Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ዳግመኛ ሊመጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፍሪካ አገሮች እየተዟዟረ የሚካሄደው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም በመጪው ዓመት መጀመርያ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

በ2007 እና በ2008 ዓ.ም. በተከታታይ በኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረው ስብሰባ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው የካሊብራ ሆስፒታሊቲ አማካሪ ኩባንያ ሲሆን፣ ዝግጅቱን ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ለማድረግ፣ የፎረሙ አዘጋጅ ከሆነውና ዋና መሥሪያ ቤቱ በእንግሊዝ ከሆነው ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱ ተገልጿል፡፡ የቤንች ኤቨንትስ ኃላፊዎች ስብሰባው በመስከረም መጨረሻ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው ታውቋል፡፡

የካሊብራ ሆስፒታሊቲ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የፎረሙ መምጣት ለኢትዮጵያ ሆቴል ኢንዱስትሪ የሚያስገኘው ኢንቨስትመንት ዕድልና ለአገሪቱም ገጽታ የሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁለት ስብሰባዎችና በሌሎችም አገሮች ውስጥ ከታዩት ለውጦች አኳያም ጠቀሜታው ጉልህ በመሆኑ ፎረሙ በኢትዮጵያ ዳግም እንዲካሄድ ድርድሮች መደረግ ጀምረዋል፡፡

የስብሰባውን መምጣት በተመለከተ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ንግግሮች መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ነዋይ፣ መንግሥት ስብሰባው እንዲካሄድ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በዚህ ዓመት መጨረሻ ለማካሄድ አሊያም በመጪው ዓመት መጨረሻ ፎረሙ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ እንቅስቃሴው ከወዲሁ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

 አዲስ አበባ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረምን እንድታዘጋጅ በቤንች ኤቨንትስና በካሊብራ ሆስፒታሊቲ መካከል ግንኙነት የተጀመረው ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ተሳክቶ የመጀመርያው ስብሰባ ከአራት ዓመታት በፊት መስተናገዱ ይታወሳል፡፡ በዓመቱም ፎረሙ ዳግመኛ ተካሂዷል፡፡

በሁለቱ ስብሰባዎች ወቅት በርካታ የሆቴል ስምምነቶች መደረጋቸው ሲታወስ፣ ካሊብራ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመወከል ከዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች ጋር በድርድር ሒደቱ መሳተፉን ያስታወሱት አቶ ነዋይ፣ ከ18 በላይ የሆቴል ፕሮጀክቶችን በማደራደርና በማፈራረም ለውጤት ማብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በሥራ ላይ የሚገኙትን ጎልደን ቱሊፕ፣ ራማዳ እንዲሁም በቅርቡ ሥራ የጀመረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን የስካይ ላይት ሆቴልንም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወገን በማማከር መሳተፉንም አቶ ነዋይ ጠቅሰዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን ስፐርስ ስቴክ የተሰኘውን ስፔሻሊቲ የፍራንቻይዝ ሬስቶራንት በማደራደር ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ሥራ እንዲጀምር በማስቻል ጭምር አስተዋጽኦ የነበረው ካሊብራ፣ ኤም ጋለሪ ባይ ሶፊቴል፣ ፑል ማን፣ ኖቮቴል፣ ዊንድሃም ጋርደን፣ ዊንድሃም ሪዞርት፣ ሒልተን ጋርደኒንግ የተባሉትን ጨምሮ 18 የሆቴል ፕሮጀክቶችን በማማከር እየተሳተፈ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የአገር ውስጥ ብራንድ ከሆኑት ውስጥም ካፒታል ሆቴልና ስፓ ከዋና ዋናዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ከሚቀርቡ ልዩ ልዩ ሪፖርቶች መካከል ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ የተሰኘውና ዋና መገኛውን በናይጄሪያ ያደረገው ተቋም የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በአፍሪካ በየዓመቱ የሚታየውን የሆቴል ኢንዱስትሪ የሚቃኙ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ተቋሙ ይፋ ያደረገው ሪፖርት በአፍሪካ እየተካሄዱ ከሚገኙ ዋና ዋና የሆቴል ኢንቨስትመንቶች መካከል ከአሥር ዋና ዋና አገሮች መካከል፣ ከግብፅና ከናይጄሪያ በመከተል ኢትዮጵያም በዚህ መስክ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችበትን የሆቴል ኢንቨስትመንት እያካሄደች ትገኛለች፡፡ ካቻምና 20 ያህል የዓለም አቀፍና የአፍሪካ ሆቴል ብራንዶች ስምምነት መፈረማቸውን ያጣቀሰው ሪፖርቱ፣ ይህ ቁጥር ዓምና ወደ 31 ከፍ ማለቱንም አስፍሯል፡፡ እነዚህ ሆቴሎች ከአምስት ሺሕ በላይ ክፍሎች ያሏቸው ከመሆናቸውም በላይ ለአገሪቱ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክቱ ተብራርቷል፡፡ በከተሞች ከሚካሄዱ የሆቴል ኢንቨስትመንቶች መካከል ከአፍሪካ ከተሞች አዲስ አበባ ቀዳሚ የሆነችበትንም አኃዝ ኩባንያው ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ እንደ አቶ ነዋይ ከሆነም ካሊብራ ያማከራቸው ፕሮጀክቶች እስካሁን ከ6,000 በላይ የሥራ ዕድል ያስገኙና ከ3,500 በላይ ክፍሎችን ለአገልግሎት ለማብቃት የሚያስችሉ ናቸው፡፡  

የሆቴልና መስተንግዶ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን የሚመሩ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት እንደመሆኑም የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የሚደረጉበት መድረክ መሆኑም ስብሰባውን ለማዘጋጀት አገሮች ፍላጎታቸውን ያሳዩበታል፡፡ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረምን የሚያዘጋጀው ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያም በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑ አገሮች እንዲሁም የሰሜን አፍሪካ ቀጣናን የሚያዳርሱ ልዩ ልዩ የሆቴልና የኢንቨስትመንት መርኃ ግብሮችን ማስተናገድ ጀምሯል፡፡ ኩባንያው በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በመከከለኛው ምሥራቅ ከሆቴል ባሻገር በአየር ትራንስፖርት ዘርፍም ተመሳሳይ ፎረሞችን በማሰናዳት ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች