በልጃቸው ላይ የደረሰው ያልተጠበቀ አደጋ መላው ቤተሰቡን ድንጋጤ ላይ ጥሏል፡፡ ከሰዓታት በፊት ሞቅ ያለው መኖሪያ ቤታቸው ወደ ሐዘን ቤትነት ተለውጧል፡፡ እንግዳ መቀበያ ክፍሉን የሚያስውቡ ጌጠኛ ሶፋዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች በፕላስቲክ ወንበሮች ተተክተዋል፡፡
የሚያውቋቸውም ሆኑ የማያውቋቸው ሊያፅናኗቸው ጥቁር ለብሰው፣ ነጠላቸውን አዘቅዝቀው ቤቱን ሞልተዋል፡፡ ድንጋጤው ያልለቀቃቸው የሟች ኤልሳቤት ምንውየለት እናት፣ ነጠላቸውን አሸርጠው ቁጭ እንዳሉ ስሟን እየጠሩ የማይሰማ ነገር ያጉተመትማሉ፡፡ የልጃቸውን አሰቃቂ ሞት ከሰሙ ጀምሮ ያለቅሱ ስለነበር ድምፃቸው ተዘግቷል፡፡ አርፎ መቀመጥ አልሆነላቸውም ይንቆራጠጣሉ፡፡ ከጠረጴዛው ላይ የተደረደሩትን የኤልሳን ፎቶዎች ያስተካክላሉ፡፡ ዓይናቸው ዕንባ እንዳጋተ ወደ መቀመጫቸው ይመለሳሉ፡፡ ሁኔታቸውን ያዩ አብረዋቸው ያለቅሳሉ፡፡ ሟቿን የሚያውቁ ስሟን እየጠሩ ‹ዋይ ዋይ› ይላሉ፡፡ ባያውቋትም ሐዘናቸው ተጋብቶባቸው አብረው ያነባሉ፡፡ ያልተጠበቀ መርዶ የሰሙ የቅርብ ዘመዶች ድንኳኑን ገና ከሩቅ ሲያዩ እጆቻቸውን እያርገበገቡ ይጮኻሉ፡፡ ለሰዓታት ሲያለቅሱ የዋሉ የሟች ቤተሰቦች እንደ አዲስ ዕንባቸውን ያዘራሉ፡፡
ሐዘኑን መቋቋም የከበደው የሟች ባለቤት ትከሻው ላይ ጋቢ እንደደረበ ይንቆራጠጣል፡፡ ድንገተኛ ሕመም እንደሚያጣድፈው ሰው ከላይ ከላይ ያቃስታል፡፡ ሁኔታው ያሳዘናቸው ጓደኞቹ አይዞህ እያሉ ሊያፅናኑት ቢሞክሩም፣ ‹‹ታውቋት የለ የእኔን ደርባባ፤›› ብሎ የበለጠ ያነባ ጀመር፡፡ እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን፣ ቢሾፍቱ አካባቢ ተከስክሶ ሕይወታቸውን ካጡ 149 ተሳፋሪዎችና ስምንት የአየር መንገዱ ሠራተኞች መካከል የበረራ አስተናጋጅ ወ/ሮ ኤልሳቤት አንዷ ነች፡፡
የጥንዶቹ የቅርብ ጓደኛ ለሪፖርተር እንዳስረዳው፣ ወ/ሮ ኤልሳቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በመጀመርያ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ከልጅነት ጓደኛዋ ጋር በትዳር ከተጣመሩም ሁለት ዓመት አይሞላቸውም፡፡ አንድ ዓመት ሊሞላው አራት ሳምንታት የቀራት ልጅም አፍርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረችም አራት ዓመት ገደማ ሆኗታል፡፡ ለቤተሰቡም የመጀመርያ ልጅ ስትሆን ሦስት እህቶች አሏት፡፡
‹‹ወደ ናዝሬት ሄደን ለመዝናናት ቀጠሮ ከባሏ ጋር ስንይዝ ጠዋት የምትመለስ ከሆነ ከእሷ ጋር አብሬ ነው የማሳልፈው፡፡ ካልሆነ ግን እንሄዳለን አለኝና ስልኩን ዘጋው፡፡ መልሶ ደወለና 8፡00 ሰዓት ላይ ነው የምመለሰው ብላኛለች ተነስ ውጣ ሲለኝ፣ የአደጋውን ዜና በቴሌቪዥን እያየሁ ነበር፡፡ ከዚያም አደጋ ደርሷል እየተባለ ነው ሚስትህ ደህና ነች ወይ ብዬ ስጠይቀው ስልኩ ተዘጋ፤›› ሲል አደጋው ከመድረሱ በፊት የነበራቸውን ፕሮግራምና 157 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ክስተት የሰሙበትን አጋጣሚ አስታውሷል፡፡ ‹‹እስካሁን መፅናናት አልቻልንም፤›› ሲልም ጓደኛው ያክላል፡፡
ቃሊቲ አካባቢ ከእነ ኤልሳቤት መኖሪያ ወረድ ብሎ ደግሞ ሌላኛው ድንኳን ይገኛል፡፡ የኤልሳቤት የሥራ ባልደረባ የሆነችው አያንቱ ግርማዬ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ነበረች፡፡ በአየር መንገዱ በበረራ አስተጋናጅነት ስትሠራ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረች የሚናገሩት አባቷ ኮማንደር ግርማዬ ደለሳ፣ የልጃቸውን መሞት የሰሙት እንደ ዋዛ በስልክ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመጪው ግንቦት ወር 25 ዓመቷን ትይዝ የነበረችው አያንቱ ሁለተኛ ልጃቸው ነች፡፡
‹‹ያለ ወትሮዬ በጠዋት ከሥራ ተመልሼ ቤት ጋደም ብዬ ነበር፡፡ ሰዎች ስልክ ደውለው አውሮፕላን ተከሰከሰ እየተባለ ነው ብለው ነጉሩን፡፡ እንደሰማን እኔና እናቷ ተያይዘን ወደ አየር መንገድ ሄድን፡፡ እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ምን ማድረግ እንችላለን ልጄ?›› በማለት የመጣውን ለመቀበል ቢቸገሩም፣ መራራውን ሐዘን መጋፈጣቸውን ገልጸዋል፡፡ የታላቅ እህቷ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት ኮማንደር ግርማዬ የወላጅ እናቷ ነገርም አስጨናቂ ነው ብለዋል፡፡
ከታላቅ እህቷ ጋር እንደ ጓደኛም ነበሩ የሚሉት ኮማንደር ግርማዬ፣ እህትማማቾቹ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አብረው እየተረዳዱ መማራቸውን ያስረዳሉ፡፡ የሆነውን ነገር እህቷ አምኖ መቀበል እንደቸገራትና በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤተሰብ የሚፅናናው አስከሬኑ ደርሶት ከቀበረ በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም መንግሥት ማድረግ ያለበትን አድርጎ የልጃቸውን አስከሬን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ልጃቸው በአደጋው መሞቷን አየር መንገዱ ያረጋገጠላቸው የአያንቱ እናት ወ/ሮ ክበቧ ለገሠ፣ የልጃቸውን የመመረቂያ ፎቶ ደርድረው ሙሾ ማውረድ ሥራቸው አድርገውታል፡፡ ነጠላቸውን ወገባቸው ላይ ሸብ አድርገው እየተንጎራደዱ ያነባሉ፡፡ መርዶው ከደረሳቸው ጀምሮ የልጃቸውን ስምና ትውስታ እያነሱ፣ ‹ዋይ ልጄን!› እያሉ ያለ ዕረፍት ያለቅሳሉ፡፡
‹‹ፍልቅልቋ አያንቱ የመጨረሻ ልጄ ብትሆንም የዓይናችን ማረፊያ ነበረች፡፡ ከቤተሰባችንም የተለየች ነበረች፡፡ ለዚህ ነው የተቀጠፈችብኝ፤›› ኮማንደር ግርማዬ ከዕንባቸው እየታገሉ ይናገራሉ፡፡ የአያንቱን ሞት ከማኅበራዊ ሚዲያ የተረዳው የቅርብ ዘመዳቸው ተስፋ መዝገቡ፣ አያንቱን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኛት ከወር በፊት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በወቅቱ ሽቶና ሻምፓኝ በስጦታ ወስዳለት እንደነበረም አስታውሷል፡፡ ልጆቹ በየጊዜው ስጦታ እንደምትልክላቸው አያንቱ ‹‹ፓይለት መሆን እንፈልጋለን ይሉኛል፡፡ የበረራ አስተናጋጅ መሆኗን አያውቁም፡፡ አሁን የቸገረኝ መሞቷን እንዴት አድርጌ እንደማስረዳቸው ነው፤›› ሲል አያንቱ ከመንገድ ያስቀረው ክስተት፣ በመላው ቤተሰቡ ላይ ያሳደረውን ሐዘንና ድንጋጤ ይናገራል፡፡
ሌላው የአደጋው ሰለባ ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሐመድ ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረዳት አብራሪነት መሥራት ከጀመረ አራት ወራትን እንዳስቆጠረ፣ በቋሚነት መሥራት ከጀመረ ደግሞ ሁለት ወራት እንደሆነው ከቤተሰቦቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የ25 ዓመቱ አህመድ ኑር ለእናቱ ወ/ሮ ሙሉሸዋና ለአባቱ አቶ መሐመድ ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ባስመዘገበው አመርቂ የትምህርት ውጤት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሎ በአርክቴክቸር ከሁለት ዓመት በፊት በመጀመርያ ዲግሪ መመረቁ ታውቋል፡፡
በትምህርቱ ታታሪ እንደነበር ያስታወሰው የታላቅ ወንድሙ ጓደኛና የቤተሰቡ የቅርብ ሰው ሐዘኑ ሁሉንም እንደጎዳ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
‹‹በተለይም ወላጅ እናቱ ብትችሉ እንኳን አመዱን አምጡልኝ እያሉ ሐዘናቸውን ይገልጹ እንደነበር፤›› አስረድተዋል፡፡
አደጋው የደረሰበት ቦታ ጨፌ ደንሳ የገበሬ ማኅበር ሲሆን፣ በተለይ አደጋው የደረሰበት የግለሰቦች እርሻ መሆኑን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ማየት ችሏል፡፡
በሥፍራው የአውሮፕላኑ የተለያዩ አካላት ወደ ጥቃቅን ስብርባሪዎች ከመቀየራቸውም በላይ፣ የተሳፋሪዎቹ አልባሳትና ቁሳቁሶች በየቦታው ተበታትነው ይታዩ ነበር፡፡ አደጋው የተከሰተበት ሥፍራ አውሮፕላን የወደቀበት አይመስልም ነበር፡፡
እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡44 ከአየር መሬት ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላኑ ተምዘግዝጎ መውደቁን፣ በተለይም የአውሮፕላኑ የፊተኛው ክፍል የፊት ጎማዎቹን ጨምሮ መሬቱን ሰርስሮ ወደ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሌላው የአውሮፕላኑ ክፍል ግን በአካባቢው ወደ ጥቃቅን ስብርባሪዎች ነው የተቀየረው፡፡
አደጋው በተከሰተበት ሥፍራ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ ኃይለኛ እሳት መፈጠሩና በሰዓቱ አደጋው ወደ ተፈጠረበት ሥፍራ መጠጋት አልቻሉም ነበር፡፡
በሻሂዳ ሁሴንና ዳዊት እንደሻው