Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክረቂቁ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ

ረቂቁ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በውብሸት ሙላት

ይኼ ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዐምድ የቀረበው ተከታይ ነው፡፡ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ የመጨረሻ ረቂቅ ላይሆን ቢችልም ረቂቁ በተለያዩ ሰዎች እጅ ስለገባ ከመጽደቁ በፊት የተወሰኑ ነጥቦች ላይ ትኩረት እንዲሰጥባቸው ለማነሳሳትም ጭምር ነው የመጣጥፎቹ ዓላማ፡፡ በዚህ ክፍልም የተለያዩ ድንጋጌዎችን በመምረጥ አስተያየት ቀርቧል፡፡

የጦር መሣሪያ ፈቃድ መሥፈርቶች

የጦር መሣሪያ ለመታጠቅ መሥፈርቶቹ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ተዘርዝዋል፡፡ ዝቀተኛው የዕድሜ ገደብ 21 ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊ በተጨማሪም የመኖሪያ ፍቃድ ያገኘ ለየትኛውም አገሮች ዜጋም የተፈቀደ ነው፡፡ የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት መሆንም ሌላው መለኪያ ነው፡፡ ፈቃድ ጠያቂው ቋሚ አድራሻና መተዳደሪያ እንዲኖረው ግድ ይላል፡፡ በፍርድ ያልተከለከለ፣ የአዕምሮ ሁኔታው የተስተካከለና አላስፈላጊ ኃይል የመጠቀም አመል የሌለበት፣ የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ግንዛቤ መኖር፣ ከሚኖርበት አስተዳደር የመልካም ሥነ ምግባር የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ፣ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የሚያወጣውን የጦር መሣሪያ ለመያዝ በቂና አሳማኝ ምክንያት በቅድመ ሁኔታነት ተቀምጠዋል፡፡

ሌሎች አገሮችም ቢሆኑ የጦር መሣሪያ ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶችን ፈቃድ ጠያቂዎች እንዲያሟሉ ይጠይቃሉ፡፡ ዝቅተኛውን የዕድሜ ገደብ፣ የመሣሪያ መታጠቅ ምክንያቱ፣ የወንጀል ታሪክ፣ የጤና ሁኔታ፣ እንዲሁም ሥልጠና መውሰድን በርካታ አገሮች ይጋሯቸዋል፡፡

ይህ ማለት ግን እነዚህ አገሮች እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በሚመለከት ተመሳሳይ ደንብ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ የዕድሜ ሁኔታን በምሳሌነት ብንወስድ አውስትራሊያ 18፣ ብራዚል 25፣ ግብፅ 21፣ ደቡብ አፍሪካ 21፣ ስዊዘርላድ 18 ነው፡፡

ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ምክንያትንም ብንመለከት አውስትራሊያ ለስፖርት፣ለአደን ወዘተ በግልጽ ለታወቀ ዓላማ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ራስን ከጥቃት ለመከላከል የሚለው ተቀባይነት የለውም፡፡ ቻይናና ጀርመንም በግልጽ ተለይቶ ለታወቀ ዓላማ ብቻ ነው የሚፈቀደው፡፡ እስራኤል ደግሞ ለምን እንዳስፈለገ ማስረዳትን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ የሚኖርበት ሰፈር ሁኔታ፣ የሥራ ዓይነት ከግምት ይገባሉ፡፡ በሜክሲኮ ራስንም መከላከል ተቀባይነት ያለው ምክንያት ነው፡፡

የጤና ሁኔታዎችንም ብንወስድ ብዙዎቹ ተቀራራቢ ቢሆንም ፈቃድ ሰጭው አካል እንዲያጣራ የሚጠበቅበትን የጤና ሁኔታን በሚመለከት ዝርዝር መሥፈርቶችን እንዲሁም ምስክርታቸውን የሚሰጡት ተቋማትንም በሚመለከት ልዩነት ይስተዋላል፡፡

ወደ ረቂቅ አዋጁ ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች መለስ ብለን እንፈትሻቸው፡፡

ማንኛውም የጦር መሣሪያ ፈቃድ ማግኘት የፈለገ ሰው የአደንዛዥ ዕፅና የመጠጥ ሱስ የሌለበት መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይኼ መስፈርት በበርካታ አገሮችም ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ይሁን እንጂ አደገኛ ዕፅም ይሁን የመጠጥ ሱስ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት፣ የጦር መሣሪያ ለመያዝ የሚያስችል አካላዊና የተስተካከለ የአዕምሮ ሁኔታ መኖርና አለመኖርን የሚያረጋግጡት የሕክምና ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ማረጋገጫ የሚሰጠው ከሕክምና ተቋማት እንዲሆን በሕጋቸው ላይ ደንግገዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁን በምንመለከትበት ጊዜ የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ (የአልኮል መጠጥ ቢባል ጥሩ ነው) ሱስ የሌለበት በማለት አስቀምጦታል፡፡ የእነዚህ ሱስ የሌለበት መሆኑን ማስረጃ ማቅረብን ሕጉ ቢጠይቅ ጥሩ ነው፡፡ በዝርዝር ደንብ ወይም መመርያ ሊወጣ የሚችል መሆኑን በመርሳት ግን አይደለም፡፡

ረቂቁ ስለ አካላዊ ጤንነት ሁኔታ ምንም ቅድመ ሁኔታ ባይጠይቅም ‹‹የተስተካከለ የአዕምሮ ሁኔታ ያለው መሆኑን በፈቃድ ሰጭው ከታመነበት›› በሚል አስቀምጦታል፡፡ ይኼም ቢሆን ፈቃዱን ለሚሰጠው ለፌዴራል ፖሊስ ከሚተው ተጨባጭ መረጃ ፈቃድ ጠያቂው እንዲያቀርብ በማድረግ እንጂ አሁን በሥራ ላይ እንዳለው ፈቃድ አሰጣጥ ዘፈቀዳዊነትንና ፈቃድ ሰጭው አካል እንዳሻው እንዲፈቅድ ወይም እንዲነሳ በሚያስችል አኳኋን መተው የለበትም፡፡

ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሌላው ቅድመ ሁኔታ አላስፈላጊ ኃይል ያለመጠቀም አመል የሌለው የሚለው ነው፡፡ ይኼም ቢሆን ከሌሎች ሰዎች ማለትም ፈቃድ ጠያቂውን ከሚያውቁት ሰዎች ዘንድ ፖሊስ ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት በራሱ መንገድ አጣርቶ የፈቃድ ጠያቂውን ባሕርይ ማወቅ የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ የተለያዩ አገሮች ይህንን መለኪያ በሕጋቸው ላይ አስፍረውት እናገኛለን፡፡ ፈቃድ ጠያቂው በራሱ የሚያመጣውን የሌላ ሰው ምስክርነትን አይቀበሉም፡፡ ረቂቁ ግን አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባሕርይ የሌለው መሆንኑን በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት በማለት አላልቶና ለፌዴራል ፖሊስ ሰፊ ሥልጣን ሰጥቶ ትቶታል፡፡

ሌላው በመስፈርትነት የተቀመጠው ፈቃድ ጠያቂው መተዳደሪያ ያለው መሆን ነው፡፡ ይኼ መሥፈርት ግልጽነት መጓደል ይስተዋልበታል፡፡ መተዳደሪያ የሌለው ሰው በሕይወት እየኖረ ሊቀጥል እንደማይችል ይታወቃል፡፡ መተዳደሪያው ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ልመናም መተዳደሪያ ነው፡፡ ሴተኛ አዳሪነትም መተዳደሪያ ነው፡፡ ከውጭ አገርም ይሁን ከአገር ቤት ቀለብ ተቆራጭ ብቻ እያገኘ የሚኖርም መተዳደሪያ አለው፡፡ አልፎ አልፎ የሚገኝ የቀን ሥራም ይሁን ድለላ ዞሮ ዞሮ ገቢ እስካስገኘ ድረስ መተዳደሪያ ነው፡፡ ይኼ መሥፈርት ግልጽና የሚለካ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የመተዳደሪያ ምንጩ ምን ዓይነት ሲሆን እንደ መተዳደሪያ አይወሰድም የሚለው ሊለይ ይገባዋል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ላይ አንድ ሰው የጦር መሣሪያ ፍቃድ እንዲያገኝ ከሚኖርበት አካባቢ ከሚገኝ አስተዳደር የመልካም ሥነ ምግባር የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼ ቅድመ ሁኔታ ስለ ፈቃድ ጠያቂው አጠቃላይ ባሕርይ የሦስተኛ ወገን ምስክርነት ለማግኘት ሲባል የገባ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በመጀመሪያ መልካም ሥነ ምግባር ማለት ምንድን ነው ምን ዓይነት ባሕርያት የጦር መሣሪያ ፈቃድ ከማግኘት ጋር ይያያዛሉ ለምሳሌ እንድ ሰው የመዋሸት ዓመል ቢኖርበት መልካም ሥነ ምግባር የለውም ሊባል ይችላል፡፡ እንዲሁም ሥራ ላይ ልግመኛ፣ ሰነፍ ቢጤ ቢሆንም መልካም ሥነ ምግባር አለው ላይባል ይችላል፡፡ ስለሆነም ስለ ሥነ ምግባሩ (ከጦር መሣሪያ መያዝ ጋር የተገናኙ) ከሌላ ሰው እንጂ ከአካባቢው መስተዳድር መጠየቁ አንድም ጥሩ ምስክርነት አይደለም፡፡ መስተዳድሩ ካላወቀው ስለባህሪው ትክክለኛውን ምስክርነት አይሰጥም፡፡

በሌላ መልኩ ለፖለቲካዊ ዓላማ ሊውል እንደሚችል ለመገመት የእስከዛሬው ታሪካችን በቂ ምስክር ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ተመሳሳይ ተሰላፊን እንጂ የማይመሳሰልን መልካም ሥነ ምግባር የጎደለው አድርጎ መመስከር የመንግሥት አስተዳደሮች ልማድ ነው፡፡

ግን ከዚህ የከፋው ደግሞ ‹‹መልካም ሥነ ምግባር ያለው መሆኑን የትብብር ደብዳቤ…›› የሚለው ነው፡፡ የአካባቢው መስተዳድር ከተባበረው እንጂ፣ ግዴታው አይደለም፡፡ በመብትነት የሚጠየቅ አይደለም፡፡ ረቂቁም የሚለው የትብብር ነው፡፡ ትብብርን ምን አመጣው? ለምን በመሥፈርትነት ተቀመጠ? በዚህ መልኩ መቀመጡ ዜጎችን ለከፍተኛ እንግልት፣ እንዲሁም ፈቃድ የማግኘትንም ያለማግኘትንም ዕጣ ፈንታ የአካባቢ መስተዳድሮች መዳፍ ላይ መጣል ነው፡፡ የአካባቢ አስተዳደር ለሥነ ምግባር አስተማማኝ ምስክር ካለመሆናቸው ባሻገር ለሙስና የተጋለጠ አለቅጥ የተለጠጠ ፍቃድ ሥልጣንን (discretion) ማሸከም ሌላው እንከን ነው፡፡

ረቂቅ ሕጉ አስቀድሞ የዘረዘራቸው መሥፈርቶች አልበቃው ብሎ የፌዴራል ፖሊስ የሚወስናቸው ሌሎች ለመታጠቅ ‹‹በቂና አሳማኝ ምክንያት›› እንዲያወጣ ሥልጣን ደርቦ ደራርቦ ጨምሮለታል፡፡ ምክንያቶቹ በሕግ አውጭው ሊወሰኑ ሲገባ ለፈቃድ ሰጭው መተው፣ በዚያ ላይ ‹‹በቂና አሳማኝ ምክንያት›› የሚባሉት ምን እንደሆኑ አስቀድመው ሳይታወቁና ቀድመው ለታጠቁት ስላልተጠየቁ ከውጤት አንፃር አድሏዊ መሆናቸው ግልጽ ስለሆነ፣ ከመጽደቁ በፊት ቢከለስ መልካም ነው፡፡

ፈቃድ የሚሰጣቸውና የማይሰጣቸው ተቋማት

የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጠው ለተፈጥሮ ሰው ብቻ ሳይሆን በሕግ ሰውነት ለተሰጣቸውም ጭምር ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 6 ላይ ፈቃድ የማይሰጣቸው ድርጅቶችን ለይቶ ዘርዝሯል፡፡ ለተቋማቱ ጥበቃ ከሚያስፈልጋው የጦር መሣሪያ ውጭ ለፖለቲካ ፓርቲ፣ ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅትና ማኅበር እንዲሁም ለትምህርት ተቋማት የጦር መሣሪያ ፍቃድ እንዳይሰጥ ከልክሏል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አንቀጽ በተገላቢጦሹ ሲነበብ ከእነዚህ ተቋማት በስተቀር ሌሎቹ ለጥበቃ ከሚያስፈልጋቸውም ውጭ የጦር መሣሪያ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይችላል እንደማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች (ለጤና ጥበቃ፣ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ወዘተ)፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች ሊሰጡ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማትስ ከጥበቃ ውጭ ምን ይሆናቸዋል? ስለሆነም በሌላ አገላለጽ መስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

ለፊልምና ለቴአትር የሚፈቀዱ መሣሪያዎች

ረቂቁ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች ሲባል የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥባቸውን ሁኔታ አንቀጽ 13 ላይ ዘርዝሮታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለአስተያየት የተመረጠው ንዑስ ቁጥር 5 ላይ ለቴአትርና ለፊልም ሥራ የጦር መሣሪያና የጥይት ዓይነት የሚመለከተውን ነው፡፡ ለቴአትርና ለፊልም ሠሪዎች የሚፈቀደው ሽጉጥ፣ ግማሽ አውቶማቲክ ጠመንጃ ሆኖ ድምፅ ብቻ የሚሰጥ የውሸት ጥይት ያለው ነው፡፡ የውሸት ጥይቶቹ ብዛትም በሚኒስትሩ እንደሚወሰን ጭምር ረቂቅ ቀርቧል፡፡

እዚህ ላይ ለቴአትርም ይሁን ለፊልም ሥራ የሚያስፈልገውን የመሣሪያ ዓይነት የሚወስነው ደራሲው እንጂ ፓርላማው አይደለም፡፡ በተለይ ለፊልም ሥራ፣ ምን ዓይነት መሣሪያ እንደሚጠቀም ደራሲው (ወይም ዳይሬክተሩ) ሆኖ ሳለ ሌላ አካል በሕግ ሽጉጥ እንጂ ታንክ መጠቀም አይችልም፣ ግማሽ አውቶማቲክ እንጂ ሙሉ አውቶማቲክ መሣሪያ ፊልም ሥራ ላይ አይውልም ማለት  ተገቢነት የለውም፡፡ በእርግጥ የውሸት ጥይቶች በትክክለኛ መሣሪያ ሊተኮሱ ይችላሉ፡፡ ለፊልም ሥራ ሊውሉም ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የፊልም ሥራ በእነዚህ መሣሪያዎች ብቻ ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ ሕግ አውጭው በዚህ መጠን የፊልምና ቴአትር ሥራ ላይ እንዲህ ዓይነት መሣሪያ ብቻ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው በማለት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ለፌዴራል ፖሊስ ሊያሸክመው አይገባም፡፡

አግዶ መውረስ

የረቂቁ አንቀጽ 18 ፈቃድን ስለማገድ ይናገራል፡፡ የዕገዳ ምክንያቶቹ ሳይገለጹ ወረድ ብሎ በንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የተደነገጉት ምክንያችን በ60 ቀናት ካላስተካከለ የፌዴራል ፖሊስ የጦር መሣሪያውን እንደሚወርሰው ንዑስ አንቀጽ 3 ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ በእነዚህ ንዑስ አንቀጾች ላይ የተቀመጠ የሚታወቅ የዕገዳ ምክንያት ግን የለም፡፡ ማስረጃው አጠራጣሪ ከሆነና ላልተፈቀደ ተግባር ውሏል ብሎ ተቆጣጣሪው ከጠረጠረ ብሎም ይኼው የጠረጠረው ፌዴራል ፖሊስ ማረጋገጥ ሳይጠበቅበት፣ አጠራጣሪነቱን ማስረዳትም ላልተፈቀደ ተግባር መዋሉንም ማስረዳት የሚገባው ፌዴራል ፖሊስ መሆን ሲገባው ወደ ባለፈቃዱ ጠቅልሎ አዙሮታል፡፡ ለፌዴራል ፖሊስ የመጠርጠር ሥልጣን ብቻ ነው የተሰጠው፡፡ የተጠረጠረው አላግባብ መሆኑን የማስረዳት ሸክም ለባለፈቃዱ የዞረ ስለሆነ ጥርጣሬው ስህተት መሆኑን በማስረዳት ይሆናል ዕገዳው የሚነሳው፡፡ የማይሆንና የሌለን ጥርጣሬ (ቢሆን) እንዴት አድርጎ በምን ማስረጃ ማስተባበል ይቻላል? በዚያ ላይ በጥርጣሬ ፈቃዱን ያገደው አካል ነው ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ራሱ ጠርጣሪ፣ ራሱ ፈራጅ! 

ከስድሳ ቀናት በፊት ማለት ስንት ነው?

አንቀጽ 17 (1) የፈቃድ አገልግሎት ጊዜው ከማብቃቱ ከ60 ቀናት በፊት የዕድሳት ጥያቄ መቅረብ አለበት፡፡ ስድሳ ቀን የመጨረሻው ቢሆንም ከዚያ በፊት ባሉት በምን ያህል ቀናት ወይም ወራት ጊዜ ነው የፈቃድ ዕድሳት የሚቀርበው? ለምሳሌ ስድሳ ቀናት ከመቅረቱ በፊት ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቢባል ግልጽ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ለአራት ዓመታት ፈቃድ ያገኘ ሰው በሁለተኛ ዓመቱ ላይ ከአራተኛው ዓመት ጀምሮ ለሚታሰብ ፈቃድ ማሳደስ ይቻላልን? በሦስት ዓመት ከመንፈቅስ?

በአደራ የመመለስ አስፈላጊነት

እንደ ረቂቅ አዋጁ፣ ፈቃድ ማሳደስ በውክልና ሳይሆን በአካል መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ባለፈቃዱ ከአገር ውጭ ቢሆን እንዲሁም መሣሪያውን በሌላ ሰው እጅ ከሚያስቀመጥ ይልቅ አንድ ሰው ከአገር ውጭ ሲሄድና ረዘም ያለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ቢያንስ በአደራ ለፌዴራል ፖሊስ  ማስቀመጥ/መመለስ  እንዲቀመጥ መፍቀድና ለዚሁም የሚሆን የሕግ ጥበቃ ማድረግ ይገባል፡፡ ካልሆነ በተለይ ከአገር ውጭ የሆነ ሰው ፈቃድ ለማሳደስ ከውጭ መምጣት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

የጦር መሣሪያ የተሰጠው ድርጅት ግዴታዎች

አንቀጽ 24 ላይ እንደተገለጸው ፈቃድ ካገኘበት መጠን በላይ በአንድ ጊዜ አለመያዝ አንዱ ነው፡፡ ላስታጠቃቸው ሰዎች እንጂ ለድርጅት ተፈጻሚ ስለማይሆን የሚታጠቁት ሰዎች በአንድ ጊዜ መያዝ ያለባቸውን ነው ስለመያዛቸው የመቆጣጠር ግዴታ ቢሆን የሚሻለው፡፡ በተጨማሪም ዕድሳቱን በአካል ይዞ በመቅረብ ማሳደስንም ይጠይቃል፡፡ ይኼም ቢሆን ለግለሰብ እንጂ ለድርጅት የሚሆን አይደለምና መስተካከል ይገባዋል፡፡

ሌላው በዚሁ አንቀጽ የተቀመጠው ክልሎችንም ሆነ ሌሎች የፀጥታ ተቋማትን፣ ለአብነት ብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ፣ የጉምሩክ ፖሊሶች ወዘተ ዕድሳቱ አልዘለላቸውም፡፡ ፌዴራል ፖሊስ  ለሚሰጣቸው አገልግሎት ተመጣጣኝ ክፍያ እንደሚያስከፍል አንቀጽ 26 (12) ላይ ተገልጿል፡፡ ክልሎች የራሳቸው ፖሊስና ሚሊሻ እንደሚኖራቸው ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የዕድሳት ክፍያም እንደማይከፍሉ አልተገለጸም፡፡ በመሆኑም መክፈላቸው አይቀሬ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ፣ በሕገ መንግሥቱ ክልላዊ ሰላምና ፀጥታን እንዲጠብቁ ሥራ ሰጥቶ እየከፈሉ ካላሳደሱ ይቀማሉ፣ ይወረሳሉ ማለት ምንድን ነው? የዕድሳት ክፍያ ባይከፈሉ ሰላምና ፀጥታው ምን ይሁን?

አንቀጽ 28 (4) ላይ እንደተገለጸው ደግሞ የፀጥታ አካላት (የክልልም ቢሆኑ) የታጠቋቸውን ለፌዴራል ፖሊስ ያስመዘግባሉ፡፡ ከተፈቀደው ዓይነትና መጠን በላይ ከሆነም ተቆጣጣሪ ተቋሙ ይወርሳቸዋል፡፡ ሕጉ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲያስመዘግቡ ይጠበቃል፡፡

የክልል የፀጥታ ተቋማት ለምሳሌ የክልል ልዩ ኃይልና ፖሊስ ቀላል የጦር መሣሪያ መያዝን የሚፈቅድበት ሕግ የለም፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ግን እነዚህን መሣሪያዎች ሊታጠቅ እንደሚችል አንቀጽ 14 (2) ላይ ተገልጿል፡፡ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው ነገሩ፡፡ አውቶማቲክ መሣሪያ ግን የፌዴራልም የክልልም ፖሊሶች ሊታጠቁ ስለመቻላቸው ከረቂቅ ሕጉ ምንም ፍንጭ የለም፡፡

ያለ ክፍያ ወራሹ መንግሥት

የጦር መሣሪያን ያለምንም ክፍያ ፌዴራል ፖሊስ እንዴት ይወስዳል? ለምን ለተፈቀደላቸው የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች መሸጥ አልተፈቀደም የጦር መሣሪያ መያዝ ማቆም የፈለገ፣ ወይም ሌላ ዓይነት መሣሪያ ለመግዛት የሚፈልግ ለነጋዴዎች ወይም በደላሎች አማካይነት መሸጥ ለምን አልተፈቀደም? ንብረትን እንዴት በነፃ ይወርሳል? ፈቃድ ላይ የተገለጹ መሥፈርቶችን ማሟላት ሳይችል ሲቀር ለሌላ ማስተላለፍ እንደሚቻለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ለመቀማትና ለመውረስ ማሰፍሰፍ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር አንቀጽ 25 (2) የተሻለ ድንጋጌ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ንዑስ አንቀጽ እንደሚለው የጦር መሣሪያውን አገልግሎት ያልፈለገ እንደሆነ ፈቃድ ለሚጠይቅና መሥፈርቶቹን አሟልቶ ፈቃድ ለሚሰጠው ሰው ማስተላለፍን ይፈቅዳል፡፡ መሸጥን ግን በይፋ ሕጉ አልተናገራትም፡፡ በግልጽና በይፋ መሸጥ ቢቻል፣ በአንድ በኩል መንግሥት በግብር ገቢ ይሰበስባል፣ በሌላ በኩል ዜጎች ለጦር መሣሪያ ግዥ ያወጡትን ገንዘብ እንደው በከንቱ መንግሥት እንዳይወስድባቸው መፍትሔ ይሆናቸዋል፡፡ በነፃ ለመንግሥት ከመስጠት ለሌላ ማስተላለፉን የመምረጥ ሁኔታቸው እንደሚያመዝን መገመት ቀላል ነው፡፡

ነጋዴው መንግሥት ወይስ ሌላ?

አንቀጽ 26 ላይ እንደተገለው የፌዴራል ፖሊስ በሚመርጠው መንግሥታዊ ተቋም አማካይነት የጦር መሣሪያ ከውጭ ያስገባል፣ ከአገር ያስወጣል፣ ይይዛል ያከማቻል፡፡ ማዘዋወርም ማስተላለፍ፣ መሸጥ፣ ማሠልጠን፣ መጠገንና ማስወገድንም ጨምሮ ፌዴራል ፖሊስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንቀጽ 20(6) ላይ የተፈቀዱ መሣሪያዎችን ገዝቶ መሸጥን፣ በአንቀጽ 13 (8) መሠረት ደግሞ የድለላ ፈቃድ ከመንግሥት ውጭ ለሆነ አካልም ሊሰጥ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ ከአንቀጽ 26 አንፃር ለተመለከተው በብቸኝነት ሁሉንም ተግባር ጠቅልሎ እንዲይዝ የሚፈለገው መንግሥት ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ ሁለት አንቀጾች ላይ ግን ለመሸጥና ለመደለል ፈቃድ እንደሚሰጥ ያመላክታል፡፡ ነገር ግን ማስቀመጥ፣ ማከማቸት የመሳሰሉትን አለጨመረም፡፡ 

ገጀራ ጠጋኝ መንግሥት?

አንቀጽ 27 ላይ ቅጣት መጠንን ይዟል፡፡ የጦር መሣሪያንም ሆነ ጉዳት የሚያደርሱ ቁሳቁሶችን ያስቀመጠ፣ ያዘዋወረ፣ የሸጠ፣ የጠገነ ወዘተ ይቀጣል፡፡ ገጀራ ጉዳት ከሚያደርሱ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው በማለት ረቂቁ ላይ ሰፍሯል፡፡ በመሆኑም ገጀራን መጠገን ያስቀጣል፡፡ ጠጋኙ መንግሥት ነው ማለት ነው፡፡ ጉዳት ማድረሻ መሣሪያ ተብለው የተለዩ ዕቃዎችንም መጠገን፣ መሥራት ክልክል ነው፡፡ ወንጀሉ እስከ አንድ ዓመት እስራትና ከአንድ ሺሕ እስከ አምስት ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት አለው፡፡

እነዚህን ጉዳት ማድረሻ ተብለው የተለዩ እንደ ገጀራ፣ ጎራዴ፣ ሰንጢ፣ ሳንጃና መሰል ቁሳቁሶች በብዛት ማዘዋወር፣ መሸጥ፣ ማከማቸት፣ መጠገን ወዘተ ክልክል እንደሆነ አንቀጽ 27 (4) ላይ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ እንደ ችግር መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በብዛት ማለትስ ስንት ነው? በቤተሰብ አባላት ልክ ቢሆን ብዙ ነው የሚባለውን? ሁለት ብዙ ነውን? ሦስትስ ብዙ ነው? በተለይ ገጀራና መሰል ቁሳቁሶች በባህላዊ መንገድ በዕደ ጠበብት የሚመረቱ ናቸውና ወንጀሉ እነሱን እንዲካተት መደረጉ ተገቢ ነውን?

የከበዱ ቅጣቶች

የተከለከሉ ቦታዎች ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት በወንጀል ያስጠይቃል፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖት ቦታን ብንወስድ ሕዝብ የጥምቀትና መሰል በዓላት ላይ፣ ሰው ሞቶ ቀብር ሲፈጸም፣ የጦር መሣሪያ መያዝና መተኮስ የተለመደ ነው፡፡ ለነገሩ፣ ይኼ ክልከላ በሥራ ላይ ባለው የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 229/1952 ላይ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው በሃይማኖት በዓላት ላይ፣ በተለይ በገጠር፣ በፍጹም ተግባራዊ አልሆነም፡፡ እንደውም ባለፈቃዱ መሣሪያውን ወደ አደባባይ ከሚያወጣባቸው ሁነቶች አንዱ ነው፡፡

ሌላው፣ መንግሥታዊ ተቋማትና ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎችም ላይ ይዞ መገኘት አሁንም ቢሆን ክልክል ነው፡፡ የገበያ ቦታዎች እንዲሁ ሕዝባዊ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው አንዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በገጠር አካባቢ ደግሞ መሣሪያ ይዞ ሰው ከሚንቀሳቀስባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ገበያ በሚሄድበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ በእግር ረዘም ያለ ሰዓት የሚወስዱ እንዲሁም መንገዶቹ የፀጥታ ሥጋት ያለባቸው ሲሆን ገበያተኞች ወይ ተሰባስበው ይሄዳሉ፣ እንደዚያም ሆኖ የጦር መሣሪያ ይይዛሉ፡፡ በብዙ የገጠር ገበያዎች ወደ መገበያያ ስፍራው ሲገባም ቢሆን መሣሪያ ተረክቦ የሚጠብቅ አካል ስለሌለ ተግባራዊ የሚሆን አይመስልም፡፡

አንዳንድ ቦታ ላይ ይህን ሕግ ለማስፈጸም ሲባል እስራትና ቅጣት መጣል በሌላ ቦታ ወጥ በሆነ መንገድ በእኩልነት ካልተተገበረ አድሏዊ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም ከሦስት ዓመት ያላነሰ እስራትና ከሁለት ሺሕ እስከ አሥር ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ድርጊቶችን በሚመለከት ቢያንስ የቅጣት መጠናቸው ከእንደገና ማጤን ለሕጉ አፈጻጸም ይበጃል፡፡

ማጠቃለያ

የጦር መሣሪያ አስተዳደርን በሚመለከት ትኩረት መደረግ የሚያስፈልገው ወደ ፈላጊዎቹ (demand side) ላይ ብቻ በአቅራቢዎቹም (suppliers) በኩል መሆን አለበት፡፡ ልዩ ትኩረት የሚያሻው የፈላጊዎቹ ሁኔታ ነው፡፡ የተለያዩ የክልከላ ሥርዓችን ከመዘርጋት አስቀድሞ የጦር መሣሪያ ለምን ይፈለጋል? ከፈላጊዎቹ አንፃር ምን ማድረግ ይጠበቃል? የሚሉትን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ሌላው ላይ እርስ በእርሳዊ ተፅዕኖ ያላቸውን ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ መረዳትም ወሳኝ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ይህ ረቂቅ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ሰፋ ያለ ምክክር ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ቢደረግ የተሻለ ይሆናል፡፡ ለምንድን ነው መሣሪያ መታጠቅ ሰው የሚፈልገው? የሚፈልግበትን ምክንያት ጠንቅቆ ሳያውቁ፣ በመስፈርትነት ሳያስገቡ የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ማስቀመጥ ተጠየቃዊ አይደለም፡፡ አንድ ወጥ መስፈርትም ማዘጋጀትም አግባብ ላይሆን ይችላል፡፡ ለአርብቶ አደር፣ ለከተማ ነዋሪ፣ በአጎራባች አገሮች ድንበር አካባቢ የሚኖሩና ከእዚያኛው አገር በኩል ተደጋጋሚ ጥቃት ለሚደርስባቸው ኗሪዎች መስፈርቱም የመሣሪያ ዓይነቱም ሊለያይ ይገባል፡፡

መንግሥት ማኅበረሰቡን ትጥቅ የማስፈታት (weapon collection) እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊትም (እንዲህ ዓይነት ተግባር ውስጥ ከገባ?) ሊያጤናቸው የሚገቡ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅ ይገባል፡፡ የጦር መሣሪያ ማስፈታት ወይም መሰብሰብ ሌላ ውስበስብ ጣጣ ሊያስከትል ይችላልና፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ፣ ተመራጭ ምክሮች ከሚባሉት ውስጥ ማንኛውም ሰው የጦር መሣሪያ ለመያዝ ፈቃድ ማግኘት ግዴታ መሆኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ መሣሪያ ለመያዝ ተቀባይነት ያለው ፍላጎት (legitimate need) እና የፈቃድ ጠያቂውን ባሕርይና ዓመል ለማወቅ የሚያስችል ጠንካራ የመረጃ ሥርዓትም መስፈርትም የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ የጦር መሣሪያ ድለላ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ የጦር መሣሪያዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን መንግሥት ሊደርስባቸው የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም ባለፈቃዶች የጦር መሣሪያ የሚስቀምጡበትን ቦታ ክትትል ማድረግን ይመክራሉ፡፡

ለአነስተኛ የጦር መሣሪያ መጠንና ዝውውር የመጨመር እንጂ የመቀነስ ሁኔታ አይስተዋልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ መዋቅራዊና ሥር የሰደደ ድኅነትና ችጋር፣ የሀብትና መጠን መራራቅ፣ መጥፎ አስተዳደር፣ የልማት አለመኖር (ማነስ)፣ የሕግ የበላይነት ዝቅተኛ መሆን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሌላው የፀጥታ አካላትን ማጠናከርና የተገራ ማድረግን ይመለከታል፡፡ በአንድ በኩል የፀጥታ አካላት ድክመት፣ ሙሰኛነት፣ አፋኝና ጨካኝነት፣ ተጠያቂነት አለመኖርን ማረምና ማስተካከል ካልተቻለ የጦር መሣሪያ ፍሰቱ ላይገታ ይችላል፡፡

ምክንያቶቹ ምንም ይሁን ምን፣ የአነስተኛ የጦር መሣሪያዎች መጉረፍ ግጭትን ሊያጎርፍ እንደሚችል የታመነ እውነት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይጨምራል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ (International Humanitarian Law) ይዞታንም መጣሱ አይቀርም፡፡ እነዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስተዋሉ አዝማሚያዎች ናቸው፡፡ ይኼ፣ በየአገሮቹ የተስተዋለውን በድምሩ ሲታይ እንጂ የጦር መሣሪያ በብዛት መታጠቅ ብቻውን ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳቶች ሁልጊዜም ያስከትላል ማለት አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ዓለም አቀፋዊው ተሞክሮ የሚያሳየው የጦር መሣሪያ ሁኔታ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ግድ ማለቱን ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥትም ከዚህ አንፃር በ1952 ዓ.ም. የወጣውን ሕግ ማሻሻሉ ተገቢ ነው፡፡

የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችልና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎችን መወጣት አንድ ነገር ሆኖ፣ የዜጎች የጦር መሣሪያ መታጠቅ መንግሥት አምባገነን ሆኖ የዜጎችን መብት እንዳሻው እንዳይጥስ ለማድረግም ጭምር ስለሚጠቅም ዜጎች የጦር መሣሪያን እንዳይዙ እንዲሁም ባሰኘው ጊዜ መንጠቅ የሚያስችል ሥልጣን ሊሰጠው አይገባም፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጁ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ጉድለቶችና መስተካከል የሚገባቸው ድንጋጌዎችን አጭቆ ይዟል፡፡ በዚህ ጽሑፍም ይሁን ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ አምድ የቀረበው ምልከታ ዓይነተኛ ዓላማው ይህ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት ሕዝባዊ ትኩረት እንዲያገኝና መሻሻል ያለባቸውን ነጥቦች ለመጠቆም ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እንከኖቹ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ምልከታውም ወፍ በረራዊ ነው፣ ጥልቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዜጎች በተጨማሪም የክልል መንግሥታትም እንዲሁ አጽንኦት ሊሰጡት ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...