Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ቢራ ፋብሪካ ምርት ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመት 1.6 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም እንዳለው የተነገረለትና ከአንድ ወር በኋላ ምርቱን ለገበያ እንደሚያቀርብ ያስታወቀው አዲስ ቢራ ፋብሪካ፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ሥራ ለመጀመር መቃረቡን ገለጸ፡፡  

ይርጋ ኃይሌና ቤተሰቦቹ ሥር ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች በተለይ በኢንዱስትሪው መስክ ካንጋሮ ፕላስት ግሩፕ በሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች ሥር የተካተተው አዲሱ የቢራ ፋብሪካ ዩናይትድ ቢቨሬጅ አክሲዮን ማኅበር የሚል መጠሪያ ያለው ነው፡፡ ይኼውም ሞሪሸስ ከሚገኘው ዩናይትድ አፍሪካ ቢቨሬጅ ጋር በተደረገ የሽርክና የንግድ ስምምነት አማካይነት በሁለቱ ወገኖች የጋራ ኢንቨስትመንት የተመሠረተ ፋብሪካ እንደሆነ የገለጹት የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ይርጋ ናቸው፡፡

አቶ ኤፍሬም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ገበያ የሚቀላቀለው የዩናይትድ ቢራ ፋብሪካ በላጋር ምርት ይጀመራል፡፡ በሞጆ ከተማ በ25 ሔክታር መሬት ስፋት ይዞታ ውስጥ የተገነባው ፋብሪካ ለወደፊት በማልት መጠጦችና በሌሎችም ምርቶች ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ ታስቦ ይህን ያህል ቦታ መረከቡን ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው በዓመት ከሚያመርተው 1.6 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ በተጨማሪ፣ 800 ሺሕ ቶን የምርት ማሸጊያዎችን የማምረት አቅም ይዞ እንደመጣም ተጠቅሷል፡፡  

ፋብሪካው ለቢራ ጠመቃ የሚረዱትን ማሽነሪዎች ክሮነስ ግሩፕ ከተሰኘው የጀርመን ኩባንያ በመግዛት መግጠሙን አስታውቀው፣ በመጠጥ ኢንዱስትሪው መስክ ለአፍሪካ አዲስ የሆነውንና በዲጂታል ሥርዓት የሚመራውን የሲስተም አፕሊኬሽንና የምርት መቆጣጠሪያ የቴክኖሎጂ ሥልት በመጠቀም የምርት ሒደቱን እንደሚመራም ተብራርቷል፡፡

ሥራ ሲጀምር ለ230 ሠራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚጠበቀው ይህ ፋብሪካ፣ የምርቱ መዳረሻ ገበያዎች አዲስ አበባና አካባቢዋን በማድረግ እንደሚጀምርም አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ሥራ ሊጀምር በተቃረበበት ወቅት የቢራ ማስታወቂያዎች ክልከላ መውጣቱ ችግር እንደሆነበት ያስታወቁት አቶ ኤፍሬም፣ ለምርት ግብዓት ግዥ የሚያስፈልገውን በቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘትም ሥጋት ከሆኑበት ጉዳዮች መካከል አንኳር ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የቢራ ጣዕምና ይዘቱ ላይ በተደረገ ጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲመረት ይደረጋል ያሉት ቢራ ስያሜው ማን እንደሆነ ከመግለጽ የተቆጠቡት አቶ ኤፍሬም፣ የቢራውን መጠሪያ ወይም ብራንድ ስያሜ ከወር በኋላ ይፋ ለማድረግ እንደተፈለገ አስታውቀዋል፡፡ ከቢራ ስያሜው ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ‹‹አይቤክስ ዋልያ›› በሚለው መጠሪያ ሳቢያ የይገባኛል ጥያቄ በሐይኒከንና በካንጋሮ ፕላስት ግሩፕ መካከል ፍርድ ቤት ያዳረሰ ሙግት ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዩናይትድ ቢቨሬጅ አክሲዮን ማኅበር በካንጋሮ ፕላስት ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩት አንዱ ኩባንያ ሲሆን፣ እነዚህን ጨምሮ ኢትዮ ሲሚንቶ፣ ዩኒቨርሳል ፉድስ፣ እንይ ኢትዮጵያ የአበባ ማምረቻ፣ እንይ ኮንስትራክሽን፣ ስሪኤፍ ፈርኒቸር፣ ፓል ኢትዮጵያ፣ ይርጋ ኃይሌ የገበያ ማከልና ሌሎችንም ኩባንያዎች በቤተሰብ ደረጃ የሚተዳደሩ ኩባንያዎች ያቀፈ የግሩፕ ኩባንያዎች ስብስብ ከተሸጋገረ ቆየት ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዓመታዊ የቢራ ምርት 14 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር እንደደረሰ ሲገመት፣ አሥር ያህል ፋብሪካዎችም በሥራ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዩናትድ ቢራ ፋብሪካ ሥራ መጀመር የአገሪቱን የቢራ ምርት ከ15 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ ከማድረሱም ባሻገር፣ ለብቅልና ገብስ አምራቾች ተጨማሪ ገበያ ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ 

አቶ ይርጋ ኃይሌ በመርካቶ አካባቢ ለዘመናት የታወቀ የንግድ መጠሪያ እስከ መሆን የደረሱበትን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን እስከ ሕልፈታቸው ድረስ ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ የዩናይትድ ቢራ ፋብሪካ ፕሮጀክት ከጥንስሱ ጀምሮ በታላቅ ወንድማቸው አቶ በላቸው ይርጋ የተጀመረ እንደነበር የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ከወንድማቸው ሕልፈት በኋላ የተጀመረውን ፕሮጀክት ከግብ በማድረሳቸው መደሰታቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች