Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ሁሌም ከቤቴ ስወጣ ፈጣሪዬን ‹‹በሰላም አውለኝ›› እላለሁ፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም የለም፡፡ ሊኖር የሚችለው ውድመትና ዕልቂት ብቻ ነው፡፡ ማንም ጤነኛ ዜጋ ደግሞ ግጭትን፣ ውዝግብንና አላስፈላጊ ጠብን የሚጋብዝ ችግር ውስጥ ከመግባት ይልቅ በውይይትና በንግግር ችግሮችን መፍታትን ይመርጣል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ከጠብ ይልቅ ሰላም ስለሚያስፈልግ ‹‹ሰላም አውለኝ›› መባል ያለበት፡፡ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ሰላማዊ ከሆነ ችግሮቻችንን በሙሉ በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት አያዳግተንም፡፡ ነገር ግን ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሲያካትት ነው፡፡ ሕዝብን ሰላም እየነሱ አውቅልሃለሁ ወይም እወክልሃሉ ማለት፣ ከገዛ ወገኑ ጋር ማጋጨትና ለግልና ለቡድን ጥቅም ሲባል ደም ማቃባትና ማፈናቀል ኃጢያት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡

የእኔ ገጠመኝ መነሻም ይኸው ነው፡፡ ከዓመታት በፊት እንደተለመደው ‹‹በሰላም አውለኝ›› ብዬ ወደ ሥራዬ ስሄድ ስልኬ ጮኸ፡፡ የደወለልኝ ጓደኛዬ ስለነበር ምን ፈልጎ ይሆን በጠዋት የሚደውለው በማለት አነሳሁት፡፡ ጓደኛዬ አራት ኪሎ አካባቢ ረብሻ መነሳቱን መስማቱን ነግሮኝ ጥንቃቄ እንዳደርግ ነገረኝ፡፡ ከምኖርበት ኬንያ ኤምባሲ አካባቢ የተሳፈርኩበት ወደ አራት ኪሎ የሚሄደው ታክሲ ግንፍሌ አካባቢ ሲደርስ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል፡፡ ረዳቱ ወጥቶ ሲያጣራ አራት ኪሎ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በመረበሹ መሆኑን ነገረን፡፡ ውረዱ ተብለን እየፈራን እየተባን ወደ አካባቢው ስንደርስ ጭር ብሏል፡፡ መንገዱ ላይ ግን የተወረወሩ ድንጋዮች ይታያሉ፡፡

እንደገና ስልኬ ሲጮህ አነሳሁት፡፡ አሁንም በዓይኔ እያየሁ ስላለሁት ረብሻ ጉዳይ የሚጠቁመኝ የማስጠንቀቂያ የወዳጅ መልዕክት ነው የተላለፈልኝ፡፡ አልፎ አልፎ ከሚሰማ ጩኸት በስተቀር እንደተባለው ያን ያህል አስጊ ነገር አይታይም፡፡ ቆየት ብዬ ግን ፖሊስ ገብቶ ረብሻውን ማስቆሙን፣ ነገር ግን በተማሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት የተጎዱ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ሰማሁ፡፡ በተማሪዎች መካከል የተከሰተው ጠብ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስጠይቅ በግቢው ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች አንድን ብሔር የሚያንቋሽሹ ስድቦች በመጻፋቸው መሆኑን ተረዳሁ፡፡ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ማንም ሰው እንኳን ወገኑን ቀርቶ ሌላ ባዕድ እንኳ ቢሆን በማንነቱ ምክንያት ለምን ይሰድባል? ያውም ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች በብሔር ምክንያት ተከፋፍለው ተጋጩ ሲባል ማፈር ያለበት ማን ነው? ማን ማንን ለመስደብ መብት አለው? ማን ከማንስ ይበልጣል? መማርና ማወቅ ለእንዲህ ዓይነት ስህተት የሚዳርግ ከሆነ የትምህርት ጥቅሙ ምንድነው? በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙ ጉደኞች እኮ ራሳቸውን እንደ ሠለጠነ ሰው የሚያዩ መሆናቸው ደግሞ አስገራሚ ነበር፡፡

ምሣ ሰዓት ላይ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን የዩኒቨርሲቲውን ካምፓስና አካባቢውን ስንቃኝ ሰላም ሰፍኖ ነበር፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች እየተገላመጡና እየተሸማቀቁ አካባቢያቸውን ሲቃኙ ማየት ግን ያሳዝን ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከስድስት ኪሎ እስከ አራት ኪሎ ድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና መብት በጋራ እንዳልተጮኸበት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን ከፍተኛ ትግል እንዳልተደረገበት፣ ብሔር መራሽ ግጭት ተከሰተበት ሲባል እጅግ በጣም ነበር የሚያናድደው፡፡ በወቅት በሐሳቤ ይመላለስ የነበረው በመጀመርያ ደረጃ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በእዚህ ድርጊት ማፈር እንደሚገባው፣ በአጠቃላይ ግን እንደ አገር ማፈር ያለብን ሁላችንም መሆናችንን ነው፡፡ ለግለሰብ መብት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት በሚባልበት በዚህ ዘመናችን፣ የብሔሮችን ስም በመጥፎ በማንሳት በሕዝባችን ውስጥ ቁርሾ መፍጠር የኋላ ቀርነት መገለጫና ከዚህም አልፎ ተርፎ የጠላት መሣርያ መሆንን በወቅቱ አመልካች ነበር፡፡

አራት ኪሎ ሰላም መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ምሣ እየበላን ስለ ጉዳዩ ስንወያይ ድንገት ሁለት ሰዎች አጠገባችን ያለው ጠረጴዛ ጋር ወንበሮች ስበው ተቀመጡ፡፡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየተነጋገሩ ስለነበር እነሱም ይኼንኑ ጉዳይ እየተወያዩበት እንደሆነ አወቅኩኝ፡፡ አንደኛው በንዴት፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ ተማሪዎች እንዴት እንዲህ ዓይነት የብልግና ስድብ ይጻፋል?›› እያለ ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም በብስጭት፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? እዚህ አገር እኮ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ከማከም ይልቅ ቸል ማለት እየበዛ ነው፤›› አለው፡፡ ያኛው እንደገና፣ ‹‹ይኼ ቸልታ ብቻ አይደለም ማለባበስና መደባበቅ የሚባል አጉል ባህል ስለተፀናወተን ነው፤›› እያሉ ወጋቸውን ሲቀጥሉ አብሮን የነበረው ጓደኛችን ደግሞ፣ ‹‹ሰማችሁ ይኼ ጉዳይ ስንቶችን እንደሚያበሳጭ? ለእኔ ግን የሚታየኝ ሌላ ነው፤›› አለን፡፡ ሁላችንም በአንድነት ‹‹ምን ይሆን?›› በማለት ጥያቄ አቀረብንለት፡፡ ጓደኛችን በአጭሩ፣ ‹‹የጠባብነትን አመለካከት በኅብረ ብሔራዊ አመለካከት በፅናት መታገል፤›› ሲለን መፍትሔው ይኼው መስሎን መለያየታችን አይረሳኝም፡፡ ምንም እንኳን ጊዜው ትንሽ ራቅ ቢልም፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ በብሔርተኝነትና በዘረኝነት የተለከፉ ዕብዶች በሚጭሩት እሳት ምክንያት ምን ዓይነት አሳዛኝ ክስተቶች እያጋጠሙን እንደሆነ እያየነው ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ከወጣ በኋላ ብሔርተኞች በቀሰቀሱት ችግር ምክንያት፣ እየገባንበትን ያለውን አደገኛ መንገድ ማንም ሰው ይረዳዋል፡፡ ከሰውነት በታች ካልወረድን በስተቀር የጋራ ስምምነት የምንፈጥርባቸው በርካታ ጉዳዮች እያሉን፣ ሁሉንም ነገር የእኔ ነው እያልን ካነስን መድረሻችን የት እንደሚሆን ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ እየገባንበት ያለው የብሽሽቅ ፖለቲካ የአንድነታችንን ገመድ እየገዘገዘ ቆርጦ እየጣለው ነው፡፡ በማይረቡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ተብዬዎች አጉል ድርጊቶች ከሰው ተራ እየወጣን አውሬ መሆን የለብንም፡፡ እኛ እርስ በርስ መተዛዘን ካቃተን ማነው የሚያዝንልን? እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንታወቀው እኮ በመዋደዳችንና በመተዛዘናችን እንደሆነ የሕዝባችንን የጋራ እሴቶች ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ይህንን የተከበረ ሕዝብ በመናቅ ክፋት እየሠሩ ያሉ ክብረ ቢሶችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰሞኑን እንዲህ ብሏቸው ነበር፡፡ ‹‹ሕይወት ቢለየንም ሞት ያገናኘናል፡፡ በአውሮፕላን አደጋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡ ወገኖች አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ ሄዱ፡፡ እርማቸውን ለማውጣት፡፡ በቦታው ሲደርሱ ሐዘናቸው ከልክ በላይ ሆኖ ለያዥ ለገራዥ አስቸገሩ፡፡ የአካባቢው እናቶችና አባቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ወጥተው አብረዋቸው አለቀሱ፡፡ ማን ናቸው? የየት አገር ዜጋ ናቸው? ብሔራቸውና ቋንቋቸው ምንድነው? ሃይማኖታቸውስ? ብለው አልጠየቁም፡፡ ለእነርሱ ከሰውነት በላይ ምን ነገር የለም፡፡ እነርሱ ሰዎች እንጂ ዘረኞች አይደሉም፡፡ እኛ ግን በእነዚህ ንፁህ ዜጎች ስም እንነግዳለን፤›› ነበር ያለው፡፡ ወገኖቼ እናንተስ ምን ትላላችሁ?

(ደንድር ሲራጅ፣ ከኬንያ ኤምባሲ)     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...