በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በዞኑ 50 ሺሕ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አብዛኞቹም አርሶ አደሮች መሆናቸውን፣ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ የመንግሥት ሠራተኞችም መፈናቀላቸውን፣ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን፣ ከቀናት በፊት ከትግራይ ክልል ዳንሻ አካባቢ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሮቃ በተባለው መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ተፈናቃዮቹን ከ40 እስከ 50 ቀናት ውስጥ መልሶ ለማቋቋም እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተከሰቱ ግጭቶች ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላው፣ ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላው ወረዳ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺሕ የደረሰው ቀስ በቀስ ነው ብለዋል፡፡ በዞኑ ውስጥ የተፈናቃዮች ቁጥር መጀመርያ ላይ 15 ሺሕ እንደነበር፣ ከዚያ ወደ 33 ሺሕ፣ ቀጥሎም ወደ 45 ሺሕ እያለ 50 ሺሕ መድረሱን፣ ቁጥሩ አሁንም እያደገ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡
ማዕከላዊ ጎንደርን ጊዜያዊ መጠለያ ያደረጉት ተፈናቃዮች አብዛኞቹ ከምዕራብ ጎንደር ቋራ፣ መተማ ዮሐንስና ከገንዳ ውኃ የተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህን ዜጎች ወደ መጡበት ለመመለስም በምዕራብ ጎንደር የዝግጅት ሥራ መከናወን እንዳለበት፣ ነገር ግን የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና መዋቅር እዚያ ባለመኖሩ፣ ተባብሮ መሥራት ላይ ክፍተት እንደፈጠረ አቶ መንበሩ አስረድተዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ችግሩ ያለባቸው አካባቢዎች ምሥራቅ ደምቢያ፣ ምዕራብ ደምቢያ፣ ጭልጋ ቁጥር አንድ፣ ጭልጋ ቁጥር ሁለት፣ አይከልና አርማጭሆ ናቸው ብለዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 4,361 ቤቶች በግጭቱ የተቃጠሉ መሆኑን፣ ይህ ቁጥር ግን ሰርቪስ ቤቶችና የመሳሰሉትን አያጠቃልልም ብለው፣ የሰዎችም ሕይወት የጠፋ በመሆኑ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እየተጣራ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም የዞኑ አስተዳደርና የክልሉ መንግሥት በጋራ እየሠሩ ነው ተብሏል፡፡ የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ ለመገንባትም ቆርቆሮና ሚስማር በክልል ደረጃ መገዛቱን፣ በቃጠሎ ለወደሙት 4,361 ቤቶች ግንባታ እንደሚጓጓዙ አቶ መንበሩ ገልጸዋል፡፡
ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ከተመለሱ በኋላ ሌላ ችግር እንዳያጋጥማቸው በፀጥታ አካላት ለግጭት የተጋለጡ ቦታዎች አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍንባቸው እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ‹‹በፊት በአጀብ እንኳን የማይታለፉት ቀጣናዎች ዛሬ አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይቻላል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በመተማ መስመር ያለውና ከጎንደር ወደ ጭልጋ የሚወስደው መስመር፣ ከጎንደር ትክል ድንጋይ ሳንጃ መስመር፣ ወደ ሽሬም አደገኛ የሚባሉ ቦታዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ መንገዶች ተዘግተውም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት እየተካሄደ መሆኑንም አቶ መንበሩ ገልጸዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩም ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ወደ ቀዬአቸው የተመለሱት ቤታቸው በግጭቱ ያልተቃጠለባቸው 770 አባወራዎች አንከርና ማደዛ የተባሉ አካባቢዎች እንዲመለሱ የተደረገው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በምሥራቅ ደምቢያ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች መልሶ የማስፈር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡