Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአዲስ አበባን የዘር ፖለቲካ ጭቅጭቅ ውስጥ መክተት አሳፋሪ ነው!

አዲስ አበባን የዘር ፖለቲካ ጭቅጭቅ ውስጥ መክተት አሳፋሪ ነው!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ስድስት ኪሎ) ሬጅስትራር ጽሕፈት ቤት ግድግዳ ላይ በተንጠለጠለ የማስታወቂያ ሰሌዳ ውስጥ ከተካተቱት ጽሑፎች አንዷ ቀልቤን ስባው ነበርና በማስታወሻዬ ላይ አስፍሬያታለሁ፡፡ እንዲህ ትላለች “Yesterday’s method may not be fit to solve today’s problem, therefore change for the better” ወደ አማርኛ ግጥም ስንለውጣት፣ ‹‹የትናንቱ ዘዴ የዛሬውን ችግር ሊፈታ ካልቻለ፣ የተሻለ ለውጥ ለተሻለ ውጤት ቢፈለግ ምን አለ?›› እንደማለት ናት፡፡ ቁም ነገሩ ያለው የተሻለ ለውጥ (Change for the better) የሚለው ላይ ነው፡፡ ዛሬ ከአገራችን አልፋ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና ለዓለም የዲፕሎማቲክ ከተማነት የበቃችው አዲስ አበባ ከ130 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረች ነች፡፡ በውስጧም በግርድፍ ግምት እስከ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ የሚደርሱ ነዋሪዎችን የያዘች ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች በታሪክ አጋጣሚ የተሰባሰቡ ዜጎችን እንዳቀፈች ይታመናል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፉት 27 ዓመታት በአገር ደረጃ ከተዘረጋው የብሔር ፌዴራሊዝም አንፃር እንኳን፣ ከየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በተለየ ኅብረ ብሔራዊነትን ተላብሳ በጋራ ቤትነት  ለመቀጠል ችላለች፡፡

ያም ሆኖ ከተማዋ ከአመሠራረቷ ጀምሮ በመሀል አገር ቀደም ሲል ሸዋ ክፍለ ሀገር፣ ከ27 ዓመታት ወዲህም ከኦሮሚያ ክልል ጋር ኩታ ገጠም እንደ መሆኗ ክፉም ሆነ ደግ እንቅስቃሴዋ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የተዛመደ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሕገ መንግሥቱም ጭምር ተደንግገው በሥራ ላይ ያልዋሉ የጥቅም ስምምነቶች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በተግባርም በአንድ በኩል በከተማዋ የመሠረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማኅበራዊ ልማት ዕድገት በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል አለ፡፡ በሌላ በኩል ከከተማዋ መስፋፋትና የመሬት ፍላጎት ዕድገት፣ የመጠጥ ውኃና የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋርም የተሳሰረ የጥቅም ግጭት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን እንደ አንድ አገር ሕዝቦችና የጋራ መንግሥት ነገሮችን ተደማምጦና በሠለጠነ መንገድ መፍታት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው፡፡

የአንድ አገር የጋራ ከተማና ዋና መዲና በሚመራበትና በሚተዳደርበት መንፈስ፣ የአገሪቱ ዜጎች በፍትሐዊነትና በእኩልነት መርህ እንዲጠቀሙበት የማድረጉ ሥራም ለነገ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥትና በቻርተሩ መሠረት የጋራና የተናጠል ጥቅምን ማስከበር ተገቢ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው በቦታ ስያሜ በዓርማና መሰል አወዛጋቢ ክስተቶች የሚፈጠር የፖለቲካ አታካሮ ግን ጉዟችንን እንዳያደናቅፍ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለረጅም ዘመናት የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ሀብት፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ የፈሰሰባትን ምድር፣ በውስጧ ያሉ ሕዝቦች ከራሷ አልፈው በየትኛውም ዓለም ለዘመናት ሠርተው ለልጅ ልጅ እያስተላለፉ የቆዩትን ሀብትና ንብረት የባለቤትነት ስሜት በሚያሳጣ መንገድ አዲስ አበባ/ፊንፊኔ/በረራ እየተባለ የአንድ ክልል ሀብት ብቻ እንደሆነች በጥቂት ጽንፈኛ ጦማርያንና አክራሪ ብሔርተኞች መቀንቀኑም በፍፁም  የሚጠቅም ሎጂክ (አመንክዮ) አይደለም፡፡ መዲናዋ በተገኘችበት ጆግራፊያዊ ይዞታ ብቻ የጋራነቷን ማሳጣትም ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው አዲስ አበባ በ540,000 ሔክታር መሬት ላይ የተዘረጋችና ወደ ጎን የምትለጠጥ እንጂ፣ ወደ ላይ ያላደገች ከተማ ናት፡፡ ወደ ላይ የመመዘዝ ዕድገቷ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ጀምሮ ጥሩ ዕርምጃ አሳይቷል፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ በሁሉም ዘርፎቿ ከፍተኛ ለውጥ ያስመዘገበች ሲሆን፣ ባለፉት መቶ ዓመታት ያልተከወኑ ሥራዎችና ልማቶች በአሥር ዓመታት አጭር ጊዜ ውስጥ ተሠርተዋል፡፡

ይህንን መሬት ላይ ያለ ሀቅ መካድ አይቻልም፡፡ ምናልባት እንደ ጉድለት የሚነሳው የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተማው መኖሪያዎቿ ከደሃ ጉሮኖዎች እስከ ታላላቅ ቪላና አፓርታማዎች ድረስ ዓይነታቸው ብዙ ነው፡፡ ነዋሪዎቿ ከምስኪኗ ቅጠል ተሸካሚ “የእኔ ቢጤ” አንስቶ በዴሉክስ አውቶሞቢል እስከ ሚንፈላሰሰው ድረስ. . . በቀን አንድ ብር ለማግኘት ከሚቸገረው ደሃ አንስቶ በሳምንት የመቶ ሺሕ ብር ዕቁብ እስከ ሚጥለው ባለፀጋ ድረስ አሉባት፡፡ ለኢፍትሐዊ ገጽታው መባባስም ዘረፋና የሥርዓቱ ብልሽት አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ከተማዋ የፊደልን ዘር ከማያውቀው ማይም አንስቶ፣ ተማረ ተመራመረ እስከሚባለው ሊቅ ድረስ የሞሉባትም ናት፡፡ ከፍርፋሪ (ቡሌ) መሸጫ ጥጋ ጥጎች እስከ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ ይገኙባታል፡፡ ሁሉም ነገር በየዓይነቱ አለባት፡፡ ይህም ሆኖ ከእነ ችግሯም ቢሆን ሁል ጊዜ በለውጥ ሒደት መቆየቷ ሊካድ አይቻልም፡፡ ከሁሉ በላይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት አገራችን በሕዝባዊ እምቢተኝነት በምትናወጥበት ወቅት እንኳን፣ ሰላሟንና አንፃራዊ ደኅንነቷ ተጠብቆ የቆየ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ መዲናነቷም የተሸራረፈ አልነበረም፡፡

አሁን ላይ ከብሔር ፌዴራሊዝሙ የተካረረ አተያይ አንፃር በከተማዋ ሕዝቦችና የአገር ሀብት ላይ የሚሠራ ሸፍጥና የፖለቲካ አተካሮ ግን ጭራሽ ፈሩን እየሳተ እንዳይሄድ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በመሠረቱ አዲስ አበባን ከየትኛውም ብሔር የወጣ ከንቲባ ቢኖራት ሕግና ሥርዓትን መሠረት አድርጎ ነዋሪዎቹን (የሌላ አገር ዜጎችን ጭምር) ለማገልገል እንጂ፣ ሕግና ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የኦሮሞን ሕዝብም ሆነ ጥቂት ልሂቃን ለመጥቀም በሚል ሌላ የፖለቲካ ሸፍጥ ሰንቆ ሊሞክረው አይችልም፡፡ የትም የሚያደርስ እሳቤም አይደለም፡፡

ከዚህ አንፃር ሲመዘን የሽኩቻ ፖለቲካውን ትተን አዲስ አበባ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ለነዋሪዎች ብሎም ለመላው አገሪቱ የኩራት ምንጭ እንድትሆን ለማድረግ፣ ይህችን ከተማ ማስተዳደር በራሱ እጅግ በጣም ከባድ ኃላፊት ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሮቿ ዘርፈ ብዙ ናቸውና፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የቤት እጥረት፣ የሥራ ዕጦት፣ መሠረታዊ የፍጆታ ግብዓቶች እጥረት፣ የመሠረተ ልማት የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የአነስተኛና ጥቃቅን፣ የበሸታው፣ የመድኃኒቱ፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛው፣ ለሥራ ወደ ውጭ በሚሄዱ ዜጎች ላይ የሚደርስ ሥቃይና እንግልቱ. . . ልዩ ትኩረትና ርብርብን የሚሹ ናቸው፡፡ ሕዝቡም በእኔነት ስሜትና በንቃት ሊሳተፍበት የሚገባ ዘርፈ ብዙ መስክ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያልተስፋፉ የመሬት አስተዳደር፣ የታክስና የፍትሕ ተግባራዊ ሒደቶች፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ገና ሙሉ ትኩረትን ይሻሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በአንድ የምክር ቤት የሥራ ዘመን (አሁን ደግሞ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ) እንኳንስ ማስወገድ፣ ሥርዓት ማስያዝ በራሱ አስቸጋሪ ስለሚሆን ደግሞ አዲሱ አመራር ከማይበጅ የእኛ/የእናንተ ፖለቲካ ውዝግብ ወጥቶ በታሪክ አጋጣሚ እጁ የገባውን የማልማት ዕድልና አገር የመቀየር ኃላፊነት  በላቀ ውጤት ሊያጅበው ይገባል፡፡ ደግሞም ሊያደርገው ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ካለሥራ ተቅምጦ ወሬ የሚጠርቀውንም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጽ አሉባልታ ላይ የተጠመደውን ሸፍጠኛ ማዳመጥና መልስ ለመስጠት መታከት አያስፈልግም፡፡ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ” እንዲሉ፣ ሁሉም በየፊናው ይተቻል እንጂ ውስብስብና ፍላጎተ ድብልቅልቅ  ከተማን ማስተዳደር እንዲህ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው፡፡ ይህን እውነት የሚገነዘበውን ኃይል ይዞ በፍትሐዊነትና በእኩልነት መርህ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡

አንዳንድ ጊዜ በጽንፈኛው ተቃዋሚና ተጠራጣሪ ኃይል ብሎም፣ ለውጡን በማይፈልገው ወገን በከተማዋ የወቅቱ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ላይ የሚደረገው ዘመቻ አስገራሚ ነው፡፡ ሰውዬው በዓይን የሚታይ ሥራ ላይ ገብተው ሲያበቁ፣ ቢሳሳቱ እንኳን በቅንነት እንዲታረሙ መንገር ሲቻል ከሌላ ፕላኔት መጥተው እየመሩ ይመስል የማያቋርጥ ዘመቻ ሲካሄድ ማየት አስገራሚና አሳፋሪ ነው፡፡ እኝህ ሰው ከዚህ ቀደም ከነበሩ የኦሕዴድ (ኦዴፓ) ከንቲባዎች ድሪባ ኡማ፣ ኩማ ደመቅሳና አሊ አብዶ የሚለዩበትን ነጥብ እንኳን የሚያስረዳ አይገኝም፡፡ በመሠረቱ የከተማ አስተዳደር ሥራ የአንድ ሰው (የከንቲባው) ወይም የምክር ቤቱ ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ ሥራው ከሰዎች ጋርና በሰዎች አማካይነት የሚሠራ በመሆኑ፣ ለዘርፈ ብዙ ሥራዎቹ ዘርፈ ብዙ የሥራ መምርያዎችና ሠራተኞች ማስፈለጋቸው የግድ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በየመዋቅሩ ከሁሉም ሕዝቦች የተወከሉ ተሿሚም ሆኑ ተቀጣሪዎች በተቻለ መጠን በብቃት ላይ በተመሠረተ መንገድ እንዲገቡ ማደረግ ላይ ነው ትኩረት መስጠት የሚገባው፡፡ በተለይ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ እንዳለፈው የሕወሓት የአንድ ሠፈር አመራሮች ያሻቸውን እንዲያደርጉ መልቀቅ ከታሪክ አለመማርን የሚያስከትል ነው፡፡ ከሰው ሀብት ሥምሪት ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ብልሹ አሠራርን  ሳይታገሱ መታገልን ከወዲሁ በማለማመድ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የነባሩ አስተዳደርና ምክር ቤትን ስህተት ላለመድገም መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም በየደረጃው በድክመት የተገመገሙ ሠራተኞችን/ኃላፊዎችን በማንነት ስም ለማቆየት ተብሎ ወደ ሌላ ቦታ ከማዛወር በቀር፣ ለቀሪው ዘራፊ አስተማሪ የሆነና የሚቆጠቁጥ ቅጣት የተወሰደበት አጋጣሚ ባለመታየቱ ችግሩ እንዳንከባለለው ተረድቶ ከወዲሁ ማረም ግድ ይላል፡፡

እዚህኛው ወረዳ ‹‹ሙሰኛ›› የተባለ ሠራተኛ እዚያኛው ወረዳ ተመድቦ ማግኘት አሠራር መስሎ የቆየውም ለእዚሁ ነበር፡፡ ግማሹ ከደረጃ ዝቅ ተደርጓል ይባላል፡፡ ከደረጃው ዝቅ ቢልም ደመወዙን ይዞ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ አይቀነስም›› የሚል አዋጅ ደግሞ አለ፡፡ በዚያ መሠረት ከተሄደ ትናንት ለከፍተኛ የሥራ መደብ የተመደበለትን ደመወዝ ይዞ ዝቅ ወዳለ የሥራ መደብ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ጥቅማ ጥቅሙ ይቀርበት እንደሆነ እንጂ ዋና ደመወዙ አይነካበትም፡፡ ይህም በአገር ሀብት እንደመቀለድ ሲቆጠር ቆይቷል፡፡ በመሠረቱ አሁን ከለውጥ በኋላም ባልጠራ ምዘናና በለውጥ ኃይል ስም በርካታ ችግር ያለባቸው አመራሮች ቆዳቸውን ገልብጠው እንደተሰገሰጉ ናቸው፡፡ በከተማው አስተዳደር ውስጥ ከዋናው መሥሪያ ቤት (ማዘጋጃ) ጀምሮ በየክፍላተ ከተሞች በኩል ቁልቁል ወረዳ ድረስ ብዙ የሠራተኛና የኃላፊ ጉድ ሊመዘዝ ይችላል፡፡ በዘመድ አዝማድ እየተጎተተና እሱም በተራው የራሱን ዘመድ እየጎተተና እያስጎተተ ካለ ብቃትና ተነሳሽነት ቦታውን የያዘ መኖሩ፣ ካለፈው ጊዜም አልፎ አሁንም ድረስ በሥጋት የሕዝቡ መነጋገሪያ የሆነው ዳግም ላለመክሰር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

እንደ ከተማ ከዚህ ቀደም የነበረው ሌላው መሠረታዊ ችግር ከግብር አሰባሰብ፣ ግመታና ትግበራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ኢፍትሐዊነትና ሌብነትም ነበር፡፡ ይህ በሁሉም ነዋሪ ጎዳና ኑሮ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርስ ተግባር እንደ ፖለቲካ መሥሪያ ተደርጎ አንዱ እየተማረረ ከአገር ሲሳደድበት፣ ሌላው እያፈነነ እንዲፈነጭበት ሲደረግ መቆየቱ የታመነ ነው፡፡ በመዋቅሩ ውስጥ በተሰገሰጉ ሌቦች አማካይነትም ስንቶች ለብዝበዛና ለምሬት ተጋልጠው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፉት ጊዜያት ግብርን በተገቢው መጠን ለማሰባሰብ አለመቻል የመስተዳድሩ ችግር እንደነበር ተገንዝቦ ከዚህ ወጥቶ የመዲናውን ሀብት በፍትሐዊነት ሰብስቦ ለላቀ ጥቅም ማዋል የሚችል አስተዳደር መገንባት ግድ ይላል፡፡ እንደ ዜጋ ግብር መክፈል ያለበትን ሁሉንም ግብር ከፋይ ወደ ሥርዓቱ ለማስገባትና ተገቢውን የግብር መጠን ተዓማኒ በሆነ መንገድ ለመወሰን ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በግብር ሥርዓቱ ዘርፍ የታየው የሙስና አካሄድና በግብር ከፋዩ አለማወቅ ለመጠቀም የሚደረጉ መሰሪ አዝማሚያዎች በተግባር የታዩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህን በመቀየር ግብር ከፋዩን ከገባርነት ስሜት አውጥቶ ሠርቶ ካገኘው ላይ ለአገሩ እየከፈለ እንደሆነ እንዲገነዘብ የማድረግ የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥራም በተገቢው መጠን ሊሠራ ይገባዋል፡፡

አሁን ያለው አስተዳደር ባለፈው ሥርዓት የተዛባውን የግብር አወሳሰን በማረም ዜጎች በፈቃደኝነትና በእኔነት ስሜት ግብራቸውን የሚከፍሉበት ሥርዓት ለመዘርጋት፣ በግብር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥልቀት መርምሮ አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነባሩ የአዲስ አበባ አስተዳደርና ምክር ቤት የሚጠበቀውን ያህልም ባይሆን የከተማይቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ባለው አቅምና ግብዓት ልክ የተቻለውን ለማድረግ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ እርግጥ የቀደመው አስተዳደር የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት በርካታ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻልም ሠርቷል፡፡ ይሁንና ግን በየጊዜው በከተማዋ ከሚፈጠረው ሥራአጥ ወጣትና ወደ መዲናዋ ከሚፈልሰው አርሶ አደር አኳያ እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድል በቂ ሊባል አይችልም፡፡

ተጨባጩ ማሳያም የሥራ ፈላጊው ዜጋ ቁጥር (ያውም የተመራው) እያደር እየጨመረ ለመሆኑ፣ ከፅዳትና ከጥበቃ ሠራተኝነት ጀምሮ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ በወጣ ቁጥር የአመልካቹ ሠልፈኛ ብዛት በየቢሮው በሁለትና በሦስት ዙር እንደመቀነት እየተጠመጠመ መታየቱ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የሥራ አጥነት ችግር ከተማይቱ የፈጠረችው ብቻ አይደለም፡፡ ለችግሩ መኖር በርካታ ባለድርሻ አካላት አሉ፡፡ ዜጎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም፣ የአገሪቱ የሥራ ትከሻ ሊሸከም ከሚችለው በላይ ኃይል መኖር ግን ለጊዜውም ቢሆን የመስተዳድሩና የክልሎችም  ራስ ምታት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አዲሱ አስተዳደር ይህን ጎርፍ የሚመለከት ግድብ ለመሥራት ነው መትጋት ያለበት፣ የሚጠበቅበትም፡፡ ከዚህ በተረፈ በዘር ፖለቲካና አሉባልታ ውስጥ ሰጥሞ ሲላጋ ሊውልና ሊያድር አይገባም፡፡

አዲስ አበባ ከአዲሱ አመራር ወዲህ የጀማመረቻቸው በርካታ የመሠረተ ልማትና የማኅበረ ኢኮኖሚያው ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመዲናዋ የአረንኋዴ ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ እስከ 29 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ ይሁንና ከተማዋ ካለባት ኃላፊነት አንፃር፣ ያላትን የሀብት ግብዓት ለየፕሮጀክቶቿ የምትመድብበት አሠራር (Resource Allocation) በማያዳግም እርግጠኝነት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ እንደ ለውጥ ኃይል ጥናትና ቅደም ተከተል (Priority) አግባብ መሠረት የማድረግ ብቃትን ማሻሻልና ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፣ ሀብትን ከዘረፋና ከብክነት ማዳንም ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ የትኛውም መንግሥት ወይም የትኛውም ከተማ የማያልቅና የተትረፈረፈ ሀብት እንደሌለው የሚታወቅ ነው፡፡ የሀብት ግብዓት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ እጅግ በጣም ውስን ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮቹን በአንዴ ለመፍታት የሚያስችል ሀብትም የትም የለም፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ከተሞች በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ደሃ ከተሞች ያላቸውን ውስን ሀብት በአግባቡ የመጠቀም ብቃት  እንዲኖራቸው፣ አዲሱ አመራር ካለፈው ጊዜ ትምህርት ወስዶ መረባረብ አለበት፡፡

ከዚህ ቀድም በተለይ በመሠረተ ልማት ግንባታ አለመቀናጀት ምክንያት ይደርስ የነበረው ብክነት ጥብቅ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ዛሬ የተሠራው ነገ እየፈረሰ መቀጠል የሚያስከትለው የሀብት ብክነትን ነው፡፡ ምክንያት ወይም ሰበብ ይኑረውም፣ አይኑረውም ዋናው ጉዳይ ሰበብ መደርደሩ አይደለም፡፡ አስቀድሞ የማያዳግም ጥልቅ ጥናት ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ይህ አካሄድም የአዲሱ አመራር ጥብቅ መመርያ ሊሆን ይገባል፡፡ ዕውቀትንና ቴክኖክራትን በመጠቀም ሊዳብር ይገባል፡፡ በእርግጥ የከተማ አስተዳደር ሥራ ወጪው ብዙ ሲባል ግልጽ ምክንያቶችም አሉ፡፡ የአንድን ከተማ ወጪ መብዛት ወይም ማነስ ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱ የሕዝብ ሁኔታ (Population Characteristics) ነው፡፡ በሕዝብ አሰፋፈር አቀማመጥ፣ በመባዛት (የቁጥር ዕድገት በውልደት የመጨመር ምጣኔ መሥፈርት) ወጪው ይወሰናል፡፡

ይህ ማለት ተጠጋግቶ የሰፈረ ሕዝብ (High Density) ያላት ከተማ ብዙ ወጪ ይጠብቃታል፡፡ የሕዝቡን ኑሮ ለማረጋጋት፣ አስፈላጊውን አገልግሎት ለማቅረብ፣ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን፣ የእሳት አደጋ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርት፣ የአረንጓዴ ሥፍራ፣ የመቃብር ቦታ፣ የባህላዊና የመገናኛ ሥፍራዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ሙዚየም፣ ቴአትር ቤት፣ መናፈሻ፣ ወዘተ. ለማሟላት ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ይህን በሕዝብ ሀብት አጠናክሮ ለመፈጸም  መረባረብ በራሱ፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሽኩቻ ሳይጨመርበት ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅና ከባድ ሥራ ነው፡፡ ይህን ተረድቶ መትጋት ነው የለውጥ ኃይልነት፡፡

በአጠቃላይ አዲስ አበባን ባለፉት 27 ዓመታት ስድስትና ሰባት ከንቲባዎች መምራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይህንኑ ያህል መንግሥታትም ተቀያይረውባታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋ፣ በተለይ ካለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ መስፋፋትና ዕድገት አሳይታለች፡፡ ፈጣን አዳጊ ከተማ እስከመባል በአኅጉሩ መድረክ  መጠቀሷንም አንዘነጋውም፡፡ በዚህ የውስጥ ዕድገቷ ምክንያት ሕይወታቸው የተቀየረና የተሻሻሉ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል፣ እንደ ነዋሪዎቿ መስፋፋት በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮችን ካለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ ማፈናቀሉ፣ በተለይ አሁን አሁን ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡ ይህን ነባራዊ ሀቅ ፈትሾ ማስተካከልና የመዲናዋን የጋራ ሀብትነት የሚመጥን የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት መረባረብ ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባን በዘር ፖለቲካ ጭቅጭቅ ውስጥ በመክተት እንቅፋት ለመደቀን መሞከር፣ አዲስ አበባንም ሆነ ነዋሪዎቿን የማይመጥን አሳፋሪ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ መጭውን ጊዜና ትውልድም የሚመጥን አካሄድ አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...