Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በዴር ሡልጣን ገዳም ላጋጠመን ችግር መፍትሔው ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ ማየት ነው 

  በዴር ሡልጣን የኢትዮጵያን ገዳም እናድን ኮሚቴ

  መግቢያ

  በግዕዝ ቋንቋ ደብረ ሥልጣን በጥንቱ ዓረብኛ ዴር ሡልጣን ማለት ትርጓሜው የንጉሥ ርስት ማለት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ትርጓሜ መሠረት ይህ ሥፍራ ሥያሜውን ያገኘው ጥንቱንም ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥት ማክዳ (የሳባ ንግሥት ወይም ንግሥተ አዜብ) እና ተከታዮቿ በየዓመቱ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ሲመጡ ማረፊያ እንዲሆናቸው በማሰብ ስለሰጣቸው ነው ይላሉ።

  የዴር ሡልጣን ገዳም የሚገኘው በቅድስት አገር በኢየሩሳሌም ከተማ ነው። ይህ እጅግ የተከበረ ገዳማችን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካውያን በሙሉ፣ አልፎም ለዓለምም ታላቅ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርስ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ገዳም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበረበት በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከተማ፣ ከቅዱስ ጎልጎታ በስተ ምሥራቅ ተዋሳኝ ሥፍራ ላይ ይገኛል። በውስጡም፣ ከላይ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከታች ምድር ቤቱ የአርባዕቱ እንስሳ (መድኃኔ ዓለም) አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም መነኮሳቱ ለመኖሪያነት የቀለሷቸው በጭቃና በእንጨት የተሠሩ ጎጆዎች አሉበት።

  የገዳሙ ታሪክ በአጭሩ

  ገዳሙ መቼና በማን እንደተገደመ ለማወቅ ያሉትን ታሪካዊ ሰነዶች በጥልቀት መመርመር ያሻል። ንግሥት ማክዳ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ በዐይኗ ዓይታ ለመረዳትና በእንቆቅልሽም ትፈትነው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም አቅንታ እንደነበረ፣ የንጉሡም ታላቅ እንግዳ እንደነበረች በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገሥት 10፡1-10 እንዲሁም ዜና መዋዕል ካልዕ 9፡1-9 ተጠቅሶ ይገኛል። ኢትዮጵያውያን ከዚያም በኋላ በየዓመቱ ለአይሁድ ፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ይሳለሙ እንደነበረጌታችን ሐዋርያትን አፍርቶ ወደመንበሩ ከአረገ ከአንድ ዓመት በኋላ በ34 .. የዚያን ዘመን የኢትዮጵያ ንግሥት የነበረችዋ ንግሥት ህንደኬ ዋና ሹም የነበረው ጃንደረባው ባኮስ በሐዋርያው ፊሊጶስ የተጠመቀበት ታሪክ በሐዋርያት ሥራ 8፡26-39 ተብራርቶ ተገልጿል። ስለሆነም ንጉሥ ሰሎሞን ይኼንን ሥፍራ ለንግሥት ማክዳና ተከታዮቿ/ተወላጆቿ ማረፊያ ርስት እንዲሆናቸው ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በቅድስት ኢየሩሳሌም ከተማ ቋሚ ነዋሪዎች እንደሚሆኑ ማጠየቅ ይቻላል።

  ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ከ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በቤተልሔም፣ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ፣ በአስተማረባቸውና ተአምራቱን ባሳየባቸው በጌቴሰማኒ፣ በኢያሪኮና በሌሎች ሥፍራዎች፣ በተሰቀለበት በቀራኒዮ እንዲሁም በተቀበረበት በጎልጎታ ገዳማት መሥርተውአብያተ ክርስቲያናትን አንጸውጽኑዕ ሃይማኖተኝነታቸውን ሲያስመሰክሩ እንደኖሩ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። እስከ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለመነኮሣቱ ኑሮ መደጎሚያ እንዲሁም ለገዳማቱ ማስፋፊያ የሚሆን ገንዘብና ንብረት ሲለግሱ ኖረዋል።

  ስለገዳሙ ይዞታ «ባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄ»

  ችግሩ እንዴት ተፈጠረ? በገዳሙ ይዞታ ላይ በግብፃውያን ኮፕቶች በኩል «የባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄ» የተነሳው መቼ ነበር? በምን ሁኔታ? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መልስ ካገኘ የችግሩን መፍትሔ ለመሻት ግማሽ መንገድ ያስኬዳል። እስከ 1770 .. ድረስ ኮፕቶች በዴር ሡልጣን ገዳም ቋሚ ነዋሪ መሆናቸው አይታወቅም ነበር። ሆኖም መዓልም ኢብራሒም (ኢብራሒም ጀወሐሪ) የተባለ ግብፃዊ በዚሁ ዓመት ወደ ዴር ሡልጣን ገዳም መጥቶ «አባቶቼ የሃይማኖት ወንድማችሁ ነኝ፤ በከተማው ማረፊያ ቤት ስለ አጣሁ እባካችሁን ከእናንተ ቦታ ማረፊያ ስጡኝ»  በማለት ደጋጎቹን ኢትዮጵያውያን መነኮሳት እንደተጠጋ በወቅቱ የሠፈሩት ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ ወቅት በኢትዮጵያ የማዕከላዊ መንግሥት መዳከምና የዘመነ መሣፍንት መጀመሪያ ጊዜ ነበር። ኢብራሒም ጀዋሪ የኢትዮጵያውያን መነኮሳቱን ፍጹም ክርስቲያናዊ ደግነት እንደ ድክመት በመቁጠር ለዚያን ወቅት የኢየሩሳሌም ገዢዎች ለነበሩት ለቱርኮች «ለእነርሱ ጉዳይ ተጠሪ እኔ ነኝ» እስከማለት እንደደረሰ፣ ከገዳሙ ቤቶች አንዱን ይስሐቅ ቤይ ለሚባል ሰው በኪራይ እንደሸጠ ተዘግቧል። ኋላም ከአገሩ ከግብፅ ቀሲስ ጊዮርጊስ የሚባል ካህን አስመጥቶ በገዳሙ እንዳስገባ እኒሁ ሰነዶች ያትታሉ። በኢብራሒም እግር የተተካው ቀሲስ ጊዮርጊስም በተራው ካለሥልጣኑ ከገዳሙ የምሥራቁን ክፍልመስኮቦች (ሩሲያውያን) እንደሸጠ፣ ከዚያም የኢትዮጵያውያን ይዞታ አብዛኛውን ክፍል ግብፆች እየቀነሱ ለአርመኖችና ለግሪኮች እንደሸጡ መዛግብቱ ያብራራሉ። በ1820 .. ደግሞ «ገዳሙን እናሳድሳለን» በሚል ሰበብ ግብፆች ኢትዮጵያውያኑን መነኮሳት ከገዳሙ እንዳስወጧቸውና ገዳሙ ከታደሰም በኋላ ተመልሰው እንዳይገቡ በማድረግ ዛሬ በሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲቀሩ እንዳደረጓቸው ተመልክቷል። በኢትዮጵያውያን መነኮሳት ላይ የከፋው ጉዳት የደረሰው በአካባቢው በ1838 .. በተሠራጨው የተሰቦ በሽታ ነበር።

  በበሽታው ሁሉም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ማለቃቸው ይነገራል። በዚያን ወቅት የኢየሩሳሌም ገዢ የግብፁ ተወላጅ እስማኤል ፓሻ ስለነበረ፣ ግብፆቹ አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያውያንን ሕጋዊ የሠነድ ማስረጃዎች ማከማቻ ቤተ መዛግብት «የተስቦውን በሽታ ያስፋፋል» በሚል የሐሰት ምክንያት ሙሉ በሙሉ አቃጥለው እንዳወደሙት በኢትዮጵያውያንና በሌሎችም የታሪክ ሊቃውንት የተዘጋጁት ታሪካዊ ሠነዶች ያስረዳሉ። ይህም በዘመኑ በነገሠው በሡልጣን አብደል ማሊክ ኢብን ማርዋን የግዛት ዘመን እንደነበረ ያትታሉ፣ የገዳሙንም መሬት እርሱ የሰጣቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ከዚያም የገዳሙ ባለይዞታነታቸው በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሡልጣን ሣላህዲን እንደተረጋገጠላቸው በየጊዜው ከሚያሠራጯቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። ሆኖም በእኛ (በኢትዮጵያውያን) እና በኮፕት ግብፃውያን መካከል ለተነሳው ውዝግብ የሚቀርቡት ማስረጃዎች ተዓማኒነት ከታሪካዊ ማስረጃዎች አንፃር ሲመዘኑ ያላቸው ፋይዳ ምን ይመስላል? የሚለውን ነጥብ በጥልቀት መመርመርና ትክክለኛውን ገጽታ ለሁሉም ባለድርሻ አካሎች ማብራራት ለዚህ ኮሚቴም ሆነ በተመሳሳይ ዓላማ ለተሠለፉ ወገኖች ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል።

  ታሪካዊ መረጃዎች ምንን ያመለክታሉ?

  በአንድ ታሪካዊ ሥፍራ በተለያዩ ተፎካካሪዎች የባለቤትነት ጥያቄ ሲነሳ መጀመሪያ ማጣራት የሚያስፈልገው ጉዳይ «ለይዞታው ማን ቅድሚያ ነበረውየሚለው ነው። ከላይ እንደተጠቀሰውየኮፕቶች የባለቤትነት ማስረጃ እጅግ ቢቀድም ከ677 .. በፊት አይሆንም፣ ለዚያውም ሡልጣን አብደል ማሊክ ኢብን ማርዋን «እንደተወለደ ነግሦ የዚያኑ ዓመት ርስቱን ሰጥቶናል» ካላሉ በስተቀር። ለኢትዮጵያውያን ግን ከጥንት ከንግሥት ማክዳ ጀምሮ የይዞታው ባለቤቶች እንደነበሩ በዚህ ጽሑፍ ተብራርቷል። ነገር ግን ኮፕቶች «በርስትነት ተሰጥቶናል» ከሚሉበት ከአርባ አንድ ዓመታት በፊት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን ያስተዳደረው የሙስሊሞች መሪ ዑመር ኢባን አል ኪታብ በ636 .. የዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን (አበሾች) ይዞታ መሆኑን ያረጋገጠበት ፊርማ (አዋጅ) አለ፡፡

  ከአረብኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው እንዲህ ያትታል፦

  «…ለሕይወታቸው ለአብያተ ክርስቲያኖቻቸውና ለገዳሞቻቸው እንደዚሁም በጌታ መቃብር ውስጥ ሆነ በውጭ፣ ጌታ ክርስቶስ በተወለደበት በቤተልሔምና በታላቁ ቤተ ክርስቲያንቀጥሎም በዋሻው ሦስት ማዕዘናት ማለት በደቡብ፣ በሰሜንና በምሥራቅ  ሆነው በይዞታቸው በሚገኙት በሮችና ቅዱሳት መካናት ሁሉ ተጠባቂነትና ደኅንነት ያገኙበታል። ይህ ውል በአገሩ ለሚኖሩት ሌሎች ክርስቲያን ሕዝቦች ማለት ለጆርዳናውያንና (ኩርዶች) ለኢትዮጵያውያን (ሐበሾች) እንደዚሁም ለመጎብኘት ለሚመጡት አውሮፓውያን፣ ለኮፕቶች፣ ለአርመኖች፣ ለኔስቶራውያን፣ ለያዕቆባውያንና የፓትርያርኩ ተከታዮች ለሆኑት ማሮኒታውያን ሁሉ በኅብረት ያገለግላል። …»  ከዑመር ኢባን አል ኪታብ ፊርማ (አዋጅ) በኋላም በየጊዜው ኢየሩሳሌምን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የሙስሊም ገዢዎች እንዲሁም ሥፍራውን የጎበኙ ምዕመናንና የታሪክ ባለሙያዎች ስለኢትዮጵያውያን መነኮሳት የዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነት አያሌ ማስረጃዎችን አትመው አልፈዋል። ስለዚህ ከዘመኑ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቀው ትልቅ ኃላፊነት እኒህን ታሪካዊ ማስረጃዎች ምርኩዝ አድርጎ ችግሩ በዘለቄታዊ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኝበትንና ኢትዮጵያውያንም ካለምንም ውዝግብ የገዳሙ ታሪካዊ ባለቤትነታችን ተረጋግጦ መንፈሳዊና ታሪካዊ ዕሴቶቻችንን ማስጠበቅ እንድንችል ነው።

  አሁን ያለው የገዳሙ ሁኔታ

  በዴር ሡልጣን ገዳም ላጋጠመን ፈተና መፍትሔ ለማምጣት ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ነገሥታትና ዜጎች የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ምንም እንኳን በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የዮርዳኖስ መንግሥት ቅድስት ኢየሩሳሌምን በሚያስተዳድርበት ዘመን በ1959 .. (... 1967) የገዳሙ ይዞታ ባለቤት ኢትዮጵያ እንደሆነች የፍርድ ውሣኔ ቢያሳልፍምኮፕቶች ባሳደሩት ተፅዕኖ በ40 ቀናት ውስጥ ፍርዱ ተቀለበሰ። ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት ግን በፊቱ ፍርድ የተረከቡትን የገዳሙን ቁልፍ ሳያስረክቡ፣ የአጋጣሚ ነገር በዚያው ዓመት ይህ የፍርድ አፈጻጸም መፍትሔ ሳያገኝየእስራኤል መንግሥት በስድስቱ ቀን ጦርነት ወቅት የኢየሩሳሌም ከተማን ተቆጣጠረ። እስካሁንም ድረስ የዮርዳኖስ ፍርድ ቤት ለኢትዮጵያውያን የፈረደው ፍርድ ተፈጻሚነትን ባያገኝም፤ የእስራኤል መንግሥት የካቲት 19 ቀን 1963 .. (... ማርች 28 ቀን 1971) የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት (የቅዱስ ሚካኤልና የመድኃኔ ዓለም) የበር ቁልፎች በኢትዮጵያውያን እጅ እንዲቆዩ በስታተስ (ባለበት ይርጋ) ደንብ መሠረት ወስኖ በዚያ ሁኔታ ይገኛል።

  ነገር ግን የእሥራኤል መንግሥት ገዳሙ ስላረጀ ለማደስ ፈቃድ ሲጠየቅ የስታተስ ሕግን በምክንያትነት በማቅረብ ግብፆች ገዳሙ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ እንዲጠቀልሉት መንገዱን ከፍቶላቸው ቆይቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት በሊቀ ጳጳሳቸው እየተመሩ በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ዋዜማ፣ የቅዳም ስዑር ዕለት እንዲሁም በሌሎችም ቀናት በኢትዮጵያውያን ምዕመናንና በመነኮሳት ላይ ከፍተኛ ረብሻ መፍጠራቸው የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። የሃይማኖት ወንድሞቻችን የሆኑትና 1,600 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ጳጳሳትን እየላኩ የእኛን ቤተ ክርስቲያን በበላይነት ሲመሩ የኖሩት የኮፕቶች ድርጊት፣ ከአንድ ክርስቲያን ይቅርና ከማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የማይጠበቅ ምግባር ነው።

  ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአምስት ዓመታት በፊት ግሪኮች ገዳማቸውን ለማደስ ርብራብ (scaffold) ለማቆም አመቺ ሥፍራ ሲያጡ ጊዜ የእኛን አባቶች በእኛ የቅዱስ ሚካኤል ጣሪያ ላይ ለማቆም እንዲፈቅዱላቸው ይጠይቁና ይፈቀድላቸዋል። ፈቃዱ ለምን ያህል ጊዜ እንደነበረ ባይታወቅም ከአንድ ዓመት በፊት ማለትም መስከረም 12 ቀን 2010 .. (የሚካኤል ዕለት) ከግሪኮች የሕንፃ ጥገና ሥራ ጋር በተያያዘ የወደቀ ትልቅ የግንብ ፍራሽ በእኛ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ጣሪያ ላይ ወድቆ ጣሪያውን ይነድለዋል፣ የቤተ ክርስቲያኑም መቅደስ ይጋለጣል፣ በዚያም ምክንያት የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ተቋርጦ ነበር። ሆኖም በመንግሥትና በሃይማኖት አባቶች በተደረገው ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ የእሥራኤል መንግሥት በቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች አማካይነት የቤተ ክርስቲያኑን ጣሪያ አድሶታል። ታቦተ ሕጉም ታኅሣሥ 12 ቀን 2011 .. ከብሮ  ቤተ ክርስቲያኑ መደበኛውን የቅዳሴና ሌሎችንም መንፈሳዊ አገልግሎቶች መስጠቱን ቀጥሏል። ይህ የተፈጸመው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ነውና እናመሰግነዋለን። ከዚህ ሁኔታ የምንረዳው ችግሩን ከሥር መሠረቱ ተረድተንበሁሉም አቅጣጫ አጣርተን መፍትሔ ከሰውም፣ ከፈጣሪም እንደሚገኝ ነው።

  ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ ምንድን ናቸው?

  ከዚህ በፊት ጥልቅ ጥናት ያደረጉና ጉዳዩን የተከታተሉት የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ዜጎችከኮፕቶች ጋር በገዳሙ የይዞታ ይገባኛል ውዝግብ መፍትሔ ይገኝባቸዋል የሚባሉትን አማራጭ ሐሳቦቻቸውን አካፍለዋል። ከእነዚህ ሐሳብ አፍላቂዎች የምንረዳው መፍትሔ ለማግኘት ቀደም ብሎ የዮርዳኖስ ሓሽማታዊ መንግሥት ፍርድ ቤት በ1959 .. (... 1967) «የገዳሙ ባለይዞታ ኢትዮጵያውያኑ ናቸው» ብሎ የፈረደው ፍርድ የእሥራኤል መንግሥት ተግባራዊ እንዲያደርግና «ስታተስ» መብታችንን እንዲያስከብርልን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማግባባት ወይም ጫና ማድረግ፣ ያሉንን ታሪካዊ መረጃዎች አጠናቅሮ እንደገና በእሥራኤል መንግሥት ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲታይ ማድረግ፣ በኮፕቶች ላይ ዓለም አቀፋዊ ጫና በመፍጠር ችግሩን በድርድር መፍታት የሚሉ ናቸው። ከእኒህ የተሻሉ አማራጮችን በማፍለቅ ወይም ከእኒሁ መካከል በማቀናጀት ችግሩን ለመፍታት መሞከርም ብልህነት ነው።

  ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ምን ይጠበቃል?

  በዴር ሡልጣን ገዳም ያጋጠመንን ችግር ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ በማየት መፍትሔ መፈለግ ያሻል። ከአንድ ዓመት በፊት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ በላዩ ላይ በወደቀበት የግንብ ፍራሽ ምክንያት በመነደሉ ቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ባቋረጠበት ወቅት፣ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን «በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን የኢትዮጵያን ገዳም እናድን ኮሚቴ» በመባል የሚጠራ ኮሚቴ አዋቅረው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የኮሚቴው ራዕይም፣ «የገዳሙ ባለቤትነት ከታሪካዊና ሕጋዊ መነሻ መሠረቱ የኢትዮጵያ መሆኑ ተረጋግጦ፣ የሚፈለግበትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች እንግዶች በተሟላና በቅልጥፍና  የሚከናወንበት መንፈሳዊ ሥፍራ ሆኖ ማየት፤» ነው። ኮሚቴው በ16 ወራት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል። ከእነዚህም መካከል፣ ሥራውን በሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎች አከፋፍሎ ዕቅድ በማውጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በእሥራኤል፣ በተለይም በቅድስት ኢየሩሳሌም ከተማ ከተቋቋሙትና «በገዳሙ ጉዳይ ያገባናል» ብለው ከሚንቀሳቀሱት ሁለት የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበሮች ጋር ሥራውን አቀናጅቶ ለመሥራት የሚያስችለውን የግንኙነት መስመር ዘርግቷል፡፡ ስለጉዳዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ ለሚመለከታቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ለፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የተማጽኖ ደብዳቤዎችን ልኳል። በቅርቡም የኮሚቴው ሊቀ መንበር አቶ ዘውገ ገድሉና አባል የሆኑት መልአከ ብርሃናት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በአካል ተገኝተው በማብራራት ኮሚቴው ለወደፊቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። በተልኳቸው ማጠናቀቂያም በአገር ቤት ሁሉም የባለድርሻ አካላት የሚወከሉበት የዴር ሡልጣን ጉዳይ አገራዊ ኮሚቴ እንዲመሠረት የሚያስችል ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ይጠበቃል።

  ለማጠቃለል የዴር ሡልጣን ገዳም ሕንፃ በአጠቃላይ በመፍረስ አደጋ ላይ የሚገኝ ነው። በተጨማሪም በዚያ የሚገኙት መነኮሳት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሰው ልጆች ከሚኖሩበት ሁኔታ አንፃር የእነርሱ አኗኗር ሲነፃፀር እጅግ የሚዘገንን በመሆኑ ሁኔታውን ለመቀየር የእኛን ሁለገብ ድጋፍ ይሻሉ። በዚህ ገዳማችን ላይ ያለው ችግር ይበልጥ የተወሳሰበው የሃይማኖት አንድነት ባለን፣ ነገር ግን በገዳሙ ይዞታችን ላይ በተፃራሪነት በቆሙብን የኮፕት (ግብፅ) ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ሴራና ተንኮል መሆኑ ደግሞ ሐዘናችንን ያበረታዋል።

  ስለሆነም በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገሮች በየአካባቢው የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዴር ሡልጣን ገዳም ጉዳይ ዙሪያ ተደራጅተን በጋራ በመንቀሳቀስ፤ ችግሩን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት መሞከር ይገባናል የሚል እምነት አለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ የመንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ምንጭ ናት። በየዓመቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ከሚገኘው ከፍተኛ ገንዘብ ውስጥ በአመዛኙ የሚመነጨው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋሞች (ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ ወዘተርፈ) ነው። ስለሆነም በመንግሥት በኩል እስካሁን ድረስ ሲደረግ ከቆየው ድጋፍና እንክብካቤ በላይ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ሊንከባከባትና ሊጠብቃት ይገባል ብለን ለማሳሰብ እንወዳለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles