የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድር መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በዴንማርክ አርሁስ ከተማ ይጀመራል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ለቅድመ ዝግጅቱ ይረዳው ዘንድ 36ኛው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር ያከናወነ ሲሆን፣ ከፍተኛ ውጤት ያላቸውና የዕድሜ ተገቢነት ያሟሉ አትሌቶች ተመርጠው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ ከ6 ኪሎ ሜትር ርቀት ጀምሮ እስከ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነውን ውድድር ያሰናዳው ፌዴሬሽኑ፣ በርካታ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች መልምሎ በአዲስ አበባ ስታዲዮም እንዲሁም በጫካ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡
በርካታ ውጣ ውረዶች ያሉት የአገር አቋራጭ ውድድር የአትሌቶችን አቅም በመፈተን ይታወቃል፡፡ አባጣ ጎርባጣ፣ ውኃማ፣ እንዲሁም ጭቃማ የመሬት አቀማመጥ መለያው ነው፡፡ ከየካቲት ወር ጀምሮ ዝግጅቱን የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ ባላቸው አሠልጣኞች በመታገዝ ጠዋትና ከሰዓት መርሐ ግብሩ ልምምዱን እያከናወነ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ውድድሩ በሁለቱም ፆታ በአዋቂዎች እንዲሁም በታዳጊዎች ዘርፍ የሚከናወን ሲሆን፣ በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር፣ በሴቶች 8 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም በታዳጊ ወንዶች 8 ኪሎ ሜትርና ታዳጊ ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር ርቀት አትሌቶች ይፎካከራሉ፡፡
ከወዲሁ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ኬንያውያን ትልቅ ግምት ተችሯቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2017 በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው 42ኛው አገር አቋራጭ ውድድር ኬንያ በ4 ወርቅ፣ በ5 ብርና በ3 ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳልያ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያ በአንፃሩ በ4 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ1 ነሐስ ዘጠኝ ሜዳልያዎችን በማምጣት ሁለተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡
በመካከለኛው ርቀት በግሉ፣ እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን በመሠለፍ ብቃቱን እያስመሰከረ የሚገኘው ሰለሞን ባርጋ በዚህ ውድድር ይጠበቃል፡፡ ሰለሞን ጃንሜዳ በተከናወነው ውድድር ላይ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች 31፡18፡36 በመግባት ነበር ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለው፡፡
እ.ኤ.አ. 1973 በተጀመረው የአገር አቋራጭ ውድድር ስማቸውንን በደማቁ ካሠፈሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል እ.ኤ.አ. 1982 መሐመድ ከድር፣ በ1985 ወዳጆ ቡልቲ፣ በ1996 አበበ መኮንን፣ በ1992 ፊጣ ባይሳና 1994 ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ የራሳቸወን አሻራ ማኖር የቻሉ አንጋፋ አትሌቶች ናቸው፡፡
ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረስ ደግሞ የታሪክ ቅብብሎሹን የተረከበው ቀነኒሳ በቀለ ነበር፡፡ ቀነኒሳ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረስ አይነኬ ነበር፡፡ በ2007 ደግሞ ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ ድል ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በሴቶቹ ደራርቱ ቱሉ በ1991 20፡27 በመግባት ድሏን ‹‹ሀ›› ብላ የጀመረችበት ወቅት ነበር፡፡
በ1997 ጌጤ ዋሚ ባለድል እስከሆነችበት ጊዜ ደራርቱ አይነኬ ነበረች፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ. 2003 ወርቅነሽ ኪዳኔ ካስመዘገበችው ውጤት በኋላ፣ እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ጊዜው የጥሩነሽ ዲባባ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በረዥም ርቀት በርካታ ገድል የሠሩ አትሌቶችን በታሪክ መዝገብ ማኖር ችላለች፡፡ ከኬንያ ጋር በየውድድር መድረኩ የነበራት ፉክክር ተጠባቂ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የረዥም ርቀት ውድድር ፀሐይ የጠለቀበት ይመስላል፡፡
ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ኤይኤኤኤፍ) እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ ከዳይመንድ ሊግ 5,000 ሜትር ሩጫ ውድድርን እንደሚሰርዝ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም 10,000 ሜትር ከውድድሩ ማስቀረቱ ይታወሳል፡፡ ከከፍተኛ ርቀት 3,000 ሜትር ብቻ እንደሚኖር በአጠቃላይ በወንድና በሴት 12 የውድድር ዓይነቶች ብቻ የዝግጅቱ አካል ሆነው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡