ለስድስተኛ ጊዜ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የጉማ ፊልም ሽልማት ስመ ጥሩ የፊልም ባለሙያ ኃይሌ ገሪማ (ፕሮፌሰር) የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነው ተመርጠዋል፡፡
የሽልማት ተቋሙ ኢትዮፊልም እንዳስታወቀው፣ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በሚካሄደው መርሐ ግብር በ18 ምድቦች ከቀረቡ 90 ዕጩዎች አሸናፊዎቹ ይፋ ይሆናሉ፡፡ ያለ ተወዳዳሪ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት ኃይሌ ገሪማ ከሠሯቸው ፊልሞች መካከል ቡሽ ማማ፣ ምርት ሦስት ሺሕ ዓመት፣ ሳንኮፋ፣ ዓድዋና ጤዛ ይገኙባቸዋል፡፡
በአፍሪካውያን እና በአፍሪካ አሜሪካውያን ላይ ትኩረት ካደረጉት ከፕሮፌሰር ኃይሌ ፊልሞች ሰባቱ በተለያዩ የዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሸላሚ ናቸው፡፡
ለዘንድሮው የጉማ ሽልማት ውድድር የቀረቡት ፊልሞች በ2010 ዓ.ም. ከመስከረም እስከ ጳጉሜን ለዕይታ የበቁ ፊልሞች ሲሆን፣ ከተሠሩት 130 ፊልሞች ለውድድሩ 61 መመዝገባቸው ታውቋል፡፡
በሰማያዊ ምንጣፍ በሚከናወነው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ከባህላዊ አለባበስ ባሻገር ስኒከር፣ ጂንስና ቲሸርት ከመድረኩ ለመቀነስ እንደሚሞከር ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል፡፡