[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ ከጸሐፊያቸው ጋር ተገናኙ]
- አንቺ ምን አደረኩሽ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያስቀየምኩሽ ነገር አለ እንዴ?
- ኧረ በፍጹም፡፡
- እውነቱን ንገሪኝ?
- ኧረ የለም፣ ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ታዲያ ለምን አልነገርሽኝም?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ሰው ሁሉ አይደል እንዴ የሰማው?
- እኮ ምኑን?
- ኮንዶሚኒየም ቤት እንደደረሰሽ ነዋ፡፡
- እ… እሱን ነው፡፡
- ታዲያ ምን አድርጌሽ ነው?
- ኧረ ምንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን የመሰለ ደስታ ለምን አላካፈልሽኝም ታዲያ?
- ደስታ ነው ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከቤት በላይ ምን ደስታ አለ ብለሽ ነው?
- እሱስ ልክ ነበሩ፡፡
- ታዲያ ምንድነው የምትይው?
- ደስታችን ላይ ውኃ ቸለሱበት እንጂ፡፡
- ማን ነው ውኃ የቸለሰበት?
- የክልሉን መንግሥት መግለጫ አላዩትም እንዴ?
- እሱንማ አይቼዋለሁ፡፡
- ታዲያ ደስታችን ላይ ውኃ ከዚህ በላይ እንዴት ይቸልሱበት?
- ቆይ ተረጋጊ፡፡
- አሁንማ ተፋስ ቆረጥኩ፡፡
- ለምን ትቆርጫለሽ?
- ክቡር ሚኒስትር መግለጫው እኮ ስለኮዬ ፈጬ ብቻ አይደለም፡፡
- ሌላ ምን አለበት ደግሞ?
- ስለ ኮልፌና ቀጨኔ ነዋ፡፡
- መቼም አንቺ ነገረኛ ነሽ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መግለጫው እኮ አዲስ አበባም የእኛ ናት ይላል፡፡
- እሱማ ሰሞነኛ ፖለቲካ ነው፡፡
- ለእኛ ግን ፖለቲካ ሳይሆን ሥጋት ነው፡፡
- ብዙ አትሥጊ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- ይኸው እኔማ ቤት ደረሰኝ ብዬ ዕቁብም ተቀብዬ ነበር፡፡
- ሁለተኛ የደስ ደስ ገጥሞሻላ፡፡
- ምን ያደርጋል ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ዕቁቡን የተቀበልኩት እኮ የቤት ዕቃ ለመግዛት ነበር፡፡
- ገዛሽበት ታዲያ?
- እንዴት አድርጌ?
- ምነው?
- እኔማ ቤቱን እረከባለሁ ብዬ ነበር ዕቃ ለመግዛት ያሰብኩት፡፡
- አሁን ተውሽው ታዲያ?
- መግለጫው እኮ ከባድ ነው፡፡
- ፖለቲካ ነው ስልሽ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲካ ብቻ አይመስለኝም፡፡
- እንዴት?
- ቤቱን ላይ ስሄድ የሰማሁት ተስፋ አስቆረጠኝ፡፡
- ምን ሰማሽ?
- መቼ ዕለት ሄጄ ስጎበኝ የአካባቢው ወጣቶች ምን እንዳሉኝ ያውቃሉ?
- ምን አሉሽ?
- ቤቱ የማን እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡
- የእኔ ነው አልሻቸው?
- እንደዚያ ስላቸው ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው?
- ምን አሉሽ?
- የእኛ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋ ይደውላሉ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ዛሬ ከየት ተገኙ?
- እኔ እኮ ሁሌም ላገኝህ እየፈለኩ ሥራ ስለሚበዛብኝ ነው፡፡
- ምነው በሰላም?
- እንደው ስለአጠቃላይ ሁኔታው እንድንነጋገር ብዬ ነው፡፡
- ስለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ስለአገራችን ነዋ፡፡
- አገራችንማ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ናት፡፡
- ምን ሆነች?
- መቼም ከአገር አልወጡም አይደል?
- የት እወጣለሁ ብለህ ነው?
- ታዲያ እዚሁ ከሆኑማ የችግር መፈልፈያ ሆናለች አይደል እንዴ?
- ተው አታሟርትባት፡፡
- እያሟረትኩባት አይደለም፡፡
- ምን እያደረክ ነው ታዲያ?
- ሀቁን ነው የነገርኩዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ እኮ ቢያንስ ባለሀብት ነህ፡፡
- ብሆንስ ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ የምታማርር ከሆነ ሌላው ምን ይበል?
- እሱንማ ሳስበው እንደው መሬት ተከፍቶ በዋጠኝ ነው የምለው፡፡
- ምን ሆነሃል?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን ያህል ምንድነው ያማረረህ?
- ክቡር ሚኒስትር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻልንም እኮ፡፡
- የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጀመርክ እንዴ?
- ወዴት ወዴት ክቡር ሚኒስትር?
- የምን እንቅስቃሴ ነው ታዲያ?
- ኢኮኖሚው ምንም እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡
- አንቀሳቅሱታ ታዲያ፡፡
- ቀልደኛ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ቀልድ ነው?
- አካላዊ እንቅስቃሴ አይደለም እኮ ያልኩዎት፡፡
- ባይሆን አንተ ነህ ቀልደኛው፡፡
- የምሬን ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ሥራችን ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡
- ለምን?
- ዶላር የለም፡፡
- አሁን ይኼን ሁሉ ችግር የምታወራው ግዛኝ እንዳልልህ ነው፡፡
- ምንድነው የምገዛዎት?
- ትኬቱን ነዋ፡፡
- የቱን ትኬት?
- የእራቱን ትኬት ነዋ፡፡
- የባለአምስት ሚሊዮን ብሩን?
- እህሳ፡፡
- እየቀለዱ መሆን አለበት፡፡
- የምን ቀልድ ነው?
- ሥራ ምንም የለም እያልኩዎት፡፡
- ትኬቱን ከገዛህ ሥራው ይመጣል፡፡
- እንዴት አድርጎ?
- ይለቀቅልሃላ፡፡
- ምኑ?
- ዶላሩ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ደወለላቸው]
- ሰለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ባክህ?
- ሥራ እንዴት ነው?
- ይኸው ወጥረናል፡፡
- እዛም ሆቴል ቀሩ እኮ፡፡
- ሥራው መቼ ያስቀምጣል ብለህ ነው?
- እሱማ አውቃለሁ፡፡
- ከላይ ከላይ እኮ ነው የሚጨመርብኝ፡፡
- በለውጡ እንቅልፍ የለም ተብሏል፡፡
- ለውጡ እንዳይቀለበስ ሌት ተቀን እየሠራን ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ለውጡን ለማሳለጥ የአቅሜን እየጣርኩ ነው፡፡
- እንደዚህ እጅ ለእጅ ካልተያያዝን ረዥም ርቀት መጓዝ አንችልም፡፡
- የኢኮኖሚው ጉዳይ ግን እያሳሰበኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው ያሳሰበህ?
- ሁሉም ነገር ተቀዛቅዟል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኸው እኛም ትንሽ እናሟሙቀው ብለን እኮ ፕሮጀክቶችን ጀምረናል፡፡
- ምን ዓይነት ፕሮጀክት?
- ሸገርን የማስዋብ ነዋ፡፡
- ዛሬ አደዋወሌ ስለእሱ ለማውራት ነበር፡፡
- ስለምኑ ለማውራት?
- ስለእራት ግብዣው ነዋ፡፡
- ምን ልትለኝ ፈልገህ?
- የእራት ግብዣው አስተባባሪ ኮሚቴ መሆንዎትን ሰምቻለሁ፡፡
- ትክክል ነው፡፡
- ያው የለውጡ ደጋፊ መሆኔን ያውቃሉ አይደል?
- አልገባኝም?
- አዲስ አበባችን ሁሌም የመናፈሻ ቦታዎች እንዲኖሯት እፈልግ ነበር፡፡
- ፕሮጀክቱም ያንን ሐሳብ ለመደገፍ ነው የታቀደው እኮ፡፡
- እንዲያው አንድ ነገር ላስቸግርዎት ነበር፡፡
- ምንድነው የምታስቸግረኝ?
- ይህ ታሪካዊ ግብዣ እንዲያመልጠኝ አልፈልግም፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- አንድ ትኬት ቢሰጡኝ ብዬ ነበር፡፡
- የእራቱን?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዋጋው አምስት ሚሊዮን ብር መሆኑን ረሳኸው?
- ኧረ አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ከየት አምጥተህ ትከፍላለህ?
- በዱቤ እንዲሰጡኝ ነው፡፡
- በዱቤ?
- አዎን በዱቤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዱቤስ ቢሆን ከየት አምጥተህ ትከፍለዋለህ?
- በጥቂት ወራት እንደምከፍለው እርግጠኛ ነኝ፡፡
- እኮ ከየት አምጥተህ?
- በቅርቡ መሥራቴ አይቀርም፡፡
- ምን?
- ሙስና!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወሉ]
- ሰላም ወዳጄ፡፡
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ጠፋህ እኮ፡፡
- ኧረ እርስዎ ነዎት የጠፉብኝ፡፡
- ምን ላድርግ ብለህ ነው፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ዕዳ ውስጥ ገብቼ ነዋ፡፡
- የምን ዕዳ?
- የቲኬት ነዋ፡፡
- የምን ቲኬት?
- የእራቱ ነዋ፡፡
- ቲኬት ሸጠው ብሩን አጠፋሁት እንዳይሉኝ?
- እሱ ቢሆን ይሻለኝ ነበር፡፡
- ታዲያ ምን ሆኑ?
- የሚገዛኝ አጣሁ፡፡
- ምንም አልሸጡም፡፡
- ከየት መጥቶ?
- ምነው?
- ሰው ሁሉ ችግር ነው የሚያወራው፡፡
- ለነገሩ እንቅስቃሴ ሁሉ ተዳክሟል፡፡
- ኧረ አንተ እንኳን አበረታታኝ፡፡
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- እንድታግዘኝ ነው የደወልኩት፡፡
- ምን ላግዝዎት?
- ትኬቱን ሽጥልኝ፡፡
- እርስዎን ያልገዙዎት እኔን ማን ይገዛኛል ብለው ነው?
- አንተ እንደምትሸጠውማ እርግጠኛ ነኝ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ይታሰብልሃል፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ኮሚሽን፡፡
- ስንት ፐርሰንት
- 10 ፐርሰንት!