እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል አዳራሽ ሁለተኛ ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን በዝግ ያካሄደው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሊፈጽም እየተንቀሳቀሰበት ለሚገኘው ውህደት የሥራ አስፈጻሚው ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ውክልና ሰጠ፡፡
የዕለቱ የጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳ ‹‹ፓርቲው ከሰማያዊ ፓርቲ፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለፍትሕ ንቅናቄ፣ ከመኢዴፓና ከሌሎች ፍላጎት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ሊያደርግ ስላሰበው ውህደት ጉባዔው ተነጋግሮ መወሰንና አቅጣጫ ማስቀመጥ›› የሚል እንደነበር፣ የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዕለቱም ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የጠቅላላላ ጉባዔው አባላት በተጠቀሰው አጀንዳ ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውንና አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አቶ ዋስይሁን አክለው አስረድተዋል፡፡
‹‹በቀን 01/07/2011 ዓ.ም. የተሰበሰብን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ፓርቲው ከሰማያዊ፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለፍትሕ ንቅናቄ፣ ከመኢዴፓና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሊያደርገው ስለፈለገው ውህደት የጉባዔ አባላት በቂ ውይይት ካደረግን በኋላ የውህደቱን አስፈላጊነት ሙሉ ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ከዚህ በታች የተቀመጡት ተግባራት መጠናቀቃቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሲያረጋግጥ ሌላ ተጨማሪ ጉባዔ መጥራት ሳያስፈልግ የውህደቱን ጉዳይ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ጉባዔተኛው የጉባዔውን ሙሉ ውክልና ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ በመወሰን ሰጥቷል፤›› በማለት ጉባዔው ለሥራ አስፈጻሚው የሚከተሉትን ተግባራት እንዲያጣራ ውክልና መስጠቱን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ሥራ አስፈጻሚው፣ የሚመሠረተው አዲሱ ውህድ ፓርቲ ኢዴፓ የታገለላቸውን መሠረታዊ መርሆዎች ማለትም ኅብረ ብሔራዊነት፣ ምክንያታዊነትና አገራዊ አንድነትን የሚያስጠብቅ አገር አቀፍ ፓርቲ አደረጃጀት ይዞ የሚቋቋም መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ ውህደቱ የፓርቲውንና የአባላቱን መሠረታዊ ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ መከናወኑን ሲያረጋግጥ ውህደቱ እንዲፈጸም ወስኗል፡፡
‹‹ውህደቱ ከወረዳ ጀምሮ የሚካሄድና ያለፉ ስህተቶችን በማይደግም መልኩ የሚጠናቀቅ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባዔው የሰየማቸው ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ የፓርቲውን የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ኦዲት አድርጎ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን አቅርቦ ሲያጠናቅቅ፣ ውህደቱን ሙሉ በሙሉ እንዲያስፈጽም በዕለቱ የተገኙ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በሙሉ ድምፅ ወስነዋል፤›› በማለት ኢዴፓ ለሪፖርተር ከላከው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
ኢዴፓ እየተጠቀመበት ያለው የመጠርያ ስም፣ የፓርቲ ዓርማና ሌጋሲ ከውህደቱ በኋላ ለሌላ የማይተላለፉ ለታሪክ ቋሚ ቅርሶች ሆነው እንዲቀመጡ፣ እንዲሁም በፓርቲው ስም የተመዘገቡ የሚንቀሳቀሱም ሆኑ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በዚህ ጉባዔ በተቋቋመው ኮሚቴ ተቆጥረው ከተጠናቀቁ በኋላ፣ የሚመሠረተው አዲሱ ውህድ ፓርቲ ንብረቶች እንዲሆኑ የጉባዔው አባላት በሙሉ ድምፅ መወሰናቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ኢዴፓ ከሰማያዊና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር በዜግነት ፖለቲካ ላይ የሚያተኩር አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት በሒደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲ ከወራት በፊት ለውህደቱ ያመች ዘንድ ራሱን ማክሰሙ ይታወሳል፡፡