Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‘አዲስ አበባ የማን ናት?' የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን በማድረግ ይፈታል!

‘አዲስ አበባ የማን ናት?’ የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን በማድረግ ይፈታል!

ቀን:

በሀብታሙ  ግርማ

በእዚህ መጣጥፍ ሁለት ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሚተላለፉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር የተነሳው ውዝግብ ነው።

አዲስ አበባ የማን ናት?

የሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳይ አዲስ አበባ የማን ናት? የሚለው ነው። የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ መነሳቱ ስህተት የለውም። ችግሩ ኢትዮጵያ የዜጎቿ የመሆኗ ነገር እጅግ ባጠራጠረበት ዘመን አዲስ አበባ የማን ናት? ብሎ መጠየቁ የፌዝ ስለሚመስል ነው። ጥያቄው የፌዝ ነው ተብሎ ግን መልስ መስጠት አለመቻል ማለቂያ ለሌለው ጠብ ያጋልጣል። ፈጣሪ ይሰውረን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጠብ መንስዔም፣ ውጤትም (አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ) ማለቂያም የለውም። ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ትዝብቴ አዲስ አበባ የማን ናት? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡትን በሦስት ቡድኖች መክፈል ይቻላል።

የመጀመሪያው በአብዛኛው አዲስ አበቤ ሲሆን፣ ይኼ ቡድን አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት ይላል። ሁለተኛው ቡድን ከአዲስ አበባ ውጪ ያለና በአመዛኙ የኦሮሞ ወገን ሲሆን አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮሞ ሕዝብ ናት ይላል (በአዲስ አበባ የሚኖር የኦሮሞ ወገን አዲስ አበቤ ራሱን በብሔር የመግለጽ ዝንባሌ የለውም የሚል እምነት ስላለኝ ነው)

ሦስተኛው ቡድን አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናት የሚለው ነው። ይኼ ቡድን ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ብዙኃኑ ሀቀኛ አይደለም፣ አልያም የመንጋ ውዝግብ ሰለባ ነው። ምክንያቱም አንድ ኢትዮጵያ ባለበት አንደበቱ የአጉል ብሔርተኝነት ጩኸት ያሰማል። በእውነቱ ይኼ ቡድን ኢትዮጵያን ጉዳዩ ስለማድረጉ እጠራጠራለሁ። እንዲያውም አወናባጅ ይመስለኛል።

ከሦስቱ ቡድኖች በተለይ በኢትዮጵያ አንድነት ስም የሚነግደው ጎራ እጅግ አደገኛ ነው፣ ምክንያቱም በአገር ቀልድ የለምና። አባላቱ በአብዛኛው የሚፈልጉትን መርጠው ማድመጥ የሚሹ፣ የሚዛናዊነት መለኪያቸው ሐሳብ ሳይሆን ግለሰባዊ ስሜታቸውን ከማስታገስ አንፃር እንጂ፣ ቆመንለታል ለሚሉት የኢትዮጵያ አንድነት ከማጠናከር አንፃር አይደለም።

ይኼ ኃይል ገሚሱ እሳት፣ ገሚሱ ቤንዚን አርከፍካፊ፣ ከፊሉ ደግሞ አራጋቢ ሆኖ አገር እየለበለበ፣ ነገር ግን ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚለፍፍ ፀረ ኢትዮጵያ ነው። እሳት ቤንዚን አነፍናፊ ነው፡፡ ቤንዚንም እሳት አነፍናፊ ነው። ውጤቱ ቃጠሎ ነው፡፡ የቃጠሎው  ወላፈን እንደወረደ የሚፈጀው ደሃው ሕዝብ ነው። በእሳት እየተለበለበ እየረገፈ ያለው የኢትዮጵያ ምሰሶና ማገር ነው። ይኼ የዘመናችን የኢትዮጵያ አሳዛኝ እውነት ነው።

ከኢትዮጵያ መፍረስ አንድም የሚጠቀም የለም። አገር ሲፈርስ የእያንዳንዳችን ዕጣ ፈንታ አንድም ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መፍረስ፣ አልያም ስደት ነው። ከሁለቱ መጥፎዎች የኋለኛው የከፋ ይመስለኛል። አገር የሌለው በሄደበት ከሰው በታች መሆኑን ለመረዳት ከአገር ወጥቶ መኖር አይጠበቅም። በእኔ ግንዛቤ አዲስ አበባ የማን ናት? የሚለው ጥያቄ  ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን በማድረግ ይፈታል።

የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውዝግብን በተመለከተ

የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የውዝግብ ጉዳይን በተመለከተ መልስ ከመስጠት ይልቅ ሁለት ተዛማጅ ጥያቄዎች መጠየቅ መርጫለሁ።

ጥያቄ አንድ፦ ከአዲስ አበባ ወሰን 25 ኪሎ ሜትር ገደማ ተገብቶ የአዲስ አበባ ቤት ማስፋፊያ ሲሠራ የወሰን ጉዳይን የወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥያቄ አንስቶ ነበር? የወቅቱ የአዲስ አበባ አስተዳደርስ ይኼን ጉዳይ ለምን ዘነጋው?

ጥያቄ ሁለት፦ የተነሳው ውዝግብ  የብሔር ጉዳይ ነው ወይስ የአስተዳደራዊ? ከዚህ አንፃር የቤት ዕጣ ከደረሳቸው 51,000 ሰዎች መካከል በብሔር መጠሪያቸው የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ እንዳሉ ይታመናል፡፡ ታዲያ ኦሮሞ በመሆናቸው ተለይተው በቤቶቹ የመኖር ዋስትና አግኝተዋል? የሌላ ብሔር ተወላጆች የቤት ዕድለኞች ደግሞ በቤቶቹ እንዳይኖሩ ተከልክለዋል? እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳቴ ችግሩን ለማቃለል ሳይሆን፣ ከስሜትናአጉል ብሔርተኝነት ወጥተን ጉዳዩን እንድንመረምር ለማሳሰብ ነው። ይህም ከውዝግቡ የሚያተርፉ አካላት የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ ወይም ተጠቂ እንዳንሆን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ።

ጥያቄዎቹን ማንሳቴ ከምንም በላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመራውን የለውጥ አመራር ባልፈጠረው ችግር ከመወንጀል እንድንታቀብ፣ በመሆኑም የለውጥ ኃይሉ ተከፋፍሎ እንዳይዳከም፣ ተስፋ ያደረግነው ሁሉ እንዳይጨልም በአስተውሎት መጓዝ እንዳለብን ለማስታወስ ነው።  እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻዎቻቸው [email protected] ወይም [email protected]            ማግኘት ይቻላል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...