Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቤቶች ኮርፖሬሽን የመጀመሪያውን ግንባታ ለመጀመር የ1.8 ቢሊዮን ብር ስምምነት ተፈራረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ሊገነባቸው ላቀዳቸው አፓርታማዎችና ቪላ ቤቶች፣ በአዲስ አበባ በአምስት ሥፍራዎች በመጀመሪያ ዙር ለመገንባት ስምምነት ተፈራረመ፡፡ የግንባታው ወጪ 1.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት እንደሚሸፈንም ኮርፖሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡

ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በመጀመሪያ የሚገነቡ ቤቶችን በተመለከተ በካፒታል ሆቴል ለተለያዩ አካላት አስተዋውቋል፡፡ በዕለቱም ግንባታውን ከሚያከናውኑ አራት አገር በቀል ድርጅቶችና አንድ የቻይና ተቋራጭ ጋር ተፈራርሟል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊዋ ወ/ሮ ደምቢቱ ሐምቢሳና የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር ዓባይ የተገኙ ሲሆን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ረሻድ ከማል ከተቋራጭ ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እቴቴ ኮንስትራክሽን፣ ኤፍኤ ኮንስትራክሽንና አብረሃም ንጉሤ ኮንስትራክሽን ተገኝተው የተፈራረሙ ሲሆን፣ አንድ አገር በቀልና አንድ የቻይና ተቋራጮች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ስላልተገኙ በቢሮ ይፈራረማሉ ተብሏል፡፡ 

ከፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በፊት በመጀመሪያ ዙር የሚገነቡትን ቤቶች በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ የቤቶች ልማትና ዲዛይን ክትትል ዳይሬክተር ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በመጀመሪያው ዙር ግንባታ የሚከናወንባቸው አምስት ሥፍራዎች በዘጠኝ ክፍላተ ከተሞች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከሰባት እስከ 12 ፎቅ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ፣ እነዚህም ሕንፃዎች ከወለል በታች ከአንድ እስከ ሦስት ምድር ቤቶች ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

የሚገነቡት ሕንፃዎች ስምንት ብሎኮች ሲኖሯቸው ቅይጥ አገልግሎት እንደሚሰጡ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በቤቶች ኮርፖሬሽን የሚገነቡ የንግድና የድርጅት ቤቶች የውል ስምምነት እንደሚደረግ፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች እጥረትን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ቤቶች ይገነባሉ ተብሏል።

በሁለት ዓመት ውስጥ ተገንብተው የሚጠናቀቁ ከሰባት እስከ 12 ፎቆች ያላቸው 435 የንግድና የመኖርያ ቤቶችን ለመገንባት ስምምነት ተደርጓል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በጠራው ውይይት ላይ ከአዳዲስ ቤቶች ግንባታው ማስጀመር ጋር ተያይዞ በንግድና በድርጅት ቤቶች የኪራይ ተመንን ማሻሻያ ማድረጉን በተመለከተ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡ ላለፉት 41 ዓመታት በአገልግሎት ላይ የነበረው የኪራይ ተመን ዋጋ ለማሻሻል የተደረገውን ጥናት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር መገባቱም ተገልጿል።

በማሻሻያው መሠረት ከ95 በመቶ በላይ ተከራዮች ውል እየፈጸሙ መሆኑን የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ በአፈጻጸም ሒደት ውይይት እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

በቀጣይም ከኪራይ ተመን ዋጋ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚመለከትም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች