Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአገሪቱ የፖለቲካ ሽግግር ጤናማ ነው ቢባልም አለመረጋጋቱ ግን ኢኮኖሚውን ሊያሽመደምደው ይችላል›› ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የኢንተርናሽናል ግሮዝ ሴንተር ካንትሪ ኢኮኖሚስት

ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) ኢንተርናሽናል ግሮዝ ሴንተር የተባለ የምርምር ተቋም ውስጥ ካንትሪ ኢኮኖሚስት በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ ተቋሙ በተለይ በኢኮኖሚና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ጭምር ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችንና ምክረ ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡ ተቋሙን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦክስፎርድና ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚ ያቋቋሙት ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ተመሳሳይ ሥራ ያከናውናል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ ወደዚህ ተቋም ከመምጣታቸው በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ውስጥ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ከአሥር ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ወቅታዊ የአገሪቱን ኢኮኖሚና ተያያዥ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ታዬ ዶ/ር ቴዎድሮስን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይታያል? የዋጋ ግሽበት ከመኖሩም በላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እንዲሁ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ምን ላይ ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ሰፊ ጥያቄ ነው፡፡ ግን ዕድገቱን በተመለከተ ከሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የዕድገት ፍጥነቱ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው፡፡ ማደግ አቁሟል ማለት ሳይሆን የሚያድግበት ፍጥነት ቀንሷል፡፡ የመቶኛ ዕድገቱ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው፡፡ ይህ ማለት የዕድገት ሞዴላችን አቅሙን እየጨረሰ ነው እንደ ማለት ነው፡፡ እየተከተልን በመጣነውና ዕድገት ያመጣል ባልነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ፣ ከዚህ በኋላ ብዙ ርቀት መጓዝ መቻላችን የሚያጠራጥርበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ማሳያው ምንድነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ይህንን ገላጭ የሚያደርጉ ብዙ እውነታዎች አሉ፡፡ አንደኛው እስካሁን የነበረው የዕድገታችን ዓይነት ነው፡፡ የፍላጎትና የአቅርቦት ጎን የምንለው አለ፡፡ የዕድገቱ ዓይነት ወጪ ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ አገሮች ነዳጅ ወይም ማዕድን ሲያገኙ ይህንኑ እየሸጡ ዕድገታቸው በዚያው ይፋጠንላቸዋል፡፡ አዲስ ምርት ሲገኝ ከምርቱ ጋር የሚወጣ ዕድገት ነው፡፡ ወጪን በመለወጥ ፍላጎት በመጨመር ወይም የግልና የመንግሥት ወጪን በመጨመር የሚመጣ ዕድገት ሲሆን፣ በፍላጎት የሚመራ ዕድገት እንለዋለን፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ሲያስብ የነበረው ይህንን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም መንግሥት ብዙ ነገሮች ላይ ኢንቨስት የሚያደርግበት ነው፡፡ መሠረተ ልማት ላይ፣ ቤቶች ላይና የመሳሰሉት ላይ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ወጪው ብዙ ነው፡፡ ይህ ቆይቶ ቆይቶ ወደ አቅርቦት ጎን ይለወጣል፡፡ የገንዘብ እጥረት ያለበት አገር ስለሆነ መንግሥት ብዙ ወጪ ባወጣ ቁጥር በቂ ገንዘብ ተፈጥሮ ይህ ነገር ወደ ግብርናና አምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ይለወጣል የሚል እሳቤ ነበር፡፡ ግን ወደዚህ ሊሻገር አልቻለም፡፡ እንዲያውም ኢንቨስትመንቱ ከአቅሙ በላይ ሆነ፡፡ ፋይናንስ የሚያደርግበት መንገድ ደግሞ ገበያውንና ማክሮ ኢኮኖሚውን እንዲዛባ አደረገው፡፡ ከዚህ በላይ ብዙ ወጪ አውጥቶ ዕድገት ሊያመጣ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ግንዛቤ አለ፡፡ በመንግሥትም በኢኮኖሚውም ፍሬን የመያዝ ነገር ይታያል፡፡ ይኼ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የተመጣበት መንገድ ውጤት ካላመጣና አካሄዱም ይህንን ካሳየ ቀጣይ ዕርምጃው ምን መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አገሪቱን የሚመራው አካል እንደ አሻጋሪ የሚታይ ቢሆንም፣ በቀጣይ መደረግ የሚኖርበት ነገር ምንድነው? ኢኮኖሚው ያሳይ ወደነበረበት የዕድገት መጠን ለመመለስ ምን መደረግ አለበት? ዕድገቱንስ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አሁን ዕድገቱን ማስቀጠል ብቻ አይደለም የጎደለው፡፡ እንዲያውም ጥግ ድረስ በመሄድ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑና የገበያ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ነገሮች ውስጥ ተገብቷል፡፡ ምክንያቱም ከልክ ያለፈ ነገር ውስጥ ተገብቶ ስለነበር ማለት ነው፡፡ ገበያውን ያዛባው ነገር እንደ በሽታ በሁለቱም በኩል ማለትም በአቅርቦትም በፍላጎትም ኢንቨስት እንዳይደረግ ያደርጋል፡፡ ወይም በአቅርቦት ዕድገት እንዳይቀጥል ያደርጋል፡፡ በፍላጎትም አቅሙን ይጨርሳል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሕመም ማከም ያስፈልጋል፡፡ አንተ የምታውቃቸው ቅድም ያልካቸውን ነገሮች በአንድ ላይ ጠቅልሎ ሰብስቦ የሚይዝልህ ነገር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ፣ የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና የመሳሰሉት አሉ፡፡ ይህም ምንድነው መንግሥት ዕድገቱን ለማስቀጠልና ፋይናንስ ለማድረግ የመጣባቸው መንገዶች፣ እንዲሁም ወጪና ገቢውን ሚዛናዊ ለማድረግ የተጠቀመባቸው መንገዶች ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያዛቡ በመሆናቸው ምክንያት የተፈጠረ ሕመም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ይሄድባቸው የነበሩ መንገዶች ማክሮ ኢኮኖሚውን እንዴት እንዳዛቡት ማሳየት ይቻላል?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ማክሮ ኢኮኖሚው የተዛባባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ መዛባቱ የተፈጠረበት  አንደኛው መንገድ ብሔራዊ ባንክ ያለ ጥንቃቄና ያለ ማሰለስ በከፍተኛ ሁኔታ ለመንግሥት የሚሰጠው ብድር ነበር፡፡ ይህ ‘ዳይሬክት አድቫንስ’ የምንለው ብድር ነው፡፡ ይህ ብድር አዲስ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ከመልቀቅ ጋር የማይተናነስ ነው፡፡ አዲስ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው በመለቀቁ ደግሞ የዋጋ ንረትን አመጣ፡፡ ያለማቋረጥ ሕዝቡን የሚያስጨንቅ የቆየ የዋጋ ንረት አመጣ፡፡ የዋጋ ንረቱ ሲመጣ ሰው አለመረጋጋት ይታየዋል፡፡ ይህ ደግሞ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዳይገባ ያደርገዋል፡፡ በጥቅል ስታየው አለመረጋጋት የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳይኖርህ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ በትንሹ ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ ዘርፎች ውስጥ ትሰማራለህ፡፡ ለምሳሌ ኮንስትራክሽንን መውሰድ ይችላል፡፡ ብሬን ላስቀምጥበት እችላለሁ በማለት ይገባበታል፡፡ የማያስተማምን ነገር ስላለ ማሽን ከምገዛ ሕንፃ ብሠራ ይሻለኛል ወደሚል አስተሳሰብ ውስጥ ይከትሃል፡፡ እንዲህ የሚሆነው የገንዘቡ የመግዛት አቅም ሲያንስ ነው፡፡ ይህ የሚያሳይህ ሰዎች ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መንግሥት ኢንቨስት ሲያደርግ ገንዘቡ የሆነ ነገር ላይ ማረፍ አለበት፡፡ ገንዘቡ ወጪ የሚደረገው ደግሞ እዚህ አገር ውስጥ የምናመርተው ምርት ላይ ወይም ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ላይ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ላይ ወጪ የሚደረግ ከሆነ ደግሞ ኢምፖርቱን በጣም እየጨመረው ይሄዳል፡፡

      ስለዚህ ያለውን የውጭ ምንዛሪ በሙሉ ሰብስቦ ለራሱ ይወስድና የግሉን ባለሀብት አፍኖ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ያስመጣበታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ይፈጥራል፡፡ ኢንቨስትመንቱ በጨመረ ቁጥር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ በመጨመሩ ምክንያት እጥረት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ከሌሎች አገሮች ጋር ያለንን ተወዳዳሪነት ይቀንስብናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ገንዘብ እየረጨን የውጭ ምንዛሪው ስለሚያጥረንና ብዙ ስለምንፈልግ፣ የእኛ ገንዘብ ገበያ ላይ ያለው ትክክለኛ የምንዛሪ ምጣኔ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ በትክክለኛ ገበያ ላይ ያለ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን የሆነ ቦታ ላይ አጥብቆ ስለያዘው ያለው የምንዛሪ ምጣኔ ትክክለኛውን ዋጋ አያንፀባርቅም፡፡ ይህ ደግሞ በርካሽ ዕቃ እንዲያስመጣ ይረዳዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ላኪዎች ብዙ እንዳይልኩ ይይዛቸዋል፡፡ የምንዛሪ ምጣኔው አርቲፊሻል ሆኖ ስለተያዘና የዶላር ዋጋ ርካሽ ስለሆነ፣ ማንኛውንም ዕቃ ወደ ውጭ ከምትሸጠው እዚህ ብትሸጠው ያዋጣሃል ማለት ነው፡፡ ሰሊጥም፣ የቀንድ ከብትም ሆነ ወርቅ እዚሁ ብትሸጠው ያዋጣሃል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን እዚህ ለመሸጥ ትሞክራለህ፡፡ ወይም ቡና በኮንትሮባንድ ትሸጥና በጥቁር ገበያ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ስለምታገኝ እዚያ ላይ ባውለው ያዋጣኛል ትላለህ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን እዚህ ለመሸጥ ትሞክራለህ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት ሌላው መገለጫ ሆኖ ይታያል፡፡ ሦስተኛው ነጥብ የሚመጣው በወለድ ምጣኔ በኩል ነው፡፡ የወለድ ምጣኔ መንግሥት በረከሰ ዋጋ ከአገር ውስጥ ማግኘት ስለፈለገ ብድር የሚወስደው ከብሔራዊ ባንክ ብቻ አይደለም፣ ከግል ባንኮችም ይወስድባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚወስድባቸው? 27 በመቶ የቦንድ ግዥ ማለት ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የ27 ቦንድ ግዥ አንደኛዋ ነች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ በአንድ ባንክ የበላይነት የተያዘ ከመሆኑ ጋር የተያያዘም ነገር አለ፡፡  አውትስታንዲንግ ብድር አንድ ባንክ ጋ ነው ያለው፡፡ ይህ ባንክ በአጭር ጊዜ የሚያገኘውን ገንዘብ ለረዥም ጊዜ ነው የሚያበድረው፡፡ ዋናው ተበዳሪ ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ ሃምሳ በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ የት ነው ያለው ካልከኝ መንግሥት ዘንድ ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት የረዥም ጊዜ ብድርን በርካሽ ከንግድ ባንኮች እየወሰደው ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን የወለድ ምጣኔ ከግሽበቱ ጋር ስታስተያየው የወለድ ምጣኔው ኔጌቲቭ የሆነ ገንዘብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ግሽበት አሥር በመቶ ሆኖ ወለዱ ሰባት በመቶ ከሆነ 100 ብር ስበደር በሚቀጥለው ዓመት የምከፍለው 107 ብር ነው፡፡ ግን የአሥር ብር ያህል ዋጋው ቀንሷል፡፡ ስለዚህ 107 ብር ማለት ከአሁኑ 100 ብር ጋር አይወዳደርም፡፡ አለመወዳደር ብቻ ሳይሆን የባንኩን ትርፍ ይነካል፡፡ መንግሥት ኢንቨስት ለማድረግ ላሰበው ነገር ከአስቀማጮች ላይ ሳይቀር ብር ይሰበሰባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የወለድ ምጣኔው ራሱ ኔጌቲቭ በሆነ የወለድ ምጣኔ (እኛ የፋይናንሻል ሪትሬሽን እንለዋለን) በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በገበያው እንዳይንቀሳቀስ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ማለት ነው፡፡ እንዲህ ባሉት ሦስት መንገዶች ማክሮ ኢኮኖሚውን ሲያዛባ ቆይቷል፡፡ ይህንን ሁሉ ያደረገው ርካሽ የውጭ ምንዛሪና የብድር ምንጮችን ተጠቅሞ እንደልቡ ለማግኘት ብሎ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕመም የሚሆንብህ ነገር ይህንን ሁሉ አድርገህ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሲስተም አዛብተህ፣ በተለይ ደግሞ ግሽበት ፈጥረህ ወይም የደሃውን የመግዛት አቅም ቀንሰህ የወሰድከውን እያንዳንዱን ብር በትክክል የመጠቀም ግዴታ ይኖርብህ ነበር ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለራሱ የሚመቸውን ይህንን ሁሉ ነገር አድርጎ ያሰበውን ሥራ ከግብ ለማድረስ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው ልንል እንችላለን? ማክሮ ኢኮኖሚውስ እንዲህ ሲዛባ ማስተካከያ ለምን አልተደረገም ይላሉ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- መንግሥት አቅሙ አለኝ፣ እኔ ካላደረግኩ በማለቱ የተፈጠረ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከዛሬ 200 እና 300 ዓመታት ጀምሮ የዓለም ኢኮኖሚስቶች ሲከራከሩበት የነበረ ነገር አለ፡፡ ይህም መንግሥት ስለሚያበላሽና ለሙስና ቅርብ በመሆኑ፣ ይህንን ነገር ለማስፈጸም አቅም ስለሌለው ለግሉ ዘርፍ መተው አለበት የሚሉ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ  መንግሥት ካልተቆጣጠረው ነጋዴ ይበላዋል የሚሉ የዕድሜ ልክ የኢኮኖሚስቶች ክርክር አለ፡፡ የእኛ መንግሥት ምን ያህል ለሙስና የተጋለጠ ነው የሚለውን ማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው፡፡ ግን ይህንን ነገር ለመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የኢኮኖሚውን የማረጋጋት ሥራና ከውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት ባንኩ ነው፡፡ እኛ ንግድ ባንኮች ጋ ብራችንን እንደምናስቀምጠው ሁሉ፣ መንግሥትም ብሩን የሚያስቀምጠው ብሔራዊ ባንክ ዘንድ ነው፡፡ ግን ብሔራዊ ባንክ መንግሥትን አልገፀሰም፡፡ ለምሳሌ አንተ ንግድ ባንክ ሄደህ አምስት ሚሊዮን ብር አበድሩኝ ብትላቸው ገቢህን እንየው ይሉሃል፡፡ ወይም ኮራቶራል አስይዝ ይሉሃል፡፡ አለበለዚያ እንቢ አናበድርህም ይሉሃል፡፡ ኮራቶራል ከሌለህ ለረዥም ጊዜም ሆነ ለአጭር ጊዜ ለምትወስደው ብድር ለመክፈል ገቢህ የማያስችል ከሆነ ብድሩን አንሰጥህም ይሉሃል፡፡ ልንሰጥህ የምንችለው ብድር ይህንን ያህል ብቻ ነው ይሉሃል፡፡ ብሔራዊ ባንክም ለመንግሥት ማለት ያለበት እንዲህ ነው፡፡ መንግሥት ብር ሲፈልግ እያተመ መስጠት አይደለም፡፡ ያለገደብ ብር እያተመ መስጠት ይችላል፡፡ ግን ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ሥልጣን ስለተሰጠው ከዚህ በላይ ብሰጥ ግሽበቱ ስለሚባባስ አልሰጥም፣ ከዚህ በላይ ብሰጥህ ኢኮኖሚውን ያዛባዋል ማለት ነበረበት፡፡ ያለገደብ የሚሰጥ ገንዘብ ደግሞ ሁሉንም ነገር ይበጠብጠዋል ማለት አለበት፡፡ ስለዚህ የምሰጥህ ይህንን ያህል ብቻ ነው ማለት ሲኖርበት፣ የእኛ አገር ብሔራዊ ባንክ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለና በራሱ መወሰን የማይችል ስለሆነ እስካሁን ድረስ ሲጠየቅ የነበረውን ሁሉ ሲሰጥ የቆየ ሆኗል፡፡ ኢኮኖሚስቶች አይሆንም እያሉ እየጮሁም አልሰማ ብሎ ነበር፡፡ ለመንግሥት የፈለገውን ሲሰጥ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ አንዱ ችግር የብሔራዊ ባንኩ ነፃነት ነው፡፡ አሁንም መደረግ ያለበት ነገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሆነ በሌላ፣ ብሔራዊ ባንኩ ነፃ ሆኖ ተጠሪነቱ ለፓርላማ እንዲሆን ታደርግና የሚሰጠው ነገር ገደብ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ የገንዘብ ልቀት ገደብን ማበጀት ይኖርበታል፡፡ ከመንግሥት በጀት ከዚህ በላይ አይሰጥም ብሎ ጥብቅ ገደብ ማበጀት ያስፈልገዋል፡፡ መንግሥት በተቀመጠለት ገደብ ከሄደና ወጪውን ከቀነሰ ግሽበት ላይም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ላይ ያለው ጫና እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ሌላው መንግሥት ራሱ ብዙ ድስት ስለሚጥድ ገበያውን እያዛባው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ለምሳሌ አንተ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት እገነባለሁ ብለህ ትነሳለህ፡፡ ሥራው 100 ሚሊዮን ብር ያስወጣኛል ብለህ ሒሳብህን በደንብ አሠርተህ የብረትና የሲሚንቶ ዋጋ ሁሉ አስልተህ በተሳካ ሁኔታ ብታሠራ ውጤታማ ትሆናለህ፡፡ ያንን የመንገድ ሥራ በአንዴ አሥር አድርገህ አሥር ድስት ስትጥድ የአንተ ፍላጎት ብቻ የብረትን ዋጋ ይጨምረዋል፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቱን ለማከናወን ያጠናህበት ዋጋና ከዚያ በኋላ ፕሮጀክቱን የምታስጨርስበት ዋጋ የተለያየ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ድስት በአንዴ ስትጥድ የገበያውን ዋጋ ራሱ ያዛባዋል፡፡ ዋጋ ተዛባ ማለት ተጨማሪ በጀት ትጠይቃለህ ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በታሰበላቸው ጊዜና ገንዘብ አያልቁም፡፡ ይህም ኢኮኖሚውን ያዛባዋል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ነው የቆየነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የተወሰነው ይሰረቃል፡፡ እንዲህ በአጭር ጊዜ ሀብታም መሆን እኮ በዓለም ላይ የለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የሚፈጠረው ያለውን ሀብት በማንኛውም ሁኔታ በአግባብ ያለ መጠቀምና ያለ ማቀድ ነው፡፡ ሌላው ከደሃ ተወስዶ የመጣ ገንዘብ ብለህ ሕመም ሊሰማህም ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚገልጹልኝ ነገር ነባራዊውን ሁኔታ የሚያሳይ ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዞ ደግሞ መቀየር ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኢኮኖሚውን ጉዞ ጤናማ ለማድረግ እስካሁን የተወሰደው ዕርምጃ ምንድነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- እንግዲህ መንግሥት በአንድ ዓመት ውስጥ እስካሁን ጠንካራ ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ለዚህም የተወሰኑ ነገሮችን መጠቆም ይቻላል፡፡ አሁንም ብሔራዊ ባንክ ዘንድ አቅም የለም፡፡ ማዕከላዊ ባንኩ ቺፍ ኢኮኖሚስት የለውም፡፡ ቺፍ ኢኮኖሚስት የለውም ማለት እንዲህ ያለውን ነገር አስቦ ጠንክሮ የሪፎርም ዕርምጃ የሚወስድ የለም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሄዶ ከተቃዋሚዎች ጋር ተደራድሮ በፖለቲካው ዘርፍ ከፍ ባለ ሁኔታ እያስፈጸመ እንዳለው ሁሉ፣ በኢኮኖሚውም ዘርፍ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈጽም ሰው ለጊዜው የለም፡፡ ይህ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ያው መንግሥት እያሰበ ያለው ነገር አለ፡፡ ግን እስካሁን ጫን ያለ ዕርምጃ እየተወሰደ አይደለም፡፡ በእርግጥ እንደእኛ ያሉ ተቋማት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ብዙ ውይይቶች አድርገናል፡፡ ሌሎችም አካላትም ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቶቹ ከገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ሁኔታውን ተገንዝበውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ምኑን ነው የሚገነዘቡት ?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ብድር መውሰድና ይህንን አሥር ድስት የመጣድ ነገር የሚያመጣውን ተፅዕኖ ተረድተውታል፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ ደረጃ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ለመቀነስ እያሰቡ ነው፡፡ የስድስት ወራት ውስጥ አፈጻጸሙ ሲታይ ብዙም የረባ ለውጥ የለም፡፡ ጠንካራ ዕርምጃ አለተወሰደም፡፡ በድሮው ነው እየተንቀጠቀጠ እየሄደ ያለው፡፡ አሁን የማያዳግም ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መቋረጥ ካለባቸው መቋረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉ በጤና፣ በትምህርት፣ በደኅንነትና በመሳሰሉት ካልሆነ በስተቀር ጠንከር ብሎ ወጪዎችን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዘንድሮ በጀት አልተያዘላቸውም፡፡ ይህ እንደ አንድ ዕርምጃ አይወሰድም? ወጪን መቀነስ አይደለም?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- እሱ ልክ ነው፡፡ መንገዶች ብቻ ሳይሆኑ ይህ ነገር ወደ ብሔራዊ ባንክ ሄዷል ወይ ማለትም አለብህ፡፡ አሁን የሚሰጠው ‘ዳይሬክት አድቫንስ’ ቀንሷል ወይ? ወይም ጣራ አበጅተውለታዋል ወይ? የሚለውን ነው ማየት ያለብህ፡፡ ይህ ወደ ግሽበት ሽግግር ያደርጋል፡፡ መንግሥት ከግል ባንኮች የሚያንቀሳቅሰውን ገንዘብ መተው አለበት፡፡ ለምሳሌ 27 በመቶ የቦንድ ግዥ መቅረት አለበት፡፡ የንግድ ባንክ የውስጥ አሠራሩ በጥልቀት መፈተሽ አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ብድር የተወሰደው እኮ በመንግሥት ዋስትና ነው፡፡ ንግድ ባንክ የመንግሥትን ዋስትና ስለያዘ ነው ብድር የሰጠው፡፡ ጥናት ተጠንቶ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ንግድ ባንክም ቢሆን አሁን እየተፈተሸ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር እንዴት ነው? የሚለውን አብጠርጥረው እያዩት ነው፡፡ የወለድ ምጣኔውን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ከቀነሰ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔውን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ‘ፓራላል ማርኬት’ (ጥቁር ገበያ) ላይ ይህንን ያህል ልዩነት ካለ የክፍያ ሚዛናችን በጣም ነው የሚጎዳው፡፡ ለምን ያልከኝ እንደሆነ ይህንን ያህል ልዩነት ካለ ሰው የፈለገ ነገር ቢሆን በሕጋዊ መንገድ የውጭ ምንዛሪ አይልክም፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያዛባል፡፡ መንግሥት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ ነው የሚያዛባው፡፡ በጥቁር ገበያ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመድኃኒት መግዣ ልታውለው አትችልም፡፡ ለነዳጅ መግዣ ማዋል አትችልም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ነገር ማስተካከል መቻል አለብን፡፡ የውጭ ምንዛሪ ሲስተምን ማስተካከል አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከጥቁር ገበያው ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የብርን የመግዛት አቅም በመቀነስ (ዲቫሉዌሽን) ማለት ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- እሱ የባሰ ነው፡፡ ዲቫሉዌሽን ይረብሻል፡፡ ስለዚህ ከሱ በመለስ ያሉትን ዕርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲቫሉዌሽን ነገር ከተነሳ ሁሌም ጥያቄ የሚያስነሳ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም መንግሥት የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ወይም ዲቫሉዌሽን ሲያካሂድ ዋነኛ ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው የወጪ ንግዱን ለማበረታታት የሚል ነው፡፡ የወጪ ንግድ ገቢ ሲያድግ የብር ምንዛሪ ለውጡ ተደርጓል ይላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ተደርጎ የተጠቀሰው የወጪ ንግድ ግን ምንም ለውጥ አላሳየም፡፡ ጭራሽ ቁልቁል ወርዷል፡፡ ይህ ምን ያሳያል?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ይህች ብቻዋን የተወሰደች ዕርምጃ ነች፡፡ አጠቃላይ አልነበረም፡፡ መንግሥት የውጭ ምንዛሪውን እየወሰደ ገንዘብ ያለው ሰው በግብርና ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ አድርጎታል፡፡ ገንዘቡንም ወስዶታል፡፡ ስለዚህ እንደ አዲስ ኢንቨስት ለማድረግ ገንዘብ ከየት አምጥቶ ሊሠራ ነው? ደግሞም ማበረታቻ የለውም፡፡ ማትጊያ ከሌለው ለምንድነው የኤክስፖርት ሸቀጦች ላይ ኢንቨስት የሚያደርገው? እነኚህ ሁሉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ እስካሁን የምንዛሪ ማስተካከያ መደረጉ ኤክስፖርቱን አሻሽሎታል አላሻሻለውም ለሚለው በቂ መረጃ የለም፡፡ ኤክስፖርት ጨምሯል፡፡ ግን ዲቫልዩ ስታደርግ አውቶማቲክ አንድ ዶላር የሚያመጣን ቡና ከ15 ብር ወደ 29 ብር ስታደርገው፣ የቡና እሴት በብር እንደጨመረ ያሳይሃል እንጂ በዶላር የሚመጣውን ገቢ አያሳይም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የተደረገው የምንዛሪ ማስተካከያ ኢኮኖሚውን በጣም እየረበሸና ኤክስፖርት እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልመጣም፡፡ ስለዚህ ብዙ አጠቃላይ የሆነ አቅርቦትህን የምትጨምርባቸው ነገሮች ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንደጠቀሱልኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተቃዋሚዎችን ከየአቅጣጫው እንዲገቡ በማድረግ በፖለቲካው ረገድ እንደወሰዱዋቸው ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎች ዓይነት በኢኮኖሚው ላይ አልተሠራም፡፡ ስለኢኮኖሚ ስናነሳ የፖሊሲው ቅርፅና ይዘት ይታሰባል፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምን እንዴት መቃኘት አለበት የሚለው ጉዳይ ግን አሁን ግልጽ አይደለም፡፡ አየር ላይ ነው ያለው፡፡ እርስዎም ኢኮኖሚውን ለማራመድ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው እንዳሉት ሁሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ጉዳይ እንዴት ነው መታየት ያለበት?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ቀደም ብዬም ጠቅሼልሃለሁ፡፡ የመንግሥትን ወጪ መቀነስና ሊበራላይዜሽን አንዱ መሆኑን ጠቅሼልሃሁ፡፡ ሌላው ገበያው የሚፈልገው ምልክት ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት አቅጣጫ እንዳለው፣ በፕራይቬታይዜሽን የበለጠ ለግል ዘርፉ ዕድል እንደሚሰጥ፣ የውጭ ምንዛሪ ብዙ እንደማይሻማና ረዘም ላለ ጊዜ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይህ ነው ብሎ የሚታመን ምልክት መስጠት አለበት፡፡ እስካሁን ቀዝቃዛ ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ ጠብ እያደረገ ነው፡፡ ጠንከር ያለ ነገር ስለሌለ ምልክቱን ገና አላመነም፡፡ እንደ መሸጋገሪያ ያለ መንግሥት ስለሆነ ምን ለውጥ ይመጣል የሚልም አለ፡፡ ግልጽ ስላልሆነና ገና ነው፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው ገንዘብ አውጥቶ ኢንቨስት የሚያደርግበት አይደለም፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ የለንም፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደ ሪፎርም መኬድ አለበት፡፡ ትንሽ ጠንከር ያሉና ደፋር የሆኑ ውሳኔዎች ማሳለፍ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ደፋርና ጠንከር ያለ ዕርምጃ መወሰድ አለበት በማለት ደጋግመው ገልጸውልኛል፡፡ ይህ ጠንካራ ዕርምጃ ምን ይሆን?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- ደፋር የሆነ ዕርምጃ የምልህ በከፍተኛ ደረጃ የመንግሥት ኢንቨስትመንት መቀነስ፣ የዋጋ ግሽበትን፣ የወለድ ምጣኔንና የውጭ ምንዛሪ ምጣኔን የበለጠ ወደ ገበያ መር ማምጣት አለበት ለማለት ነው፡፡ ገበያው መንግሥት በጣም ወደሚቆጣጠረው ሳይሆን በራሱ የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ንግድ ባንክ በገበያ መር እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ማድረግን ሁሉ ያጠቃለለ ዕርምጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ ጤናማ ባንክ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለግል ዘርፉ ምልክት መስጠትና የመሳሰሉት ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በሦስት ዓመታት ውስጥ ይህንን ለግሉ ዘርፍ እናስተላልፋለን፣ በዚህ ጊዜ ይህንን ቀንሰን ይህንን ያህል ገንዘብ እናቀርባለን በማለት በደንብ የታሰበበትና ጠንከር ያለ ነገር ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ቺፍ ኢኮኖሚስት ያስፈልገዋል፡፡ ሌሎች ሰዎችም መሳተፍ አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነው ደፋር ዕርምጃ የምልህ፡፡

ሪፖርተር፡- ኤክስፖርት እንዲህ የወደቀው ለምንድነው? ከሌላው አገር የተለየ ፖሊሲ ስላለ ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- መረበሽ ነው፡፡ ስለተረበሸ እንጂ ዶላር የማይፈልግ ማን አለ? ማንም ሰው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ የተረጋጋ ኢንቫይሮመንት ውስጥ ከሆነ አምርቶ መላክ ይፈልጋል፡፡ የውጭ ገበያ መሳብ ይፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት በኤክስፖርት ዘርፍ ታስበው የነበሩትንና ያልተሳኩትን ሁለት ነገሮች እንይ፡፡ አንደኛው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብዙ ኤክስፖርት አድርገው ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ያልተሳካበት ምክንያት ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የኃይል ማመንጫዎች ተገንብተው ለኤክስፖርት አልደረሱልንም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ግን በሙሉ አቅም እንዲሠሩ ለማድረግ ለሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ ሳቢ አይደለም፡፡

ከዚህ ሌላ እሴት ጨምረው የሚሠሩት ትንሽ ነው፡፡ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ብዙ ነገር ከውጭ አስመጥተን ሠርተን የምንልከው የተጣራ ኤክስፖርት ገቢ ትንሽ ነው፡፡ ለሰው ኃይል የሚወጣው ነው እንጂ እንዳለ ዕቃዎቹ ወጥተው ነው የሚሄዱት፡፡ በአገር ውስጥ ሰፕላይ ቼን አልፈጠርንም፡፡ ከአገር ውስጥ ግብዓት ሰብስቦ የሚሠራ የኢንዱስትሪ ፓርክ አይደለም ያለን፡፡ በአንፃሩ እየተገነቡ ያሉት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነሱ የተሻለ ነገር እናገኛለን፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የጨርቃ ጨርቁ በጣም ችግር ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም ከክርና ከባጅ ጀምሮ አስመጥቶ የሚልክ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ኢንቨስትመንት የወጣበት ነገር ኤክስፖርቱ ትንሽ ነው፡፡ ተጠቃሚ የሚሆነው ኢንቨስተሩ ነው፡፡ ኢንቨስተሩም ቢሆን በጣም ውጤታማ ያልሆነ የሰው ኃይል ስለሆነ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ የሰው ኃይሉ ርካሽም ቢሆን ምርታማነቱ ዝቅተኛ ስለሆነ እስከሚለምድ ድረስ ያስቸግራል፡፡ ደግሞም ሠራተኛ ቶሎ ይለቅባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የተሻለ ይገኝባቸዋል የሚባሉት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው ነው ያሉት ጥሬ ዕቃ ከዚህ ስለሚጠቀሙ ነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- አዎ፡፡ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪም እዚህ ያስቀራሉ፡፡ በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይልን የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ ተብሎ እንደታሰበው አልሆነም፡፡ በጎንዮሽ ገበያ ላይ ክፍተት ካለ ማንም ሰው ባገኘው አጋጣሚ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይጠቀማል እንጂ በይፋ ማስመጣት አይፈልግም፡፡ ሌላው የቁጥጥር ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢኮኖሚው ዘርፍ የአገሪቱ ተስፋና ተግዳሮት ምንድነው?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የአገሪቱ የፖለቲካ ሽግግር ጤናማ ነው ተብሎ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ የውጭ ኢንቨስተሮችም አሉ፡፡ ደህና የፋይናንስ ምንጭና የውጭ ምንዛሪ መገኛ ይኖራል፡፡ የግል ዘርፉም ወደ አምራች ዘርፍ ለመሰማራት ምልክት አለው የሚለውም መልካም ዕድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን በፍጥነት እያደገች ያለችና ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ነች የሚለው ጥሩ ስም ነው፡፡ በሥጋት በኩል የፖለቲካ አለመረጋጋት ኢኮኖሚውን ሊጎዳ የሚችል ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሽግግር ጤናማ ነው ቢባልም አለመረጋጋቱ ግን ኢኮኖሚውን ሊያሽመደምደው ይችላል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ብዙ ገንዘብ የፈሰሰው ወደ አንድ ዘርፍ ስለሆነ እነዚያ ሰዎች ብራቸውን ይዘው ቁጭ ብለዋል፡፡ ሕንፃ ሠርተዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ደግሞ ሕንፃ ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ በማስያዣ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ረብሻ አጋጥሞ ሕንፃዬን ሽጬ ልውጣ ዓይነት ነገር ከተፈጠረ የሕንፃ ዋጋ ይወርዳል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኮላቶራል ዋጋ ማለት ነው፡፡ በዚህም የተበደረውን ብድር አለመክፈል ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህም የፋይናንስ ዘርፉን ይጎዳል፡፡ ይህ ትልቅ ሥጋት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የመተማመን ማነስ ካጋጠመና ኢንቨስትመንት ቶሎ መነሳት ካልቻለ አሁን ያለውን መቀዛቀዝ ይዘን ለረዥም ጊዜ መቆየት አንችልም፡፡ ስለዚህ ቶሎ ብሎ ወደ ሪፎርም መገባት አለበት፡፡ ሥራ አጥነት አደጋ ስላለው በቶሎ ሊሠራበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ሲታሰብ ደግሞ አሁንም ተመልሰን የፖሊሲ ጉዳይ ልናነሳ ነው፡፡ የግል ዘርፉ በሰፊው እንዲሠራ ፖሊሲው መለወጥ አለበት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የግሉ ዘርፍ ጉዳይም አብሮ መታየት አለበት፡፡ የግል ዘርፉ ደካማ ነው ይባላል፡፡ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የግል ዘርፉ ሚና ወሳኝ ነው ከተባለ ከእርሱ የሚጠበቅ ነገር የለም ወይ? ለምሳሌ እስካሁን የመጣበት መንገድ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት ቅርፅ ይዞ መጓዝ አለበት?

ዶ/ር ቴዎድሮስ፡- የግል ዘርፉ በንድፈ ሐሳብ ለትርፍ የሚወጣ አካል ስለሆነ ትርፉን ነው የሚከተለው፡፡ ትርፍህን አትከተል ብለህ የምትነግርበት ምክንያት የለም፡፡ ግን የተረጋጋ ሲስተምና የተረጋጋ ፖለቲካ ይፈልጋል፡፡ ሌላው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ነው፡፡ አብሮ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ የሚችልበትን ማሰብና ማስጠናት ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ላይ መግባት ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሚያደርጉህ በዕውቀት ላይ በተመሠረቱ ሥራዎች ስለሆኑ እነዚህ ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...