Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመረጃ ሳጥን ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው

አደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመረጃ ሳጥን ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ በደረሰበት ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ላይ በፈረንሣይ ፓሪስ ምርመራ እየተካሄደ ነው፡፡

አደጋው በደረሰ ማግስት ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. አደጋው በደረሰበት ሥፍራ በተካሄደ ፍለጋ የተገኘውን የመረጃ ሳጥን ወስዶ ለመመርመር፣ የአሜሪካ ናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና የእንግሊዝ ኤር አክሲደንት ኢንቬስትጌሽን ብራንች ቢጠይቁም፣ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት የመረጃ ሳጥኑን ወደ ፈረንሣይ ለመላክ ወስነዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በጋራ ያቋቋሙት የአደጋ ምርመራ ቢሮ፣ ለመረጃ ሳጥኑ ምርመራ የፈረንሣይ ቢሮ ኦፍ ኢንኳየሪ ኤንድ አናሊስስ (BEA) መርጧል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) እና የአደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ አምድዬ ፈንታ (ኮሎኔል)፣ የመረጃ ሳጥኑን ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌሊት ይዘው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓሪስ እንዳቀኑ ምንጮች ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

የመረጃ ሳጥኑን ይዞ የተጓዘው የኢትዮጵያ ልዑክ ሐሙስ ማለዳ ፓሪስ እንደገባ ሊቦርጄይ ኤርፖርት (በፓሪስ ሁለተኛ ኤርፖርት) ወደሚገኘው የምርመራ ዋና መሥሪያ ቤት አቅንቷል፡፡ የምርመራ ቢሮው እ.ኤ.አ. በ2010 በቤይሩት ሊባኖስ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን የመረመረ ድርጅት እንደሆነ ታውቋል፡፡

የአሜሪካ ናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ባለሙያዎች ምርመራውን ለማገዝ ወደ ፓሪስ እንዳቀኑ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

የመረጃ ሳጥኑ ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት፣ የመጀመሪያው በበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል የነበረውን ድምፅ የሚቀዳ ኮክፒት ቮይስ ሪከርደር (CVR)፣ ሁለተኛው የአውሮፕላኑን የበረራ መረጃ መዝግቦ የሚያስቀረው ፍላይት ዳታ ሪከርደር (FDR) ነው፡፡ ድምፅ መቅጃው አብራሪዎቹ እርስ በርስ የተነጋገሩትንና ከበረራ መቆጣጠሪያ ማማ ተረኛ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር የተለዋወጡት መልዕክት የሚቀዳ ሲሆን፣ የዳታ ሪከርደሩ ደግሞ አውሮፕላኑ አደጋው ከመድረሱ በፊት ይበርበት የነበረ አቅጣጫ፣ ከፍታና ፍጥነት መዝግቦ ያስቀራል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመረጃ ሳጥኑ ሐሙስ ማለዳ ፓሪስ እንደገባ አስታውቋል፡፡ የምርመራ ቢሮው በትዊተር ገጹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በምርመራ ሒደት እንዲያግዛቸው እንደጠየቁት ገልጾ፣ ማንኛውም መረጃ የመስጠት ኃላፊነት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) አንቀጽ 13 መሠረት የአውሮፕላን አደጋው በኢትዮጵያ የአየር ክልል የተከሰተ በመሆኑ፣ የአደጋ ምርመራ ሥራውን የሚመራው የኢትዮጵያ አደጋ ምርመራ ቢሮ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሥር ይተዳደር የነበረው የአውሮፕላን አደጋ መከላከልና ምርመራ ክፍል ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ ከባለሥልጣኑ ተነጥሎ እንዲወጣ፣ የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ ቢሮው በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል፡፡

የፈረንሳይ ምራመራ ቢሮ መርማሪዎች ከመረጃ ሳጥኑ መቅረፀ ድምፅና የበረራ መረጃ መሰብሰቢያ ሜሞሪ ቺፕስ መረጃ እንደሚገለብጡና እንደሚተነትኑ አንድ የመስኩ ባለሙያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መርማሪዎቹ ሥራቸውን ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደጀመሩ የዘገቡት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ የበረራ መረጃ መሰብሰቢያው መሣሪያው በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ፣ መቅረፀ ድምፁ ግን ጉዳት እንደደረሰበት ዘግበዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ባለሙያ ከተጎዳ ሜሞሪ ቺፕስ ላይ መረጃ መልሶ ማግኘት የሚያስችል ዘዴ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

‹‹መሣሪያው ምን ያህል ተጎድቷል የሚለው መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን በከፋ ሁኔታ የተጎዳ እንኳ ቢሆንም በዲስትራክትቪ ቴስቲንግ (የጠፋውን መረጃ መመለስ) የሚቻልበት አሠራር አለ፤›› ያሉት ባለሙያው፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ተረኛ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ ከአብራሪዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በመቅረፀ ድምፅ እንደሚቀዳ ተናግረዋል፡፡ ከመረጃ ሳጥኑ የሚገኙት መረጃዎች ለአደጋ ምርመራ ወሳኝ ግብዓት ቢሆኑም፣ ሌሎች ከአደጋው ሥፍራ የተሰበሰቡ ቁሳዊ መረጃዎችም ጠቃሚ ፍንጭ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ አራት ክፍሎች እንዳሉት የገለጹት ባለሙያው መረጃ መሰብሰብ፣ መተንተን፣ ድምዳሜና ምክረ ሐሳብ መስጠት እንደሆኑ ጠቁመው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በሦስት ወራት ጊዜ፣ የመጨረሻ ሪፖርት ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡

አደጋው በደረሰ ማግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገሮች የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ሲያደርጉ፣ ቦይንግና የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን (FAA) ዕርምጃ ለመውሰድ አሳማኝ መረጃ እንደሌለ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

ሆኖም ረቡዕ መጋቢት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማክስ አውሮፕላኖች እንዲቆሙ መወሰኑን ማሳወቃቸውን ተከትሎ፣ የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን የማክስ አውሮፕላኖች እንዲቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ዕርምጃውን የወሰደው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ማክስ አውሮፕላን ላይ ስለደረሰው አደጋ አዲስ የሳተላይት መረጃና አደጋው ከደረሰበት ሥፍራ በተገኘ መረጃ ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የቦይንግ ኩባንያ ለጥንቃቄ ሲባል የተወሰደውን ዕርምጃ እንደሚደግፍ ገልጾ የውሳኔውን ሐሳብ ለፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን ያቀረበው ራሱ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የአሜሪካና የካናዳ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች አዲስ አገኘነው ያሉዋቸው መረጃዎች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ B737-8 ማክስ አውሮፕላን አደጋና ባለፈው ጥቅምት ወር በጃካርታ ኢንዶኔዥያ በላየን ኤር ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ተመሳሳይነት እንዳላቸው እንደሚጠቁሙ አስታውቀዋል፡፡

የማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለበት የአቪዬሽን ባለሙያዎች እየጠቆሙ ባሉበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ዋና አብራሪ ያሬድ ጌታቸው አደጋው ከመድረሱ በፊት የበረራ መቆጣጠሪያ ችግር እንደገጠመው በመግለጽ ወደ አዲስ አበባ ኤርፖርት ለመመለስ ፈቃድ ጠይቆ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የበረራ ዕገዳውን ተከትሎ በአጠቃላይ 371 ማክስ አውሮፕላኖች እንዲቆሙ የተደረገ ሲሆን፣ 100 ያህሉ ቻይና ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 30 ማክስ አውሮፕላኖች ከቦይንግ ኩባንያ በማዘዝ ስድስት መረከቡን፣ አንዱን በአደጋ ሲያጣ አምስቱ እንዲቆሙ አድርጓል፡፡

አየር መንገዱ ካሉት 110 አውሮፕላኖች 80 ያህሉ ቦይንግ ሥሪት እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ሪፖርተር ባገኘው መረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት ከአሜሪካ ቦይንግ ኩባንያ ለገዛቸው አውሮፕላኖች ከሌሎች ሞተር አምራችና መገናኛ መሣሪያዎች፣ የበረራ ሶፍትዌሮች በአጠቃላይ 21 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ እንዳላቸው፣ በዚህም አሜሪካ ውስጥ ለ115,000 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ታውቋል፡፡

ከዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው 69 ቦይንግ አውሮፕላኖች እንደገዛ፣ በመጪው አምስት ዓመታት የሚረከባቸው 44 አውሮፕላኖች ዋጋ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት መረጃው ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም አየር መንገዱ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ተለዋጭ የአውሮፕላን ሞተሮችና የተለያዩ የአውሮፕላን መሣሪያዎች በስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደገዛ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...