Wednesday, May 29, 2024

መንግሥት ያረቀቀው የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ ፖለቲካዊ ፋይዳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚና የሰላም ኢንስቲትዩት ... 2018 ይፋ ባደረገው ዓለም አቀፍ የሰላም ኢንዴክስ መረጃ መሠረት፣ የሰላም ሁኔታቸውን በመተንተን ከተመዘኑ 163 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 139 ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚሁ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 44 የአፍሪካ አገሮች ሲመዘን ደግሞ 38 ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚህ ምድብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙት እንደ ቅደም ተከተላቸው ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ናቸው።

በዚህ የዓለም የሰላም ኢንዴክስ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ባገኘችው ደረጃ ከዓመት በፊት ትገኝበት ከነበረው በስድስት ደረጃ አሽቆልቁላለች። ለዚህም ተጠቃሽ የሆኑት ምክንያቶች የአገር ውስጥ የእርስ በእርስ ፖለቲካዊ ግጭትና የጦር መሣሪያ ይዞታ መጨመር ዋነኞቹ ናቸው።

‹‹ሃንድ ገን ፖሊሲ›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ የጥናትና መረጃ፣ ተቋም ያቀረበው መረጃ  በኢትዮጵያ በሲቪል ግለሰቦች እጅ የሚገኝ ቀላል የጦር መሣሪያ ይዞታ ..አ. 2017 በተደረገ ግመታ 377,000 እንደሚሆን ያመለክታል።

ይህ የጦር መሣሪያ ግምት በትክክለኛ ቆጠራ ላይ ያልተመሠረተ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ገበያ በሕግ የተከለከለ ከመሆኑ አንፃር ሲመዘን ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህከፍተኛ ደረጃ የጦር መሣሪያ ዝውውር እየጨመረ ከመሆን አልፎ፣ የመንግሥት ሕግ አስከባሪ አካላት በየሳምንቱ የሚይዟቸው የጦር መሣሪያዎች የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን የየዕለት ዘገባዎቻቸው እየሆኑ ይገኛሉ። ይህም የጦር መሣሪያ ዝውውርና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ገበያ መድራቱን ያመላክታል።

ይኼንን የጦር መሣሪያ ዝውውር መጨመር ምክንያትን አስመልክቶ የፌዴራል ፖሊስ ያደረገው አነስተኛ የዳሰሳ ጥናት፣ ከወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ራስን ለመጠበቅ ሲባል መስፋፋቱን ያሳያል።

በመፍትሔነት የተቀየሰው ሕጋዊ ሥነ ሥርዓት

በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የጦር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ የማስገባትና የደራውን ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ግብይትና ዝውውር በሕግ አግባብ ሥነ ሥርዓት ለማስያዝና ለመቆጣጠር መንግሥት አንድ አዋጅ አርቅቋል። 

ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በተዋቀረ የሕግና ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ የቴክኒክ ዕውቀት ባላቸው የባለሙያዎች ቡድን ሲሆን፣ የሕግ ሰነዱ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ የሕግ ሰነድ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፣ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የአገርን፣ የሕዝብን፣ ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የዜጎችንና የሕዝቦችን መብትና ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተረቀቀ መሆኑን የሰነዱ መግቢያ ያስገነዝባል።

በማከልም ግለሰቦች የታጠቋቸው የጦር መሣሪያዎች የኅብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ብቻ ሊውል የሚቻልበትን አሠራር መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ባሉ ሕጎችና አሠራሮች ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን በዝርዝር ሕግ መደንገግና ወጥነት ያለው ሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉ ሕጉ መዘጋጀቱን የሕግ ሰነዱ መግቢያ አንቀጾች ያስረዳሉ። 

ረቂቅ ሕጉ ከዚህ ቀደም ጥብቅ ክልከላ የሚደረግበትን የሲቪል ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ትጥቅ በከፍተኛ ደረጃ በማላላት፣ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ለመታጠቅና ለመገልገል የሚችሉባቸውን የሕግ አግባቦችንም አካቷል።

በዚህም መሠረት የአዕምሮ ሁኔታው የተስተካከለና አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው ተቆጣጣሪ ተቋም የታመነበት ማንኛውም ዕድሜው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ያለው ሰው፣ጦር መሣሪያ የመያዝና የመገልገል ሕጋዊ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ያመለክታል።

ከዚህ አኳያ የተጨማሪ መመዘኛዎች አመላካች የሆኑ መሥፈርቶች በረቂቅ ሕጉ የተካተቱ ሲሆን፣ የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት፣ ቋሚ አድራሻና መተዳደሪያ ወይም ገቢ ያለው፣ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ወይም በሕግ ችሎታውን ያላጣ፣ የጦር መሣሪያን አጠቃቀምና በዚህ በሕግ የሚጣልበትን ግዴታ በተመለከተ ግንዛቤ ያለው ወይም ትምህርት የሚወስድ ለመሆኑ በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት ሊሆን እንደሚገባ ይዘረዝራል። 

ለግለሰብ የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ አንድ ሽጉጥ ወይም አንድ አውቶማቲክ ያልሆነ ጠብመንጃ ወይም አንድ ግማሽ አውቶማቲክ ጠብመንጃ ብቻ መሆኑን፣ እንዲሁም ለግለሰቦች የተፈቀደውን የጥይት ብዛት የሰላም ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ይደነግጋል።

ራሳቸውን ለመከላከልና የአካባቢያቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በተለምዶ የጦር መሣሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑና የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎች፣ የያዙት የጦር መሣሪያ በረቂቅ ሕጉ ለግለሰብ ያልተከተለ የጦር መሣሪያ ዓይነት እስከሆነ ድረስ፣ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ በሚወጣ የጊዜ ሰሌዳ በየአካባቢው ሥልጣን ወደተሰጠው ተቋም በአካል ቀርበው ፈቃድ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውና ለአንድ ሰው የሚፈቀደውም አንድ የጦር መሣሪያ ብቻ እንደሆነ የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል ፈጽሞ ክልክል የነበረውን የአገር ውስጥ የጦር መሣሪያ ንግድ በመተው፣ ለአገር ውስጥ የጦር መሣሪያ ንግድ በሕግ እንቀጽ በረቂቅ ሕጉ ተካቶ ቀርቧል።

በዚህም መሠረት የሕግ ሥልጣን በሚሰጠው አካል መሥፈርቶችን አሟልተው ፈቃድ ማግኘት የሚችሉ አካላት የጦር መሣሪያ ወደ አገር ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ ማከማቸት፣ መሸጥ፣ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሠልጠን ወይም መጠገን በሚያስችላቸው የንግድ ሥራዎች መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ በረቂቅ ሕጉ ተካቷል። 

በተጨማሪም በተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል ሕጋዊ ፈቃድ በማውጣት የጦር መሣሪያ ኤግዚቢሽን ለማሳየትና ከተሠሩ ሃምሳ ዓመት ያለፋቸው የጦር መሣሪያዎችን በቅርስነት ለመያዝ፣ የጦር መሣሪያ በአገር ውስጥ የመደለል ሥራ ለማከናወን እንደሚቻል ያመለክታል። 

በመንግሥት ይዞታ የሚገኝ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር

የተረቀቀው ይኸው አዋጅ በአገሪቱ የሚስተዋለውን አጠቃላይ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመቆጣጠርና ሥርዓት ከማበጀት ባለፈ በመንግሥት አካላት ይዞታ ሥር የሚገኙ የጦር መሣሪያዎችን በተመለከተም፣ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ድንጋጌዎችን አካቷል። ይሁን እንጂ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኝን የጦር መሣሪያ ለመቆጣጠር ሲባል የተረቀቁት አንቀጾች የመከላከያ ሠራዊቱን አይመለከቱም።

በመሆኑም ረቂቅ ሕጉ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት ላይ ትኩረት አድርጓል። ለዚህም ሲባል ረቂቅ ሰነዱ ሕግ አስከባሪ አካላት ለሚለውም የሕግ ትርጓሜን አካቷል።

‹‹ሕግ አስከባሪ ማለት የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሲሆኑ፣ በፖሊስ አካላት የአካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚደራጁ የግል ታጣቂዎችን ይጨምራል፤›› በማለት ሕጋዊ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡

እነዚህ ሕግ አስከባሪ የፀጥታ አካላት ሊታጠቁ የሚችሉት የጦር መሣሪያ ዓይነቶች በመወሰን ዓይነቶቹን ይዘረዝራል።

በዚህም መሠረት ሕግ አስከባሪ የፀጥታ አካላት በረቂቅ ሕጉ ተወስኖ እንዲታጠቁ የተፈቀድላቸው የጦር መሣሪያ ዓይነቶች  ሽጉጥ፣ አውቶማቲክ ያልሆነ ወይም ግማሽ አውቶማቲክ የሆነ ጠብመንጃ፣ ቦምብና ሌሎች ተያያዥ ዕቃዎች ሊሆኑ  እንደሚችል ረቂቁ ይገልጻል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት ‹‹አውቶማቲክ ያልሆነ ጠብመንጃ›› ማለት አንድ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የማይችል ማለት ሲሆን፣ ‹‹ግማሽ አውቶማቲክ ጠብመንጃ›› ማለት ደግሞ አንድ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የሚችል እንደሆነ በረቂቁ የቃላት ትርጉም ክፍል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

በዚሁ የረቂቁ የቃላት ትርጓሜ መሠረት ‹‹ሙሉ አውቶማቲክ ጠብመንጃ›› ማለት ከአንድ በላይ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የሚችል ሲሆን፣ ይኼንን ዓይነት መሣሪያ የክልል የሕግ አስከባሪ አካላት መታጠቅ እንደማይችሉ በረቂቅ ሕጉ በክልከላነት ተቀምጧል።

ይሁን እንጂ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለሥራቸው በሚያስፈልገው መጠን ከቀላልና አነስተኛ የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ውስጥ ተመርጦ እንዲታጠቁ ሊፈቀድ እንደሚችል፣ የዚህም ዝርዝር የረቂቅ አዋጁን መፅደቅ ተከትሎ በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ይገልጻል።

በሌላ በኩል የሰላም ሚኒስቴር ለእያንዳንዱ የሕግ አስከባሪ ተቋም እንደየ ሁኔታው ለሥራው የሚያስፈልገውንና የሚፈቀደውን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና አስተዳደር በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ በማውጣት እንዲወስን ረቂቅ ሕጉ ሥልጣን ይሰጠዋል።

የፀጥታ አስከባሪ ተቋም አባላት የጦር መሣሪያ የሚይዙት በተቋማቸው ለሥራቸው አላስፈላጊ ሆኖ ሲሰጣቸው እንደሆነ የሚገልጽ ረቂቅ ድንጋጌ የሕግ ሰነዱ የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ የሕግ አስከባሪ አባላት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የተቋማቸውን የደንብ ልብስ መልበስ ወይም ፈቃዳቸውን ወይም እንደ አግባብነቱ የሥራ መታወቂያ ወረቀት መያዝ እንደሚኖርባቸውም ያመለክታል።

የሕግ አስከባሪ ተቋማቱ አባላቶቻቸው የጦር መሣሪያን እንዲይዙ የሚፈቅዱት ተቋማትን ለመጠበቅ፣ የሕግ ማስከበር ሥራ ወይም ኦፕሬሽን ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ፣ የኃይል ተግባር ሊያጋጥም ይችላል በሚል እምነት ለሥራ ሲሰማሩ፣ ለራስ መጠበቂያ ያስፈልጋቸዋል በሚል ምክንያት እንዲታጠቁ ሲያስፈልግ ብቻ እንደሆነም የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

የሕግ ሰነዱ አንድምታና ፋይዳ

ሪቂቅ ሕጉን የተመለከቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደኅንነት ባለሙያዎች፣ የሕግ ሰነዱ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና በአገሪቱ የሚስተዋለውን የተዝረከረከ የጦር መሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም ፈር ሊያስይዝ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ረቂቅ ሕጉ ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን ነገር ግን እየተሸረሸረ የመጣውን ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ሕጋዊ መብት ጨርሶ ከመጥፋቱ በፊት ሊታደገው እንደሚችል ያስረዳሉ።

አንድ መንግሥት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ሕጋዊ መብት አለው የሚባለው፣ ኃይልን የመጠቀም መብትን በብቸኝነት ሲይዝና ያልተማከለ መንግሥታዊ አስተዳደርን ለማስፈን ራሱ ማዕከላዊው መንግሥት ኃይልን የመጠቀም መብቱን በተገደበ ሁኔታ ለሌሎች ፈቅዶ ሲያከፋፍል መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓትና የታክስ ሥርዓትን ያሰፈነ እንደሆነ፣ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብቱን ያሰፈነና በተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ መንግሥት እንደሚያስብለው ይገልጻሉ።

ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ሲመዘን ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብቱ እየተዳከመ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። የፌዴራል መንግሥቱን ኃይል በብቸኝነት የመጠቀም መብት እያዳከሙ ከሚገኙት መካከል ራስን በራስ ከማስተዳደር ፖለቲካዊ መብቶች፣ እንዲሁም ብሔር ተኮር ከሆኑ ፖለቲካዊ ጡዘቶችን መነሻ ያደረገ የክልል መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎች ከመደበኛ የሕግ ማስከበር ተልዕኮ በመውጣት የኃይል ሚዛን ፉክክር ውስጥ መግባታቸውና የፀጥታ አካላቱም ከሕግ ማስከበር ተግባር በዘለለ ሁኔታ፣ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማስፈጸም የመሠለፍ አዝማሚያ በማሳየት ላይ የሚገኙ መሆኑን ያመለክታሉ።

የፌዴራል መንግሥት በወንጀል የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልሎችን ድጋፍ ማግኘት አለመቻሉ፣ ወይም በራሱ ማድረግ አለመቻሉ በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቋሚ እንደሆነም አንስተዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የታጠቁ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ማስፈታት አለመቻል ወይም የታጠቀው ኃይል ትጥቅ አልፈታም ብሎ ወደ ጫካ መግባቱ ሌላው አመላካች አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የተነሳውን የድንበር ውዝግብ መፍታት የሚቻልበት የሕግ ሥነ ሥርዓትን ወደ ጎን በመተው ውዝግቡን በኃይል ለመፍታት የመፈለግ፣ በድንበሮቻቸው አካባቢ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ብቻ የተሰጣቸውን የፖሊስ ኃይሎቻቸውን በማሠለፍ ለጦርነት የሚገፋፉ ቃላትን የመወራወር ተግባር ውስጥ መግባታቸውን ያወሳሉ።

ይኼንን ችግር የፌዴራል መንግሥት በፍጥነት ከመፍታት ይልቅ የተራዘመ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆይ ማድረጉ፣ የክልሎቹ ነዋሪዎችንም የጦር መሣሪያ በነፍስ ወከፍ እንዲታጠቁ እያደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል የክልል ሕግ አስከባሪ አካላት የታጠቁት የጦር መሣሪያ ዓይነትና ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመደበኛ የፖሊስ ኃይል ከሚፈቅደው ደረጃ የገዘፈ ከመሆን ባለፈ፣ የፌደራል መንግሥትን የኃይል የበላይነት ጭምር የሚገዳደር መሆኑ ሥጋትን የሚያጭር እንደሆነ ይናገራሉ።

የፖለቲካ ችግሮቹን በፍጥነት መፍታት አለመቻላቸውና በዚህ የጊዜ መጓተት ውስጥ በነፍስ ወከፍ እየታጠቀ የሚገኘው ማኅበረሰብ የፖለቲካ ግጭቶቹ ተዋናይ እየሆነ መምጣቱ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ያመለክታሉ። ሌላውም ማኅበረሰብ ራሱን ለመከላከል መታጠቅን አማራጭ እያደረገ መሆኑ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣቱን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

ይህ አዝማሚያ በፍጥነት መፍትሔ ካልተበጀለት ለፖለቲካ ችግሮቹ በራሱ የኃይል መፍትሔ ለመስጠት የመደራጀት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል፣ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ግጭቶቹ ማንነትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ምቹ እንደሚያደርገው ያስገነዝባሉ።

ይህ ሁኔታ በፍጥነት መፍትሔ ካለገኘ በደቡብ ሱዳን እንደተፈጠረው የተከፋፈለ የኃይል ሚዛን ሁኔታ ውስጥ አገሪቱን በመክተት፣ የተዳከመ መንግሥት ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።

በመሆኑም  የተረቀቀው አዋጅ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን፣ ነገር ግን ፖለቲካዊ መፍትሔም መሠረታዊ ስለመሆኑ አጽንኦት በመስጠት ያስረዳሉ።

ፖለቲካዊ መፍትሔው በመሠረታዊነት አብሮ ካልታሰበበት ሕጉንም ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይችል፣ በመሆኑም የጦር መሣሪያ ታጥቆ የተደራጀ የፖለቲካ ቡድን ወይም የዝርፊያ ቡድን እንቅስቃሴ የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

የረቂቅ ሕጉን ዓላማና ፋይዳ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ጦርነት መሣሪያ አስተዳዳር ሕግ ባለመኖሩ የሕግ ማቀፍ ለማበጀትና የክልል የፀጥታ መዋቅሮች የትጥቅ ደረጃንና አስተዳደሩን ለመቅረፅ ሲባል መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የጦር መሣሪያ መያዝና ማዘዋወር በኢትዮጵያ ወንጀል መሆኑን በሌሎች አገሮች ግን እንደ አንድ ሀብት እንደሚቆጠር የገለጹት ኃላፊው በዚህ የተነሳም ከፍተኛ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር መኖሩን አመልክተዋል።

ከወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ጋር ተያይዞ ሕገወጥ ይዞታና ዝውውር መጨመሩን፣ ስለሆነም በአገር አቀፍ ደረጃ የፌዴራል መንግሥት በበላይነት የሚመራው የጦር መሣሪያ አስተዳደር ሕግ ማስፈለጉን አስረድተዋል።

ረቂቅ ሕጉ የክልል የፀጥታና የሕግ ማስከበር ተቋማት የጦር መሣሪያ ትጥቅ ምን መምሰል እንዳለበትም የሚወስን መሆኑን አመልክተዋል።

‹‹በአንዳንድ  ክልሎች የሚገኙ የፖሊስ ተቋማት ከፌዴራል ፖሊስ በላይ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ይገኛሉ፤›› ያሉት ኃላፊው፣ የሕግ ማዕቀፉ ይኼንን ሁኔታ እንደሚያስተካክልም ተናግረዋል።

ሕጉ ከፀደቀ በኋላ ይኼንን ተግባራዊ ለማድረግ ከተቀመጠው ደረጃ በላይ የታጠቁ ክልሎች ፈቃደኛ ባይሆኑ እንዴት ማስፈጸም እንደሚቻል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ሁሉም ክልሎች እንደሚያከብሩ እሳቤ መኖሩን ካልሆነም የፌዴራል መንግሥት በበላይነት የሚመራው በመሆኑ በማስገደድም ማስፈጸም እንደሚቻል ገልጸዋል።

ነገር ግን ረቂቅ ሕጉን አስመልክቶ ከክልሎች ጋር ውይይት እንደተደረገና ሁሉም  ክልሎች የሕጉን ዓላማ እንደሚቀበሉት መግባባት መቻሉን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ጉዳዮች ለአብነት ያህልም በረቂቅ ሕጉ ለፌዴራል ፖሊስ የተሰጠው ሥልጣንን በተመለከተ፣ ከክልል መንግሥታት የአስተዳደር ሥልጣን ጋር የሚጣረስ ስለመሆኑ በክፍተት መነሳቱንና ይኼንን በግብዓትነት በመቀመበል የመፍትሔ አማራጮችን ለማካተት መታቀዱን አስታውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -