‹‹ሕገወጡንና ሕጋዊውን ይዞታ የመለየት ሥራ እያከናወንን ነው››
የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር
በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን የሱሉልታ ከተማ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ምልክት በማድረጉ ‹‹ሊፈርስብን ነው›› የሚል ሥጋት ስለገባቸው፣ የክልሉ መንግሥት ወይም የፌዴራል መንግሥት እንዲታደጋቸው ተማፅኖ አቀረቡ፡፡
የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ከሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ መሬት በወረራ የያዙትን፣ ከአርሶ አደሮች ላይ የገዙትን፣ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸውንና የሌላቸውን የከተማውን ነዋሪዎች ለማወቅ የመለየት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጾ፣ ከሕዝቡና ከክልሉ መንግሥት ጋር ሳይወያይና ሳይመካከር የሚወስደው ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሌለ አስታውቋል፡፡
የሱሉልታ ከተማ በአራት ቀበሌዎች የተከፋፈለች ሲሆን፣ በሁሉም ቀበሌዎች ላይ በመደዳውና አልፎ አልፎ በቤቶቹ ላይ ምልክት እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ቢራቱ ጌታነህ፣ አቶ ሰለሞን ይገዙና ወ/ሮ ባፈና ቶሌራ የተባሉ የከተማው ነዋሪዎች ለሪፖርት እንደገለጹት፣ በከተማው ቤት ሠርተው መኖር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቤቱን የገዙት ከአርሶ አደሮች ቢሆንም ሕጋዊ ውል እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የቤት ቁጥር ተሰጥቷቸው፣ የውኃ ቆጣሪና የኤሌክትሪክ ኃይል አስገብተው እየኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማው ኃላፊዎች ከሁለት ወራት በፊት ሰብስበው ሲያወያዩዋቸው፣ የመሬት ካሳ በተወሰደበት፣ ለአረንጓዴ ቦታነት በተተወና በሕገወጥ መንገድ በወረራ በተያዘ መሬት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ነግረዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ያንን ቃላቸውን አጥፈው በመደዳ ለማፍረስ ምልክት በማድረጋቸው ነዋሪዎች ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥጋታቸው ያለ ምክንያት አለመሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ባፈና፣ ልጃቸው ትምህርቷን አቋርጣ ዓረብ አገር ሄዳ ሰው ቤት ሠርታ የገዛችው ቤት ቢፈርስ፣ የት እንደሚገቡ እያሰቡ እየተጨነቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቀን ሥራ፣ የታክሲ ሾፌርነትና ተባራሪ ሥራ ሠርተው ባገኟት ገቢ ጎጆ ቀልሰው ልጆቻቸውን እያስተማሩ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ሰሞኑን ልጆቻቸው የሚያነሱላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እኛም ከትምህርት ቤት ስንመለስ እንደ ለገጣፎ ነዋሪዎች ቤታችን ፈርሶ ነው የምናገኘው?›› የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቤታቸው ላይ አልፎ አልፎ ምልክት ሲደረግና ቦታውን የሸጡላቸው ሰዎች ቤት ሲታለፍ፣ ተመርጦ የእነሱ ብቻ ይፈርሳል የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ መሠረታዊ የሆነውን መጠለያ ተፍጨርጭረው የቀለሱት ሕግ ለመጣስ ወይም አገርንና ወገንን ለመበደል አለመሆኑን፣ የከተማው አስተዳደርም ሆነ የክልሉ መንግሥት ተገንዝበው ከማፍረስ እንዲታደጓቸው ጠይቀዋል፡፡
የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ሮዛ ዑመርን ለማነጋገር ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ሄደው እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ለማነጋገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በሕዝብ የተመረጠና ሕዝብን የሚመራ የመንግሥት ኃላፊ ሕጋዊ ወይም ሕገወጥ ጥያቄ ሲቀርብለት፣ ጥያቄውን ካዳመጠ በኋላ ልዩነቱን አስረድቶ ተገቢ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሰውን አዳምጦ መፍትሔ መስጠት እንጂ ዝምታ ችግርን እንደማይፈታም ጠቁመዋል፡፡ ቤታቸው ላይ የተደረገው ምልክት እንቅልፍ እንደነሳቸውና በነጋታው ምን ይፈጠር ይሆን በማለት በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ በመሆናቸው፣ የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡
የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ሮዛ ዑመርን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ የከተማ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ወይንሸትን አነጋግሯቸዋል፡፡ ወ/ሮ ወይንሸት የሱሉልታ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ሳይሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ያፈረሰው ወይም ለማፍረስ ያደረገው ነገር የለም ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በሕገወጥ መንገድ በወረራ የተሠሩ ቤቶችን፣ ለአረንጓዴ የተዋቸው ቦታዎች ላይ የተገነቡ፣ በአርሶ አደር ይዞታዎች ላይ የተገነቡና ሌሎችንም የመለየት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይኼም እየተከናወነ ያለው በደንብ በተዘጋጀ ቅጽ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በዚህም ሕጋዊውንና ሕገወጡን ይዞታ ለመለየት እየተመራ ነው ብለዋል፡፡
የመለየት ሥራውን የጀመሩት ከመጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ወይንሸት፣ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሕዝቡ፣ የክልሉ መንግሥትና አስተዳደሩ እንደሚወያዩና ውሳኔ እንደሚተላለፍ አስረድተዋል፡፡ ነዋሪዎችንና አስተዳደሩን፣ እንዲሁም ሕዝቡን እርስ በርስ ለማጋጨት ሆን ብለው የሚሠሩ የተለያዩ የድረ ገጽና የፌስቡክ ሰዎች ያልሆነውን እንደሆነ በማስመሰል የሚያሠራጩት መረጃ፣ ሕገወጥና ሐሰተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡም በጥንቃቄ ማንኛውንም መረጃ ከአስተዳደሩ ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡