Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ…

ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ…

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ውብ አገራችን ኢትዮጵያ የጋራ ገንዘባችን ናት፡፡ መዲናችን አዲስ አበባማ በበለጠ ምክንያት የየትኛውም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈባት የሁላችንም መዳረሻ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ግብዞች ከተማይቱ መሀል ኦሮሚያ ላይ ስለምትገኝ፣ ይህ ኩነት ብቻውን ዛሬ ኦሮሚያ የሚባለው ክልል አንጡራ ሀብት ናት ሊሉን ሲዳዳቸው እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከልብ ያስቃል፣ ያንከተክታልም፡፡

እስቲ የአፍሪካ አኅጉርን ካርታ ግለጡና ለአንዳፍታ ዓይናችሁን ወደ ደቡባዊው አካባቢ አቅኑ፡፡ ሌሴቶ የምትባለውን ትንሽ አገር ብታዩ አጠቃላይ መልክዓ ምድሯ የተከበበው በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ሆኖም ይህ አጋጣሚ ብቻውን ነፃይቱን አገረ ሌሴቶ የደቡብ አፍሪካ ክፍልና አካል ያደርጋታል እንዴ?

እንዳለመታደል ሆኖ በጥንቃቄ ያልተሰናዳውና አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ ፺(5) ሥር አዲስ አበባችን በኦሮሚያ እምብርት ላይ ከመገኘቷ ጋር በተያያዘ በስም ለተጠቀሰው ክልል ‘ልዩ ጥቅሞችን’ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባት እምብዛም ባልተብራራ መንገድ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚኖሩ ዜጎቻችን ከአንድ ብሔር የተውጣጡ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወይም የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ወይም እምነት ተጋሪዎች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ የትኛውም ማዕዘን ብንንቀሳቀስ እንዲህ ያለውን ወጥና ልሙጥ የሕዝብ አሠፋፈር ማግኘት አይቻለንም፡፡ ቀድሞ ነገር ብዙኃኑ ዜጎቻችን በጎሳ፣ በዘርና በሃይማኖት እየተጠራሩ መንደር አልመሠረቱም፣ ሠፈር አልቆረቆሩም፡፡

ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ዓይነተኛ መለያችን ዝንቅነታችን ወይም በተለመደው አነጋገር አብሮነታችን ነው ቢባል ፈጽሞ ማጋነን አይሆንም፡፡ በሕገ መንግሥት ደረጃ መሬት እየተሸነሸነና በብሔር ወይም በጎሳ ስም እየተከለለ የተሰጠበት አደገኛ ፕሮጀክት ለጊዜው ሊለያየን የሞከረ ቢመስልም፣ በየምንኖርበት አካባቢ ይህንን ዕውን ማድረግ ከቶ አይቻልም፡፡ እኛ የምንኖረው ከጫፍ እስከ ጫፍ በማንነጣጠልበት ሁኔታ እርስ በርስ ተደበላልቀን፣ ተጋምደንና ምናልባትም የሠርገኛ ጤፍ ያህል ተዋህደን ነው፡፡ አማራውን ከትግሬው፣ ኦሮሞውን ከሶማሌው፣ ጉራጌውን ከወላይታው፣ ወዘተ. ለመለየት ያዳግታል፡፡ መሬታችንም ሆነ ሌላው የተፈጥሮ ሀብታችን ለአኛ ለሁላችን በጋራ እንድንጠቀምበት የተሰጠ እንጂ፣ የትኛውም ቡድን በግል የይገባኛል ጥያቄ የሚያቀርብበትና የተናጠል ባለቤትነት የሚመሠርትበት አይደለም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ታዲያ ጽንፍ ለረገጠ ብሔርተኝነት ተግቶ ከሚሠራው ከኢሕአዴግ ማህፀን የተገኙት ኦቦ ለማ መገርሳና ዓብይ አህመድ በኢትዮጵያዊነት ላይ አዲስና የተሻሻለ ትርክት ይዘው ብቅ ባሉበት ወቅት፣ ‹‹ከእባብ እንቁላል እርግብ ማግኘት እንደምን ይቻላል?›› በማለት ብዙዎቻችን የግርምት ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ እነሆ በጊዜው ያደረብን ሥጋት አላስፈላጊ እንዳልነበር አሁን አሁን እየታዘብን ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› በማለት ሲያማልሉን የቆዩት አቶ ለማ መገርሳ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ባለቤቶች እኛ ኦሮሞዎች ብቻ ነን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ድርጅታቸው ኦዴፓም በመሪው በኩል የተቀነቀነው የአገር ባለቤትነት በመሬት ላይ እስኪረጋገጥ ድረስ አበክሮ እንደሚታገል፣ የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው ኃፍረ ተቢስ መግለጫ ያለ ይሉኝታ ነግሮናል፡፡

‹‹የቆመ የመሰለው ሁሉ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ›› ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ አጥብቆ ይመክረናል፣ ያስጠነቅቀናል፡፡ ይታወስ እንደሆን ከአንድ ዓመት በፊት በዛሬው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እሽኮኮ ባይነት ሳያስቡት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት፡፡ ሰውየው እነሆ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን እርካብ እንደጨበጡ ከውጭ እየጠሩ ባሰባሰቧቸው ረብ የለሽ የኦሮሞ አማፅያን ተጠልፈው በመንገዳገድ ላይ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል በኦዴፓ መሪነታቸው አዲስ አበባን ለኦሮሞዎች ብቸኛ ገጸ በረከት አድርጎ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን ይፋዊ መግለጫ በድፍረት ፈርመው እያወጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መዲናይቱ የሁሉም ነዋሪዎቿ የጋራ መሰባሰቢያችን ናት ሲሉ ራሳቸውን በማግሥቱ ተፃረው እንዴትና በምን ዓይነት ወኔ በአደባባይ ሊያውጁ እንደሚችሉ ማሰብ ያዳግታል፡፡ መቼውንም ጊዜ ቢሆን አንድ አገልጋይ በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ ለሁለት ጌቶቹ ሊገዛ አይችልም፡፡

በሌላ አነጋገር ኦዴፓ ራሱን በአደገኛ ሁኔታ አጥቦ ያወጣውን አክሳሪ መግለጫ እንደለመዱት አላየሁም አልሰማሁም ይሉን ይሆናል እኮ፡፡ ሰውየው በዚህ ረገድ ያላቸው ልዩ ችሎታ የሚናቅ አይመስለኝም፡፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን እዚያው አፍንጫቸው ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ ስም በኃይል እያፈናቀለ ስለበተናቸው ዜጎች የሰሙት አንዳች ነገር እንዳልነበረ ያለ ኃፍረት ከነገሩን ብዙ አልቆዩም፡፡ ጨምረውም ያ በእርግጥ የእርሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳልሆነና በቅርብ እንዳልተከታተሉት ጭምር ሚዲያ ላይ ወጥተው ሲናገሩ እምብዛም እንዳልተሸማቀቁ በአንክሮ ተመልክተናቸዋል፡፡

በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ የሚገኘው የእነ ኦቦ ለማ ድርጅት ሕገ መንግሥቱ ራሱ የሚለውን እንኳ በቅጡ የተገነዘበው አይመስልም፡፡ ምን ማለትነቱ ለጊዜው ቢያወዛግብ እንኳ በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ይሽከረከርባቸዋል ተብለው የተጠቀሱት ጉዳዮች ‘በአገልግሎት አቅርቦት፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ አተካራዎች’ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ኦዴፓ ሊያሳምነን እንደሚከጅለው ‘የአገር ባለቤትነት’ የሚባል ግዙፍ ጽንሰ ሐሳብ በዝርዝሩ ውስጥ ተካቶበት አናገኝም፡፡

ቀድሞ ነገር በብሔር ፖለቲካ የተቃኘው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከ24 ዓመታት በፊት የፈጠራት ኦሮሚያ እንደ የትኛውም ክልል ሁሉ የኢትዮጵያ ክፍልና አካል የሆነች ክፍለ አገር እንጂ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ራሷን የቻለች አገር ባለመሆኗ የአገር ባለቤትነት የሚለው ሐረግ ከመነሻው አደናጋሪና ብዥታ ፈጣሪ ስለሆነ በዘፈቀደ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው አይደለም፡፡ ይህ ቢታለፍ እንኳ ሰፊውና ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ አገሩ ኦሮሚያ ብቻ ሳትሆን መላዋ ኢትዮጵያ እንደሆነች መታወቅ አለበት፡፡ በግልባጩ ኦሮሚያ ራሷስ ብትሆን የኦሮሞዎች ብቻ ናት ያለው ማነው? ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የምንጋራት፣ በተባበረ ጥረት ሠርተን የምንበለፅግባትና ጥቃት ቢደርስባት ደግሞ እኩል የምንዋደቅላት ምድራችን መሆኗን እንደምን መካድ ይቻላል?

ይህ ጠንካራ ጥያቄ አዘል አስተያየት በደመ ነፍሳዊ ሥሌት የተሰነዘረ አይደለም፡፡ ይልቁንም በጥልቅ አመክንዮ የተደገፈ ለመሆኑ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ (3) ድንጋጌ በዋቢነት ይመለከቷል፡፡ ተጠቃሹ ድንጋጌ ‹‹የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ›› ከማወጅ አለፍ ብሎ፣ በየትኛውም ክልል የሚገኝ ‹‹መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብትና ንብረት ነው›› ሲል በማያሻማ ኃይለ ቃል እንደሚገልጽ፣ በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ ተገቢነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡

ከዚህ ውጪ አዲስ አበባ ከተወላጆቿም ባሻገር ከአራቱም ማዕዘናት የተሰባሰቡ የዝንቅ ነዋሪዎቿ መናኸሪያ ማዕከል እንጂ፣ ትናንት የተፈጠሩት የኦዴፓ ካድሬዎች ቁንጽል በሆነ አቀራረብ አብዝተው እንደሚተርኩላት የየትኛውም ብሔር የተናጠል ሀብትና ንብረት ሆና አታውቅም፣ አሁንም አይደለችም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ (2) ድንጋጌ በወፍ በረር መቃኘት ብቻ ይበቃ ነበር፡፡ ድንጋጌው እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡››

ሌላው ቀርቶ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ አስተዳደራዊ ወሰን ከመበጀቱ በፊት በመዲናዋ አፋፍ ላይ ልዩ ስሙ ኮዬ ፈጬ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ የተገነቡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሰሞኑን ለዕድለኞች በዕጣ እንዲከፋፈሉ መደረጉ አግባብ አልነበረም በማለት፣ ከራሱ የፖለቲካ አብራክ የወጡትን ታከለ ኡማን (ኢንጂነር) በአደባባይ ሲወቅስና ሲከስ ኦዴፓ ፈጽሞ አላፈረም፡፡ ይህ ጸሐፊ እንደሚያምነው ለእርሱ ይብላኝለት እንጂ በሕግ መሠረት በተገባ ውልና በተወሰደ ዕርምጃ ዕጣ የወጣላቸው ደሃ ወገኖች በዚህ የኦዴፓ ዕርምጃ በዕጣ ያገኟቸውን ቤቶች እንዲነፈጉ ማድረግ፣ በነውረኛነት ከማስነቀፍ አልፎ በኃላፊነት ያስጠይቃል፡፡

በመሠረቱ ኦዴፓ በግብር ሲታይ ገና የእናቱን የኢሕአዴግን ጡት ያልለቀቀ እምቦቃቅላ ሕፃን ቢመስልም፣ ራሴን ችያለሁ ባይ የፖለቲካ ድርጅት ነውና በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በሕግ ፊት የሚፀናና አከራካሪ ጉዳይ አለኝ የሚል ከሆነ የሕግ ጠበቆቹን አማክሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በሕግ ሊጠይቅና ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀር ሊወስደው ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ ዕጣው የወጣላቸውንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዕድለኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት በናወዘ ስሜት በመነሳሳት ማገድ፣ ወይም ማሳገድ ግን ከመብቱ ያለፈ የሥርዓተ አልበኝነት ዕርምጃ ይሆንበታል፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ኦዴፓ በመግለጫው የግርጌ ማስታወሻ ላይ ‹‹እመኑኝ፣ ይህንን የጠብ አጫሪነት ዕርምጃ የወሰድኩት በመዲናዋ ውስጥ ከሚኖሩት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት ለመሸርሸር አስቤ ሳይሆን፣ የኦሮሞን ሕዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፈልጌ ነው፤›› ሲል እስከማላገጥ መድረሱ ነው፡፡

ምን ዓይነት የዋዠቀ አቋምና የከሰረ ፖለቲካዊ ድራማ ነው ጎበዝ?

ሰተት ብሎ ገብቶ ሰውየው ከሰው ቤት፣

ምጥ እንደያዛት ሴት እመቤት እመቤት፣

ይላል የአገራችን ሰው፣

ልብ ብለን ልብ ብንገዛ ምን አለበት?

ከአዘጋጁጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን 1981 .. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 .. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ በነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...