Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኩሪ አተር በምርት ገበያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ የገበያ አድማስ መያዝ ችሏል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአንድ ወር ከ14 ሺሕ ቶን በላይ ምርት ለግብይት ቀርቧል

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ከሚገበያዩ አዳዲስ ምርቶች አንዱ አኩሪ አተር ሲሆን፣ በዘመናዊው የግብይት መድረክ እንዲስተናገድ በመንግሥት ተወስኖ በኢትዮጵያ መገበያየት ከጀመረ ሩብ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

በምርት ገበያው በኩል ሰፊ የግብይት ዕድል ማግኘቱ ለወጪ ንግድ የሚቀርበውን የአኩሪ አተር የምርት መጠንና ጥራት ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሲታሰብ፣ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥም ተስፋ ሰጪ የግብይት እንቅስቃሴ ማሳየቱም ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የየካቲት ወር 2011 ዓ.ም. የአኩሪ አተርና የሌሎች ምርቶች የግብይት አፈጻጸም የሚያሳየው፣ የቦሎቄ የግብይት መጠን በየዕለቱ ጭማሪ እየታየበት እንደሚገኝ ነው፡፡

የአኩሪ አተር የየካቲት ወር ግብይት አፈጻጸም፣ ከጥር ወር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ እንደታየበትና በየካቲት ወር ለምርት ገበያው የቀረበው የአኩሪ አተር ምርት በመጠን፣ የ216 በመቶ ዕድገት እንዳሳየም ምርት ገበያው ገልጿል፡፡ አኩሪ አተር የተገበያየበት የገንዘብ መጠንም ከጥር ወር አንፃር ሲታይ፣ በዋጋ የ221 በመቶ ዕድገት እንዳስመዘገበ አመላክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥር 2011 ዓ.ም. 59.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 4,632 ቶን አኩሪ አተር አገበያይቶ ነበር፡፡

ሆኖም በየካቲት ወር ያገበያየው የአኩሪ አተር ምርት መጠን 14,650 ቶን በመሆኑ በአንድ ወር ልዩነት ውስጥ አራት እጥፍ ገደማ ብልጫ ያለው ምርት መቅረቡን የሚያሳይ አኃዝ ነው፡፡ በየካቲት ወር ምርት ገበያው ካገበያያቸው ምርቶች ውስጥ አኩሪ አተር በግብይት መጠኑ 19 በመቶና በዋጋ ድርሻም 191.4 ሚሊዮን ብር እንደያዘ የምርት ገበያው መረጃ ይጠቀሳል፡፡

ከአኩሪ አተር ባሻገር በየካቲት 2011 ዓ.ም. በምርት ገበያው የተገበያዩትን ምርቶችና የዋጋና የመጠን ብዛት የሚያመለክተው መረጃም በ20 የግብይት ቀናት ውስጥ ብቻ 30,199 ቶን ቡና፣ 26,749 ቶን ሰሊጥ፣ 14,650 ቶን አኩሪ አተርና 7,420 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ3.6 ቢሊዮን ብር መገብየቱን ነው፡፡

በየካቲት ወር ቡና በግብይት መጠኑ 38 በመቶ፣ በዋጋም 57 በመቶ በመሸፈን ቀዳሚ ሲሆን ከጥር 2011 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ10.77 በመቶ፣ በዋጋ 10.54 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ በየካቲት ወር በምርት ገበያው ከተገበያየው 30,199 ቶን ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን 64 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ በዋጋም ደረጃ ቢሆን በየካቲት ወር በምርት ገበያው ከቀረቡት ምርቶች 61 በመቶ በዋጋ በመያዝ ቡና ቀዳሚ ሆኗል፡፡ እንዲሁም 18,383 ቶን ያልታጠበ ቡና በ1.17 ቢሊዮን ብር፣ 1,062 ቶን የታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይቱን 40 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡

ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርብ 4,773 ቶን ቡና በ295.8 ሚሊዮን ብር የተገበያየ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የታጠበ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና በ52 በመቶ የግብይት መጠኑን ይዟል፡፡ እንዲሁም 5,981 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ509.95 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ የየካቲት ወር የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በመጠን የ2.67 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ፣ በግብይት ዋጋው ግን የ1.53 በመቶ ቅናሽ እንደታየበት ጠቅሷል፡፡

በየካቲት ወር የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ግብይት 26,749 ቶን ሰሊጥ በ1.2 ቢሊዮን ብር ሲገበያይ ሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ የግብይት መጠኑን 74 በመቶ እንዲሁም የግብይት ዋጋውን 76 በመቶ በመሸፈን ቀዳሚ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የሰሊጥ ግብይት በግብይት ዋጋ የ12.99 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የየካቲት ወር የሰሊጥ ግብይት ከጥር ወር ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ ያሳየ መሆኑን ነው፡፡ በጥር 2011 ዓ.ም. ለምርት ገበያው 32,004 ቶን ያህል ሰሊጥ ለግብይት ቀርቦ በ1.4 ቢሊዮን ብር የተገበያየ እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡ ይህም ከየካቲት 2011 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በመጠን ከአምስት ሺሕ ቶን በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በሌላ በኩል በየካቲት ወር 7,420 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ130.45 ሚሊዮን ብር ስለመሸጡ የሚጠቁመው የምርት ገበያው መረጃ፣ የነጭ ቦሎቄ አማካይ መሸጫ ዋጋ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ4.7 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀርም የ31 በመቶና የ48 በመቶ በግብይት ዋጋና፣ መጠን ጨምሯል፡፡ በተመሳሳይም የነጭ ቦሎቄ የግብይት ዋጋም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ጭማሪ ስለማስመዝገቡ የምርት ገበያው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥር 2011 ዓ.ም.፣ 27,263 ቶን ብር 10,130 ቶን ነጭ ቦሎቄ 32,004 ቶን ሰሊጥና 4,632 ቶን አኩሪ አተር በአጠቃላይ 74,029 ቶን የግብርና ምርቶችን በ22 የግብይት ቀናት ውስጥ ማገበያየቱ ይታወሳል፡፡ በተጠቀሰው ወር ሰሊጥ 43 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ አፈጻጸም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በሁለት በመቶ ቀንሷል፡፡ አጠቃላይ የቦሎቄ የግብይት መጠን በስምንት በመቶ እንዲሁም የግብይት ዋጋውም በአሥር በመቶ ቅናሽ አሳይቶ ነበር፡፡

ባለፈው ወር (ጥር 2011) ሁሉም የቡና ዓይነቶች ማለትም ስፔሻሊቲ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል 27,263 ቶን ቡና ለገበያ ቀርቦ በ1.8 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ የቀረበ ቡና 44 በመቶ የግብይት መጠንና 42 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ የመጀመርያውን ደረጃ ሲይዝ ስፔሻሊቲና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ቡና ተከታዩን ደረጃ ይዞ ነበር፡፡ የቡና ግብይት መጠንና ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ23 በመቶና በ29 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ የቡና አማካይ ዋጋውም አራት በመቶ ቅናሽ አሳይቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች