Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአውሮፕላን አደጋው ምርመራ እስኪጠናቀቅ በትዕግሥት እንጠብቅ!

በመጀመርያ እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 የበረራ ቁጥር ET 302 አውሮፕላን ላይ በደረሰው አስደንጋጭ አደጋ፣ ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽን መፅናናትን እንደመኛለን፡፡ ይኼንን ዓይነቱ ልብ ሰባሪ አደጋ እኛ ኢትዮጵያዊያንንና የ35 አገሮች ዜጎችን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ዓለም ያስደነገጠና በሐዘን ያቆራመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚገለገሉ በመላው ዓለም የሚገኙ የአገር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች፣ የታላላቅ ኩባንያዎች መሪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ግለሰቦች፣ ወዘተ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጥልቅ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን የአደጋውን ምርመራ በተመለከተ በከፍተኛ ትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡ የአደጋው ምርመራ ተጠናቆ ሪፖርቱ እስከሚቀርብ ድረስ፣ ከማናቸውም ዓይነት ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች መታቀብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ድንጋጌን ጠንቅቀን በመረዳት፣ በጨዋነት የሟች ቤተሰቦችን እያፅናናን መቆየት አለብን፡፡

እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) አሠራር መሠረት ማንኛውም ዓይነት የአውሮፕላን አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅት፣ በሲቪል አቪዬሽን ባለሙያዎች የአደጋ ምርመራ ሥራ ተከናውኖ ሪፖርቱ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ የአደጋውን መንስዔ በተመለከተ መናገር ከግምት ያለፈ አይሆንም፡፡ ግምት ደግሞ እውነት አይደለም፡፡ በመሆኑም ማናቸውም ወገኖች ስለአደጋው መንስዔ እንዳይናገሩ ይከለከላሉ፡፡ ይህ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ገዥ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ አሠራር ውጪ ማንኛውም አካል ስለአደጋው መንስዔ መናገር አይችልም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተቋቋመው የአደጋ ምርመራ ቡድንና ከውጭ የመጡ ባለሙያዎች የሚያከናውኑትን የአደጋ ምርመራ ሒደት አጠናቀው እስከሚያቀርቡ ድረስ፣ ሁሉም ወገኖች በትዕግሥት የመጠባበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡

የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአውሮፕላን አደጋን በተመለከተ በመተዳደሪያ ደንቡ ባሰፈረው አንቀጽ፣ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ዋና ዓላማ ትክክለኛውን የአደጋ መንስዔ በመረዳት ወደፊት ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል መሆኑን ያስታውቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ለመወነጃጀልና ለመወቃቀስ ምርመራ እንደማይከናወን በማስረዳት፣ በአውሮፕላን አምራቾችም ሆነ በአየር መንገዶች ላይ የምርመራው ውጤት ሳይጠናቀቅና ሳይታወቅ ጣት መቀሰር እንደማይቻል በአፅንኦት ያሳስባል፡፡ የምርመራው ውጤት ከታወቀም በኋላ ቢሆን የተፈጸመ ስህተት ቢኖር እንኳ በትምህርታዊነቱ መውሰድ ይበጃል እንጂ፣ መወቃቀስ ፋይዳ እንደሌለው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ያስገነዝባል፡፡ በዚህም መሠረት የምርመራው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ተገቢ ካልሆነ ድርጊት መታቀብ ያስፈልጋል፡፡ ለማንም አይጠቅምምና፡፡

በዚህ የሐዘን ወቅት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ክቡር ለሆነው የሰው ሕይወት ነው፡፡ በአውሮፕላኑ አደጋ ላይ ስንነጋገር በተቻለ መጠን በአደጋው ምክንያት ወገኖቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች ማሰብ አለብን፡፡ እነዚህ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች መረጃ ለማግኘት መደበኛ የመገናኛ ብዙኃንና የኢንተርኔት የመረጃ አውታሮችን ሲያስሱ ልንጠነቀቅላቸው ይገባል፡፡ በሐሰተኛና ባልተረጋገጡ መረጃዎች አናወናብዳቸው፡፡ አደጋውን በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶች በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም በከፍተኛ ጥንቃቄ የታጀቡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የአውሮፕላን አደጋው ሰለባዎች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ፣ ቤተሰቦቻቸውን በሽብር ግራ ማጋባት ከጤነኛ ሰዎች አይጠበቅም፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ግራ የሚያጋቡ አስተያየቶች፣ መላ ምቶች፣ ሐሰተኛ ምሥሎችና ስሜትን የሚረብሹ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ከመልቀቅ መታቀብ ያስፈልጋል፡፡ በመደበኛው ሚዲያም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ከእንስሳት በታች የሚያደርግ ባህሪ በመያዝ ሰውን መጉዳት አፀያፊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ሕግ አክብሮ የሚሠራና በበረራ ደኅንነቱም የተመሠከረለት የአገር ሀብት እንደ መሆኑ መጠን፣ በዚህ አሳዛኝና አስደንጋጭ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከጎኑ መቆም አለባቸው፡፡ ይህ ታላቅና ስኬታማ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ክብር እንዳለው በርካቶች ምስክርነታቸውን እየሰጡለት ይገኛል፡፡ ሕግና ሥርዓት አክብሮ በዓለም ታዋቂ ከሆኑ አየር መንገዶች ጋር በመወዳደር ዝና የተጎናፀፈ ከመሆኑም በላይ፣ በስኬት ላይ ስኬት እየደራረበ ለአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት ሆኗል፡፡ በሕግና በሥርዓት ተመርቶ ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚቻልና ለታላቅ ስኬት እንደሚያበቃ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መማር ይቻላል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ተሻግሮ በዓለም ዝነኛ የሆነው አየር መንገዳችን፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ቅርስ በመሆኑ በእጅጉ ልንጠነቀቅለት ይገባል፡፡ አየር መንገዱን ከማናቸውም የፖለቲካ አጀንዳዎች ውጪ በባለቤትነት ስሜት በመደገፍ፣ በዚህ ከባድ ጊዜ ካላስፈላጊ ድርጊቶች መቆጠብ አለብን፡፡ በአጠቃላይ የተጀመረው የአደጋ ምርመራ በአግባቡ ተካሂዶ እውነቱ እስኪታወቅ ድረስ፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በትዕግሥት የመጠባበቅ ኃላፊነት አለብን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...

በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት አንድ ድንጋይ ደጋግሞ እንዳይመታን

ከጣሊያን ቅኝ ተገዥነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኮንፌዴሬሽን፣ ቆየት ብሎም እንደ አንድ የኢትዮያ ግዛት አካል የነበረችው ኤርትራ ከደርግ ሥርዓት መውደቅ በኋላ ነፃ አገር ሆናለች፡፡ ነፃ አገር መሆንና ከኢትዮጽያ ጋር መቀጠል በወቅቱ ብዙ ሲባልለት የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...