Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየካራማራ - ጅግጅጋ ድል 41ኛ ዓመት

የካራማራ – ጅግጅጋ ድል 41ኛ ዓመት

ቀን:

ዞሲማስ ሚካኤል ከሚኖርበት የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ 15 ቀበሌ 28 አዳራሽ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. በዕለተ እሑድ ምሽት ለወጣቶች የሚሰጠውን የፖለቲካ ንቃት (ትምህርት) እየተከታተለ ነበር፡፡ አዳራሹ ሙሉ ነው፡፡ ድንገት ውይይቱ ተቋረጠ፡፡ በቀበሌው ነዋሪ የሆነው ወጣቱ ተዋናይና የፕሮግራም አስተዋዋቂ በኋላ መቶ አለቃ፣ አሁን የማስታወቂያ ባለሙያ ብንያም በቀለ፣ ‹‹የምሥራች አለኝ›› እያለ ከመድረክ ላይ ወጣ፡፡ አዳራሹ ፀጥ ረጭ አለ፡፡ ምን ይሆን? ብሎ ጆሮውንም ቀሰረ፡፡

 ‹‹ጀግናው አንደኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዛሬ የሶማሊያን ወራሪ ደምስሶ ካራማራን  ነፃ አውጥቷል፤›› ሲልም አስተጋባ፡፡ ከአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ የምሽት ዜና አንደበተ ርቱዑ ታደሰ ሙሉነህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበሰረውን የድል ዜና ነው ለቀበሌው ወጣት ብንያም ያስተጋባው፡፡

ዞሲማስና በአዳራሹ የተገኘው ወጣት፣ ‹‹አያ ሆሆ ማታ ነው ድሌ፣ ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ›› እያቀነቀነ አዳራሹን ለቆ ወጣ፡፡ በአዋሬ በቀበሌ 28 ሜዳ አድርጎ የድል ሆታ እያሰማ ካዛንቺስ ዘለቀ፡፡ ‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ›› እያለም በኅብረ ዜማው ካዛንቺስን አደመቃት፡፡

ከአራት አሠርታት በፊት ኢትዮጵያ ከወራሪው የሶማሊያ ሠራዊት ጋር ጦርነት የገጠመችበት ነበር፡፡ በ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› ቅዠት የተለከፉት የሶማሊያ መሪዎች እነዚያድ ባሬ በ1969 ዓ.ም. በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቀው ተቆጣጥረው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር መሪ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታሪካዊውን የእናት አገር ጥሪ ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. ያቀረቡት፡፡

ሕዝቡ የሶማሊያን ወረራ እንዲገታ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጥሪ ያቀረቡት ወታደራዊ ልብስ ለብሰውና ፊታቸውን አኮሳትረው ነበር፡፡ እኛና አብዮቱ በተሰኘው የሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ መጽሐፍ ላይ የጥሪውን ይዘት በጥቅሉ እንዲህ ተቀምጧል፡፡

‹‹…ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአብዮታዊት እናት አገራችን ዳር ድንበርና የማይገሰሰው አንድነታችን በውጭ ኃይል እየተደፈረ ነው፡፡ በአብዮታችንና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ኅልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራና ድፍረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል… ለብዙ ሺሕ ዘመናት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ክብርንና ነፃነትህን ለመድፈር፣ አገርህን ለመቁረስ… የተጀመረውን ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሠልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ! ዝመት! ተዋጋ! እናሸንፋለን!!››

የጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተነስ ታጠቅ ዝመትን ተከትሎ ቀድሞ ሥጋ ሜዳ ይባል በነበረውና በክተቱ አዋጅ መሠረት ታጠቅ የጦር ሠፈር በተባለው ቦታ ለሦስት ወራት የሠለጠነው 300 ሺሕ ሚሊሺያ (ሕዝባዊ ሠራዊት) ከመደበኛው ጦር ጋር ሆኖ በአብዮት አደባባይ ታላቅ ሠልፍ አሳየ፡፡ በዘመኑ አጠራርዋ ከአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጎን በሶቭየት ኅብረት አማካይነት ሶሻሊስት አገሮች ከጎኗ ሲቆሙ በተለይም ኩባ እና ደቡብ የመን እግረኛ ሠራዊት፣ ታንከኞችና መድፈኞችን በመላክ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እኛና አብዮቱ ታሪካዊ ክንውኑን እንዲህ ዘክሮታል፡፡

‹‹ኦጋዴንን ተቆጣጥሮ የያዘውን የሶማሊያን ጦር በተባበረ ኃይል ወግቶ ለማስወጣት ኩባ በጄኔራል ኦቸዋ የሚመራ ከሠላሳ ሺሕ በላይ ወታደሮች አሠልፋ ወሳኝ ውጊያ አካሂዳለች፡፡ የሶማሊያን ጦር ለመውጋት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር የሚሠለፉ የደቡብ የመን የታንከኛና የመድፈኛ ክፍሎችን ልካለች፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራዊትና የውጭ መንግሥት ወታደሮችን አስተባብሮ በበላይነት የሚመራና የሚዋጋ የጦር አዛዥ ሶቪዬት ኅብረት ጄኔራል ፔትሮቭ የሚባሉ ታዋቂ የጦር ጄኔራል ላከች፡፡ በጦር ክፍሎችም አማካሪ መኮንኖች መደበች፡፡ በዚህ አኳኋን የተደራጀ ግዙፍ ጦር በሊቀመንበር መንግሥቱ ጠቅላይ አዛዥነት እየተመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሶማሊያን ጦር አንኮታኩቶ ብዙውን ገድሎና ማርኮ በሽሽት ያመለጠውን ቀሪ ጦር ከግዛታችን በማባረር የኢትዮጵያን አንድነት አስጠበቀ፡፡ ድንበራችንንም አስከበረ፡፡

‹‹የሶማሊያ ጦር የቆሬን የመከላከያ ቀጣና በጎን በማለፍ በጃርሶና በኮምቦልቻ በኩል አድርጎ ድሬዳዋን፣ በፌዲስና ሐኪም ጋራ በኩል ሐረርን ለመያዝ ከታኅሣሥ 15 ቀን 1970 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ ማጥቃት ሰነዘረ፡፡ የኢትዮጵያና የኩባ ሠራዊትም ወደ ሐረር በመገስገስ ላይ የነበረውን ፌዲስ ላይ፣ ድሬዳዋን ለመያዝ በመገስገስ ላይ የነበረውን ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው አጠገብ እንደደረሰ ሁለት ከፍተኛ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዎችን አካሄደ፡፡ በዚህ መልሶ ማጥቃትም ኮሎኔል ፋንታ በላይና (በኋላ ሜጀር ጄኔራል) የአየር ኃይል ባልደረቦች እንደ አንድ እግረኛ ወታደር ጠበንጃ ይዘው በግንባር ተሠልፈው በጀግንነት ተፋልመዋል፡፡ በዚህ ቀውጢ ሰዓትም ለራሳቸው ሳይሳሱ የጠላትን ጦር በአየር ደብድበዋል፡፡

ከጠላት ወገንም ወደ ሦስት ሺሕ የሚሆን ሠራዊት ደመሰሱ፡፡ ጠላት በተለይ በድሬዳዋ አካባቢ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ታንኮች ብዛት ያላቸው መድፎች የተለያዩ ቀላልና ከባድ መሣሪያዎች በከፊል ሲወድምበት ከፊሉን ደግሞ ጥሎ በመሸሹ ከፍተኛ የንብረት ኪሳራ ደረሰበት፡፡ በዚህ ሽሽት ገና ከእሽግ ያልወጡ የኔቶ መሣሪያዎችም ተማርከዋል፡፡ የሶማሊያ ጦር ከዚህ ሽንፈት በኋላ ዋናው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ባልተጠበቀና ባልታሰበ ፍጥነት ይዞታውን በመልቀቅ መፈርጠጡን ተያያዘው፡፡

‹‹ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና የኩባ ሠራዊት ቀደም ብሎ በታቀደው መሠረት በየካቲት ወር 1970 ዓ.ም. ዋናውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻቸውን ጀመሩ፡፡ አብዛኛውን ምሥራቃዊ ደጋ ክፍል ነፃ በማውጣት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. እጅግ ስትራቴጂካዊ የሆነውን የካራማራን ኮረብታና አካባቢ ከወራሪው ጠላት አስለቀቀ፡፡ የካቲት 27 ቀን 1970 ዓ.ም. የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋን በቁጥጥር ስር አውሎ ሰንደቅ ዓላማችን በነፃነት እንድትውለበለብ አደረገ፡፡

የ41ኛው ዓመት ክብረ በዓል

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ያስከበረውን የካራማራ ጅግጅጋ ድል 41ኛ ዓመት የቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በወቅቱ የደርጉ ዋና ጸሐፊ (በኋላ የኢሕዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ረዳት ዋና ጸሐፊ በኋላ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታን ጨምሮ በጦርነቱ የዋሉ ጄኔራል መኰንኖችና ሌሎችም በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅት ተከብሯል፡፡ በትግላችን ሐውልትና በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ጉንጉን አበባም ተቀምጧል፡፡

ዞሲማስ፣ የካራማራ -ጅግጅጋ ድል 41ኛ ዓመት ላይ ሆኖ የዘመኑን አብዮታዊ መዝሙር በምልሰት አስታወሰና አዝማቹን

‹‹ነፃ አውጪው አብዮታዊ ጦራችን፣

እንደ ካራማራ እንደ ጭናስከን…›› እያለ ጉዞውን ቀጠለ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...