Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርግብር በሩጫ. . . !? በኮንሰርት. . . !?

ግብር በሩጫ. . . !? በኮንሰርት. . . !?

ቀን:

በቁምላቸው አበበ ይማም

የኦቶማን ኢምፓየር ፍልስጤምን ይገዛ በነበረበት ጊዜ ግብር ይጥል የነበረው ተክልና ዛፍን በመቁጠር ነበረ፡፡ ፍልስጤማውያን፣ ዓረቦችና አይሁዳውያን ይኼን ከባድ ቀረጥ በመፍራት ግብር በመጣያው ሰሞን ዛፍን ይቆርጡ፣ ተክሉን ይነቃቅሉ ነበር፡፡ በዚህም አካባቢውን ክፉኛ አራቁቶት በረሃማ አድርጎት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ዓረቦችና አይሁዳውያን ግብር ለኦቶማን ላለመገበር የሄዱበት ርቀት የሃይማኖት፣ የማንነት፣ የባህል ተምሳሌት በሆነውና እንደ ልጅ በሚሳሱለት የወይራ ዛፍ ላይ እንዲያ ያስጨከናቸውጥላ መጠለያ የሚሆናቸውን ዛፍ ያስመነጠራቸውነገሩን ግብር ከመክፈል በላይ ከፍ አድርገን እንድናየው ያስገድደናለን፡፡

አዎ! ከግብሩ ባሻገር የኦቶማንን አገዛዝ መቃወማቸውንበገዥዎቻቸው ላይ እምነት ማጣታቸውን ያሳያል፡፡ የአገራችን አብዛኛዎቹ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች በግብር መወሰኛ ሰሞን ምርትና ሸቀጥ በማሸሽ መጋዘናቸውንና የሱቃቸውን መደርደሪያ ባዶ ከማድረግ አንስቶ ግብርን ለመሰወር፣ ከስረናል ለማለት የሚሄዱበትን ርቀት እዚህ ላይ ያጤኗል፡፡ ከዚህ በፊትም አይሁዳውያን፣ የሰባ ሽማግሌዎች ሸንጎ፣ ፈሪሳውያን፣ ፃፍትለሮማውያን ገዥዎቻቸው ግብርን ላለመክፈል በተደጋጋሚ ከማጉረምረማቸው ባሻገር ፈጣሪያቸውን እስከ መፈተን መድረሳቸውን ከታላቁ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡

ምንም እንኳ ዘመኑ፣ መልካው፣ ባህሉ፣ ዓውዱ ለየቅል ቢሆንም የእኛን ግብር ከፋዮች ከሮማውያንም ሆነ ከኦቶማን ግብር ከፋዮች ጋር የሚያመሳስላቸውን ገጽ አብረን እንግለጽ ‹‹. . . እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?›› አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ፣ ‹‹እናንተ ግብዞች ስለምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ›› አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም ‹‹ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?›› አላቸው። የቄሳር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ ‹‹እንኪያስ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።. . .›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 ቁጥር 17_ 20)

በሮማ፣ በኦቶማን አገዛዝ ሥር የነበሩ አይሁዳውያን፣ ዓረቦችና ፍልስጤማውያን ለገዥዎቻቸው ግብር ላለመክፈል ሲያንገራግሩ፣ ሲያቅማሙ፣ ሲቃወሙ የነበሩት ‹‹የቄሳሩን ለቄሳር. . .›› መሆኑን ስተው፣ ዘንግተው ሳይሆን የሚያስገብሯቸው ማለትም  ሮማውያንም ሆኖ ኦቶማኖች ወራሪ እንጂ፣ ከአብራካቸው የወጡ ፈቅደው የሚገዙላቸውበዚህ የተነሳም  ገባር  መሆናቸውን አምነው መቀበል ካለመፈለጋቸው ባሻገር የሚከፍሉት ግብር ለምን ዓላማ እንደሚውል እርግጠኞች ስላልሆኑ ግብርን ላለመክፈል ብዙ ጥረዋል፡፡ ጉዳዩ ግብር ያለመክፈል ብቻ ሳይሆን ሰፊ አንድምታና ትርጉም ያለው የሚያደርገው ለዚህ ነው፡፡

ዛሬ በአገራችን እየሆነ ያለውም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ እስካለፉት 11 ወራት ድርስ አገዛዙ በስም ኢትዮጵያዊ ቢሆንም በምግባርና በባህሪ ባቢሎናዊ፣ ፋርሳዊ፣ ቤዛንታናዊ፣ ሮማናዊ፣ ኦቶማናዊ ነበር፡፡ እንግዲያስ ግብር ከፋዩየቄሳሩን ለቄሳር. . .›› የሚለውን ቀኖና ዘንግቶአልያም ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታም ክብርም መሆኑ ጠፍቶት አይደለም፡፡ ግብር ለመክፈል እግሩን ወደ ኋላ የሚጎትተው፣ የሚያመነታውላለመክፈል የማይቧጥጠው አቀበት፣ የማይወርደው ቁልቁለት፣ የማይፈነቅለው ድንጋይ የሌለውብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋናው ምክንያት ግን ግብር በሚከፍለው አካል ላይ እምነት ስለሌለው መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይኼን አምነን ከተቀበልን ዕዳው ገብስ ነው፡፡ በአገዛዙና በተቋማቱ እምነት ያጣበትን ምክንያት ለማወቅ ደግሞ የሮኬት ሳይንስ ሊቅአልያም ሞራ ገላጭ፣ አባይ ጠንቋይ፣ አድባር ቆሌ ተለማማኝ መሆን አይጠይቅም፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ እንደ ተቀረው ሕዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ፍትሕ ሲዛባ፣ ፍርድ በአደባባይ ሲገመደል፣ በእናት አገሩ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታይ፣ ፍትሐዊነት፣ እኩልነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ አሳታፊነት፣ የሕግ የበላይነት ሲጓደል፣ ዴሞክራሲ ሲዘበትበትሙስና አገዛዙን ሲደፍቀው  የግብር አወሳሰኑአሰባሰቡ ፍትሐዊ እንዳልሆነ በዓይኑ በብረቱ እየተመለከትእንደ ሮማውያኑ አይሁዶች፣ ፍልስጤሞች፣ ዓረቦች ግብር ለመክፈል ቢያመነታ፣ ቢያንገራግር ለምን እንፈርድበታለን!?

ይልቁንም ግብር የመክፈል እምነቱን የሸረሸሩ ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮችን ነቅሰን ደረጃ በደረጃ ብንፈታ የጠፋውን እምነቱን መመለስ እንችላለን፡፡
የግብርን ጉዳይ ለብቻው ነጥለን ማየቱን ትተንየሰሞኑን ዓይነት የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻንና እሳት የማጥፋት ሥራን ገታ አድርገን የተቋማዊ፣ የመዋቅራዊ፣ የሥርዓታዊ ሕመማችን አካልና ቅርሻ መሆኑን ተገንዝበን ሁሉን አቀፍ፣ ዙሪያ መለስ ዕይታን በመከተል ካልሆነበተናጠል ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡

አዎ! የግብር ጉዳይ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማዕቀፉ አካል ሆኖ ነው መታየት ያለበት፡፡ ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባዜጋው የእኔ ነው የሚለው መንግሥት ሲኖረው በዚያን ጊዜ አይደለም ግብር ሕይወቱን ለመገበር አያመነታም፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የክቡር ቅላይ ሚኒስትር የድጋፍ ሠልፍ ላይ ገና በይሆናል፣ በተስፋ መስቀል አደባባይ ላይ ቦምብ የቀለበው፣ ስለመሪው መስዋዕትነት የከፈለው ለዚህ ነው፡፡

የአገራችን የግብር አሰባሰብ ደረጃ (Index) ስንመለከት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያቆሙ አገሮች እጅግ ከፍ ያለ ግብር ከዜጎቻቸው ይሰበስባሉ፡፡ በተቃራኒው ዴሞክራሲያዊ ባልሆኑና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣና ሙስና በሚስተዋልባቸው አገሮች የግብር አሰባሰቡ እጅግ ዝቅ ያለ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በአገራችን ሰሞኑን እየሆነ ያለው ግን ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት ነው፡፡ ችግሩ የግንዛቤ እጥረት ብቻ ተደርጎ እየታየ ከመሆኑ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ተቋማትን ከመገንባት ይልቅ ግብር አሰባሰቡ ላይ እየተረባረብንጊዜና ሀብት  እያባከንን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰሞነኛ ተረኛው የአገራችን መነጋገሪያ፣ መወያያና መከራከሪያ ከሆኑ ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮችየግብር ጉዳይ ቀዳሚ የሆነው፡፡ የኅትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ቀልብ የተቆጣጠረው፡፡ በዚያ ሰሞን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ግብር ከፋዮች ታዋቂ ሰዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የግብር አሰባሰቡን ለማሻሻል የሚያግዝ አገራዊ ንቅናቄ ይፉ የሆነው፡፡ ይህንን ተከትሎም በየደረጃው ሰፊ ውይይትና ምክክር እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በቅርቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በአዲስ አበባ ሩጫና የሙዚቃ ኮንሰርትም ተካሂደዋል፡፡ በክልሎችም ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህ ተከታታይና ተደጋጋሚ የአህዝቦት፣ የተግባቦትና አመለካከትን የመቀየር ዘመቻ አካል ንቅናቄ ከላይ ለማንሳት እንደ ሞከርኩት የግብር አሰባሰብና አሠራር ችግራችን መዋቅራዊ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ ስለሆነ በተለይ የአመለካከት ለውጥ ላይ ብቻ ያነጣጠረው አካሄድ በራሱ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡

አዎ! የግብር ከፋዩ ችግር ግብር ለአገር ልማት ያለውን የማይተካ ሚና መገንዘብ ላይ ውስንነት ስላለበትግብር መክፈል የዜግነት ኃላፊነትና ግዴታ መሆኑንም ስቶት አይደለም፡፡ በነበረው አገዛዝ ላይ እምነት ሊጥልበት ስላልቻለ አብዛኛው ቢሆንለት በዚህም በዚያም ብሎም  ግብርን  ላለመክፈልካልተሳካለት ግብሩን ለማስቀነስ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ የሰው ልጅ በባህሪው አይደለም ግብር ለመክፈልካለው ለወዳጁ ለማበደር ወይም ለመለገስ እንኳ በቅድሚያ ማመን አለበት፡፡ አይደለም 21ኛው ፍለ መን በሮማውያን አገዛዝ ፈሪሳውያንና ፃፍት አምላካቸውን እንዲያ እስከ መፈተን የደረሱት ግብር በዚያ ዘመንም ሆነ ዛሬ የማመንና ያለማመን ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡

መንግሥቱን የሚያምንና የሚቀበል ከሆነ ግብሩን ከመክፈል ወደ ኋ አይልም፡፡ ካላመነና ካልተቀበለ ሐሰተኛ የወጪ ደረሰኝ ከማቅረብ፣ ደረሰኝ ካለመቁረጥ፣ ካሽ ሬጅስተር ከማበላሸት፣ ጉቦ ከመስጠት አንስቶ ግብር ላለመክፈል የማይበጥሰው ቅጠል የለም፡፡ ስለሆነም የጠፋውንና የተሸረሸረውን የዜጋውን በተለይም የንግዱን ማኅበረሰብ እምነት ለመመለስ ደረቅ የተግባቦት (Communication) ሥራውን ቀነስ አድርገን፣ የግብር ከፋዩንና የዜጋውን እምነቱን ለመመለስ በሚቆጠርና በሚታይ ተግባር የታጀበ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ 

ሆኖም ሁሉም ግብር ከፋዮች ግብር በአግባቡ የማይከፍሉትና የሚሰውሩትበሥርዓቱ በተቋማት እምነት ስላጡ ነው የሚለው አመክንዮ ለሁሉም የሚሠራ አይደለም፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በአቋራጭ ለመበልፀግ ስለሚፈልጉ፣ በአየር በአየርና በሕገወጥንገድ በመሰማራት ግብር የማይከፍሉ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሌላ በኩል በብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም የሚፈለግባቸውን ግብር በፍፁም ታማኝነት በመክፈል፣ የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡ ዜጎችን ማክበር ዕውቅና መስጠት ይገባል፡፡

ሌላው የግብር አሰባሰቡ ፈተና አርዓያ፣ ምሳሌ (Role Model) በሚሆን መሪ ተቋም እጥረትና ድርቅ ክፉኛ መመታቱ ነው፡፡ የቀድሞው ቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ ‹‹እስካልተያዘ ድረስ ሌብነትም ሥራ ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህን እየሰማ ያደገ የንግዱ ማኅበረሰብ እንዴት ታማኝ ግብር ከፋይ ሊሆን ይችላል? የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን፣ የስኳር ኮርፖሬሽንን፣ የልማት ባንክንና የሌሎች ድርጅቶች ብልሹ አሠራርና ሙስና እንደ እጅ መዳፉ የሚያውቅ ዜጋና የንግዱ ማኅበረሰብ እንዴት ለአገሩ ታማኝ ግብር ከፋይ ሊሆን ይችላል?

በአደባባይ በኮንቮይ ታጅበው ኬላ እየተከፈተላቸው መርካቶ ኮንትሮባንድ በማገላበጥ የከበሩ ጥቂት ምርጦች ባሉበትያለ ቀረጥ የፓርቲ ከለላ እየተሰጣቸውም ግብር በአግባቡ የማይጠየቁ ድርጅቶችና ግለሰቦች በነበሩበት የግብር ሥርዓቱ ግልጽ፣ ተጠያቂና ፍትሐዊ ባልነበረበት አገር ታማኝ ግብር ከፋይ እንደ መና ከሰማይ እንዲወርድ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ግብር ከፋዩ ላይ ብቻ ከመረባረብና ከመነቃነቅ የራስን ተቋምና አመራር ማጥራትና ወደ ትውልድ ምሳሌነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ዛሬ ላይ ክቡር ቅላይ ሚኒስትር ዓብይንና ኦቦ ለማን የመሳሰሉ አርዓያና ምሳሌ መሪዎች ቢኖሩንም በቂ ተከታይ ግን አላፈሩም፡፡

ከተቋም በምሳሌነት እገሌ የሚባል አንድ ተቋም እንኳ መጥራት እንቸገራለን፡፡ ኑ ምሳሌ የሚሆን ተቋምና መሪ እንፍጠር ብሎ የሚጣራ የተግባር መሪ ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ እልፍ አዕላፍ ታማኝና ንፁህ አመራሮችንና ተቋማትን ስንገነባ፣ አይደለም ታማኝ ግብር ከፋይ ዜጋ ከዚህ የሚሻገሩ ዘመኑን የሚዋጁ ተከታታይ ትውልዶችን መፍጠር እንችላለን፡፡ ሌላው መፈተሽና መፈታት ያለበት እንቆቅልሽ የአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማሳያ መረጃዎች፣ አኃዞች፣ ቀመሮች ምን ያህል ሀቀኛና ተጨባጭ ናቸው የሚለው ነው፡፡ ምንም እንኳ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ብቻ የዕድገት መለኪያ መሆኑ ላይ የዘርፉ ሊቃውንት ባይስማሙበትም፣ በተለይ እኛ ዕድገታችንን የምንለካበትና የምናሳይበት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት የምናሠላበት ቀመር አወዛጋቢ መሆኑን ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት?›› መጽሐፍ አጠናቃሪና የአደባባይ የኢኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው አስፋው ይሞግታል፡፡

አቶ ጌታቸው የአገራችን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በዓለማችን ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ የብርሃን ፍጥነት 25 ዓመታት ውስጥ በመቶ እጥፍ አድጎ1981 .ም. ከነበረበት 15 ቢሊዮን ብር ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት 2006 .ም. እንደ መንኳራኩር ወደ  1.5 ትሪሊዮን ብር መጥቋል (ክስተቱን ይገልጻል በሚል ቃሉ የደራሲው ሳይሆን የእኔ ነው)፡፡ በዚህ አይቆምም 2010 .ም. ደግሞ ወደ ሁለት ትሪሊዮን ብር ማደጉን አስነብቦናል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከዚህም መሻገሩን እየሰማን ነው፡፡

እንግዲህ አገሪቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ ማብቂያ ላይ የጥቅል ምርቱን ማለትም ሁለት ትሪሊዮን ብር 17 በመቶ 300 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰብ አለባት ብለን ግብ የጣልነውአሁንም 10.7 በመቶ ደርሰናል ያልነው በዚህ ወለፈንዲ፣ ግርምቢጥ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሥሌት ስለሆነ ተጨባጭና ተደራሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትንም ሆነ ሌሎች ኢኮኖሚ አኃዞችን የምንቀምርበትን አግባብ እንደገና ተመልሰን በሀቀኝነትና በቅንነት ልንፈትሽ ይገባል፡፡

የጠፋውን የግብር ከፋዩንም ሆነ የሕዝብን ዓመኔታ ለማግኘትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፣ መንግሥት እዚህ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትንም ሆነየተቀናጀና የተደራጀ ዘረፋ የፈጸሙ ባለሀብቶችን፣ ባለሥልጣናትንና ቋማትን አጣርቶ ለሕግ ሲያቀርብና ተጠያቂ ሲያደርግ ከአገር የሸሸውን የሕዝብ ሀብት ሲያስመልስ በአንድ ጠጠር እንዲሉ የጠፋውን የሕዝብ ዓመኔታና ይሁንታ ከማስመለስ ባሻገር በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ዜጎች ሕግን ሲተላለፉ መጠየቅ እንዳለ መልዕክት ለማስተላለፍና ለማስገንዘብ ይረዳዋል፡፡ እንደ ትናንቱ ዛሬም ሆነ ነገ ወንጀል እንዳይፈጽም ይከላከላል፡፡ 

ማጠቃለያ

1ኛ. በአገራችን የሚስተዋለውን የግብር አሰባሰብ ለማሻሻል በተናጠል ከሚወሰዱ ጊዜያዊ ዕርምጃዎች ይልቅ ዘላቂ ተቋማዊ፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ በሆነ ማዕቀፍ ልንመራና ስትራቴጂካዊ ዕይታ ልንከተል  ይገባል፡፡

2ኛ. ከዚህ ጎን ለጎን ለትውልዱ ለአገራችን አርዓያ የሚሆኑ መሪዎችንና ተቋማትን መገንባትና መፍጠር ላይ ግብ ጥለን ልንሠራ ይገባል፡፡

3ኛ. በመጨረሻም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ መረጃዎቻችንን ገለልተኛ በሆነ የኢኮኖሚና ተያያዥነት ባላቸው ሙያዎች ሊቃውንት መማክርት ተመልሰን ልንሰልቃቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!!! አሜን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ