም አለበት። የመንግሥት ባለሥልጣናትን መጋፋት የሚያመጣው መዘዝ ቀላል እንዳልሆነ በተቋሙ ውስጥ በ1991 ዓ.ም. መጨረሻ ከተከሰተው ተጨባጭ ክስተት መማር የሚቻል ቢሆንም፣ የራስን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ሲባል የምርጫው ፍትሐዊነት ሲዛባ እየተመለከቱ በዝምታ ማለፍ በምድርም በሰማይም ያስጠይቃል።

መንግሥት በቅርቡ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሾሟል። ሰብሳቢዋም በሚመለከታቸው አካላት እየታገዙ ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። አዋጁን፣ ማስፈጸሚያ ደንቦቹንና ዝርዝር የአሠራር መመርያዎቹን የማስተካከል፣ ሚዛናዊ አመለካከት ብቻ ሳይሆን በቂ ተሞክሮ ያላቸውን የቦርድ አባላት የማፈላለግ፣ ጽሕፈት ቤቱን እንደ አዲስ አስተማማኝ በሆነ መንገድ የማደራጀትና የመሳሰሉት ግዙፍ ተግባራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ ናቸው። ተቋሙን የማዋቀሩ ሥራ ከላይ ነው የተጀመረው ከጣራው። ይኼ ምንም ችግር የለውም። አደረጃጀቱ ከታች ከሚጀመር ከላይ መጀመሩ ፖሊሲ የሚቀርፅ፣ ስትራቴጂ የሚነድፍ፣ ማስፈጸሚያ ሥልቶችንና አሠራሮችን የሚዘረጋ ሁነኛ ባለቤት እንዲኖረው ስለሚያግዝ እንደ ምርጫ አስተዳደር ባለሙያ አካሄዱ በጣም ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። ተቋሙ አገሪቱና ሕዝቦቿ የሚጠብቁበትን ግዙፍ ተልዕኮ እንዲወጣ ለማስቻል ደግሞ ለጣራው ከተሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ፣ ለመሠረቱ ወይም ለንጣፉ ዝግጅትና ከታች ጀምሮ ላለው አደረጃጀትና አሠራር ከወዲሁ የተለየ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ይኼ ጉዳይ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከተነሱት መሠረታዊ ጉዳዮች ሁሉ የበለጠ ትኩረት ያሻዋል።

በ1986 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በሽግግሩ ወቅት በጊዜያዊነት ተቋቁሞ ለሁለት ዓመታት ያህል ሲሠራ የቆየውን ምርጫ ኮሚሽንን ተክቶ በቋሚነት ሲቋቋም፣ በአገራችን የነበረውን የፖለቲካ ባህርይ እናስታውስ። “ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” የሚለው ብሂል ያላግባብ አልተባለምና።

ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱም በምርጫ አዋጁም ነፃና ገለልተኛ (Impartial) ምርጫ ቦርድ አቋቁማለሁ ብሎ መፎከር የተያያዘው ገና በሽግግር ሒደት ላይ እያለ ነው። ነገር ግን ሳይውል ሳያድር ሕገ መንግሥቱንና አዋጁን የሚንድ እንቅስቃሴ ነበር የተጀመረው። በቀጥታ ለዋናው ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት የየክልሎቹ ምርጫ ቦርድና ለየክልል ቢሮዎቹ ተጠሪ የሆኑት የየዞኑ የመምርያ ኃላፊዎች ተመልምለው (Nominate) እንዲላኩ የተደረጉት በየክልላቸው ፕሬዚዳንት ነው። ፈላጭ ቆራጩ ፓርቲና አጋሮቹ የሚፈልጓቸውንና በትክክል ዓላማቸውን ሳያዛንፉ የሚያስፈጽሙላቸውን ግለሰቦች መርጠው በየፕሬዚዳንቶቻቸው ፊርማ ለምርጫ ቦርዱ አቀረቡ። “እገሌን ካልፈለጋችሁ እገሌን ውሰዱ” የሚል አማራጭ እንኳን አልነበረውም። ቦርዱም በዚህ ሁኔታ ተመርጠው የተላኩለትን የቢሮና የመላ አገሪቱ የዞን የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በሙሉ ተቀብሎ መዋቅሩን እንዲመሩ አደረገ። አልቀበልም የማለት አቅሙም ሐሳቡም አልነበረውም። የምርጫ ቦርድ አቅሙ በወረቀት ላይ ነው የቀረው። ከዚያ በታች በምርጫ ክልሎች (Constituencies) እና በምርጫ ጣቢያዎች (Polling Stations) የነበረው ሁኔታ ከዚህ የባሰ እንደነበረ ገልጾ ማለፉ ብቻ ለዚህ ጽሑፍ በቂ ይሆናል።

የምርጫውን እንቅስቃሴ በትክክል አልመሩም ተብሎ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ተጨባጭ መረጃ የቀረበባቸውን የራሱን ኃላፊዎች/ሠራተኞች ለማንሳት ተቋሙ የነበረበት ፈተና ፍፁም አይረሳም። የክልሉ ፕሬዚዳንት ካላመነበት ቀድሞ ነገር ማን ማንን ከኃላፊነቱ ያነሳል? ሰውየው እንዲነሳ ስምምነት ላይ ቢደረስም ለፖለቲካ ሥርዓቱ ባለውለታ ነውና ከፍ ብሎ እንደተገለጸው የክልሉ ፓርቲ ወዲያውኑ ወደ እሱ መዋቅር ወስዶ የተሻለ ሥልጣን ይሰጠዋል። ያኔ የፓርቲው ቁልፍ ሰው መሆኑ ወይም ድብቅ ማንነቱ በገሃድ ይወጣል። ተፎካካሪዎች ከመንጫጫት በስተቀር የሚያመጡት ለውጥ አልነበረም። ፈተናው፣ ንትርኩና ውጣ ውረዱ ከባድ ነበር። ታዲያ ከዚህ የተዛባ አካሄድ ተምረን ብልሹ የፖለቲካ ጨዋታው እንዳይደገም ከወዲሁ መሠረታዊ (Fundamental) ለውጥ መደረግ አለበት። ምርጫ ቦርድ ላይ ጥገናዊ ለውጥ በፍፁም በምንም መንገድ ቦታ ሊኖረው አይገባም። ሕገ መንግሥቱንና የሕዝቡን የፖለቲካ ሥልጣን መሸራረፍ እየተተከለ ባለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ እሳት የመለኮስ ያህል ነው።

የጽሑፉ አቅራቢ እነዚህን ሁሉ ሐሳቦች የሚያነሳው አዲስ የተሰየሙት የቦርዱ ሰብሳቢና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይህ ሁሉ ይጠፋቸዋል ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት እንዳልሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት። ቢሆንም ጉዳዮቹ ይታወቃሉ ተብለው ሊታለፉ አይገባቸውም። ተመላልሰው ቢነሱም ያለፈው የምርጫ ሒደት ከፈጠረው ሥጋት የመነጩ ስለሚሆኑ መቀበል ያስፈልጋል። በማናቸውም መንገድ ይበልጥ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ለማሳሰብና የጋራ አገራችን ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትሸጋገር፣ የናፈቅነው ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ጤናማ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ለሕዝባችን የእውነት ተቆርቋሪ የሆነ መንግሥት ተፈጥሮ ለማየት ይመለከተናል የምንልና መረጃው ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሚመለከታቸው ወገኖች መረጃውን በትክክል ማስጨበጥ ግዴታችን ነው።

ቀድሞ ነገር ምርጫ ቦርዱ ገና ሲጠነሰስ ጀምሮ ከላይ እስከ ታች ሙሉ በሙሉ በገለልተኛ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተደራጀ መዋቅር ቢኖረው ኖሮ ምርጫዎቹስ መቼ ይጭበረበሩ፣ ኮሮጆስ መቼ ይገለበጥ፣ ነቀዝ  የበላው የፖለቲካ ሥርዓትና ተቋሙም ሲፈጠር ጀምሮ ለብልሹ አስተዳደር የተጋለጠ ተቋም መቼ ይሆን ነበር? ይኼ እንግዲህ ይበልጡኑ ተቋሙ ከተቋቋመ ጀምሮ የነበሩትን የመጀመሪያዎቹን አሥር ዓመታት ሥዕል በጉልህ ያሳያል ተብሎ ይታመናል። ከዚያ ወዲህ በደምሳሳው የሚታወቅ ችግር ቢኖርም፣ ተጨባጭ መረጃ ግን ስለሌለው የጽሑፉ አቅራቢ በማሳያዎች አስደግፎ አስተያየቱን ለመስጠት ይቸገራል። የሆነ ሆኖ ግን ተቋሙ ጉድፍ እንዳይበዛበት ከሁሉም በፊት በአስተማማኝ ንጣፍ ወይም መሠረት ላይ እንዲቆም፣ ለታችኛው እርከንም ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ያለ ምንም ማመንታት ሐሳቡን ይገልጻል።

ሌላም ጠቃሚ ነጥብ እናንሳ። የሽግግሩ መንግሥት አዲስ የምርጫ ቦርድ ለማቋቋም ሲያስብ የተጠቀመው የስዊድንን የምርጫ ተሞክሮ መሆኑን ስንቶቻችን መረጃ አለን? የስዊድን የምርጫ ባለሙያዎች (Election Experts) ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በምርጫ ኮሚሽኑ ግቢ ውስጥ ቢሮ ተሰጥቷቸው ያማክሩ ነበር። በእነዚህ የውጭ ምሁራን የመነሻ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች የተሳተፉባቸው ልዩ ልዩ ግብረ ኃይሎች ተደራጅተው የምርጫ አዋጁ፣ የተቋሙ ሙሉ አደረጃጀት፣ የሎጂስቲክስ፣ የሲቪክ ትምህርትና ሥልጠናና የመሳሰሉ ጥናቶች ተካሂደው ሰነዶች ተዘጋጅተው ቀርበዋል። የቦርድ አባላት እንዲሁም ዋናና ምክትል ኃላፊዎች ተመርጠው በሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት በአቶ መለስ ዜናዊ አቅራቢነት ሹመታቸው በጥቅምት ወር 1986 ዓ.ም. ለወቅቱ ፓርላማ ቀርቦ ፀድቋል። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ቀደም ሲል የምርጫ ኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሆኖ የተቋሙን የአደረጃጀት ጥናት ግብረ ኃይል በሰብሳቢነት ይመራ በነበረው፣ በኋላም ምክትል ዋና ኃላፊ ሆኖ በተሾመው ግለሰብ የሚመራና አራት ጽሕፈት ቤቱ የዋና መምርያ ኃላፊዎችን ያካተተ ትልቅ ቡድን ተሞክሮ ቀምሮ እንዲመጣም ወደ ስዊድን ነበር የተላከው።

ይህ ነጥብ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንዲነሳ ያስፈለገበት ምክንያት አለው። ስዊድኖች በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በፓርቲዎቹ አመራሮችና አባላት መካከል ከመከባበር፣ ከመግባባት፣ በነፃ ውድድር አገራቸውን በጋራ ከመገንባት በቀር መገፋፋት እንደሌለባቸው ትልቅ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ይዞ መጥቷል። ተሞክሮው ግን ፋይዳ ቢስ ነው የሆነው። አልተሠራበትም። ተግባራዊ የማይደረጉ ተሞክሮዎችን በማምጣት ረገድ የኢትዮጵያ ተቋማት የሚስተካከላቸው የለም። አዲሶቹ የለውጡ መሪዎቻችን በእነዚህ መሰል ጉዳዮች ላይ ዘመቻ ስለጀመሩ እናደንቃቸዋለን። ምርጫ ቦርድ በጎ ይሁኑም አይሁኑ ያለፉትን የውስጥ ተሞክሮዎቹን በደንብ ከመፈተሽ ባለፈ፣ አዲስ የውጭ ተሞክሮም ያስፈልገዋል። መሪዎቻችን ይህንን ሊያደርጉ እንደማይሳናቸው ከተግባራቸው አረጋግጠናል።

አርቲ ቡርቲ ሐሳቦችን በመወርወር የጋዜጣውን ገጽ መሻማት ወይም አንባቢያንን ማሰልቸት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። የኃያሉና የገዥው ፓርቲ መሪዎች ተፎካካሪዎቻቸውን እግር ከወርች ከማሰርና ከማሰቃየት ወጥተው፣ ዴሞክራሲን በተግባር እንዳረጋገጡ አገሮች ሊያደርጉ ይችሉ ነበር። በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ምርጫ ቦርዱ በጣም መሥራት ያለበት ለዚህ ነው። በአገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት (Consensus) መፍጠር፣ እኩል ለመሮጥ የሚያስችል የፖለቲካ መደላድል ማዘጋጀት፣ የጎሪጥ ያለ መተያየት፣ መናቆርንና መገፋፋትን የማስወገድ ሥራው ከወዲሁ መጀመር ይኖርበታል። ለዚህም በዕውቀታቸው፣ በተሞክሯቸው፣ በግል ስብዕናቸው እስከመጨረሻው በሚዛናዊነት በጽናት ሊቆሙ የሚችሉ የቦርድ አባላት ብቻ ሳይሆን የምርጫ አስፈጻሚዎች (Election Officers) በመዋቅሩ ላይ መቀመጥ አለባቸው።

ስለምርጫ አፈጻጸም ከተራው ሕዝብ የተሻለ ክህሎት የሌላቸው፣ በየሠፈሩና በየመሥሪያ ቤቱ የውይይት ክበብ ላይ እኔ ብቻ ልናገርና ልታይ የሚሉ፣ ለአበልና ለጥቅማ ጥቅም፣ ከመሥሪያ ቤት ሥራ ለመሸሽ፣ ወዘተ. ሲሉ በመዋቅሩ ውስጥ ገብተው ጫጫታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሰዎች እዚያው በፀበላችሁ ሊባሉ ይገባል። የምርጫ ቦርዱ መዋቅር ራሱ ምን ያህል በብልሹ አሠራር የተናጠ እንደነበረ በ1991 ዓ.ም. ግንቦት ወር ላይ በተካሄደው የፓርላማው ስብሰባ ላይ ስለምርጫ ቦርዱ የቀረበውን ሪፖርትና የተካሄደውን ውይይት ዘገባዎች ማየቱ ብቻ በቂ አብነት ይሆናል። የመዋቅሩ ንቅዘት በወቅቱ የነበሩት የሁሉም ሚዲያዎች ትኩስ ዜና ነበር። አሁንም ከጎሳ አስተሳሰብ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከግል ጥቅምና ከመሳሰሉት ብልሽቶች ፍፁም የፀዳ አደረጃጀት መፍጠር ካልተቻለ ዞሮ ዞሮ “ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ” ይሆናል። ተቋሙ በመዋቅሩ ላይ በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት የሚመድባቸው ሰዎች አመራረጥ የተለየ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።

በሌላ በኩልም የምርጫ ክልልና የመራጮች ጥመርታው ሚዛን (Ratio)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ በነበረበት ጊዜ የተሠራና ጥያቄም እያስነሳ ያለ የውክልና ጉዳይ ስለሆነ እንደገና ቢፈተሽ ተገቢ ይሆናል። በደርግ ጊዜ የአገሪቱ ብሔራዊ ሸንጎ ከ800 በላይ የሕዝብ እንደራሴዎች ነበሩት። የፓርቲው፣ የሕዝባዊ ድርጅቶች (አርሶ አደሮች፣ ወዛደሮች፣ የሙያ ማኅበራት፣ ወዘተ.)፣ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ ዕድገታቸው ያልተመጣጠነ ማኅበረሰቦች (Minorities)፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉት ውክልና ተብሎ በኮታ የሚመደብ ነበር። ከዝሆን፣ ከአንበሳና ከጎሽ ምልክቶች ቱባ ባለሥልጣናት ዝሆንን ይጠቀሙ ስለነበር፣ አንበሳና ጎሽ ላይ የተመደቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለዝሆኑ እንዲለቁለት እየተገደዱ ከውድድር ይወጡ እንደነበር ይታወሳል። ያን ጊዜ በአገራችን የምርጫ ውድድር ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስላልነበሩ የነፃ ምርጫ ጥያቄ እምብዛም ራስ ምታት አልነበረም። በሽግግሩ ወቅት ከ100 ያነሱ ተወካዮች ነበሩ። በፖለቲካ ድርጅቶች ኮታ ላይ የተመሠረተ ስለነበረ ያኔም ብዙ ችግር አልነበረም።

ባለፉት አምስት የፓርላማ ምርጫዎች ደግሞ ከ500 በላይ (ወደ 550 የሚጠጉ) መቀመጫዎች አሉ። የብሔር ብሔረሰቦች ልዩ ውክልናን (Special Representation) ጨምሮ ማለት ነው። ከዚህ አንፃር በመቶ ሺሕ ቁጥር የተደራጀው የምርጫ ክልሎች አመሠራረት ትክክለኛነት አሁንም እንደገና ቢፈተሽ ተገቢ ነው። ፓርላማው በደርግ ጊዜ ደመወዝ ተከፋይና በቋሚነት የሚሠራ አልነበረም። አሁን ግን በቋሚነት የሚሠራ ፓርላማ ነው። ከዚህ አንፃር የአገሪቱ የበጀት አቅም ከግምት ገብቶ፣ የትልቅ ታሪካዊትና በሀውርታዊት አገር ፓርላማም መሆኑ ሳይዘነጋ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር እንዳይጣረስ መፍትሔ ከተገኘለት፣ የፓርላማ አባላት ቁጥር ቢበዛ ይሻላል ወይስ ቢቀንስ የሚለው ጉዳይ ለውይይት ቢቀርብ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የምርጫው ሒደት ከተጀመረ በኋላ በአንድ ምርጫ ክልል ውስጥ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን በየስርቻው በብዛት ማደራጀት፣ በሕጉ መሠረት በአካባቢው ነዋሪ ያልነበሩ መራጮችና ከሌላ ቦታ በመከላከያ ካሚዮኖች ተጓጉዘው የመጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መራጮችን ነዋሪ እንደነበሩ ተደርጎ መታወቂያ እየተሰጠ፣ ከቦታ ወደ ቦታ አዘዋውሮ ድምፅ እንዲሰጡ በማድረግ አሸናፊ ለመሆን መቻል ባለፉት ምርጫዎች በጣም የተለመደ ብልሹ አሠራር እንደነበረ ሊዘነጋ አይገባውም። በመሆኑም ያለፈው የሕዝብ ቆጠራ ያስነሳው ጫጫታ ሳይበርድ አሁንም ችግሩ እንዳይደገም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ከቦርድ አባላት አመራረጥ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንዳለፉት ዓመታት የአንድ ብሔር የበላይነት ፈጦ እንዳይወጣና ከጎሳና ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ በምርጫ ወቅት የሚነሱ ውዝግቦች እንዳይፈጠሩ ጉዟችንን መሰናክል በሌለበት ሁኔታ መጀመሩ ተገቢ ነው። ከምንጊዜውም በላይ ሀቀኝነትና ግልጽነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።

የቦርዱ አባላት ከጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጎን ቋሚ ቢሮ ተሰጥቷቸው ደመወዝ ተከፋይ ሆነው እንደ ቅጥር ሠራተኛ ሆነው ይሥሩ የሚለው አስተሳሰብስ፣ ከቦርዱ ተልዕኮና አሠራር አንፃር ምን ያህል ያስኬዳል? በጽሕፈት ቤቱ የቀን ተቀን አስተዳደራዊ ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት አያስከትልም ወይ? በአምስት ዓመት ወይም በየሁለት ዓመት ተኩል ለሚካሄድ አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫ (ማሟያ ምርጫዎች ሳይዘነጉ ማለት ነው) የቦርድ አባላቱ ቋሚ ሠራተኞች ይሁኑ ከተባለ የሙሉ ጊዜ ሥራስ ይኖራቸዋል ወይ? ከዚህ ይልቅ የጽሕፈት ቤቱን አቅም በጠንካራና አስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት አይሻልም ወይ? ጥቅምና ጉዳቱ ቢመዛዘን። በተቋሙ አደረጃጀት ውስጥ ሴቶች ጉልህ የአመራርና የአስፈጻሚነት ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ሊዘነጋ አይገባውም። ከምርጫ ኮሚሽኑ አሥር አባላት ውስጥ አንድም ሴት አልነበረችም። በምርጫ ቦርድ ውስጥም እንደዚሁ ከአንድ ሴት በላይ ውክልና አልነበራቸውም። ወንድ የነበረው የምርጫ ቦርድ ፆታ ምጥንን በተጀመረው ሁኔታ ትርጉም ባለው መንገድ ማረጋገጥ አለበት።

በመጨረሻም የምርጫ ቦርዱ እንደገና በሚደራጅበት ጊዜ በላዕላይ መዋቅሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በታዕታይ መዋቅሩ፣ አደረጃጀትና አሠራሩ ላይም የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት አለበት። በፅኑ መሠረት ላይ ያልተገነባ ሕንፃ ጣራው የፈለገው ቢያምር ወይም ጠንካራ ቢሆን፣ ለግድግዳው ምንም ያህል ትኩረት ቢሰጥ የተሟላ ሊሆን አይችልም። ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት (በሁለቱም ሥርዓቶች) በተካሄዱት ምርጫዎች የምርጫ ክልሎችንና ጣቢያዎችን የውክልና መሥፈርትና አደረጃጀት በአግባቡ መፈተሽ፣ ችግሮቻቸውን ነቅሶ ማውጣት አስፈላጊ ነው። ቢቻል ጥናቶቹን ያጠኑ፣ በጂአይኤስ ያደራጁ፣ የውክልና መሥፈርቱን የቀመሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንን ባህሪ በጥልቀት የሚገነዘቡ፣ በክልል አከላለል ጥናቶች ሰፊ ሚና የነበራቸው፣ ምርጫዎቹን ያስፈጸሙ፣ የክልል መንግሥታት ሲመሠረቱ የተመሠረቱበትን ዝርዝር ሁኔታ የሚያውቁ፣ በሎጂስቲክስ፣ በሲቪክ ትምህርትና ሥልጠና፣ ወዘተ. ተግባራት ቁልፍ ተሳትፎ ያደረጉ፣ በየክልሎቹና በየብሔረሰቦቹ መካከል ሲፈጠሩ የቆዩትን ውዝግቦች ለመፍታት በተካሄዱት እንቅስቃሴዎች በጥናትና በገለልተኛ አደራዳሪነት አስተዋጽኦ ያደረጉና በየሥፍራው ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን እስከ ዛሬ ቢዘነጋም፣ በቀጣዩ ሒደት ላይ ማሳተፉ ግን እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል። ያለበለዚያ ያለፈውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ተሞክሮ በአግባቡ ሳንመለከትና ሳንጠቀምበት ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ እንሥራው ካልን መነሻችንንና ምክንያቶቻችንን፣ እንዲሁም ታሪካዊ ዳራችንን መዘንጋት ይሆናል። በበኩሌ ዳር ቆመን ከመተቻቸት በስልክም፣ በኢሜይልም፣ ከተቻለ በአካልም በመገናኘት ብንመካከርና ሐሳቡን በጋራ ብናበለፅገው ለአገራችን ጠቃሚ አስተዋጽኦ ልናበረክት እንደምንችል አምናለሁ። በቸር ይግጠመን።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻችን [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...