ምስጦች ቅርፃቸው ሞላላ ሆኖ ስድስት እግሮችና ጥንድ ክንፍም አላቸው፡፡ መልካቸው ቡናማ ቀለም ነው፡፡ በጋራ መኖርና ዕርጥብ እንጨት መመገብ ይወዳሉ፡፡ ምስጦች ድምፅ አልባ አጥፊዎች በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህ ስም የተሰጣቸው ዛፎችን፣ የዛፍ ሥሮችንና ተክሎችን እንዲሁም የእንጨት ውጤቶችን ከላይ ሳይሆን ከሥር ገብተው ውስጡን ቦጥቡጠው ስለሚበሉና ቅርፊት ብቻ ስለሚያስቀሩ ነው፡፡ የፔስት ወርልድ ፎር ኪድስ ድረ ገጽ እንደሚያስነብበው፣ ምስጦች ለ24 ሰዓት ሳያቋርጡ ይመገባሉ፡፡ የተመቻቸ ስፍራ ካገኙ እዚያው መጠለያቸውን ሠርተው ይኖራሉ፡፡
በዓለም 3,000 ያህል የምስጥ ዝርያዎች ሲኖሩ፣ በዓመት አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ተክልና የእንጨት ውጤቶችን ያወድማሉ፡፡ ምስጦች አጥፊዎች ቢሆኑም፣ ዛፍ አርጅቶ በየጫካው ሲገነደስ ስለሚመገቡት፣ ደን በማፅዳትም ይታወቃሉ፡፡ ንግሥቲቷ እስከ 50 ዓመት ልትኖር ትችላለች፡፡